Saturday, 31 August 2013 11:59

‘የተሻለ ጊዜ’ መናፈቅ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለዋዜማ ሰሞን አደረሳችሁማ! መቼም ‘የተሻለ ጊዜ’ የሚሉትን ማየት ከህልምነት ወደ ቅዠትነት እየተለወጠ ያለ የሚያስመስሉ ነገሮች ቢበዙብንም፣ ካለፉት ብዙ ዓመታት ይልቅ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ‘መንገድ እየሳቱ’ የሄዱ ነገሮች እየበዙብን ቢሆኑም፣ “ሆዴ፣ አካላቴ…” ከማለት ይልቅ “አካኪ ዘራፍ…” የምንል ሰዎች እየበዛን ብንሄድም፣ ይቺን ‘የፈረደባት’ አገር እንደ ግል ‘ርስተ ጉልታችን’ የፈልግነውን ልናደርጋት ‘ሊቼንሳ ያለን’ የሚመስለን ቁጥራችን ቢጨምርም ደግ መመኘት ክፋት ስለሌለው …መጪውን ጊዜ ‘የተሻለ’ ያድርግልንማ!
የአምናን ቀን ረገምኩት ለአፌ ለከት የለው
የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው፡፡
ከሚል አልላቀቅ ያለን እንጉርጉሮ የሚያላቅቀን ‘የተሻለ ጊዜ’ ይሁንልንማ!
የዘንድሮ ዓመት መለስ ብላችሁ ስታዩት…አለ አይደል…ከሚያስደስቱ ነገሮች ይልቅ የሚያስከፉት አልበዙባችሁም! የማይሰበሩ በሚመስሉ መስታወቶች የሚብለጨለጩ ህንጻዎች ከተማዋን እየወረሯት…‘ተሰባሪ’ ሰዎች እየበዙ ያሉበት ዘመን በእርግጥም ያሳስባል፡፡
ስሙኝማ…ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ከተማ ውስጥ ከገጠር የመጡ የሚመስሉ የሚለምኑ ሰዎች አልበዙባችሁም! እንዴት ነው እንዲህ ሊሆን የቻለው! ህጻናቶቻቸውን ሰብስበው ወደ አዲስ አበባ በዚህ አይነት ብዛት ለመፍለስ ያስገደዳቸው ምን እንደሆነ የማይነገረንሳ! አሀ…ልክ ነዋ ይሄ “ሁለት ዲጂት…” ምናምን የሚባለው ነገር እነሱን አያካትትም? ለነገሩ በቀደም “የምትበልጡት ኒጀርን ብቻ ነው…” ብለው አወጡብን አይደል!)
እናላችሁ…አንዱ ዓመት አልፎ ሌላው ሊተካ ነው፡፡ ስሙኝማ…ዘንድሮ በአቆጣጠሩ አንድ ዓመት ባለፈ ቁጥር በአኗኗር ደግሞ ወደ አራት ዓመት ገደማ ይሆናል፡፡ ልክ ነዋ…ይኸው ስንቱ ‘ወጣት የነብር ጣት’ አለጊዜው እየገረጀፈ አይደል! አንዱ ወጣት ምን አለ መሰላችሁ… “አባቴ የጥንቱን እያስታወሰ ድሮ በግ በአምስት ብር ይገዛ ነበር ምናምን ይለኝ ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ እኔ ከሁለት ወር በፊት እኮ አንድ ቅቅል ሃያ አራት ብር ነበር፣ አሁን አርባ ብር ሆኗል፡፡”
እናማ…‘የድሮ ጊዜ’ ስፋት እየጠበበ በአሥርት ዓመታት ሳይሆን… በ‘ወራት’ መቆጠር እየጀመረ ነው፡፡ “እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገረህ” ስንባባል…አለ አይደል…ልክ “እንኳን በአንድ ዓመት የአራት ዓመት ዕድሜ ጨመርክ…“ አይነት እየሆነ ነው፡፡
ከዚህ በፊት ያወራናትን ልድገማትማ…አንድ ወዳጄን ጓደኛው ‘ዕድሜ ጠገብ’ መሆኑን ሲነግረው ምን አለው መሰላችሁ…“አንተ እኮ ሀሊ ኮሜትን ሁለቴ አይተህ ሦስተኛ ጊዜ እየጠበቅሀት ነው፡፡” ምን መሰላችሁ…ሀሊ ኮሜት የምትመጣው በየስንት ጊዜ መሰላችሁ…በየስድሳ ዓመቷ!
