Saturday, 31 August 2013 12:23

“ስሙኒዬን ኮሳት---”

Written by  ገዛኸኝ ፀጋው(ፀ.)
Rate this item
(2 votes)

ታክሲው እንዳወረዳቸው የቤታቸውን አቅጣጫ ትተው ወደ ማርያም ቤተክርሥቲያን በሚወስደው አስፋልት አቀኑ - ወይዘሮ ተዋቡ፡፡ ጭንቅላታቸው በሃሳብ ተወጥሯል፡፡ ሆስፒታል ውስጥ በጭንቀት ነው ያደሩት… በደም የጨቀየው ቀሚሳቸውን አልቀየሩትም፤ በነጠላቸው ሸፈኑት እንጂ… ዛሬ የ1995ዓ.ም.፣ የመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሰኞ ነው፤ መጋቢት 21 ግን አይደለም፡፡ ካልተሳሳቱ የሚሄዱበትን ቤት ጧት ጧት ማርያምን ሊሳለሙ በሚመጡ ጊዜ ያዩት መስሏቸዋል፡፡ ‘እቺ ጭራቅ… እንዴት ልጇን አትፈልግም!... እባክሽ አንቺ ማርያም፣ እናቴ አማላጄ ከዚህ ጉድ አውጭኝ!’ እያሉ በልባቸው ይፀልያሉ፡፡
ተዋቡ፣ በላስቲክ የተገጠገጠው መንደር፣ በርቀት ታያቸው፡፡ ወደ አይጠየፍ ማርያም በሚወስደው የአስፋልት መንገድ ዳርና ዳሩ በሚገማሸሩ ትላልቅ ዛፎች ተሞሽሯል፡፡ በስተግራ በኩል በስርአት የተሰደሩት የላስቲክ ህንፃዎች፣ አካባቢውን የስደተኞች መጠለያ አስመስለውታል። ከእነዚህ የላስቲክ ህንፃዎች መካከል የትርፌን ቤት መለየት ፈተና የሆነባቸው ይመስላሉ…
“ከመለመን ይሻላል!... ልጆችሽንም አታንከራቻቸው… አይዞሽ ከሰራሽ ገንዘብ ታገኛለሽ። ልጆችሽም ያድጋሉ.. የኔን ብቻ ሳይሆን የድፍን መንበረ ፀሐይን ጠላ ሻጭ የጠላ ቂጣ እንድትጋግሪ፣ ጌሾውን እንድትወግጭ… አነጋጋርሻለ፡፡ አየሽ መለመን’ኮ የሚያሳፍር አጉል ልማድ ነው!” ብለው ማንም ሳያስታውሳቸው ከእኔ ቢጤዋ ትርፌ ጋር የተግባቡበትን ቀን እያማረሩ፣በአይናቸው አሁንም ቤቷን እየፈለጉ ነው… በፊት ለፊት የሚታያቸው የላስቲክ ቤት እንደነበረ ትዝ ይላቸዋል፡፡
‘አንቺም እኔን መቀመቅ ከተሽ… በርሽ ላይ ተጐልተሻል!... እንኳን ልጅ ምንም የጠፋባት አትመስልም… ለነገሩ አሁን ምን ልላት ነው!? ልጅሽ…’ ብለው ሳይጨርሱት በሃሳብ እየባዘኑ አይናቸውን ከትርፌ ላይ ተከሉ፡፡ አሁን ግን አንዳች ነገር እንደተፈጠረ አወቁ…
“እንዴ! አረ ወየው!...” አሉ ለራሳቸው - ማንም ግን አልሰማቸውም፡፡ መራመዳቸውን ትተው ቆሙ፡፡ ካለ ነገር ያ ህፃን በጨለማ እየተክለፈለፈ እንዳልመጣባቸው ተገነዘቡ፡፡
