Saturday, 19 November 2011 15:04

የኢንተርፕሪነር ሳምንት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(4 votes)

እየተጠናቀቀ ባለው ሳምንት ከህዳር 4- ቀን ዓም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ4ኛ፣ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን የኢንተርፕሪነሮች ሳምንትን በተመለከተ፤ በኢምፓክት ካፒታል በኩል ለተሰባሰቡት የፕሮግራሙ አዘጋጆች የድጋፍ ሀሳባቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በመልዕክታቸው፤ በኢትዮጵያም የኢንተርፕሪነሮች ሳምንት በመዘጋጀቱ መደሰታቸውን አመልክተው “እኔም በኢንተርፕሪነርነት ብዙ ዓመታትን አሳልፌያለሁ፡፡ በኢንተርፕሪነርሽፕ የራሱን ሥራ ፈጥሮ የኢኮኖሚ ነፃነቱን የሚቀዳጅ ሰውን አደንቃለሁ፡፡ ኢንተርፕሪነርሽፕ ከራስ ባለፈ ለሌሎች ሥራ መፍጠር ከማስቻሉም ባሻገር ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

“እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ አገራት በተለይ ወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል የኢንተርፐሪነርሽፕ ስልጠና የሚያገኝበት ዕድል ቢመቻች ሥራ እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው መልስ ያስገኝላቸዋል፡፡ በወጣቶች አእምሮ ላይ የኢንተርፕሪነርሽፕ ጽንሰ ሐሳብን መዝራት ድህነትን መዋጊያ አንዱ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል” ብለዋል፡፡ 
እንግሊዝኛ ቋንቋ ከሌሎች ወስዶ የራሱ ካደረጋቸው ቃላት አንዱ የሆነው ኢንተርፕሪነርሽፕ ምንጩ ፈረንሳይ ነው፡፡ ዶ/ር ወሮታው በዛብህ “ኢንተርፕሪነርሽፕ ራስንና አገርን ለማበልፀግ” በሚል ርዕስ በ1998 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ፤ “ኢንተርፐረንደር” የሚለው የፈረንሳይኛ ቃል “ኃላፊነት ወስዶ አንድን ሥራ ከተለመደው በተለየ መንገድ መፈፀም” የሚል ትርጉም እንዳለው ያበራራሉ፡፡ ለኢንተርፕሪነርሽም መነሻ የሆነው ይኸው ቃል ነው፡፡
እንግሊዝኛ ከፈረንሳይ እንደወሰደው ሁሉ አማርኛ ቋንቋም ከእንግሊዝኛ ወስዶ የራሱ እያደረገው ያለው “ኢንተርፕሪነርሽፕ”፤ከሥራ ፈጠራ ጋር የተያያዘና በፍጥነት ዕድገት የሚገኝበትን ሂደት አመልካች ነው፡፡ የኢንተርፕሪነሮች ሳምንት በአገራችንም ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
ሂደቱና ፈፃሚዎቹ በተለይ በሚታወቁባቸው መስፈርት ተመዝነው ኢንተርፕሪነርሽፕ ኢንተርፕርነር በሚል ስያሜ ዕውቅና በመስጠት መቶ ዓመታት ያስቆጠሩ አገራት አሉ፡፡ በተቃራኒው በኢትዮጵያ ገና 20ኛ ዓመቱን ሊያስቆጥር ነው፡፡ ኢንተርፕሪነርሽፕ ወይም ኢንተርፕሪነር የሚለውን ቃል፣ በቃሉ ውስጥ ያለውን ጽንሰ ሐሳብና ለሕዝቦች ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ለኢትዮጵያዊያንም መገልገያ እንዲሆን አስበው ተግባራዊ በማድረግ ሁለት አካላት ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ አንደኛው አቶ ሮቤርቶ ያኮና ሲሆኑ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ነው፡፡
በሙያቸው ነጋዴ ባይሆኑም ንግድን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል፣ ሕዝብንና አገርን ለማበልፀግ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ጠቃሚ መሆኑን በመረዳታቸው ምክንያት መጽሐፍ አዘጋጅተው በማሳተም የሚታወቁ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ፡፡ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር”ን ያሳተሙት ገ/ሕይወት ባይከዳኝ፣ “ጃፓን እንዴት ሠለጠነች”ን ያቀረቡት ከበደ ሚካኤል የመሳሰሉትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ልምዳቸውን ለሌሎች ማካፈል በመፈለጋቸው ምክንያት በንግድ ሙያ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ፣ ሥራውን እንዴት ማሻሻልና ማሳደግ እንደሚችሉ ለመጠቆም መጽሐፍ አዘጋጅተው በማሳተም አቶ ሮቤርቶ ያኮና ቀዳሚ ናቸው፡፡ “ሥራ” በሚል ርዕስ በ1985 ዓ.ም ያሳተሙት መጽሐፍ የደራሲውን የትውልድ፣ የትምህርት፣ የቤተሰብና መሰል ታሪክ በዝርዝር ባያቀርብም፤ ባለሀብቱ ከትንሽ ሥራ ተነስተው ትልቅ ደረጃ ላይ እንዴት መድረስ እንደቻሉ ከልምዴ ተማሩበት በማለት በቀናነት ተነሳስተው ያዘጋጁት መጽሐፍ ነው፡፡
