Saturday, 31 August 2013 12:34

ስብሐትን ሳይሆን ራሳቸውን የተረኩልን ፀሐፍት!

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

ካለፈው የቀጠለ
ይህን ካለፈው ፅሑፍ የቀጠለ ምልከታ እንድንጽፍ መነሻ የሆነን መፅሐፉ (“መልክአ ስብሃት”) ውስጥ ያለ አንድ የካርቱን ስዕል ነው፤ ካርቱኑ ስብሃት ላይ የተንጠለጠሉ ሰዎች ያሳያል፡፡ ሰዓሊው ካርቱኑን የሳለው መቼ እንደሆነ ባናውቅም 2004 ብሎ ፈርሞበታል፡፡ ማለታችን ካርቱኑን የሳለው “መልክአ ስብሀት…” ውስጥ ያሉትን ፅሑፎች ረቂቅ በሙሉ አንብቦ ይሁን አይሁን አናውቅም፡፡ እኛ ግን “መልክአ ስብሃት...” ውስጥ ያሉ ፀሐፊዎችን ብቻ ወስደን፣ ከሰላሳዎቹ ውስጥ ምን ያህሉ ስብሃት ላይ ለጉድ እንደተንጠለጠሉበት እናሳያለን፡፡ የምንጠቅሳቸው ፀሐፊዎች መልክአ ስብሃታቸውን የፃፉት ስብሃት እንዴት እንደሚያያቸው (ያያቸው እንደነበር፣ አሁንም የሚያያቸው ይመስላቸው ይሆን እንዴ?) ነው፡፡
ለአንባቢዎች ሌሎች ፀሐፍት ስብሃትን እንዴት እንደሚያዩት ብቻ ሳይሆን፣ሌሎች ፀሐፍትን ስብሃት እንዴት እንደሚያየቸው (ያያቸው እንደነበር) ሊያሳዩን በየበኩላቸው የጣሩትን ማየቱም፣ ሰብሰብ አድርጎ ማቅረቡም አንድ ነገር ነው፡፡ እንዲያ ለማድረግ የሞከሩትን ሰባት ፀሐፍት በንዑሳን ርእሶች እናሳያለን፡፡ ዘናጩ ደራሲ እና ስብሃት (አለማየሁ ገላጋይ) እብዱ ጂኒየስ እና ስብሃት (ከበደ ደበሌ ሮቢ) “አሜሪካዊው” ባለቶክ-ሾው እና ስብሃት (መስፍን ሃብተማሪያም) ወጣት ደራሲ መሆኑ የማይቀረው ሰው እና ስብሃት (ጌታቸው ወርቁ)፣ ሞጋቹ ጠያቂ እና ስብሃት (ተሾመ ገብረስላሴ፣ አባቱ፣እሱ፣ እና ስብሃት (አልአዛር ኬ)፣ የሆነ ሰውዬ እና ስብሃት…በሚሉ፡፡
ይህቺ እኔ እና ስብሃት ብላ ነገር አልተመቸችንም፤ እንዲያውም አንድ ቀልድ አስታወሰችን፤ ስብሃትና አንዱ ናቸው አሉ፤ አንዱ ስብሃትን፡-
“ስብሃት የአምስት መቶ ብር ጥያቄ?” ይለዋል፡፡
“እንስማዋ፡፡”
“የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ስንት ነው?”
“በርግጠኛ እርግጠኝነት አናውቀውም፤ ግን እንሞክር፡፡”
“ሸጋ፡፡”
“ሁለት ናቸው፡፡” አለ ስብሃት ብዙ ከአሰበ በኋላ፡፡
“ምን?! ሁለት ብቻ?!”
“አንክት!”
“እሺ ይሁን፤ ሁለቱ እነማን ናቸው?”
