Saturday, 31 August 2013 12:38

“ላማ ሰበቅታኒ”

Written by  ከዮሐንስ ገ/መድህን
Rate this item
(0 votes)

የውድነህ ክፍሌ ፋንታዚ
በፀሐፌ ተውኔትነቱ የምናውቀው ውድነህ ክፍሌ ሰሞኑን “ላማ ሰበቅታኒ” በሚል ርእስ 174 ገፅ ያለው መፅሐፍ እነሆ ብሎናል እንድናነብ፡፡ የመፅሐፉ ደራሲ በመግቢያው ላይ “ይህ መፅሐፍ በአብዛኛው ገደብ የለሹን የስነ-ፅሁፍ ዘውግ በእንግሊዝኛው fantasy የተሰኘውን የአፃፃፍ ቅርፅ ተከትሏል” ይላል፡፡ የስብሐት ገ/እግዚአብሔርን “ስምንተኛው ጋጋታ” ልብ ይሏል፡፡ ነገሩን ካነሳሁት አይቀር አለማየሁ ገላጋይ ባሳተመው “መልክአ ስብሃት” የተሰኘ መፅሐፍ ውስጥ፣ ፀደይ ወንድሙ የተባለች ፀሐፊ፤ “እውን አከል- ህልም፣ አለማዊነትና ህይወት በስምንተኛው ጋጋታ ውስጥ” በሚል ርእስ እንዲህ ስትል ፅፋለች፡- “ይህ አጭር ፅሁፍ የስምንተኛው ጋጋታን የድርሰት ዓለም በመፈተሽ ፋንጣዚ (fantasy) ብቻ ሳይሆን ህልመ-አለማዊ (surrealist) ነው፣ እንዲሁም ከእውን አከል (Virtual reality) አንፃር ሊታይ ይችላል የሚል አቋም ይዞ ተዘጋጅቷል፡፡”
ይህ የፀደይ ወንድሙ የፅሁፍ መግቢያ ለውድነህ ክፍሌ “ላማ ሰበቅታኒ”ም ተስማሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ፋንጣዚ (አንዳንዶች እንደሚሉት ፈንጠዝያ) ብቻ አይደለም፤ ህልመ-ዓለማዊ ብቻም አይደለም፡፡ እውን አከል የሆነን ምስል እንድናይ የሚያደርግም ነው፡፡
በምዕራፍ አንድ በወዶ ዘማችነት “እናት ሀገር ወይም ሞት” ብሎ ጦር ሜዳ የዘመተና አንድ እግሩን፣ አንድ እጁንና አንድ ዐይኑን አጥቶ የመጣ ስም የለሽ ሰው… ወደ ቀዬው ሲመለስ ሚስቱ ሌላ አግብታ የጠበቀችው ሰው፤ ከራሱ ጋር የሚያደርገውን መብሰልሰል ምሬቱን ያስደምጠናል።
“አይ እግሬ? በእግሬ ስላሰብኩኝ እንጂ መቼም በጭንቀላቴ ባስብ ከገባሁበት ቤት “አልወጣም” ብዬ መከራከር እችል ነበር፡፡ ግን እኔ ለመሆኔ ደግሞ ምን ምስክር አለኝ? ሞተ ተብዬ ብቀበር አይደለም እንዴ ጡረታዬ እየተበላ ያለው፡፡ ለነገሩስ አሁንስ ላለመሞቴ ምን ማረጋገጫ አለኝ? ከአካሌ ሦስቱ ቀድመውኝ ተቀብረዋል፡፡ በመቶኛ ቢሰላኮ ግማሽ ሊሞላ ምን ይቀረዋል?”
(ምዕራፍ ሁለት፤ ገፅ 9) እያለ ይነግረንና ገፅ 14 “ሰው መሆን መረረኝ! መረረኝ! ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ እልሃለሁ፤ ስትፈልግ ድመት አድርገኝ! ድመት! እደግመዋለሁ ድመት!”
በምዕራፍ ሶስት ድመት ሆኖ በድመትኛ ያወጋናል፡፡ ልክ እንደ ስብሃት ኮምቡጡር፡፡
“እህ! አንተ ኮምቡጡር አይደለህም እንዴ?”
“ነኝ”
“እኮ ኮምቡጡር የኛ ውሻ?”
“አዎን”
“ታዲያ ከመቼ ወዲህ ነወ የሰው ቋንቋ የተማርከው ባክህ?”
“እርስዎ እንጂ የእንስሳት ቋንቋ መቼ ነው የተገለፀልዎት?”
በዚህ የፋንጣዚ አፃፃፍ ገደብ የለሽነት እንደፈለጉ መሆን፣ የፈለጉትን ማለም ይቻላል፡፡ በዚህ ሁሉ መሃከል ግን የሚነግረን እውን አከል ወግ ደግሞ አለ፡፡ በምዕራፍ ሶስት ድመቱ በድመትኛ እንዲህ ያወጋናል፡-
“ድመት ድመትን አትሸውድም… ድመት ቁጣዋም ፍቅሯም ለድመት ፊት ለፊት ነው። ‘አይጤን አትንኩብኝ፡፡’ የሚል ድመት አይጡ እንዲነካበት አይፈልግም፡፡ ድመት ለድመት ድብብቆሽ አይወድም፡፡ የኛ ድብብቆሽ ከአይጥና ከሰው ጋር ብቻ ነው፡፡ ሰው ግን ድብብቆሽ ነው ህይወቱ፡፡ በዚህ ግቢ እንኳን የማየው ድብብቆሽ ያስገርመኛል፡፡ ያውም ትንሽ ሰው በሚኖርበት ቤት፡፡”