አቶ ሮቤርቶ ያኮና ከቀድሞው ዘመን ፀሐፊዎች በሁለት ነገር ይለያሉ፡፡ አንደኛው ራሳቸው በተግባር ካለፉበት በመነሳት ነው ሌሎች እንዲሚሩበት መጽሐፍ አዘጋጅተው ያቀረቡት፡፡ ሌላው በአማርኛ ቋንቋ ባዘጋጁት መጽሐፍ ውስጥ ኢንተርፕሪነር የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በመጠቀም ቀዳሚው ናቸው፡፡ መጽሐፉ ሥራ ፈጠራ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፤ ዕድገት፣ ፈጣን ለውጥ፣ ቀጣይነት ያለው ባለሀብትና ባለሥራ መሆን እንዴት እንደሚቻል “Entrepreneur” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በመጠቀም ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎችን ለመርዳት ጥረት አድርገዋል፡፡
አቶ ሮቤርቶ ያኮና በመጽሐፋቸው መቅድም የሚከተለውን ሐሳብ አስፍረዋል:-
“ዓለም አሁን ከሚገኝበት የሥልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሰው እንዲሁ በተአምር አይደለም፣ ሌት ተቀን ተግቶ በመሥራት ነው፡፡ ለራሴ ብሎም ለአገሬ ምን ልሥራ ብሎ በመመራመርና {vሰበውን ለመሥራት በአደረገው ጥረት ነው፡፡
እያንዳንዱ ሰው ለአላማው ጥረት ከአደረገ እውቀቱን ለሌላው ማካፈል ከቻለ፣ እራሱን ይጠቅማል፡፡ ሌላውን ይረዳል፣ አገሩን ያሳድጋል፡፡ እውቀቱን ያካፈለ ባለሙያ ድርሻውን በመወጣቱ የህሊና ደስታና የአእምሮ እርካታ ያገኛል፡፡
“እዚህ ላይ ስህተት እንዳይደረግና ጉድለት እንዳይፈፀም ለሚደረግ ጥንቃቄ ቀደም ብሎ በሌላው ላይ የደረሰውን ችግር መረዳት ይጠቅማል፤ የአንድ ሥራ መበላሸት ብዙ ዓይነት ጉዳት አለው፣ የጊዜ በከንቱ መጥፋት፣ የጥሬ ዕቃ አላግባብ መበላሸት፣ የጉልበት በከንቱ መጥፋት፣ የደንበኞች በሁኔታው ማዘን፣ የተሠሩትን ዕቃዎች እንደገና ለመሥራት ተጨማሪ ወጭ ማድረግ፣ የመሳሰሉት ችግሮች ውስጥ ያለፍኩ ስለሆነ ሌሎች እንዲማሩበት ከልምዴ በመነሳት መጽሐፉን አዘጋጅቻለሁ ይላሉ፡፡
የኢንተርፕሪነርሽፕን ጽንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፋት ጥረት ያደረጉ አቶ ሮቤርቶ ያኮናን መሰል ሌሎች ግለሰቦችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ በቀጣይነት ትልቁ ሥራ የተሰራው ግን በተቋም ደረጃ ነበር፡፡ ኢምፐርቴክ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሶሳይቲ “የብልፅግና ቁልፍ ቁጥር 1” በሚል ርዕሰ በ1999 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፍ ላይ የሚከተለው ታሪካዊ መረጃ ሰፍሯል፡፡
በ1970ዎቹ ኢንተርፕሪነርሽፕን ለማስተዋወቅ ሙከራ አድርገው እንደነበርና የደርግ መንግሥት ይከተለው በነበረ የእዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት ምክንያት እንዳልተሳካ የሚገልፁት አቶ አንዱዓለም ተገኝ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፀሐፊ በነበሩበት ወቅት በ1987 ዓ.ም በUNDP፣ UNIDO ፣ UN-DDSMS፣ EDII - India እገዛና ከፍተኛ ተባባሪነት የመጀመሪያው የሙከራ የኢንተርፕሪነርሽፕ ስልጠና መካሄዱን ያብራራሉ፡፡
አሁን በኢንተርፕሪነርሽፕ ዙሪያ እየሰሩ ያሉ ማህበራት፣ ስልጠናውን በመስጠት የሚታወቁ ተቋማትና ግለሰቦች፣ የኢንተርፕሪነርነት መለያ ያላቸው ባለሀብትና ሥራ ፈጣሪዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በ1987 ዓ.ም የተጀመረው ስልጠና ያስገኛቸው ውጤት መሆናቸው ይነገራል፡፡
ኢንተርፕሪነርሽፕ የሚለው ቃል ታች ካለው የሕብረተሰብ ክፍል እስከ ከፍተኛ ባለስልጣናት ድረስ ለአንደበት ቅርብ ሆኗል፡፡ ዘንድሮ የኢንተርፕሪሮች ሳምንትን ካከበሩት 123 የዓለም አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ሆናለች፡፡ በዓሉ በአገራችን መከበር በመጀመሩ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ የተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ ኢምፐርቴክ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሶሳይቲ፣ አድማስ ዩኒቨርስቲ የመሳሰሉ የተለያዩ ተቋማት የየራሳቸውን ዝግጅት በማሰናዳት በዓሉን አክብረዋል፡፡ ማክሰኞ ህዳር 5 ቀን 2004 ዓ.ም በ6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ እሸቱ ጮሌ ህንፃ ውስጥ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ የዓመቱ ምርጥ ኢንተርፕሪነር ተብላ የተመረጠችው ወ/ሮ ቤተልሔም ጥላሁን ከኢንተርፕሪነሮች ሳምንት አዘጋጆች ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡ የበረባሶ ጫማን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የታወቀችውና የሶል ኮብል ካምፓኒ መሥራች ወ/ሮ ቤተልሔም “በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ሽልማቶችን አግኝቻለሁ፤ ይህ ሽልማት ግን በአገር ውስጥ የመጀመርያው ነው” ብላለች፡፡

 

Read 6847 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 15:06