“እኔ እና ሌሎች፡፡”
ዘናጩ ደራሲና ስብሃት (አለማየሁ ገላጋይ)
የነሐሴ 11 ቀን የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ስብሃት ላይ የመንጠልጠል ጣጣ” በሚል ርዕስ የጻፈው መልካም ሰው አባተ ተሳስቷል እንላለን፡፡ መልካም ሰው አባተ እንደጻፈው አለማየሁ ገላጋይ ስብሃትን ቅዱስ አላደረገውም፡፡ ከሁሉም ልቆ ስብሃት ላይ የተንጠለጠለው አለማየሁ እንደሆነ እናውቃለን፤ ግን ቀድሶት ሳይሆን አርክሶት ነው። ምክንያቱም ገጽ 245 ላይ እንዲህ ብሎ ጽፏላ፡- “እንግዲህ ከብዙ መስፈርቶች አንጻር ለተበላሸው የደራሲነት ሰብዕና ምንጭ ሆኖ የምናገኘው ስብሃት ገብረእግዚአብሔርን ይሆናል፡፡”
“በስብሐት የጠፋውን የደራሲነት ስብዕና ፍለጋ” በሚለው ፅሑፉ አለማየሁ ገላጋይ፣ ስለአለማየሁ ገላጋይ እንዲህ ጽፏል፡-
“ደራሲ እንዴት ያለ ቁመና አለው? ብዬ እራሴን የጠየኩበት የመጀመሪያ ገጠመኜ ይሄ ነው፡- 2001 ክረምት ይመስለኛል የሐዋሳው 60 ሻማ የሥነ-ጽሑፍ ክበብ እንግዳ ሆኜ እንድገኝ ጋብዞኛል። ስምምነቴን በቃል ሳረጋግጥ የክበቡ ተወካዮች ለቅድመ-ዝግጅት ስለፈለጉኝ እዚሁ የአዲስ አበባዋ ፒያሳ አንድ ካፌ ውስጥ ተቀጣጠርን፡፡ በአካል ስለማንተዋወቅ በሞባይል ምሪት ለመገናኘት ነበር ተስፋ ያደረግነው፡፡ ጥቂት ዘግይቼ ስለነበረ ይመስለኛል የክበቡ ተወካዮች ደውለው ካፌው በረንዳ ላይ እንደተቀመጡ ነገሩኝ፡፡ እቦታው ስደርስ መንገድ መንገዱን በጉጉት የሚመለከቱ ሁለት ሰዎች አይቼ፣ እነሱ መሆናቸው ገባኝ፡፡ አጠገባቸው ስደርስ በፉክክር መልክ “ያ ነው”፣ “አይ ያኛው ነው” ይባባሉ ነበር፡፡ ጠረጴዛቸውን ከከበቡት ክፍት ወንበሮች አንዱ ላይ ለመቀመጥ ፈቃዳቸውን ጠየቅሁ፡፡ እንድቀመጥ ፈቅደውልኝ ልብም ሳይሉኝ አሁንም መንገዱ ላይ አይናቸውን አነጣጠሩ፡፡
“ያ ነው”
“አይ፣ ያኛው ነው”
እኔን እንዳይገምቱ ያደረጋቸው ሁኔታ ጥያቄ ስለፈጠረብኝ ዝም ብዬ ተቀመጥኩ፡፡ እኔ ስለመሆናቸው የሚጠረጥሯቸው ሰዎች በኑሮ የተጎሳቆሉና ድሎት የማይታይባቸው ነበሩ። የጠረጠሩዋቸው አልፈው ሲሄዱ ደግሞ ሌላ ጠውላጋ ፈልገው “ያውና” ይላሉ፡፡
“ሰው እየጠበቃችሁ ነው?” ስል ጠየኳቸው፡፡
“አዎ፣አዎ” ብለው አሁንም ከቁብ ሳይፅፉብኝ ለጠውላጋ አደን አይናቸውን ጎዳና ላይ ደገኑ፡፡
“እኔ ነኝ” አልኳቸው፡፡
ሁለቱም በመገርም ዞሩ፣በመገረም አተኮሩብኝ፣ በመገረም “አትመስልም፣አትመስልም” አሉኝ፡፡ ጥርጣሬአቸው መታወቂያ እስከመጠየቅ የሚዘልቅ አይነት ነበር፡፡
“እንዴት ዓለማየሁ ገላጋይን ሳልመስል ቀረሁ? ዓለማየሁ ገላጋይ ምን ይመስላል? በፅሑፍ እንዴት ተገምቶ ኖሯል?... ለደራሲ የተሰጠው አንዳች ተመሳሳይ ቁመናና ጠባይ በሁላችንም ውስጥ አለ ማለት ነው?”
ከአለማየሁ ገላጋይ ጽሁፍ የጠቀስነው ረዘመ አይደል? ምን እናድርግ ብላችሁ ነው? ይኸውላችሁ በአለማየሁ ገላጋይ አርታኢነት የተጻፈ “መልክዐ ስብሃት…” እንዲህ ሆነ፡፡ በዚህ ሁሉ ረዥም ጽሁፍ አለማየሁ ያልተጎሳቆልኩ እና ድሎት የሚታይብኝ ነኝ እያለ ነው፡፡ (እንዴት ነው ብዙ ስለማይበላ ሰው መጽሀፍ መጻፍ ያበላል እንዴ?)
