Saturday, 07 September 2013 10:00

“አንድነት” በአዳማና በአዲስ አበባ ማጠቃለያ የተቃውሞ ሰልፍ ያካሂዳል

Written by 
Rate this item
(8 votes)

“እስካሁን በሁለቱ ከተሞች እንቅፋት አላጋጠመንም”

ከሃያ በሚበልጡ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችንና ስብሰባዎችን ሲያካሂድ የቆየው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፤ ነገ በአዳማ ናዝሬት ከተማና በአዲስ አበባ የማጠቃለያ ሰልፍ ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለፁ፡፡
በሶስት ወራት ውስጥ ሰላሳ ያህ ሰልፎችንና ስብሰባዎችን ለማካሄድ አቅዶ ብዙዎቹን ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ ብዙ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙንም ከመቀሌና ከወላይታ ሶዶ በስተቀር ብዙዎቹን እቅዶች አከናውነናል ብለዋል፡፡ የፀረሽብሩ ህግ እንዲሰረዝና የዜጎች ማፈናቀል እንዲቆም የህዝቡን ድምፅ እያሰማን ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ የተጫነው ሸክም እንዲነሳና ለአሳሳቢው የወጣቶች ስራ አጥነት በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ጥያቄያችንን እያቀረብን ነው ብለዋል፡፡

የህዝቡን ድምፅና ጥያቄ ለማስተጋባት ጎንደር ላይ የጀመረው የአንድነት ሰላማዊ ሰልፍ እንቅፋቶች ቢገጥሙትም እንደተሳካና በአዲስ አበባ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል - አቶ ዳንኤል፡፡ የአዳማው ሰላማዊ ሰልፍ ለነሀሴ 19 ቀን ቀጠሮ ተይዞለት እንደነበረና በእለቱ በሚካሄድ ሌላ ሰልፍ ለፀጥታ አካላት ስምረት አስቸጋሪ እንደሆነ በመስተዳድሩ ስለተነገረ ለአንድ ሳምንት እንደተራዘመ ገልፀዋል፡፡ ሰልፉ እንደገና በሳምንት ተራዝሞ ወደ ነገ የተሸጋገረው ደግሞ ነሃሴ 26 ቀን በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራ ሰልፍ ይካሄድ ስለነበረ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአዳማ ናዝሬት ከመንግስት ወይም ከገዢው ፓርቲ እንቅፋት እንዳልገጠማቸው አቶ ዳንኤል ገልፀዋል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ባደረግናቸው ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ከፍተኛ ጫናዎች፣ ድብደባዎችና እንቅፋቶች ገጥመውናል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ግን ፖስተር ስንለጥፍና ከሀምሳ ሺህ በላይ በራሪ ወረቀቶች ስንበትን ምንም ችግር አልገጠመንም ብለዋል፡፡

Read 16397 times