Saturday, 07 September 2013 10:23

በሕገ መንግሥት የተረጋገጠ መብት በባለሥልጣናት ሲጣስ!

Written by  ታምራት ታረቀኝ
Rate this item
(3 votes)

አዲስ አድማስ ባለፈው ሳምንት እትም ሁለት ሰላማዊ ሰልፎች በአንድ ቀን መጠራታቸውን አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ፣ የጠቀሳቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር “የሚጠበቅብን ማሳወቅ ነው፤ ይህንኑ በወቅቱ ፈጽመናል” ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ደግሞ “ማሳወቅ ብቻ አይበቃም፣ ማስፈቀድ ያስፈልጋል” ማለታቸውን አስነብቦናል፡፡ ሁለቱም በአንድ ሀገር የሚኖሩ፣ በአንድ ህግ የሚተዳደሩ ናቸውና ለተናገሩት ዋቢ የሚያደርጉት የትኛውን አዋጅና የትኛውን አንቀጽ እንደሆነ መጠየቅ ቢቻል አንባቢያን በቂ ግንዛቤ በጨበጡ ነበር፡፡
አቶ ሽመልስ ዳኛም አቃቤ ህግም ሆነው የሰሩ እንደመሆናቸው ስለ ሕገ መንግሥቱም ሆነ ስለሌሎች አዋጆች ከሌላው ሰው በተሻለ ግንዛቤ ይኖራቸዋልና ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ፈቃድ መጠየቅን የግድ የሚያደርጉትን ህጎች ቢገልጿቸው ሁሉም በቂ ግንዛቤ ይዞ በህጉ አግባብ በመሄድ አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ ባልተገባ፣ ፖሊስም መሀል ቤት ከመቸገር በዳነ ነበር፡፡
እስካሁን የምንሰማውም የምናውቀውም መሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን አስመልክቶ የሚጠቀሱት የህገ መንግሥቱ አንቀጽ 30/1 እና የሰላማዊ ሰልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ ስርዓት አዋጅ ቁ.31/1983 ናቸው፡፡
“የመሰብሰብ፤ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታ የማቅረብ መብት” በሚል ርዕስ በሁለት ንዑሳን አንቀጾች የተገለጸው የህገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጪ የሚደረጉ ስብሠባዎችና ሰላማዊ ሠልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሄድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሠልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ” ይላል፡፡
በዚህ ንዑስ አንቀፅ ድንጋጌ ውስጥ ፍቃድ የመጠየቅ ግዴታም ሆነ የመከልከል መብት የለም። ሕግ ይወጣል የሚለውም ከቤት ውጪ ለሚካሄዱ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው በቤት ውስጥ የሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው በአድራጊው አቅምና ፍላጎት ብቻ የሚከናወኑ መሆኑን ነው፡፡
ከቤት ውጪ የሚደረግን ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍን በሚመለከትም “አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ” ተብሎ በሕገ መንግሥቱ ቢገለጽም የወጣ አዋጅ፣ ደንብም ይሁን መመሪያ የለም፡፡ ወይንም አላየሁም፡፡ በዚህ ንኡስ አንቀጽ የተገለጸውን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ለማስፈጸም ሥራ ላይ የዋለው ከህገ መንግሥቱ ቀድሞ በ1983 ዓ.ም የወጣው “የሰላማዊ ሠልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 31/1983” ነው፡፡ ይህ አዋጅ በአንቀጽ 6/2 ስብሰባ ወይንም ሠላማዊ ሰልፍ የሚያደርገው አካል ከ48 ሰዓት በፊት አስቀድሞ ለአካባቢው የመስተዳድር አካል እንዲያሳውቅ ግዴታ ይጥላል፡፡ ማወቅ አለበት ለተባለው የአካባቢ መስተዳድር ደግሞ የጸጥታ ጥበቃ የመመደብን ኃላፊነት ይሰጣል፡፡ ስብሰባው አዘጋጆቹ ባሰቡት ቀን እንዲካሄድ የማያስችል በቂ ምክንያት ሲኖር ደግሞ ይህንኑ ገልጾ ለሌላ ቀን እንዲያስተላልፉ ሀሳብ ይሰጣል፡፡ ህጉ ከዚህ ውጪ በሰልፍ አዘጋጆች ላይ የሚጥለው ግዴታ ለመስተዳድሩም የሚፈቅደው መብት የለም፡፡