አለማየሁ ሌላም ብሏል፡፡
አለማየሁ ገላጋይ በእጅ አዙር ፀጉሩን በየጊዜው እንደሚስተካከል፣ ባለትዳርነት እንደሚስማማው፣ እንደ ነገሩ ሳይሆን ሽክ ለማለት እንደሚለብስ፣ የአምላክ መኖርን እንደማይጠራር፣ የማያጨስ፣ የማይቅም፣ ጫማው ሁሌ የሚወለወል እንደሆነ፣ ጠውላገ ሳይሆን ደጓሳ፣ ንትርክ የሚጠላ እንደሆነ ጽፎልናል፤ በእጅ አዙር፡፡ ጎበዝ ልጅ¡
እብዱ ጂኒየስ እና ስብሃት (ከበደ ደበሌ ሮቢ)
የከበደ ደበሌ ሮቢ ፅሑፍ የወጣለት ስም ወይም ርዕስ “ህያው ስብሃት” ነው ብለናል፡፡ አንድ ጓደኛችን የከበደን ፅሑፍ ካነበበ በኋላ “አይ ከበደ ስብሃትን በጣም አካበደው” አለን፡፡ እኛ ደግሞ እንዲህ አልነው፡- “እራሱን ደግሞ ምን ያህል እንዳከበደ ብታስተውል እንዲህ አትልም ነበር፡፡” አባባላችንን በመረጃ እናስደግፋለን፤ ከበደ የፃፈውን እንጠቅሳለን።
“ተሰድበው የማያውቁ ሰዎች አሉ፤ በፍቅር በተለሰነ የቀልድ መልክ ባለው አቀራረብ እንኳ ተሰድበው የማያውቁ ሰዎች አሉ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እኔ አንዱ ነኝ፡፡ ጋሼ ስብሃት ባለበት አንዲት በፅሑፍ ጥበብ ዙሪያ ያለች ወዳጅ ምናልባት ለቀልድ ሊሆን ይችላል… ባለጌ… አለችኝ”
“ጋሽ ስብሃት እኔ ባለጌ ነኝ ወይ?” ብዬ ጠየኩት፡፡
“እውነቱን ለመናገር ነው ወይስ ከጉድ ለመውጣት…?” ብሎ ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰልኝ፡፡
“እውነቱን ለመናገር….” ብለው፡፡
“…አንተ እብድና ጂኒየስ ነህ እንጂ ባለጌ አይደለህም”
ለአንድ ስብሃትንም ከበደ ደበሌ ሮቢንም ለሚያውቅ ጓደኛችን መፅሐፉ ላይ ስብሃት ለከበደ ደበሌ ሮቢ አለ የተባለውን በጣታችን ጠቆምነው፡- “…አንተ እብድ እና ጂኒየስ ነህ…” አነበባት፡፡
“እናስ?” አለኝ፡፡
“ስለመወድሱ እርሶ ምን እንደሚሉ ለማወቅ ፈልገን ነው፡፡” አልነው፡፡
“የመጀመሪያዋ የመወድስ ቃል ትገባዋለች፣ ትሆነዋለች፤ ይውሰዳት፤ ሁለተኛዋን ግን ቢተዋት መልካም ነው፤ ሸክም ትሆንበታለች እንላለን፡፡” አለን፡፡
ከበደ ደበሌ ሮቢ ትንሽ ዝቅ ብሎ ደሞ እንዲህ ይላል፡-
“ስብሃት ለአብ፡- ራሱ የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማድነቅ የሚወድድ፣ በአድናቆት የተመላ፣ ገር፣ ደግና ጨዋ፣ ተዝቆ የማያልቅ ሰው ነው፤”
ይህን የሚለው ቀጥሎ ስብሃት ለሚወረውረለት የአድናቆት ድርጎ ሲያመአቻቸን ነው፤ ለዚህ፡-
