Saturday, 24 August 2013 11:40

“የሚገርም ተሰጥኦ የታደለ ታላቅ አርቲስት”

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ከአዘጋጁ፡- የድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ድንገተኛ ህልፈትን ተከትሎ በፌስቡክ ላይ ከወጡ በርካታ አስተያየቶች ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ለባለቤቱ፣ ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን እንመኛለን፡፡
ከጥቂት አመታት በፊት አንድ የበጎ አድራጎት ትርኢት ላይ ለመሳተፍ፣ ከዘፋኞች ጋር ወደ ደሴ ተጉዤ ነበር፡፡ የተሣፈርንበት አውቶብስ ጉንጫቸውን በጫት አሎሎ በወጠሩ ዘፋኞች ተሞልቷል፡፡ ዘፋኞቹ ሲሻቸው ይተራረባሉ፣ሲሻቸው ይጮሃሉ፣ይጨፍራሉ፡፡ የአውቶብሳችን ሽማግሌ ሹፌር ሳይቀር፣አልፎ አልፎ መሪውን እየለቀቀ በማጨብጨብ፣ በ ‹‹ቅወጣ›› ከዘፋኞች እንዳማያንስ በማሳየት ላይ ነበር፡፡ በጫቱም፣በጭፈራውም የሌለበት ድምጻዊ ኢዮብ መኮንን ብቻ እንደሆነ ተመለከትሁ፡፡ በእርጋታ ተቀምጦ፣ በአውቶብሱ መስኮት አሻግሮ የሚሮጡ የግራር ዛፎችን ይመለከታል፡፡ ልዩነቱ ግልጽ ነበር፡፡
ድሮ ድሮ፣ ኢዮብ መኮንን አቤሴሎም የሚዘናፈል ረጅም ጸጉር ያለው ጎልማሳ ነበር፡፡ ድንገት ጸጉሩን ተሸለተ፣ ከጸጉሩ ጋር የጥንት ባህርይውን አራገፈ። ጭምት፣ መንፈሳዊና በመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር የነደደም ምዕመን ሆነ፡፡
በተገናኘን ቁጥር፣ኢዮብ ስለእምነት እንድንወያይ ይፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ እምነት የሚያጠብቅ ሰው አንዳች ችግር ይኖርበታል ብዬ አስብ ነበር፡፡ ኢዮብ ግን እጅግ መልካም ሊባል በሚችል ሕይወቱ፣ ይሄንን አመለካከቴን ውድቅ አድርጎብኛል፡፡
የዛሬ ሳምንት ገደማ ኢዮብ ዘፈን በመሥራት ላይ ነበር፡፡ እና ለአንድ ዜማው ግጥም እንድሠራለት ጋበዘኝ፡፡ ከዚህ በፊት የሞከርኳቸው የዘፈን ግጥሞች ስለከሸፉብኝ ግብዣውን ለመቀበል አመነታሁ፡፡ ግን ደሞ ወዲያው፣በኢዮብ ድምጽ ግጥሜ ተዘፍኖልኝ ለማየት ጓጓሁ፡፡ ውሀ ልማት አካባቢ፣ሌክስ ፕላዛ ሕንጻ ሥር መኪናው ውስጥ ቁጭ ብለን ዜማዎችን ማድመጥ ጀመርን፡፡ ዘፈኑ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች አብዛኞቹ ወደ መዝሙር ያዘነብላሉ፡፡ ኢዮብ ዘፈኑን ለፈንጠዝያ ሳይሆን ለስነምግባር ግንባታ ሊጠቀምበት ፈልጓል፡፡ አንድ በጣም ልብ የሚበላ የሶማሌ ዘፈን አስደመጠኝ፡፡
‹‹ሶማሊኛ ትችላለህ እንዴ?>>
‹‹አዎ፣ትግርኛም አውቃለሁ!››
‹‹የት ተማርከው?>>
‹‹አስመራ፣ የወታደር ልጅ መሆኔን አትርሳ››
ከዘፈን ውጭ ምን ታደርጋለህ?