አቶ ሽመልስ ከማል በጣም ርግጠኛ ሆነው (ከጋዜጣው እንዳነበብነው) “ማስፈቀድ ያስፈልጋል” ሲሉ፣ እርሳቸው የሚያውቁት ከላይ ከተጠቀሱት ሌላ ስለ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ የተደነገገበት አዋጅ ደንብ ወይንም መመሪያ ይኖር ይሆን? ኖረም አልኖረ ሙግት ሳይነሳ ተቀባይነት የለውም። ለምን ቢባል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9/1 “ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይንም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም” ተብሎ ተደንግጓልና፡፡
አቶ ሽመልስ “ፈቃድ ያስፈልጋል” ለማለት ያበቃቸውን የህግ አንቀፅ እስካልነገሩን ድረስ ንግግራቸው ሕገ መንግሥቱን በግልጽ የጣሰ ነው። የመንግስት ቃል አቀባይ እንደመሆናቸውም ህገ መንግስት የመጣስ ክሱ መንግሥትንም ይመለከታል።
አቶ ይልቃል የተናገሩት ተብሎ እንደተጻፈው፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ኃላፊነቱን አልተወጣ ከሆነ እንዲሁም የአቶ ሽመልስ “ፈቃድ ያስፈልጋል” የሚል ንግግር፣ መሀል ቤት ለችግር የሚዳርገው ፖሊስን ነው፡፡ ፖሊስ በመንግስት መገናኛ ብዙሀን “የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ እውቅና ያላገኘ ነው” ለማለት የበቃውም በዚሁ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ ግን ፖሊስ ለምን?
ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ በዚሁ ክፍል ኃላፊነት የምናውቃቸው (በፊት ፈቃድ በኋላ ማሳወቂያ የተባለው ክፍል) አቶ ማርቆስ፤ ለአዲስ አድማስ በግልጽ አይናገሩት እንጂ ሰላማዊ ሰልፍ ከጠሩት ሁለት ክፍሎች ደብዳቤ እንደቀረበላቸው በገደምዳሜም ቢሆን ተናግረዋል፡፡ ታዲያ ዘግይቶ ደብዳቤ ላመጣው አካል “እናንተ በጠየቃችሁን ቦታና ቀን፣ ከእናንተ ቀድሞ ሰልፍ ማዘጋጀቱን የገለጸልን አለ” በማለት ወዲያውኑ መልስ በመስጠት ጉዳዩን በአጭሩ መቅጨት ለምን ሳይቻል ቀረ? ዘግይቶ የመጣው ከቀደመው በተለየ ሁኔታ ጥያቄው መስተናገድ ያለበት ከሆነም፣ ይህንኑ ገልጾ ቀድሞ ያሳወቀው ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ በመንገር፣ የተፈጠረውን አላስፈላጊ ነገር ሁሉ ማስቀረትስ አይቻልም ነበር? ይህ ሁሉ ካልሆነም አንደኛው ፍቃድ ማግኘቱን ሌላኛው መከልከሉን ወይንም ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑን (ፈቃድ የምለው እነርሱ ስላሉ እንጂ ሕገ ወጥ ነው) መግለጽና ያልተፈቀደለት ያሉት ፓርቲ ሰልፉን ቢቀጥል ሕገ ወጥ መሆኑን ማሳወቅ የዚሁ ክፍል ኃላፊነት መሆንስ አልነበረበትም? ፖሊስን አጣብቂኝ ውስጥ መክተትና በዜጎች የመብት ጥያቄ ላይ አሉታዊ አመለካከት ያለው መስሎ እንዲገመት ወይም እንዲታይ ማድረግስ ተገቢ ነው? “ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ እንደሚያደርግ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ያልተገለጸልኝ በመሆኑ” እውቅና ያልተሰጠው በመሆኑ” የሚለው የፖሊስ ገለጻ፣ ጥንቃቄ የተሞላበት ነው፡፡ ይህም ጥንቃቄ ከላይ የገለጽኩት ስሜት በህብረተሰቡ ውስጥ እንዳያድር ለማድረግ ከማሰብ የተፈጸመ ነው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ለቃላት ሲጠነቀቅ የነበረው ፖሊስ፤ “የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችንና አባሎችን ከቢሮአቸው አፍሶ ወሰደ፤ ብዙዎቹንም ደበደበ” የተባለው በርግጥ ተፈጽሞ ከሆነ፣ የባለሥልጣናት ትዕዛዝ ከህገ መንግሥት በላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡
የዛሬ 10 ዓመት የተፈጸመን ድርጊት ዛሬ ከሆነው ጋር በንጽጽር ማየት ምን አልባት ያስተምር ከሆነ በአጭሩ ላስታውስ፡፡ ኢዴፓ በመስቀል አደባባይ ያቀደው ሰላማዊ ሰልፍ በተለያየ ምክንያት ሲተላለፍ ቆይቶ፣ ለየካቲት 2/95 ዓ.ም ይወሰንና አቶ ማርቆስ ለሚመሩት ክፍል የማሳወቂያ ደብዳቤ ይጻፋል። በክፍሉ በኩል የታዩ ተደጋጋሚ ችግሮችን ግምት ውስጥ በማስገባትም ለፖሊስ በግልባጭ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ አቶ ማርቆስ የሚመሩት ክፍልም “በአደባባይ ሳይሆን በአዳራሽ ብታደርጉት” የሚል ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ በተባለው ቀን አደባባዩ ነፃ መሆኑ እየታወቀ፣ በአዳራሽ አድርጉ ማለቱ ህጋዊም አሳማኝም አልሆነምና ኢዴፓ የአደባባይ ዝግጅቱን ይቀጥላል፣ በዚህ መሀል ፖሊስ ግራ በመጋባቱ፣ ጥር 25/1995 ዓ.ም በወቅቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ከነበሩት ሻለቃ በፍቃዱ ቶሌራ ቢሮ “ልናነጋግራችሁ ስለምንፈልግ ሶስት ሰዎች ከሰአት ብትመጡ” የሚል የስልክ መልእክት ደረሰን፡፡ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ፣ አቶ ክፍሌ ጥግነህና እኔ ሆነን ስንሄድ፣ ሻለቃ በፍቃዱ አሁን ስማቸውንና ማዕረጋቸውን ማስታወስ የቸገረኝ የወንጀል መከላከል ሀላፊ ከነበሩት ጋር ሆነው ጠበቁን፡፡ አቶ ማርቆስ ብቻቸውን መጡ፡፡ ሻለቃ በፍቃዱ “የአዲስ አበባ መስተዳድር በ23 በጻፈው ደብዳቤ በመስቀል አደባባይ ሳይሆን በአዳራሽ ማድረግ የምትችሉ መሆኑን ገልጾ ጽፏል፤ እናንተ በ25 የጻፋችሁትን ደብዳቤ ግልባጭ አድርጋችሁልናል፡፡ በዚህም ፖሊስን ግራ ስላጋባችሁት ተገናኝታችሁ ተነጋገሩ በማለት ነው አቶ ማርቆስ ባለበት የጠራናችሁ” አሉ።
አቶ ማርቆስም “ከዚህ በፊት ሰፊ ስብሰባ በአደባባይ አድርጋችኋል፣ በህዳር ወርም ተፈቅዶላችሁ የተዋችሁት እናንተ ናችሁ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ተጋፍተን አታድርጉ ማለት አይቻልም፤ ደብዳቤያችንም ይህን አይልም” አሉ። በእኛም በኩል በአዳራሽ አድርጉ ሲባል የቀረበው ምክንያት አሳማኝና ተገቢ ባለመሆኑ የአደባባይ ፕሮግራማችንን ለመሰረዝ የሚያበቃን ስላልሆነ ዝግጅታችን መቀጠሉን አስረዳን፡፡ የወንጀል መከላከል ኃላፊውም “ኢዴፓ ሕግ አክብሮ የሚሰራ ነው፤ ይህንንም መስቀል አደባባይ በተደጋጋሚ ባደረጋቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች ከፖሊስ ጋር ተባብሮ በመስራት አሳይቷል፣ አሁን ችግሩ ያለው በእነ አቶ ማርቆስ በኩል ነው” አሉ፡፡ አቶ ማርቆስም ጉዳዩ በርሳቸው ክፍል የማያልቅ የበላይ አካልን ውሳኔ የሚጠይቅ እንደሆነና ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ውሳኔ አለማግኘቱን ገለጹ፡፡ ከሶስታችንም በኩል ሀሳቦች እየተሰነዘሩ ከተነጋገርን በኋላ፣ ሻለቃ በፍቃዱ “ጥያቄዬን አንስቻለሁ፤ መስተዳድሩ በአደባባይ መሆን ይችላል ካለ ጥበቃ ለማሰማራት፣ የለም በአዳራሽ ያልኩትን አላነሳሁም ካለ ለጥበቃ ላለመዘጋጀት ነው፣ የእኔ የቤት ሥራ ይህ ነው” ብለው በዚሁ ተለያየን፡፡
ከላይ በተገለጸው ድርጊት ፖሊስ “ተፈቅዷል አልተፈቀደም” የሚል ሕግ መንግሥቱን የሚጋፋ ተግባር ውስጥ አልገባም፡፡ “ሕጋዊ ነው፤ ሕገ ወጥ ነው” የሚል ዳኝነትም አልሰጠም፡፡ አቶ ማርቆስም “ሕገ መንግሥታዊ መብትን ተጋፍተን አታድርጉ ማለት አንችልም” ነው ያሉት፡፡ ዛሬ ከ10 ዓመት በኋላ ከፖሊሲም ሆነ ከአቶ ማርቆስ አሊያም ከአቶ ሽመልስ የሰማነው እድገትና መሻሻል ነው ወይስ የኋሊት ጉዞ?