“አንተ ገና ልጅ ሆነህ ይሄንን ሁሉ ከየት አመጣኸው ያለኝ ገና እንደተዋወቅን ነው፡፡ … በሌላ ጊዜ “ሩሶን ትመስለኛለህ” አለኝ፤ ሩሶ በነቮልቴር ዘመን የኖረ ፈረንሳዊ ፈላስፋ ነው፤…” (ዣንዣክ ሩሶ አብዶ ነው የሞተው)፤ ከበደ ደበሌ ሮቢ አሁንም ይቀጥላል… “…ውድ ተወዳጅ ወዳጃችን ዘነበ ወላ ቤት ለሰባት ሰዓታት ያህል በመነካትና በከፍታ ስናወራ ከቆየን በኋላ በመጨረሻ፡- “በርናርድ ሾውን ትመስለኛለህ” አለኝ፤ (ይታያችሁ በርናርድ ሾው እንግሊዞች የሚመኩበት ጸሃፌ ተውኔት ነው፤ ከበደ ደበሌ ሮቢስ? ምናልባት የዚያን ቀን ዘነበ ወላ ቤት የሚገርም ትያትር ሰርቶ ይሆናል፡፡)
“አሜሪካዊው” ባለቶክ-ሾው እና ስብሃት (መስፍን ሃብተማሪያም)
የመስፍን ሃብተማርያም ጽሁፍ ርዕስ “ስብሃት ሞቶም ይናፈቃል” ትላለች፡፡ እውነት ተብሏል፤ ስብሃት ናፍቆናል፡፡
“…የሳቅ ጨዋታ የድሮው ያሁኑ ውሎዎች አሳልፈናል፡፡ የሱ ቢበልጥብኝም እኔ የማስቀውን ያህል ያስቀኛል፡፡ “እስቲ ጋሽ ስብሐት ብርቅዬ ገጠመኝህን ወርውርልን” እያልኩ እንዲያስደስተን እኮረኩረዋለሁ፡፡ …ጥሩ ጨዋታ እሚያጫውቱት ሰዎች አገናኘዋለሁ፡፡”
እንዲህ ያለው መስፍን ኃብተማርያም፤ ስብሃት ለእሱ ነግሮት ካሳቁት ቀልዶች አንዱንም አልነገረንም፤ ወይም መስፍን ለስብሃት ነግሮት ስብሃትን ያሳቁትን ቀልዶች አንዳቸውንም አልጻፈልንም፡፡ ኃይለጎርጊስ ማሞ ከዚህ በፊት ስብሃት ጽፏት አንብበናት የማናውቅ ስብሃት ያጫወተውን አንድ ምርጥ ቀልድ ጽፎልናል፤ ስቀናል፤ የይሁዲው እና የካቶሊኩ ቀልድ አንደኛ ደረጃ ቀልድ ናት፤ ሰቃይ ቀልድ ናት፡፡
“በውሎአችን ሁሉ ሞቅ ብሎን ጨዋታ ሳጫውተው፣ ጋሽ ስብሐት በውስጤ የተደበቀውን ወይም ተዳፍኖ የሚላወሰውን የተዋናይነት ፍቅር እያሰበ፣ ትክ ብሎ ያየኝና የሚያምሩ ጥርሶቹን ፍልቅልቅ አድርጎ “አሜሪካ ብትፈጠር ቶክ ሾው ላንተ ነበር” ይለኝ ነበር፡፡”
ኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፤ አሁንም ለቶክ ሾው የአየር ሰዓት የሚሸጥ ይመስለናል፡፡
ደራሲ መሆኑ የማይቀረው ልጅ እና ስብሃት (ጌታቸው ወርቁ)
እከሌ ደራሲ ትሆናለህ ስለተባለ የሚኮን ነገር እንዳይደለ እናውቃለን፡፡ ጌታቸው ወርቁ ግን ከስብሃት ጋር ባሳለፋቸው ቆይታ ይህችን ነገር አይረሳትም፤ ጽፏት ለእኛም አድርሷታል፡፡
“አሁን መጨዋወት እንችላለን” አለኝ አይኑን ጨፍኖ፡፡ በወቅቱ በአእምሮዬ ላይ ይመላለስ የነበረውን አንድ ጥያቄ ወረወርኩለት፡፡ “አቦይ ለመሆኑ የተስፋዬ ገብረአብ ሥራዎችን የጋዜጠኛው ማስታወሻ እና የደራሲው ማስታወሻ አንብበሃቸዋል አልኩት፡፡”
“በሚገባ!”