እያለ በዚያ ግቢ ወስጥ የሚመለከተውን የሰው ስራ በትዝብት ያወጋናል - ጆሮው ላይ ሎቲ ያንጠለጠለውና ቴሌቪዥን ሲመለከት የሚውለው ድመት፡፡
ከምቾት ኑሮው ባለቤት ነኝ የሚሉ አሮጊት መጥተው፣ ሎቲውን አውልቀው ድጋሚ እንዳይጠፋ ጭራውን ቆርጠው በር ዘግተውበት ይሄዳሉ፡፡ ቁንጫዎች ሰውነቱን ሲወሩት ድመት መሆን በቃኝ! በ…ቃ…ኝ!” ይላል፡፡ በምዕራፍ ስድስት ውሻ ሆኖ ብቅ ይላል - እንዲህ ሊያወጋን፡-
“ሰምቶ መቻል ምንድን ነው?” አባወራው ጠየቀኝ፡፡ ቋንቋዬ አይገባውም፤ ሃሳቤም አይረዳውም፡፡ ብዙ ጊዜ እኛ ውሾች ሰዎች የሚሉንን እንረዳ ይሆናል እንጂ ሰዎች እኛ የምንለውን ሊረዱን አይችሉም፡፡ የሚረዱት ነገር ቢኖር ውሻ ታማኝ ወዳጅ መሆኑን ብቻ ነው። ታማኝ ስለሆንን ከአጥቂ ይከላከሉናል ብለው ልባቸውን ይሰጡናል። ስላልተግባባንም የማየው አይታያቸውም፡፡ የማዳምጠውን አይሰሙም፡፡ እነሱ የሰሙትና ያዩት ብቻ ትክክል እንዲሆን ይፈልጋሉ፤ የኔን ማየት ካላስተዋሉ፣ ስህተቱ የኔ ሆኖ ጀርባዬ ላይ ቆመጥ ያርፍብኛል፡፡
“በተኛሁበት እሪ ብዬ ስጮህ አሳልፈው የሰጡኝ ወዳጆቼ በአስገራሚው አመታቱ አጨበጨቡለት። ሲያጨበጭቡለት እሱና ከስክስ ጫማው ባሰባቸው። እየደጋገመ ሰውነቴ ላይ ዘለለበት፡፡
በቃ…በቃኝ! ስትፈልግ አህያ ወይንም በረሮ አድርገኝ! በረሮ ብሆን ይሻለኛል፡፡
በረሮ!...
(ከምዕራፍ አስራ ሶስት እስከ መጨረሻው) ከበረሮው ጋር እያወጋን እናዘግማለን… ምዕራፍ አስራ ሶስት፤ ገፅ 111 ላይ)
“እኔ ብልጥ ነኝ… አራዳ በረሮ! እንደዚህ ያለ አደጋ ከመድረሱ በፊት በቤቴ ወስጥ ሁለት ውድ ንብረቶች አሉ፡፡ አንዱ ባይሰራም ጥቁርና ነጭ ቲቪ ነው፡፡ ሌላኛው አሮጌ ፊሊፕስ ሬዲዮ! እኔ ለብዙ ጓደኞቼ በችግር ጊዜ ከነዚህ ምሽጐች አትራቁ እላቸዋለሁ፡፡ እነሱ ግን አይሰሙም፡፡ ባለመስማታቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው በረሮዎች ተበልተዋል፡፡
“እኔ ቅፍፍ ካለኝ ለሊትም ቢሆን ከነዚህ ምሽጐች መራቅ አልፈልግም፡፡ በተለይ ቲቪው ይመቸኛል፤ ሰፊ ነው፤ ጭለማው ውጡ ውጡ አይልም፡፡ አቧራና ጥቀርሻው ተፍ ተፍ ይላል፡፡ የሚተነፍገው ሽታ በሀሴት ይሞላል፡፡ እዚህ ቲቪ ውስጥ የሚበላ አይጠፋም… ካሉት ስፍር ቁጥር በረሮዎች ውስጥ በእያንዳንዱ ለሊት በእርጅና፣ በረሃብ፣ በፀብና በህመም የሚሞቱ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ለኛ በስጋ ላለነው መኖ ይባላሉ፡፡
በዚህ መፅሐፍ ውስጥ በወዶ ዘማቹ ሰው፣ በድመቷ፣ በውሻውና በበረሮው በኩል የተነገሩን እውነታዎች ብዙ ናቸው፡፡ በረሮዎቹ በአሮጌው ቲቪ ውስጥ ያደረጉት ድንገተኛ ስብሰባ የሚያስተላልፍው መልእክት እንዲሁ ስለ በረሮ ብቻ የሚተርክ ትረካ አይደለም፡፡ ለእያንዳንዳችን ልብ የሚደርስ አንዳች ሹክ የሚለን ነገር አለ፡፡ በረሮው በመጨረሻ ገፅ 174 “በቃኝ!.. ሰለቸኝ!… ቀፈፈኝ! በረሮ መሆን መረረኝ!… ሰው መሆን ይሻለኛል… በቃ… ሰው! ….” ይለናል፡፡
ሰው መሆን ሸጋ ነገር ነው፡፡ እንደኔ ከሆነ የውድነህ ክፍሌ “ላማ ሰበቅታኒ” ሸጋ ፅሁፍ ነው። ሸጋ ነው ስል የአለማየሁ ሞገስን አንድ ቅኔ በማስታወስ ነው፡፡
ጓዒ… ጓዒ ጉባዔ ቃና ድመት
አምጣነ ተክወ ለኪ ልበ ተማሪ ወተት
ትርጉም - አንቺ ድመት የሆንሺው ጉባዔ ቃና
ነይና ወተት የሆነውን የተማሪ ልብ ላሺው
አንባቢዎችስ… እንደ ተማሪ መሆናችን አይደል? የነገ ሰው ይበለን!

 

Read 2649 times