“አዎ! እናቲቱ አብዳ ነው!... ልትገለው ስትል ነው ከእኔ ቤት የመጣው! ትርፌ አበደች ማለት ነው!?... አረ!... አረ!... ገደለችው!...” አጉተመተሙ። በድርጊቱ ተገርመዋል፡፡ ስለማበዷም አምነዋል። ትርፌ በማረስመስ በሽታ የሚሰቃየውን የሦስት ዓመት ህፃን በአንድ እጇ፣ አንድ እጁን አንጠልጥላ ፈቀቅ አድርጋ ስትወረውረው ሰቀጠጣቸው። እንዳያናግሯትም ለራሳቸው ፈሩ፡፡ ካበደ ሰው ጋር ትግል መግጠም አይችሉ፤ የሚጠቅመው ወደ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ፖሊስ ማምጣት ነው፡፡ ትርፌ ሩጣ ከኋላቸው የምታንቃቸው ይመስል አስር ጊዜ እየዞሩ ወደ መጡበት ተመለሱ…
ትርፌ ህፃን ሲያለቅስባት መለኛ ናት፤ ማባበል ተክናበታለች… ሁለት ጊዜ ዝም እንዲል እንደ ጡሩንባ ታምባርቅበትና በሶስተኛው ዝም አልል ካለ በጥፊ ትለጋዋለች፡፡ የድሃ ልጅ ማጫወቻው፣ ማባበያው ይሄ ነው… በቃ… ልጅ መደብደብ፣ ማሰቃየት ጐጂ ልማድ እንደሆነ ማንም አልነገራት፤ ቢነግራትም አትሰማም፡፡ ከቡጢ ያልተናነሰ ጥፊ ያረፈበት ህፃን፣ የማልቀሻ ህዋሶቹ በለቅሶ ብዛት እስኪሰልሉ ድረስ እርር እያለ እያለቀሰ ነው፡፡ እሷ ግን የህፃኑን አይነ ምድር በያዘችው ጭራሮ ቆፈረችው… አይኗንም ከአይነ ምድሩ ሳትነቅል፣ “እንግዲህ ሙተህ እረፈውይ!... አንተ ሙትቻ!” ብላ ወስፋት የወጠረውን ሆዱን እንደ ከበሮ ጐሰም ጐሰም አደረገችው፡፡ ወዲያው መንጋጋውን በሃይል መልቅቃ ጉሮሮውን አየች… የፈለገችው አልታያትም። አንገቱን ወደታች ተጭና ማጅራቱን መታ መታ አደረገችው፡፡ ለሀጩ እየተዝረበረበ፣ አይነ ምድር ሲነካካ የቆየውን ጣቷን፣ወደ አፉ ከታ ጉሮሮው አካባቢ ዳሰሰች፣ ጣቷን ሳታወጣ ህፃኑ በትውኪያ ተጨነቀ፡፡ ትውኪያውን አፍጣ ብታየውም ምንም ነገር አላገኘችም…
“ዝም በል ስልህ አሰማይም!… አንተ ሙትቻ!... ካንተው ብሶ እልክ ደግሞ!...’እ’ በል!... ‘እ.እ’ በልህ አምጥይ!” ብላ ፊንጢጣውን አካባቢ እንደ ወፍጮ ቋት ጠበጠበችው፡፡ ቋቱ ባዶ በመሆኑ ፍጭ አላደረገም… የፊንጢጣውን ዳር ዳር በእጇ ጫን ጫን ካደረገች በኋላ፣ ሌባ ጣቷን በህፃኑ ፊንጢጣ ላከችና እንደወጥ አማሰለችው፡፡ ባእድ ነገር የተሰነቀረበት ህፃን፣ በዚህ ጊዜ ልሳኑ እስኪዘጋ ድረስ አምባረቀ፡፡ በርግጥ በለቅሶ ብዛት ሃይሉን ስለጨረሰ ጩኸቱ ቀንሷል፡፡