“እንዴት አገኘኸው?” አልኩት፡፡
“አየህ አንተ እንግዲህ ወጣት ደራሲ መሆንህ ስለማይቀር (ይህቺ አባባሉ አንድ ጊዜም የአንባቢያን ጥያቄ በዓምዱ ላይ ሲመለስ “በጌቾ እድሜ ያላችሁ ወጣት አንባቢያን አንዳንዶቻችሁ ወጣት ደራሲ መሆናችሁ ስለማይቀር…” እያለ የሚፈጥረው ማነቃቂያ ናት) አስተውል፡፡ በአብዛኛው እውነት ከሀሰት ጋር ተጣምራ ነው የምትቀርበው፡፡ ተስፋዬም ይህቺን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አሪፍ ደራሲ ነዋ፡፡”
ጌቾ እንግዲህ ስብሃት እንደተነበየልህ፣ እንደበየነብህ ወይም እንደፈረደብህ የድርሰት ስራዎችህን እንደምታስነብበን እርግጠኛ ነን፡፡ እንዲህ ተባልኩ ያልከው እንደምትሆን ወይም እንደሆንክ አውቀህ ይመስለናል፡፡ ደራሲ መሆንህ አይቀርም ብሎሃል አይደል? ይቀር ይሆን እንዴ ብለን አንጨነቅም፡፡
አባቱ፣እሱ እና ስብሃት (አልአዛር ኬ.)
ስለእራስ በማተት በማተት፣ እዚህ መደበል ላይ የአላዛር ኬ “ስብሃት አባዬ እና እኔ” ከሁሉም ይልቃል፤ አንደኛ ነው፤ ይኸውላችሁ፡-
“ያደኩት አስራሁለት ወንድምና እህት የሆንን አባላት በነበርንበት ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ አራት ታላላቆቻችን የእውነትም ታላላቆቻችን መሆናቸው በግልፅ ያስታውቅ ነበር፡፡ በተቀረነው መካከል የነበረው የእድሜ ልዩነት ግን ከሁለት አመት ያልዘለለ ስለሆነ ሁሌም በአንድ ላይ ሆነን የሚያዩን ሰዎች፣ ታላቁን ከታናሹ ለመለየት በጣም ይቸገሩ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
አባታችን የቤተሰቡ ራስ ሲሆን እናታችን ደግሞ አባታችን ራስ ሆኖ የቆመበት ቤተሰብ ዋነኛ ምሰሶ ነበረች፡፡ መላው የቤተሰቡ አባላትም በዋናነት እናቴና አባቴ ያስፈፀሙት የሃይማኖታችንን ደንብ ስርዓትና ትዕዛዛት መሰረት ያደረገና ለረጅም ዘመን የዘለቀ ጠንካራና ጥብቅ የሆነ የእርስ በርስ ግንኙነት ነበረን፡፡ አብዛኞቻችን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከገባንበት ድረስ አንድም ጓደኛ እንኳ አልነበረንም፡፡ አንዳችን ለአንዳችን ወንድም ወይንም እህት ብቻ አልነበርንም፡፡ የምር ጓደኛሞችም ነበር፡፡ ከመካከላችን ለየት ያለው አባል አባታችን ነበር፡፡ እርሱ አባታችን ብቻ ሳይሆን እጅግ የቅርብ ጓደኛም ነበር፡፡ በተለይ ለእህቶቻችን የሚስጥር ጓዳቸው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ የምናደንቀውም ሆነ የምናነውረው ነገር በአብዛኛው ተመሳሳይ ነበር፡፡”
ከዚህ ቀጥሎ የዚህ አይነት አምስት ስድስት ሰባት … አንቀጾች ይቀጥላሉ፤ መጽሀፉ ላይ አሉላችሁ፡፡

ሞጋቹ ጠያቂ እና ስብሃት (ተሾመ ገብረስላሴ)