‹‹ኦን ላይን፣ጊታር እየተማርሁ ነው፡፡ ቆይ ላሳይህ››…ላፕቶፑን ለኮሰና ጥቂት አስጎበኘኝ፡፡ ከዛ ከመኪናው ስወርድ የመኪናው እጀታ ስለማይሠራ ወርዶ ከውጭ ከፈተልኝ፡፡ ኢዮብ ብዙ ብሮችን መቁጠር የሚችል ልጅ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ እንኳን መኪናውን የመኪናውን እጀታ ማስቀየር አልፈለገም፡፡ ምናልባት፣ዓመት በአልን ጠብቆ ልብስ የሚቀይር ብዙ ሰው ባለበት አገር ውስጥ፣መኪና መቀያየሩን እንደ ኃጢአት ቆጥሮት ይሆናል፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ ልኡል የተባለ ዘፋኝ ጓደኛዬ፣ የኢዮብን በድንገት መውደቅ ሲነግረኝ ወደ ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ሄድኩ፡፡ ዘፋኞችና አዘጋጆች መጠበቂያው ክፍል ላይ ተደርድረው ይተክዛሉ፡፡ ዘሪቱ፣ ዳግማዊ አሊ፣ እቁባይ በርሄ፣ አጃቸውን አገጫቸው ላይ ጭነው፣ ተቀምጠዋል። የኢዮብ ባለቤት ወዲያ ወዲህ እየተንቆራጠጠች ታነባለች፡፡
ዛሬ ደግሞ ይሄው ሞቱን ሰማሁ፡፡ኢዮብ!!! በጠፈሩ ውስጥ፣ ያለግብ ከሚዞሩ ኮረቶች፣ ያለ ምክንያት ከሚበሩ ኮከቦች በቀር ምንም የለም ብዬ እንደማምን ታውቃለህ፡፡ ይሁን እንጂ ለዛሬ እንኳ፣ የኔ እምነት ከሽፎ ያንተ እምነት እውነት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ በምድር ለገጠመህ መራራ እጣ ሰማያዊ ካሳ (ጉማ) እንድታገኝ እመኛለሁ፡፡
(በዕውቀቱ ስዩም ከፌስ ቡክ)
ኢዮብ የስራ ባልደረባዬ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጓደኛዬም ነበር፡፡ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በፋራናይት ክለብ አብረን ሰርተናል፡፡ ይሄ ቅርብ ግንኙነት እንዲኖረን አድርጐናል፡፡
እኔና ኢዮብ የወንድማማቾች ያህል ነበር። የአስር ዓመት ጓደኝነት ከዚያ ውጭ ምን ሊሆን ይችላል? የኢዮብ ሞት ለእኔ ያልጠበቅሁትና በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ ወደ ኬንያ ለህክምና ሲሄድ ተሽሎት ወደ አገሩ እንደሚመለስ ጽኑ እምነት ነበረኝ፡፡ ኢዮብ ከእንግዲህ አብሮን እንደማይኖር የሰማሁትን ዜና አሁንም ድረስ አምኖ መቀበል አዳግቶኛል፡፡ ኢዮብ የሚገርም ተሰጥኦ የታደለ ታላቅ አርቲስት ነበር፡፡ ይሄን ተሰጥኦውን ገና በቅጡ ሳይጠቀምበት ህይወቱ አለፈ፡፡ ብዙ አስደናቂ ችሎታዎቹን ለማየት በምንጠብቅበት ሰዓት ነው ሞት የቀደመው፡፡ አሁን ምን ማለት አይቻልም - እግዚአብሔር ነፍሱን በሰላም እንዲያሳርፍለት ከመፀለይ በቀር፡፡
(ድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ)
