Saturday, 31 August 2013 11:51

የብሔራዊ ቴአትር ተዋንያን ቴአትር መቋረጡን ተቃወሙ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)
  • “አዘጋጁን አስፈቅደን ያደረግነው ስለሆነ ችግር የለውም” 
  • - አቶ ሳሙኤል ተስፋዬ (የቴአትር ክፍል ኃላፊ)

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ቤት የሚሰሩ ተዋንያን ቅዳሜ በቋሚነት የሚታይ ቴአትር ተቋርጦ ሌላ ፕሮግራም መካሄዱ ከቴአትር ስነ-ምግባር ጋር የሚቃረን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡ በዛሬው ዕለት ትያትር ተቋርጦ በብሔራዊ ቴአትር የሚካሄደው ፕሮግራም የቴአትር ቤቱን ችግሮች ለመፍታት ያለመ ነው ተብሏል፡፡ የፕሮግራሙ አላማ የተቀደሰ ቢሆንም ቴአትር ማቋረጥ የሞያውንም ሆነ የሞያተኛውን ክብር የሚነካ ነው ብለዋል - ተዋንያኑ፡
የቴአትር ቤቱ የቴአትር ክፍል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ዋናው ጉዳይ አዘጋጁን ማስፈቀድና አዘጋጁ መፍቀዱ መሆኑን ገልፀው፤ የቴአትሩን አዘጋጅ አርቲስት ጌትነት እንየውን የቴአትር ቤቱ አመራሮች ስላስፈቀዱት ችግር እንደሌለው ገልፀዋል፡፡
ተዋንያኑ በበኩላቸው፤ የሙያው መርህ “The show must go on” የሚል በመሆኑ ዝግጅቱን በሌላ ቀን ማካሄድ እየተቻለ ቅዳሜ ማድረግ ሙያውን የሚያንኳስስ ነው ብለዋል፡፡ አንድ ተዋናይ የመድረክ ስራ እያለው እናቱ ብትሞት እንኳን መቅበር አይችልም ያሉት ተዋንያኑ፤ ምንም ቢሆን ቴአትር መቋረጥ እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡
“እኛ የቴትር ቤቱን አካሄድና አሰራር ለማሻሻል የተያዘውን ፕሮግራም አልተቃወምንም፤ ነገር ግን የውይይትና የግብዣ ፕሮግራሙ በሌላ ቀን መሆን ሲችል ቴአትሩን አቋርጦ ማካሄዱ አግባብ አይደለም” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
“የሰውን “ህይወት በአደራ ይዞ የሚሰራው የህክምና ዶ/ር እንኳን ቤተሰብ ቢሞትበት ሌላ ዶ/ር ቀይሮ ቤተሰቡን መቅበር ይችላል” ያሉት ባለሙያዎቹ፤ በቴአትር ሙያ ግን ማንንም መተካት፣ ስራ አቁሞ ዘመድ መቅበርም አይቻልም ብለዋል፡፡
የቴአትር ቤቱ የቴአትር ክፍል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው፤ ቴአትሩ እንዳይቋረጥ ዝግጅቱ ሊካሄድ የነበረው ሀሙስ ቀን እንደነበር አስታውሰው፤ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር የሀሙሱ ባለመሳካቱ ለዛሬ መዛወሩን ገልፀዋል፡፡
የፕሮግራሙ ዋና አላማ ቴአትር ቤቱ መስራት ባለበት መጠን ባለመስራቱና የታለመለትን ግብ ባለመምታቱ፣ ለዚህ ችግር እልባት ለመስጠት የተዘጋጀና ለሙያውም ሆነ ለባለሙያው ክብር ትኩረት የሰጠ ፕሮግራም እንደሆነ ያብራሩት አቶ ሳሙኤል፤ ጉዳዩ በበጐ መልኩ ሊታይ ይገባል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ቴአትር ቤቱን ይመሩ በነበሩት አቶ አዳፍሬ ብዙነህ ጊዜ ለአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ “አባይ ወይስ ቬጋስ” ፊልም ምርቃት ቴአትር ቤቱን በመፍቀዳቸው ከፍተኛ ወቀሳና ትችት እንደደረሰባቸው ያስታወሱት ተዋንያኑ፤ ይህን ድርጊት ከተቃወሙት ውስጥ አንዱ የአሁኑ የትያትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሽመልስ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሽመልስ፤ “ይሄ በፊትም ያለ ነው፤ ኮሚቴውን አነጋግሩ” በማለት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ የቴትሩን አዘጋጅ አርቲስት ጌትነት እንየውን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

Read 16639 times