ይኸውላችሁ አሁን በረዥሙ ከምንጠቅሰው የተሾመ ገብረስላሴ ጽሁፍ ማን እና ምን ጎልቶ እንደወጣ ታዘቡ፡- “1992 ዓ.ም ክረምት ላይ ራስ መኮንን ድልድይ “ፋና ዴሞክራሲ አሳታሚ” (እፎይታ ጋዜጣ) ቢሮ የተስፋዬ ገብረአብ እንግዳ ሆኜ ስለዚህችው ስለኪነ ጥበብ እያወጋን እያለ በመሃል የጋሼ ስብሃት ስም ተነሳ፡፡ እንዲያውም ላስተዋውቃችሁ አለንና ጋሼ ስብሀት መቀመጫ ዘንድ ወሰደኝ፡፡ ጋሼ ስብሀት ኢንሳይክሎፒዲያ ያገላብጣል፡፡ ተዋወቁ አለን ተስፋዬ፡፡
“ጋሼ ስብሃት እጅግ ትሁት በሆነ እጅ መንሳት፣ እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ “ስብሃት” አለኝ፡፡ ሳቄ ሊመጣ ነበር፤ ረስቶኛል፡፡
“ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ልተዋወቅህ፤ ከአምስት ዓመት በፊት ይርጋለም ዶክተር አብርሃም አስተዋውቆን ነበር፡፡”
“አዎ አስታውሳለሁ፡፡ በጣም መጠየቅ የሚወድ ሞጋች ወጣት ገጥሞኝ ነበር፡፡ እርሱ ነኝ እንዳትለኝ!” አለ፤ ሶስታችም ተሳሳቅን፡፡
እርሱ በተካፈለበት “እፍታ” መጽሐፍ መድብል ውስጥ የኔም ጽሑፍ ስትካተት ደስታዬ ወሰን አልነበረውም፡፡
“ከአራት ዓመት በኋላ በድሉ ህንጻ ፊት ለፊት ካለው አሸናፊ መጽሐፍት መደብር ውስጥ ቁጭ ብሎ በአትኩሮት ሲያነብብ አገኘሁት፡፡ ያኔ እኔ ራዲዮ ፋና የኪነ ጥበብ ፕሮግራም አዘጋጅ ነበርኩ፡፡ በፕሮግራሙ አንድ አከራካሪ አጀንዳ ይነሳና ለሳምንታት፣ለወራት እያነጋገረ እንዲቀጥል የማድረግ አካሄድ እከተል ነበር፡፡ “ኪነጥበብ ለጥበብነቱ ወይስ ለማህበራዊ ፋይዳ?” የሚል አጀንዳ አንስቼ ብዙዎች ሙግት የገጠሙበት ጊዜ ስለነበር እርሱንም ላሳትፍው ጠየቅሁት፡፡
“ሙዱ” ጥሩ ስለነበር ቴፔን አውጥቼ በክርክርና ጥያቄ አጣደፍኩት፡፡
የሆነ ሰውዬ እና ስብሃት
“መልክዐ ስብሃት…” ላይ “ስብሃትን ከሌላ መዐዘን” የሚል ጽሁፍ አለ፡፡ የዚህ ሰው ጽሁፍ መነጋገሪያ ሆኗል፤ ሚልኪ ባሻ የሰውየውን ጽሁፍ “ዱልዱም ሰይፍ” ሲለው፣ ጠርጢዮስ “ባለሁለት ሰይፍ ጽሁፍ” ነው ብሎ ጽፏል፤ ከዚያ ለጥቆም ሚልኪ ባሻ በመልስ ጽሁፉ ተነስቶ ስብሃትን ለምን የጎሪጥ እንደሚያየው፤ አፍጥጦ አይቶት አሳየን፤ መልካም ሰው አባተ ደግሞ “ስብሃትን ከሌላ ማዕዘን” የሚለውን ጽሁፍ የጻፈው ሰውን ስብሃት ላይ አትንጠላል ብሎታል፡፡
የዚህ ስብሃት ወጣትነቴን አባከነብኝ የሚል ብኩን ጸሀፊ (እራሱ ነው ባከንኩኝ ያለው፣ አይዞህ አይባል ነገር¡)፣ስብሃትን ሰነፍ ጸሀፊ ነው ይላል፡፡ ኢዮብ ካሣ ደግሞ “በመልክዐ ስብሃት…” ገፅ 236 ላይ ያሰፈረውን መመልከት ይቻላል፤፡- “ለሥራው በነበረው ፍቅር (passion) እና ዲሲፕሊንም ቢሆን የተሻለ እንጂ ያነሰ አልነበረም፡፡ ጋሽ ስብሃት ከ10 በላይ መጻህፍትን ያበረከተልን ለጋዜጦች ወይም ለመጽሄቶች በሳምንት ይሁን በወር ከሚያቀርባቸው