“እንግዲህ ሙተህ እረፈው… በቃ!... ያ መናጢ ገሎህ ሄደ!” እያለች የኔቢጤዋ ትርፌ በህፃኑ ላይ ተነጫነጨች… “ደሞ ልጅ ብሎ ነገር… አሞኝ ብልከው አይዴል… ያ ወደላ ጉድ የሰራኝ!... ቆይ!... የትም አድሮ አሁን እንዳመሉ ይመጣ የለ… እረግጠዋለሁ!” እያለች የማታውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናዋ እያየች ፉከራዋን ቀጠለች…
* * *
ትርፌ ሰሞኑን አሟት ስለነበር ከላስቲክ ቤቷ ኩርትም ብላ ነው የሰነበተችው፡፡ እንደሷ ግምት የህመሟ መንስኤ የጠላ ቂጣ መጋገሯ ነው። ለሷ የሚያዋጣት ሳይለፉ ቁጭ ብሎ መለመኑ ነው። “እጅግር እያለው ልመና ምንድን ነው!?... የሚያሳፍር መጥፎ ልማድ አይደል!” እያሉ እነ ተዋቡ እየጨቀጨቋት እንጂ መሥራቱን አትፈልገውም፡፡ ግን ለልጆቹም የሚበላውን እየሰጡ፣ አይዞሽ እያሉ እድሜ ለተዋቡ ሰርቶ መብላት እየለመደች ነበር…
ዛሬ እርሃቡም የልጆቹም ለቅሶ ሲብስባት፣ ወደ ማታ ለልመና ወደ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን አቀናች፡፡ እስከ ልጆቿ ቁጭ ብላ ስትለምን አመሸች። ሥራን የጠሉት እጆቿ ግን እንደ እስከዛሬው ብዙ ሳንቲም አላፈሱም፡፡ በለመኑት አንድ ብር ካሥር ሳንቲም ስኳር ድንች ገዝታ ልጆቿን ሸነጋግላ፣ እሷም ወደ አፏ አለች፡፡ የአምስት አመቱ የመጀመሪያ ልጇ ግን አንድ ሰውዬ የሰጡትን ሃያ አምስት ሳንቲም “አንጣ!” ብትለውም አልሰጣትም፡፡
“ክንዴ ስሙኒዊን አምጣትና ቡና ልግዛበት - እራሴን አሞኛል” አለችው፣ በዝችው በላስቲክ ቤቷ አንዳንድ ጊዜ ሞቅ ሲለው፣ ማታ ማታ ፍቅር የሚያጋራትን የቀን ሠራተኛ ወዳጇን እያሰበች፡፡
“እምቢየው!... ዲያቦ እገዣበታለው!” በማለት ሞገታት፡፡ እሷም ነገሩን ትታ የጐናቸውን ማረፊያ ማሰናዳት ጀመረች፡፡ የመደብ ላይ የወሲብ አጋሯ ዛሬ ድንገት ሊመጣ ስለሚችል ልጆቿን አስተኝታ መቆየት ይጠበቅባታል፡፡ ህፃን ክንዴ ግን እናቱ እንዳትሰማው በለሆሳስ፣ “እንካ ሻንቲምና ዲንች ስጠኝ” እያለ ትንሽ ወንድሙን ያባብሰዋል፡፡ ክንዴ ህፃኑ የፈረፈረውን ድንች ሲጠለቅም ጥርሱ ላይ እየቀረ ወስፋቱን ስላጮኸበት ሳያስበው በእጁ ከያዘው ላይም ቆረሰበት፡፡ ህፃኑ እንደ አንቡላንስ መኪና ሊጮህበት ሲያኮበኩብ ማታለያ ሳንቲሙን ሰጠው… ካለበለዚያ የወንድሙን ቀምቶ በመብላቱና በማስለቀሱ ከመሬት ጋር እንደምትቀላቅለው ያውቃል - ትርፌ ጋር ቀልድ የለም፡፡
