Saturday, 07 September 2013 09:59

ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፉን ለመስከረም 12 ለማዛወር ተስማማ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

“የነፃነት ፈለግ” የተሰኘ ቴአትር በቅርቡ ያስመርቃል
አክራሪነትን ለማውገዝ በመስቀል አደባባይ ሰልፍ በተካሄደበት እለት፣ ሌላ ሰልፍ ለማካሄድ አቅዶ በፖሊስ የታገደው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ለዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጋር ሲወዛገብ ከሰነበተ በኋላ ሃሳቡን በሁለት ሳምንት ለማራዘም ተስማማ፡፡
ሰላማዊ ሰልፍ እንደምናካሂድ በደብዳቤ ለማሳወቅ ብንጥርም፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ጽሕፈት ቤት ሊያስተናግደን ፍቃደኛ አልሆነም ያሉት የፓርቲው መሪዎች፤ በከንቲባው ጽ/ቤት በኩል ከካቢኔ ጉዳዮች ሃላፊ ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ እንደደረሱ ገልፀዋል፡፡
የእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ የመንግስት ታጣቂ ሀይሎች በወሰዱት ኢፍትሐዊ እርምጃ ተደናቅፎብኛል በማለት መግለጫ ያወጣው ሰማያዊ ፓርቲ፤ የተደናቀፈውን ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ቅዳሜ ለማካሄድ በመወሰን እቅዱን በአዲስ አበባ መስተዳድር ለማስመዝገብ ሲጥር መሰንበቱን አውስቷል፡፡
ሰላማዊ እንዲሆን፣ የፀጥታ ጥበቃና የአስተዳደር ድጋፍ ያስፈልገዋል ያሉት የፓርቲው መሪዎች፤ በህጉ መሰረት ለማስመዝገብ ለከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ጽ/ቤት ደብዳቤ ያቀረብነው ሰኞ እለት ነው ብለዋል፡፡ በአካል ተገኝተንም ጠይቀናል፣ ነገር ግን ጽ/ቤቱ ደብዳቤውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም ብለዋል - የፓርቲው አመራሮች፡፡ “ተስፋ ሳንቆርጥ ደብዳቤውን በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በኩል ልከናል፣ ጽ/ቤቱ ግን እምቢተኝነቱን ገፍቶበታል” በማለት የተናገሩት የፓርቲ አመራሮች፤ በጉዳዩ ላይ በመወያየት ለከንቲባው ጽ/ቤት ለማመልከት መወሰናቸውን ገልፀዋል፡፡
በከንቲባው ጽ/ቤት በኩልም የፓርቲው መሪዎች ከካቢኔ ጉዳዮች ም/ሃላፊው ጋር ለመወያየት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡
ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ድርጅቶች የገበያ እድል ለመፍጠር በጳጉሜ ቀናት በርካታ ቦታዎች ለግብይት እንቅስቃሴ እንደሚውሉ ም/ሃላፊው እንደገለፁና ለዛሬ የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ ለሌላ ቀን እንዲዛወር እንደጠየቁ የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች አውስተዋል፡፡ ይህንንም በማገናዘብ የበዓሉ ዋዜማና በዓሉ ካለፈ በኋላ ሰልፉን ለማካሄድ ወስነናል ብለዋል - የፓርቲው መሪዎች፡፡
በሌላ በኩል፤ “የነፃነት ፈለግ” የተሰኘና በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ቴአትር ማዘጋጀቱንና በቅርቡ ለእይታ እንደሚያበቃ ፓርቲው ገልጿል፡፡

Read 13663 times