መጣጥፎች ጎን ለጎን ነበር፡፡ በአዲስ ዘመንም ሆነ በአዲስ አድማስ ጋዜጦች በአምደኝነት (colomunist) ሲሰራ ስራዎቹን በሰዓቱ ከማቅረብ የተስተጓጎለበት ጊዜ አልነበረም ወይም ስለማስተጓጎሉ ሲነገር አልተሰማም፡፡ ለምሳሌ በህይወት ዘመኑ ማገባደጃ ገደማ፣ በአዲስ አድማስ ላይ ሲፅፍ የሁለትና የሶስት ሳምንቶችን ፅሑፎች ቀደም አድርጎ ይልክ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ይሄ ዲሲፕሊኑ በሰራባቸው የህትመት ውጤቶች ዘንድ ሁሉ በግልፅ የሚነገርለት ሀቅ ነው፡፡ ክፋቱ ግን አክብሮት እና እውቅና ለማግኘት እንደተጨማሪ ነጥብ አልተቆጠረለትም፡፡ ፅድቁ ቀርቶብሽ በወጉ በኮነነሽ የሚለው ተረት እውን የሆነ ይመስላል…” በእርግጥ እውን ሆኗል እንላለን፡፡
ስብሃት ሰነፍ እንዳልሆነ ሌላም ምርቃት አለን፤ ጌታቸው ወርቁ ከፃፈው የምንዋሰው፣ መልክዐ ስብሃት ገፁ 80 ላይ ጌቾ (እንዲለው ስብሀት) እንዲህ ፅፏል፡- ያኔ በየሁለት ሳምንቱ ለንባብ በምትቀርበው ሮዝ መፅሔት ላይ ይፅፍ ስለነበር…. ይሁን እንጂ ነባር ፅሁፎቹ እንዳይደገሙ ከእድሜው ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ አመም የሚያደርገውን ሁሉ ችሎ አዲስ ለመፃፍ ሲታትር ላይ በእውነት እቀናበት ነበር፡፡ አይበቃም? ስብሃት ሰነፍ እንዳይደለ የሚናገር ሌላም ምስክር እንመርቅ፡፡ ምን ምን ላይ እንደፃፉት ባላውቅም አለማየሁ ገላጋይ የጻፉት ምስክር ናት፡- አለማየሁ ስብሃት ቤት ሲደርስ ስብሃት በአንድ እጁ ሀዱን ግጥም አርጎ ይዞ፣ በሌላ እጁ ብዕር ግጥም አድርጎ ይዞ ስቃይ ፊቱ ላይ እየተነበበ ይፅፋል
“ምን ሆነሀል?” አለማየሁ፡፡
“አሞኛል፡፡” ሰነፉ ሰውዬ፡፡
“እና ምን እያደረክ ነው?” አለማየሁ፡፡
“እየፃፍኩ፡፡” ሰነፉ ሰውዬ፡፡
“እንዲህ እያመመህ ምንድነው የምትፅፈው?” አለማየሁ፡፡
“ለዚህ ሳምንት የሚሆን ፅሁፍ፡፡” ሰነፉ ሰውዬ፡፡
“አሞሀል ፤ ለምን አትተወውም?” አለማየሁ፡፡
“አንተ ነህ እንዳመመን አይተህ ያወቅከው፤ አንባቢዎች በምን ሊያውቁ ይችላሉ?” (ወይስ አሞናል ብለን አዋጅ እናስነግር? ሳይል ይቀራል፡፡ አይልም አይባልም፡፡)
እና “ስብሃት ገብረእግዚአብሄርን ከሌላ ማዕዘን” በሚል የጻፈው እና ስብሃት “ሰነፍ እና ወጣትነቴን ያባከነብኝ ሰው ነው” የሚል ሰነፍ እና ብኩን ፀሀፊ፤ ስብሃትን ከወቀሰባቸው ጉዳዮች መሀል አንደኛው እንዲህ የሚል ንዑስ ርዕስ አለው፡- የአባት ጉርሻ፡፡ ከዚህ ስር የተፃፈውን እንጥቀስ፡-
“ከስብሐት ጋር ጥቂት ዘመናት ያሳለፍን ወጣቶች የስብሃትን “የአባት ጉርሻ” እናውቃለን፡፡ ዘነበ ወላ ስለዚህች ጉርሻ አጠራጣሪነት በማስታወሻ ላይ ሲመሰክር፡-