ትንሹ ህፃን የተቀበላትን ሳንቲም ከድንቹ ጋር በድንገት ሲሰለቅጥ፣ “ኦዎ!...” ብሎ የማስመለስ ድምፅ አሰማ፡፡ ትርፌ ውልክሽ እያለች ስታየው ህፃኑ እየተናነቀው ነው፡፡ “አረ ይሄ ወዲያም!... ቀስ ብሎ አይበላም!...” ብላ ቀና ስታደርገው አይኑ ፈጦ ይተናነቀዋል፡፡ አንገቱን ወደ ላይ ቀና እያደረገች፣ “አንት እውር ሳንቲሙን ሰጠኸው እንዴ!...” ብላ ስታንባርቅበት ክንዴ ተብረከረከ፡፡ ህፃኑም እየጓጐረ ሳንቲሙን ወደ ከርሰ መቃብር ሲያወርዳት እናት ደነገጠች… በአፉ ምንም የሳንቲም ዘር የለም። ይልቁንም፣ ህፃኑ ምንም እንዳላየ ቁልጭልጭ ሲልባት ተጨነቀች፡፡
“ማን አባህ ስጥ አለህ!... እኔ አምጣ ብልህ እምቢ አላልክም!” ብላ ክንዴት በጥፊ ጆሮ ግንዱ ላይ ስታቀረናው መሬት ላይ ተዘረረ፡፡ ልትደግመው አንካሳ እግሯን እየጐተተች ስትጠጋው፣ ተነስቶ ነፍሴ አውጭኝ እያለቀ በጨለማው ፈረጠጠ፡፡ “አንት ሙትቻ! ቆይ… ትመጣ የለ!” ብላ ከላስቲክ ቤቷ በረንዳ ላይ ሁና ስትጮህበት፣ ጆሮ ግንዱን በእጁ ደግፎ እየተንሰቀሰቀ አስፋልቱን ይዞ ሮጠ፡፡
ክንዴ ጆሮውን እያሻሸ ትንሽ እንደሮጠ ቆመ። በጣም ይንሰቀሰቃል… በጥፊ የቀረናው ጆሮው ጭው ብሎበታል፡፡ አንዳች ነገር በጨለማው ውስጥ የመጣበት መሰለውና ደነገጠ፡፡ ድምፅ እያሰማ ማልቀሱን ተወ፡፡ ቀስ እያለ ወደዛችው ላስቲክ ቤት አመራ፡፡
ትርፌ የላስቲክ ቤቷን በር ዘግታ እየጮኸች ነው። ትንሹ ህፃንም ያለቅሳል፡፡ ከሁለተኛው የላስቲክ ቤት ያሉት የኔቢጤዎች መጥተው ስለተዋጠችው ስሙኒ ይንጫጫሉ፡፡ ክንዴ ወደ ቤቱ አጠገብ ሆኖ ሁሉንም ያዳምጣል፤ ቢገባ ምን እንደሚከተለው ያውቃል። ተጨነቀ፡፡ በጨለማው አይኑን ፍጥጥ ሲያደርግ፣ አንዳች ነገር ወደሱ እየመጣ መሰለው… ያቺ ትንሽ ልቡ በፍርሃት ቆፈን ተቀፈደደች፡፡ የእናቱ ንዴት እንዳልበረደላት ሲያውቅ ከቆመበት ተንቀሳቀሰ…
ክንዴ፣ “አባጅቦ እየመጡ ነው፣ ዝም ብላችሁ ተኙ… እርቦኛል ብሎ የሚያለቅስ ልጅ ካገኘ ጅቦ ይበላሉ…” እያለች ትርፌ ማታ ማታ እየራባቸው ሲያለቅሱ የምታስፈራራቸው ትዝ አለውና በፍርሃት እራደ፡፡ መምሸቱን እንጂ ከምሽቱ 3፡00 መሆኑን አያውቅም - በስኳር ድንች ተታሎ “ሙስና” የፈፀመው ረሃብተኛው ክንዴ፡፡
