Saturday, 31 August 2013 12:53

የመሲና የጥሩ ትንቅንቅ ከ2 ሳምንት በኋላ ይቀጥላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

               የ2013 የዳይመንድ ሊግ ፉክክር ባለፈው ሐሙስ ዙሪክ ላይ ሲካሄድ በ5ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኗ መሰረት ደፋር የቅርብ ተቃናቃኟን ጥሩነሽ ዲባባ በመቅደም አሸናፊ ሆነች፡፡ በዙሪኩ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ መሰረት ደፋር እና ጥሩነሽ ዲባባ በሩጫ ዘመናቸው ለ33ኛ ጊዜ መገናኘታቸው ሲሆን ከሃሙሱ ውጤት በኋላ ፉክራቸው በጥሩነሽ ዲባባ 19 ለ14 ድል አድራጊነት ቀጥሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር በታሪካቸው ለ34ኛ ጊዜ ከሁለት ሳምንት በኋላ በቡፓ ግሬት ኖርዝ ናን ግማሽ ማራቶን መፋጠጣቸውም ተጠብቋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ በቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን የግማሽ ማራቶን ሞ ፋራህ፤ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ መወዳደራቸው ሲያነጋግር ቆይቶ ነበር፡፡ በሴቶች ምድብ የጥሩነሽ ዲባባ እና የመሰረት ደፋር በግማሽ ማራቶን መገናኘት ከሰሞኑ መሰማቱ ማን በይበልጥ ከፍተኛ ትኩረት ሊስብ እንደቻለ ታውቋል፡፡ በሞስኮ ተካሂዶ በነበረው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የጥሩነሽ ዲባባ እና የመሰር ደፋር ተቀናቃኝነት በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት ተሰጥቶ ነበር፡፡ የሚታወስ ይሁንና ለወጣት እና አዳዲስ አትሌቶች እድል እንዲሰጥ በፌደሬሽን ተጠይቆ ሁለቱ አትሌቶች በየምርጥ የውድድር መደባቸው ገብተው የዓለም ሻምፒዮኖች ሆነዋል፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ ሜትር እንዲሁም መሰረት ደፋር በ5ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን መውሰዳቸው አይዘነጋም፡፡ የዳይመንድ ሊጉ የአንድ ከተማ ፉክክር እየቀረው መሰረት ደፋር በ5ሺ ሜትር ማሸነፍ የቻለችው በ18 ነጥብ አንደኛ መሆኗን አረጋግጣ ሲሆን የዳይመንድ ቀለበት እና የ50ሺ ዶላር ሽልማት ተጎናፅፋለች፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ12 ነጥብ ሁለተኛ ሆና የዳይመንድ ሊጉን ፉክክር አጠናቅቃለች፡፡ በተያያዘ በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሌሎች ሁለት የኢትዮጵያ አትሌቶችም በየውድድር መደባቸው የመሪነት ደረጃውን በመያዝ ለአሸናፊነት እየገሰገሱ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በኋላ በቤልጅዬም ብራሰልስ የሚደረገው ውድድር ይጠብቃቸዋል፡፡ በ800 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው መሃመድ አማን የዳይመንድ ሊግ ፉክክሩን በ14 ነጥብ አንደኛ ሆኖ እየመራ ሲሆን የኬንያው ዴቪድ ሩዲሻ በ8 ነጥብ እንዲሁም የፈረንሳዩ ፒዬሬ አምብሮሴ ፒርስ በ6 ነጥብ በ2ኛ እና በሶስተኛ ደረጃ ይከተሉታል፡፡በ5ሺ ሜትር በዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ የወሰደው አትሌት ሃጎስ ገብረህይወት እና የኔው አላምረው በዳይመንድ ሊጉ ፉክክር ተያይዘዋል፡፡ ሃጎስ ገብረህይወት በዳይመንድ ሊጉ በ5ሺ ሜትር መሪነቱን የያዘው በ13 ነጥብ ሲሆን የኔው አላምረው በ11 ነጥብ ይከተለዋል፡፡ የእንግሊዙ ሞፋራህ እና የኬንያው ኤድዊን ሶይ እያንዳንዳቸው አራት ነጥብ ይዘው 3ኛ ደረጃን ተጋርተዋል፡፡
የውድድር ዘመኑን በ3ሺ ሜትር በማሸነፍ በጥሩ ብቃት የጀመረችው አትሌት መሰረት ደፋር በኒውኦርሊዬንስ ግማሽ ማራቶን ከወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመወዳደር ርቀቱን በ67 ደቂቃ ከ25 ሴኮንዶች በመሸፈን የቦታውን ሪከርድ አስመዝግባ አሸንፋለች፡፡ በሴቶች 5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ በምንግዜም የዓለማችን ምርጥ ሴት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የተያዘ ቢሆንም በትልልቅ ዓለምአቀፍ ውድድሮች በርቀቱ ባስመዘገበችው ውጤት መሰረት ደፋርን የሚስተካከላት አልተገኘም፡፡ በ5ሺ ሜትር ሴት አትሌቶች የዘንድሮ ዓለም አቀፍ ደረጃን መሰረት ደፋር፤ በ1389 ነጥብ በአንደኝነት እየመራች ነው፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ በ5ሺ ሜትር በ2004 እኤአ በአቴንስ እና በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችና በ2008 እኤ በቤጂንግ ኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳልያ የሰበሰበችው መሰረት ደፋር በዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ሁለት ወርቅ ሜዳልያዎች በ2007 እኤአ ኦሰካና በ2013 እኤአ ሞስኮ ላይ፤ የብር ሜዳልያ በ2005 እኤአ ሄልሲንኪ ላይ እንዲሁም ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች በ2009 እኤአ በርሊንና በ2011 እኤአ ዳጉ ላይ በማግኘት ተሳክቶላታል፡፡መሰረት ደፋር በ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር፤ በ3ሺ ሜትር እና በ2 ማይል ውድድሮች ሶስት ክብረወሰኖችንም የያዘች ናት፡፡ በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ወድድር ከ2004 እስከ 2010 እኤአ ለአራት ተከታታይ የውድድር ዘመናት አራት የወርቅ ሜዳልያዎችን ከመሰብሰቧም በላይ፤ በኦሎአፍሪካን ጌምስ ለሁለት ጊዜ ሻምፒዮን፤ በአፍሪካ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና አራት ሜዳልያዎች እንዲሁም በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች በ5ሺ ሜትር በማስመዝገብ ተሳክቶላታል፡፡

 

Read 5990 times