“በኔና በአብሮ አደጎቼ መካከል ያሳለፍነውን ህይወት በፈጠራ ጥበብ ተጠቅሜ የጻፍኩትን ሳነብለት ይደሰታል፡፡ አንዳንድ ቀንም “ልጅነትን አንብብልኝ እንጂ ይለኛል፤ የጠየቀኝን አደርጋለሁ፡፡ አንዴ አንዷን ምዕራፍ አንብቤ እንዳጠናቀቅሁለት ተነስቶ ቆመ፡፡ ወገቡን ይዞ ቁልቁል እያስተዋለ “ለዚህ መጽሐፍ እኔ ነኝ መግቢያውን የምጽፍልህ… Master Piece ወደ አማርኛ ስነጽሑፍ እየመጣች ነው” አለኝና ለሽንት ወጣ፡፡ … “በእንዲህ ባለ የአድናቆት ወቅት የማደምጠው አስር በመቶውን ያህል ብቻ ነው” ይለናል፡፡ ዘነበ ወላ ሲያብል ካልሆነ በስተቀር የስብሀትን አድናቆት አስር በመቶ ብቻ የሚወስድበት በቂ ምክንያት የለውም፡፡ ስብሐት ለርሱ አዋቂ ነው፡፡ ልባዊ ነው፡፡ ሽንገላና ውዳሴ ከንቱን የሚጠየፍ ነው፡፡ ታዲያ ስለ ዘነበ ወላ “ልጅነት” ያቀረበው ያድናቆት አስተያየት በምን ሰበብ ዘጠና በመቶ የሚወድቅ ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ዘነበ ወላ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ስለራሱ ያለው ግምት በስብሀት አስተያየት አልተነካም ቢለን ለማመን እንቸገራለን፡፡ ምክንያቱም ዘነበ በዚህ አባባሉ አንድም ስብሀት ይዋሻል፣ ይሸነግላል እያለን ነው፤ አንድም ደግሞ ከሥር ጀምሮ ስለስብሀት ልባዊነትና እውቀት ሲነግረን የመጣውን ሊያፈርሰው ነው ማለት ነው፡፡
የስብሃትን ጉርሻ በተመለከተ ሰዎችን በሶሰት መክፈል እንችላለን፤ አንድ፡- የስብሃትን ጉርሻ ለራሳቸው ያጎረሱ፡፡ ሁለት፡- ስብሃት ጉርሻውን ያጎረሳቸው፡፡
ሶስት፡- የስብሃት ጉርሻ እንዳማራቸው የቀሩ እና እጅጉን የተናደዱ፡፡እዚህ ጋር አንድ ያስተዋልነው ነገር ቢኖር፣ ፀሀፊው የስብሃትን ጉርሻ ያላገኘ ይመስላል፤ እናም ባለማግኘቱ በጣም የተናደደ እና የተቆጨ፤ እጅግ ስንጠራጠር ደግሞ፣ እጅግ በጣም የተናደደው እሱ እንዳለው ስብሀት ለሁሉም የሚያድለውን፡- “…ልባዊነት የማይነበብባቸው የግድ የለሽ አስተያየቶች…” ስላልደረሱት ይሆናል፡፡ ምስኪን!
አንድ የምታስቀኝ ነገር አለች፤ ዘነበ ወላ ማስታወሻ ላይ ጽፏት ያነበብኳት ናት፤ ዘነበ ወላ በደንብ ቢያስተውላት የሚጽፋት አይመስለኝም፡፡ የማስታወሻ ጽሁፍ ስራ እንዴት እንደተጠነሰሰ ነው የጻፈው፡፡ ስብሃት ዘነበን እንዲህ አለው፡-
“ሞትን እንቅደመው/እናሸንፈው እንዴ? ”አለ ስብሀት፡፡
“አዎ፡፡” አለ ዘነበ ወላ፡፡
“በል በቃ ስለኔ ጻፍ፡፡”
ማስታወሻ ተጻፈ፤ ያኔ ስብሃትም ዘነበም ሞትን ቀደሙት ወይም አሸነፉት፡፡ ስብሃት ስብሃትን ሆኖ፤ ዘነበ ስለስብሃት ጽፎ ሞት ተሸነፈ፡፡
ሌላም የምር የምታስቀኝ (የውሸት እስቃለሁ እንዴ?) አንድ ትርክት አለች፡፡ ስብሃትን ሁሌ አስፋልት የሚያሻግረውን ልጅ፡- “ሙሴያችን ነው፡፡” ብሎ ተሳልቆበታል፡፡ አለማየሁም የስብሃት ሙሴ ይሆን እንዴ? ዘመንን አሻግሮታል፡፡

 

Read 2815 times