ለዚህ አስተያየት መጻፍ ምክንያቴ የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ መካሄድ አለመካሄዱ አይደለም፡፡ የህገ መንግስቱ ድንጋጌ መከበር አለመከበሩ ነው፡፡ አቶ ማርቆስ የዛሬ 10 አመት ያሉትን ዛሬም ማጽናት መቻል ነበረባቸው፡፡ የያኔው ፖሊስ አዛዥ የተናገሩትን የዛሬውም ሊደግሙት በተገባ ነበር፡፡ የህገ መንግስቱ ድንጋጌ አልተለወጠም አልተሻሻለምና፡፡ ከዛ ወዲህ ሰልፍና ስብሰባን የሚመለከት አዋጅ ስለመውጣቱ አይታወቅም፡፡
አቶ ሽመልስ እንደ ህግ ባለሙያነታቸውና እንደ መንግሥት ቃል አቀባይነታቸው “ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ፈቃድ መጠየቅ ግዴታ ነው” ሲሉ ይህ ሊሆን የሚችለው በርሳቸው አስተሳሰብ ወይንም ፍላጎት ሳይሆን በህግ ድንጋጌ ነውና ፈቃድ መጠየቅን ግዴታ የሚያደርገውን የህግ አንቀጽ ጠቅሰው ማስረዳት ነበረባቸው፡፡ አንድም የህግ አንቀጽ ሳይጠቅሱ፣ በህገ መንግስት ለተረጋገጠ መብት የባለሥልጣናት ፈቃድ ያስፈልጋል ብለው በጋዜጣ መናገራቸው፣ በሕገ መንግሥቱ ገዢነትና ተግባራዊነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚያጠናክር ይሆናል፡፡
አቶ ሽመልስ የመንግሥት ቃል አቀባይ ናቸውና የሚናገሩት ሁሉ የመንግሥት አቋም፣ እምነትና ውሳኔ ተደርጎ ስለሚወሰድ ሲናገሩ ማስረጃ እያጣቀሱ፣ ማስረጃ ከሌለ ደግሞ ባይናገሩ ሳይበጅ አይቀርም፡፡
ሕገ መንግሥት የሚምሉ የሚገዘቱበትና ሌላውን የሚያስፈራሩበት ሳይሆን በአንቀጽ 9/2 እንደተገለጸው የሚገዙበት መሆኑ በተግባር መታየት አለበት፡፡ የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሆነው ህገ መንግስት ካልተከበረ ወይንም ለድንጋጌዎቹ ከራስ ፍላጎትና ስሜት አንጻር የተለያየ ትርጉም እየተሰጠ የሚሸራረፍ ከሆነ የህግ የበላይነት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ዜጎችም በህግ የማመናቸውና ለህግ የመታመናቸው ስሜት ይዳከማል፡፡ ይህ ደግሞ አጠቃላይ የሆነ ሀገራዊ ችግር ያስከትላል፡፡ ለዚህም ነው ባለፈው ሳምንት የሆነውን ነገር የሰማያዊ ፓርቲ፣ አቶ ማርቆስ የሚመሩት ክፍል እንዲሁም የአቶ ሽመልስና የፖሊስ ጉዳይ ብቻ አድርገን ልናየው የማይገባን፡፡ ይህን እንድናደርግ ደግሞ የህግ መንግሥቱ አንቀጽ 9.2 “ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለህገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው” በማለት ግዴታ ጥሎብናል፡፡

Read 3084 times