ስሙኝማ…የጊዜን ነገር ካነሳን አይቀር በጣም ትልቅ የሆነ በሽታ ምን መሰላችሁ…የመጣንበትን ‘ሆነ ብሎ’ መርሳት! በተለይ በሆነ ነገር ‘ስኬት አገኘ/ኘች’ የሚባሉ ሰዎች የመጡበትን መንገድ ሲጠየቁ ቅልጥ ያለ ኮረኮንች የነበረውን በ‘ሬድ ካርፔት’ ያነጥፉታል፡፡
ስሙኝማ…በፊት እኮ ሀብታም የሆኑ ሰዎች ሲጠየቁ…አለ አይደል…“መጀመሪያ ቄጤማ እሸጥ ነበር…” “እህል በረንዳ የጉልበት ሥራ እሠራ ነበር…” ምናምን ብለው እቅጯን ያገሩ ነበር፡፡
የዘንድሮ ‘ባለገንዘብ’ ግን ልክ ሲወለድ ሰባት ቁጥሮች ያሉት የባንክ ደብተር በቀኝ እጁ ይዞ የወጣ ነው የሚመስለው፡፡ እናማ… በዘንድሮ የ‘ገንዘብ ስኬታቸው’ ያለፈ ታሪካቸውን ‘አፈር ድሜ የሚያገቡ’ መአት ናቸው፡፡
እናላችሁ…የመጣንበትን የምንረሳ ሰዎች በዝተናል፡፡
ዘንድሮ መቼም በቀጥታም በተዘዋዋሪም ‘ቦተሊከኛ’ ያልሆንን ጥቂት ነን፡፡ እናላችሁ…ሁላችንም… ምን አለፋችሁ…ዓለም በሙሉ ‘የሚድንበት ቅዱስ ቃል’ ጋር ያለ ነው የሚመስለን፡፡ ታዲያላችሁ…
የዘንድሮ ‘ቦተሊከኞችን’… “ለመሆኑ ፖለቲካ ውስጥ እንዴት ገቡ?” ሲባል “ይገርምሀል፣ ከልጅነቴ ጀምሮ ድሀ ሲበደል ማየት አልወድም ነበር…” ምናምን ነገር ይላል፡፡
እንትናዬ “አስተዳደግሽ እንዴት ነው?” ስትባል ምን ትል መሰላችሁ…
“ውይ! ምን ልበልህ፣ ብቻ አይደለም በዓል መጥቶ አዲስ ልብስ የሚገዛልኝ በየወሩ ነበር፡፡ ነገርዬው እኮ…አለ አይደል…የጎረቤት ሰዎች እኮ አባቷን.. “አቶ…. ኸረ እባክህ ይቺ ልጅ ሦስት ዓመት ሙሉ አንዲት ጨርቅ ሳትለውጥ…እግዜሐሩስ ምን ይላል!” ይሉ ነበር፡፡
ለከርሞ መጽሐፍ ማንበብ…
“ይገርምሀል…በልጅነቴ መፅሐፍ በጣም አነብ ስለነበር እንዳላብድ ፈርተው መፅሐፎች ይደብቁብኝ ነበር…” አይነት ጉራ ሞልቶላችኋል፡፡ ምን መሰላችሁ… እዚህ አገር ጉራ ሲነዛ እስከ ጥግ ነው የሚኬደው! (ከብዙ ጊዜ በፊት አንድ ትንሽ አእምሮ ችግር ስለገጠመው ሲወራ ምን ይባል ነበር መሰላችሁ…“ዲክሺነሪ መሸምደድ ጀምሮ ደብልዩ ላይ ሲደርስ ሳተ…” ይባል ነበር፡፡
ደግሞላችሁ ሌላው አለ…መጀመሪያ ላይ “እዚህ አገር ምን ሰዓሊ አለና ነው!” ምናምን ብሎ ለታሪኩ መግቢያ ምናምን ይሠራል፡፡ ከዚያ ዋናው ታሪክ ይመጣል… “የሚገርምህ ነገር የእንቁጣጣሽ አበባ ስስል አጎቴ ‘ይሄ ልጅ ሲያድግ ቫን ጎህ ይሆናል’ ይል ነበር፡፡” አጎትዬው እኮ፣ አይደለም ቫን ጎህን ሊያውቅ፣ ዓለም ላይ ከሀበሾች በስተቀር ያሉ ህዝቦች ጣልያኖችና ደርቡሾች ብቻ የሚመስሉት አይነት ነው! እና የመጡበትን ‘ሆነ ብሎ የሚያስረሳ’ አብሾን የሚያጠፋልን የተሻለ ጊዜ ያምጣልንማ!