Saturday, 31 August 2013 11:53

አየር መንገድ ከምንጊዜውም የላቀ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

የኢትዮያ አየር መንገድ ባለቀው በጀት ዓመት ከምንጊዜውም በላይ የላቀ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም እንደገለፁት፤ አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ ከምንጊዜው የላቀ የ2.03 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል፡፡ ትርፉ ከአምናው 734 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 178 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከሰውና ከዕቃ ማጓጓዝ የተገኘው 38.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ከአምናው 33.8 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ14 በመቶ ብልጫ እንዳለው፣ እንዲሁም ሰውና ዕቃ ከማጓጓዝ የተገኘው 2.7 ቢለዮን ብር ለፕሬቲንግ ፕሮፊት ከአምናው 1.0 ቢሊዮን ጋር ሲነፃር የ165 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
የአየር መንገዱ የተጣራ ትርፍ ከዓለም አቀፍና ከአፍሪካ የአውሮፕላን ኢንዱስትሪ አማካይ የተጣራ ትርፍ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት አቶ ተወልደ፤ የአፍሪካ የተጣራ ትርፍ 0.9 በመቶ፣ የዓለም አቀፍ ደግሞ 1.8 በመቶ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ 5.3 በመቶ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አየር መንገዱ ለዚህ ውጤት የበቃው በሠራተኛውና በማኔጅመንቱ ብልህ አመራርና ቆራጥነት፣ ትክክለኛ የረዥም ጊዜ ስትራቴጂ፣ በአፍሪካና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በመዝገቡና ደንበኞቹ እምነት ሰጥተው ስለሚመርጡት…እንደሆነ ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ ለአየር መንገዱ ዕድገት ሌላው ምክንያት የዘጠኝ አዳዲስ መዳረሻዎች መከፈትና የነባሮቹም የምልልስ ጊዜ መጨመር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ አየር መንገዱ፣ የማርኬቲንግና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ማሠልጠኛ ሕንፃ 95 በመቶ መጠናቀቁን፤ አዲስ ተርሚናልና ዕቃ ማቆያ ለመገንባት ፋይናንስ በመፈለግና የዲዛይን ሥራ መጀመሩን የጠቆሙት ሥራ አስፈፃሚው፤ ለባለ 4 ኮከብ ሆቴል ግንባታ የብድር ስምምነት እየተካሄደ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ ለአየር መንገድ ሠራተኞች የ1192 ቤቶች ግንባታ 30 በመቶ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጠናቀቅ የጠቀሱ ሲሆን ባለፈው ወር ለሠራተኞቹ እንደየስኬሉ ከ6 እስከ 8 ደረጃ የደሞዝ ጭማሪና የአንድ ወር ደሞዝ ቦነስ መስጠቱ ታውቋል፡፡
ባለፈው ጥርም ለእያንዳንዱ ሠራተኛ እንደየስኬሉ ከ15 እስከ 25 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ መደረጉ ታውቋል፡፡

Read 23901 times