አሁን ትንሿ የክንዴ ጭንቅላት በሃሳብ ታጥራለች፡፡ የት እንደሚያድር እያሰበ ነው። ወደ እናቱ መሄድ አይታሰብም፤ እንደ ሙቀጫ ትወቅጠዋለች፡፡ ዘመድ አክስት አጐት የላቸውም፤ ወላጅ አባቱንም፣ እንኳን እሱ ትርፌም አታውቀው። ማታ ማታ ከዛች ላስቲክ ቤት እየመጣ ከእናቱ ጋር የሚላፋውን የቀን ሠራተኛ “አባቴ… ዳቦ….” ሲለው አይኑን እያጉረዘረዘበት መጥራቱን አቁሟል፡፡ እናም የት እንደሚያድር ጨነቀው…
ከደቂቃት በኋላ ያቺ ትንሽ ልቡ ሲብስባት መላ ፈጠረች፡፡ አዎ! ሲርበው የሚያጐርሱት፣ ሲጠማው የሚያጠጡት ተዋቡ ትዝ አሉት፡፡ ደስ አለው፡፡ ተዋቡ ቤት ደርሶ ሲገባ፣ “ለምን በጨለማ መጣህ?” ቢሉት ምን እንደሚል እያሰበ ወደ ጠላ ቤቱ አቀና። አሁን በርቀት የተዋቡ ቤት በር ገርበብ ብሎ እየታየው ነው… የጊቢው የሸንበቆ በራፍ ብትዘጋም ብዙ አላስጨነቀችውም፤ ገፋ ተደርጋ እንደምትከፈት ያውቃል፡፡
ምስኪኑ ክንዴ አሁን ከተዋቡ በር ላይ ደርሷል… የለመዳትን የሸንበቆ በር ገፋ ሲያደርጋት ግን እንደለመደው ሸተት አላለችለትም፡፡ እየደጋገመ እየገፋት እያለ ግን ታስሮ የሚውለው የጐረቤት ውሻ እየበረረ ከላዩ ላይ ተከመረበት፡፡ “ዋይ!” ብሎ ጩኸቱን ለቀቀው፡፡ የጠላቸውን ሂሳብ ከልጃቸው ጋር እያሰቡ፣ በትርፋቸው ማነስ ሲበሳጩ የነበሩት ተዋቡ፣ በር በርግደው ሲወጡ የጐረቤታቸው “መቻል” ከበራቸው ላይ ግዳይ ጥሎ አዩ፡፡
“መቻል!... አረ ሂድ!... የማነው ልጅ አረ!?” ተዋቡ የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጡ፡፡ ጐረቤቱ እየተሯሯጠ መጣ፡፡ ህፃኑ በድንጋጤ ፀጥ አለ፡፡ “በጣም ተጐድቷል!... ቶሎ ሃኪም ቤት ይሂድ!...” አሉ፣ የተዋቡ ጐረቤቶች፡፡
“አረ በጣም ተጐድቷል!... ደም እየፈሰሰው ነው… ከማዘላችሁ በፊት በነጠላ ይታሰር…” ሁሉም በየፊናው ይጮኻል፡፡ የተዋቡ ልጅ፣ የተነከሰውን ህፃን አዝላ፣ ጐረቤት አስከትላ ሮጠች፡፡ ሙጋድ አካባቢ ያገኙትን ታክሲ ለምነው ወደ ሆስፒታል አመሩ፡፡ ክንዴ ሆስፒታል ገብቶ ሲታይ፣ ከእጁ የበለጠ ትከሻው ላይ ቦጭቆታል፡፡ ሀኪሞቹ እየተሯሯጡ አከሙት፡፡ መሰፋት ስላለበት አልጋ እንዲይዝ ተደረገ፡፡ ጐረቤቱ ሲመለስ ተዋቡ እስከ ልጃቸው ሆስፒታል አደሩ፡፡
