Saturday, 31 August 2013 12:27

የባለ ቅኔ ቀን

Written by  ደመቀ ከበደ
Rate this item
(2 votes)

ዓባይ ድልድዩ ስር...
ዓባይ እያጓራ - እየተፎገላ
ደም መሳይ ገላውን - ወርሶ ከአፈር ገላ
ሽልምልም እያለ - ከጣና ሲነጠል - ከጣና ሲከላ
ቁጭ ብዬ እያየሁ
እኔ እጠይቃለሁ
ከሀሳብ አድማሳት ሀሳብ አስሳለሁ
የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤
ይህ ሽበታም ድልድይ...
በጫንቃው መኪና - እንደተሸከመ
በጉያው ዓባይን - ሰርክ እንዳስተመመ
በቁር ሳይርድ ገላው - ሳይበድን አካሉ
የመጣን፣ የሄደን
እየተሸከመ - ሲያሳልፍ እያየሁ
በሸክሙ እደክማለሁ - በሸክሙ እዝላለሁ፤
እና እንዲህ እላለሁ
የልቡን እምቃት - እስትንፋሱን ሁላ - አልፎ ሂያጅ ለቀማው
እህ ባለ ጊዜ - ላጣ የሚሰማው
ከእንጉርጉሮው ዜማ - ሀሳብ ለመቀመር
ከሸክሙ ቅኔ ውስጥ - ትንሳኤ ለማብሰር
ሀሳብ አወጣለሁ
ሃሳብ አወርዳለሁ
ሀሳብ አስሳለሁ
የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤
‹‹ዓባይ ሽልምልሙ
ጣና ስልምልሙ
ድልድዩ ሽልሙ
አንድም ሳይጣሉ
አንድም ሳይስማሙ
እሾህ ያበቅላሉ
ዋርካ እያወደሙ፤››
ይላሉ ወፎቹ ከጣና ስርቻ - ከዓባይ በስተግርጌ - ዛፍ ላይ የሰፈሩት
የድልድዩን ቅኔ - በጣና ሙዚቃ - በዓባይ ሲቀምሩት፤
ይህን እያየሁ
ሀሳብ እጥላለሁ
ሀሳብ እሰቅላለሁ
ከሀሳብ አድማሳት
ሀሳብ አስሳለሁ
የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤
እላለሁ፤ እላለሁ
በቁጭት ሰበዜ
የህልሜን አክርማ ስፌት እሰፋለሁ፤
ስፌቱ ጣናዬ
ዓባይ አክርማዬ
ድልድዩ ሰበዜ የወፎቹ ዜማ - ወስፌ ነው መስፊያዬ - ስል እሞግታለሁ
በሀሳቤ ውጥን - ህዝብ እሰብዛለሁ - አገር እሰፋለሁ
ከመሸችው ጀንበር
ግራምጣ ሰግስጌ - ህዝብ አተልቃለሁ - አገር አልቃለሁ፤
ይህንን ከፍታ - ደግሜ አደምጣለሁ
ባሳብ ሰረገላ - እመነጠቃለሁ
ከዝምታ ስፌት - ህልም አስቀምጣለሁ፤
ከወፍ የተቀዳ - ከዓባይ የተሰማ - ከሀይቅ የተገኜ - ሙዚቃ እየሰማሁ
ድልድይ ስር ሆኜ - ዋርካ ተከልዬ - የባለቅኔ ህልም ልፈታ እጥራለሁ፤
አሁንም ያው አለሁ
ሀሳብ አወጣለሁ
ሀሳብ አወርዳለሁ
ከሀሳብ አድማሳት - ሀሳብ አስሳለሁ
ህልም እሚፈታባት
የባለቅኔ ቀን
የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤
ታዲያ ሁላችሁም - በድንገት መጥታችሁ
ተነስ ካለህበት - ቤት ግባ ብላችሁ
ተውኝ አትቀስቅሱኝ
ካሳቤ አትመልሱኝ
ህልሜን አገሬ አውቃው - በአገሬ እስኪሰማ - በአገሬ እስኪነገር
ተውኝ ሳስስ ልኑር - የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር!

Read 3480 times