Print this page
Saturday, 31 August 2013 12:47

ዋልያዎቹ ለወሳኙ ፍልሚያ 1 ሳምንት ቀራቸው ከብራዛቪል ወደ ብራዚል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

              የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዛሬ ሳምንት በኮንጎ ብራዛቪል ከሴንተራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር የሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ እንደዘበት ደረሰ፡፡ ዋልያዎቹ በዚሁ ወሳኝ ፍልሚያ አድራጊነት ብቸኛው አማራጫቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበቂ የዝግጅት ግዜ እና የተጨዋቾች ስብስብ ሳይሰራ መቆየቱና የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጉ ያለውን እድል አስጨናቂ አድርጎታል፡፡ ዋልያዎቹ በኮንጎ ብራዛቪል መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክን ካሸነፉ ብራዚል በ2014 እኤአ ላይ ለምታዘጋጀው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን ለሚደረገው የ10 ብሄራዊ ቡድኖች የመጨረሻ ጥሎ ማለፍ ማጣርያ ይበቃሉ፡፡ በምድብ 1 ሌላ ጨዋታ በደርባን በሚገኘው የሞሰስ ማዲባ ስታድዬም ደቡበ አፍሪካ ቦትስዋናን ታስተናግዳለች፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ከምድባቸው የማለፍ እድል የሚኖራቸው ኢትዮጵያ ከተሸነፈች ብቻ ነው፡፡ በምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ የማለፍ እድል የሚኖራት ቦትስዋናን ካሸነፈች በኋላ ኢትዮጵያ ከሴንተራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር አቻ ከወጣች ወይንም ከተሸነፈች ብቻ ይሆናል፡፡ በምድቡ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቦትስዋና በበኩሏ ማለፍ የምትችለው ደቡብ አፍሪካን ማሸነፍ ከቻለች እና ኢትዮጵያ በሴንተራል አፍሪካ ከተረታች ይሆናል፡፡
የቦትስዋናው ጋዜጣ ሜሜጌ በድረገፁ እንደፃፈው ዜብራዎቹ በደቡብ አፍሪካ በሚኖራቸው ጨዋታ በቀላሉ 3 ነጥብ እንደማይጥሉ እና እጅ እንደማይሰጡ አትቷል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለወሳኙ ጨዋታ በጣም ጠንካራ የቡድን ስብስብ ለማዋቀር ደፋ ቀና ስትል መሰንበቷን ሲያወሳም፤ ከ23 የባፋና ባፋና አባላት ከ8 በላይ በአውሮፓ ፕሮፌሽናል ደረጃ የሚጫወቱ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ ቦትስዋና ለሳምንቱ ጨዋታ በአብሳ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን እንዳሰባሰበች የሚገልፀው ጋዜጣው እነዚህ ልጆች በደቡብ አፍሪካ ሊግ ባላቸው ከፍተኛ ልምድ ጨዋታው የካይዘር ቺፍ እና የኦርላንዶ ፓይሬትስ ደርቢ ይመስላል ብሏል፡፡የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እያደረገ ባለው ዝግጅት አንድም የወዳጅነት ጨዋታ አለማሳቡ የሳምንቱን ግጥሚያ አቋሙን ሳይፈትሽ የሚደርስበት ሆኗል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በተለያዩ አገራት ለፕሮፌሽናል ቅጥራቸው የተሰማሩ ምርጥ ተጨዋቾችን በቶሎ ማሰባሰብ ባይችሉም፤ 32 ተጨዋቾችን በመጥራት እየተዘጋጁ ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ስብስብ በደቡብ አፍሪካ ሊግ የሚጫወተው ጌታነህ ከበደ፤ በሱዳን ሊግ ያለው አዲስ ህንፃ፤ በእስራኤል ያለው አስራት መገርሳ እንዲሁም በስዊድን ያለው ሳላዲን ሰኢድ በቶሎ አለመካተታቸው በቡድኑ መቀናጀት የተወሰነ ተፅእኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በዝግጅት ቡድኑ ጊዮርጊስ 11፤ ኢትዮጵያ ቡና 4፤ ደደቢት 3፤ መከላከያ 2 ፤ መብራት ሃይል 2 ተጨዋቾች ሲያስመለምሉ በ2006 የውድድር ዘመን ፕሪሚዬር ሊጉን የሚቀላቀለው የዳሸን ቢራ ክለብ 3 ተጨዋቾች በማስመረጥ ብሄራዊ ቡድኑን ማጠናከሩ አስደንቋል፡፡ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተደርጎ በነበረ ጨዋታ እያንዳንዳቸው ሁለተኛ የቢጫ ካርዳቸውን ያዩት የኋላው ደጀን አይናለም ሃይሉና ግብጠባቂው ጀማል ጣሰው በሳምንቱ ጨዋታ በቅጣት አይሰለፉም፡፡

Read 3979 times
Administrator

Latest from Administrator