ሀኪሞቹ “ውሻው ጤኛ ስለሆነ… ትንሽ ቁስሉ ያሰቃየው እንደሆነ እንጂ… ስለ ህይወቱ አያስቡ!...” ቢሏቸውም ተዋቡ ግን ይሄ ምስኪን ህፃን ወደ እሳቸው ቤት እየገባ ስለተነከሰ… እሳቸውን ባለእዳ አድርጐ እንዳይሞትባቸው ፈርተዋል፡፡ የእናቲቱ ልጇን አለመፈለግ ግን እንደ እግር እሳት እያንገበገባቸው ነው ያደሩት፡፡ ለዚህ ነው፣ በማለዳ የከረፋ ልብሳቸውን እንኳ ሳይቀይሩ፣ ጧት ከታክሲ እንደወረዱ በቀጥታ ወደ ትርፌ ቤት ያመሩት…
* * *
…ከትርፌ በር ላይ የሚያዩት ትእይንት የጤንነት አልመስላቸው ያሉት ተዋቡ፣ አሁን ካንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አንድ ፖሊስ ይዘው ወደ ላስቲክ መንደሩ እያመሩ ነው፡፡
“አይዝዎ! እስዎን እኮ አያስጠይቅዎትም፣ በጨለማ እስዎ አላኩት… የገዛ እናቱ ትጠየቅ እንጂ!” ሲላቸው ፖሊሲ… ተዋበች፣ “የምልህን አልሰማኸኝም!... አብዳለች’ኮ ነው የምልህ… አየህ ትልቁ መሮጥ ስለቻለ ወደኔ መጣ… ያኛውን ህፃን ግን እንደ እባብ እየቀጠቀጠችው አይቼ!... በፊንጢጣው እንጨት፣ ጣቷን እየላከችበት ስልህ… አይ!... ትርፌማ አብዳለች… እሱማ ድህነቱስ ያሳብድ የለ!... ባይሆን ግን እሷ ሥራ ጠልታ ነው…” አሉ ተዋቡ፣ ምን እንዳሉ በወጉ ሳያጤኑ፡፡ ተዋቡ ልጁ ቢሞት ያስጠይቀኛል ብለው ፈርተዋል፡፡
“አየህ!... አረ እውልኝ… አሁንም አልተወችውም… ልትገለው ነው!”
“እህ!... እቺስ አመለኛ ናት! አንድ ጊዜ የማርያም እለት ጣቢያው ፊት ለፊት ቁጭ ብላ እየለመነች ሳለ እንደዚሁ ልጇን በድንጋይ መታው፣ አድምታው አስፈራርተን… ልጅ… የራስ ልጅም ቢሆን መደብደብ እንደማይገባ፣ ጐጂ ልማድ እንደሆነ አስተምረናት ነበር’ኮ” አለ ፖሊሱ፣ ያለፈውን ገጠመኝ እያስታወሰ።
“ዛሬማ አብዳለች’ኮ ነው የምልህ… አየህ… ቆይ ተመልከት… ቂጡን ምን እያደረገችው ነው ልጄ!?... ቆይማ እያት…” አሉ ተዋቡ ድምፃቸውን ቀንሰው በሹክሹክታ፡፡ ትርፌ የህፃኑን ፊንጢጣ መልግዛ አጐንብሳ እያየች ጣቷን ስትልከው፣ ይሄ መከረኛ ህፃን ድምፁ ሰልሎ ሲያላዝን አዩ… ፖሊሱ በሁኔታው ደነገጠና ፈንጠር ፈንጠር ብሎ በመራመድ፣ “አንቺ እብድ ልትገይው ነው!” አላት፡፡