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ስሙኝማ…ሁለት ወዳጆች አውቶብስ ይሳፈራሉ፡፡ እናማ… ትርፍ ወንበር የነበረችው አንድ ብቻ ስለነበረች ‘አንተ ተቀመጥ… አንተ’ ምናምን እያሉ ይግደረደራሉ፡፡ አንደኛው ምን ይላል… “ግዴለም በዕድሜም በለጥ ስለምትለኝ አንተ ተቀመጥ” ይለዋል፡፡ ጓደኛው ምን ቢለው ጥሩ ነው…ተው እባክህ አንተ እኮ የአንዱን ባቡር አይተህ የሁለተኛውንም ባቡር ልታይ ነው፡፡”
እናማ… “ሦስት መንግሥት አይቷል…” እንደሚባለው ‘ሁለት ባቡር ማየት’ም የዕድሜ ባለጸጋነት ምልክት ሊሆን ነው፡፡
አንደ ወዳጄ ታክሲ ላይ ያየትን ጥቅስ ምን ይል መሰላችሁ…“ታሪኩን የማያውቅ ሰውና ስፖክዮ የሌለው መኪና አንድ ናቸው፡፡” አሪፍ አይደል!
ታዲያላችሁ…ልክ ሰው የሌለበት ዓለም ላይ የኖርን ይመስል… ለራሳችን የምንፈጥራቸው ልብ ወለድ ታሪኮችን ስንናገር…‘ምላሳችንን ያዝም’ አያደርገንም፡፡
እናማ ለራስ የልብ ወለድ ታሪክ መጻፍን የሚያስቀር ‘የተሻለ ጊዜ’ ያምጣልንማ!
ታዲያላችሁ…ቤተሰብን የሚያስተሳስሩ ክሮች እየላሉ፣ ወላጆች የወላጅነት ግዴታቸውን እየረሱ ሲሄዱ ማየት “የእውነት የተሻለ ቀን መቼ ነው የሚመጣው?” የማያሰኝሳ! ይቺን የጥንት ግጥም ስሙልኝማ…
በበጋ እረስ ቢሉት ፀሀዩን ፈራና
በሐምሌ እረስ ቢሉት ዝናቡን ፈራና
ልጁ እንጀራ ቢለው በጅብ አስፈራራ
አዎ፣ የዚች አባባል ሀሳብ ለዘንድሮም ይሠራል፡፡ አሀ…በጊዜ ገብቶ ጋቢ ለብሶ ከሚቀመጥ አባት ይልቅ በጓደኞች ሸክም ተይዞ፣ በሰፈር ልጆች ተሸኝቶ በውድቅት የሚገባ አባት በዝቷላ!
ስሙኝማ…‘ጅብ’ የሚለውን ከጠቀስን አይቀር የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… በዛ ሰሞን የሆነ ኮንዶሚኒየም ላይ ወጥቶ ተገኘ የተባለው ጅብ…አለ አይደል… ከሆነ፣ ልጁን ከሚያስፈራራ አባት ጋር ተማክሮ ነበር እንዴ! ልክ ነዋ…ዘንድሮ እንደሁ የወላጅና የልጅ ግንኙነት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ አንዳንዴ እኮ አንዳንድ ወላጆችን…“ለመሆኑ ልጆችሽ እንዴት አድርገው ነው የሚያሳድጉሽ?” ልንል ምንም አልቀረን፡፡ ማን ማንን እንደሚያሳድግ ግራ እየገባን ነዋ!
ደግሞም ሌላ አለላችሁ…
አንጀቴን አንጀቴ ሲበላው አደረ
አባት የሌለው ልጅ እያንጎራጎረ
እንዲህ ያለ ወራት የተደናገረ
አባቱ በልቶበት ልጁ ጦም አደረ፡፡
አባቶች እየሰለቀጡ ልጆች ጦም የሚያድሩበትን ጊዜ አስወግዶ… ‘የተሻለ’ ጊዜ ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 3365 times