Saturday, 07 September 2013 09:52

እነ ውብሸት ታዬ በድጋሚ ይቅርታ ሊጠይቁ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የይቅርታ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ረቡዕ የተነገራቸው የአውራምባ ታይምስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና የኢብአፓ ፓርቲ አመራር አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚያብሄር፤ በየአመቱ የይቅርታ ጥያቄ ማቅረብ ስለሚቻል በድጋሚ እንደሚሞክሩ ቤተሰቦች ተናገሩ፡፡
በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አመፅ የሚያስነሳ ፅሁፍ አቅርባችኋል በሚል የ14 እና 17 አመት እስር እንዲሁም ከ30ሺ ብር ያላነሰ ቅጣት እንደተፈረደባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ለይቅርታ ቦርድ በደብዳቤ ጥያቄ ያቀረቡት ከአንድ አመት ከአራት ወር በፊት እንደሆነ የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ባለቤት ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ ይቅርታ እንደሚያገኙ ጠብቀን ነበር የምትለው ወ/ሮ ብርሃኔ፤ በተመሳሳይ ጉዳይ ሁለት የስዊድን ዜጐችም ይቅርታ ተደርጐላቸው ከእስር እንደተፈቱ በማስታወስ፣ በኢትዮጵያዊነታቸው አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያገኙ ተስፋ ነበረን ብላለች፡፡
የይቅርታ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲነገራቸው በጣም ደንግጠናል ያለችው ወ/ሮ ብርሃኔ፤ በህጉ መሠረት ዘንድሮም የይቅርታ ጥያቄያቸውን እንደገና ለማቅረብ አስበዋል ብላለች፡፡
ከጋዜጠኛ ውብሸት እና ከአቶ ዘሪሁን ጋር የተከሰሱት ሂሩት ክፍሌ ያቀረቡት ተመሳሳይ የይቅርታ ጥያቄ ውድቅ እንደተደረገ በደብዳቤ የተገለፀላቸው ከሦስት ሳምንት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡
የ14 አመት እስርና የ30ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶባት ይግባኝ ያቀረበችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ቅጣቱ ወደ 5 ዓመት ዝቅ እንደተደረገላት ይታወሳል፡፡

Read 1756 times