ትርፌ ድንግጥ ብላ፣ “ምን ብዬ እኔ እገለዋለሁ!... ይሄ ሙትቻ እራሱ ሊሞት ነውይ… ለቡና መጠጫዬ ያልኳትንም…” እያለች ሳለ ንግግሯን አቋርጠው ተዋቡ፣ “ያኛውንም ልጅሽን በጨለማ አባረሽ ለጅብ አስበላሽው አንቺ ጨካኝ!” በማለት ጮኹባት፡፡
“ተነሽ ቀጥይ!... አውቆ አበድ!” በማለት ፖሊሱ ገላመጣት፡፡
“ደሞ በልጄ የፈለኩት ባረገውሳ!... ልታሰር ነው የምሄደው!” በማለት ትርፌ በተራዋ በሃይለ ቃል ተናገረች፡፡
“ልጅሽንስ ቢሆን ገለሽ ትቀመጭ መስሎሻል!... ‘እፀድቅ ብዬ ባዝላት…’ አሉ… ጦስሽ ለኔም ተረፈኝ!” አሉ ተዋቡ፣ ቁጣና ግርምት እየተቀላቀለባቸው፡፡
“ለዚህ ሁሉ የሚያበቃኝማ… ያ ዴንዴሳም ነው!” የቡና መግዣዬን ሰጥቶ…” አለች ትርፌ፣ ያዘለችውን ልጇን በትከሻዋ እያመናጨቀች፡፡
“አንቺ!... ቀስ አርጊው!... ማሳደግ የማትችይውን ከመውለድ መጀመሪያ ሰብሰብ አትይም ነበር… እንደ እባብ ቀጥቅጠሽ ከምትገያቸው!... ከዚህ በፊትም ተነግሮሻል!...” አለ ፖሊሱ በሁኔታዋ እየተበሳጨ፡፡
“አይ ተዋቡ! አውቆ አበድ ናት ብዬሁ የለ…”
“እህ!... አውቆ ይታበዲያል ደ’ሞ!?...” አለና ወደ ቢሮ ሳይገቡ በቁማቸው፣ ትርፌን በጥያቄ አዋከባት።
“ለመሆኑ በጨለማ ልጁን ለምን ከቤት አስወጣሽው!?”
“የቡና መግዣ ስሙኒዬን ሰጥቶ ይህን ሲያሳንቀው እሳ!”
“እና ምንም የማያውቀውን ህፃን በጨለማ ታባርሪያለሽ?... አንቺ ጨካኝ!”
“መች አባረርኩት፣ ገና በጥፊ ሥጋጋው ሩጦ ሄደ እንጂ…” እያለች ሳለ ጀርባው እንደ ወፍጮ ቋት ሲጠበጠብ፣ መላ አካሉ ሲጐረጐር አድሮ፣ ያረፈደው ህፃን ከእናቱ ትከሻ ላይ እያለ በድንገት ተቁነጠነጠ፡፡ ወዲያው ከጀርባዋ ወርዶ ጣቢያው በር ላይ ቁጢጥ አለ፡፡ የልጇ ነገረ-ሥራ ያላማራት ትርፌ፣ እንደ መብረቅ ብትጮህበትም፣ በህፃኑ ፊንጢጣ በኩል አንዳች ቆሻሻ አመለጠ፡፡
ትርፌ ቀልጠፍ ብላ ወደ ልጇ አይነምድር ስትጐነበስና ስንጥር ስታነሳ፣ ለጣቢያው ንፅህና በመጨነቋ ሁሉም በውስጣቸው አደነቋት፡፡ እሷ ግን ግዳይ ለመጣል አንደሚያደባ አስተዋይ አዳኝ አይኖቿን ተክላ፣ አይነምድሩን በስንጥሯ ደጋግማ ቆፈረችው… ወዲያው የሳንቲም ብልጭታ ከዓይነምድሩ ላይ ስታይ በስሜት፣ “እሰይ!... ስሙኒዬን ኮሳት…” በማለት ስትደመም፣ ከበዋት የነበሩት ሰዎች ሁሉ በሳቅ ተንከተከቱ… ድህነትም በተራው በሳቅ ተንከተከተ… ቂ.ቂቂቂ…

Read 4003 times