ይሄንን ባለተሰጥኦ ድምፃዊ ለማወቅና ለመተዋወቅ የቻልኩት አንድ ግሩም ወዳጄ ሥራውን በዳላስ፣ ቴክሳስ ሲያስተዋውቅለትና በመስከረም ወር 1997 ዓ.ም ለኮንሰርት ባመጣው ጊዜ ነበር፡፡ ኢዮብ ያኔ “እንደ ቃል” የተሰኘው አዲሱ አልበሙ ወጥቶ ስለነበር ዝናው መናኘት ጀምሯል፡፡ “ኢትዮ - ሬጌ” የተባለ አዲስ የሙዚቃ ዘይቤ ለኢትዮጵያ በተለይ ለዳያስፖራው ያስተዋወቀ አዲስ ዘፋኝ በሚል ነበር የሚታወቀው፡፡ ከዜማው የበለጠ የዘፈን ግጥሞቹ ማራኪ ነበሩ፡፡ ፍቅርን፣ መከባበርንና ትሁትነትን በዘፈኖቹ ሰብኳል፡፡ ኢዮብን በሞት ብናጣውም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ባበረከተው ታላቅ አስተዋጽኦና በትሁት ባህርይው ዘላለም ሲታወስ ይኖራል፡፡
ዳኒ (ከዋሺንግተን ዲሲ)
ከሁለት ዓመት በፊት ኢዮብ በኒውዮርክ ያቀረበውን ኮንሰርት የመታደም ዕድል አግኝቼ ነበር። ገና በመጀመሪያውና ብቸኛ በሆነ አልበሙ ዝነኛ ለመሆን የበቃ አርቲስት ነው፡፡ ያለጊዜው ህይወቱ ማለፉ በጣም ያሳዝናል፡፡
ቢኒያም ጌታቸው (ከአሜሪካ)
የቅርብ ጓደኛው አልነበርኩም፡፡ እኔን ጨምሮ በአብዛኛው ሰው ዘንድ ይወደድ እንደነበር ግን አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ተወዳጅ የነበረ ወጣት የሬጌ አቀንቃኝ አጥታለች፡፡ እግዚአብሔር ነፍሱን በመንግስተ ሰማያት ያኑርለት፡፡ ለቤተሰቡ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡
ለማ ገብረማርያም (ከኢትዮጵያ)
ልብን የሚያላውስ ዘፋኝ ነበር፡፡ አዲስ አበባ እያለሁ ኮንሰርቶቹንና በምሽት ክለብ የሚያቀርባቸውን ሥራዎች ታድሜያለሁ፡፡ በተለይ በክለብ H20 እና በፋራናይት በሚያስገርም ድምፁ መድረኩን የቀወጠባቸውን ሌሊቶች ፈጽሞ አልረሳቸውም፡፡ የእሱ ሞት በተለይ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ እጦት ነው፡፡ ሁላችንም አዲሱን አልበሙን እንጂ ሞቱን አልጠበቅንም ነበር፡፡ በጣም አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡
አለማየሁ ጨቡዴ (ከኩዌት)
በአዲስ አበባ ኮንሰርቶቹን ተከታትያለሁ፡፡ በምሽት ክበቦች ሲዘፍን ታድሜያለሁ፡፡ ዘፈኖቹን በመኪና ውስጥ፣ እቤቴና ቢሮዬ እሰማቸዋለሁ። በዘፈኖቹ ተለክፌ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ጂም አብረን ስንሰራ ከስፖርት በኋላ ስቲም ውስጥ እናወራለን፡፡ በጣም አሪፍ ሰው ነበር - ለጨዋታና ለጓደኝነት የሚመች፡፡ ሁላችንም ነን ያጣነው፡፡ የእሱ ሞት ለሁላችንም ትልቅ ጉዳት ነው፡፡
ብሩክ ኢትዮ (አዲስ አበባ)
አሁንም ድረስ ከድንጋጤ አልወጣሁም፡፡ እኔና ኢዮብ የፌስቡክ ጓደኛ የሆንነው ሙዚቃውን ከሰማሁ በኋላ ነው፡፡ የዓለም ተጓዦች የሆኑ ሰዎች ሲዲውን ይዘውት ስለነበር ከእነሱ ተውሼ ነው ያደመጥኩት፡፡
በቅርቡ ካሊፎርኒያ ለኮንሰርት በመጣ ጊዜ “All night pressure” የተባለው የእኔ ባንድ እንዲያጅበው ተስማምተን ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አልተሳካም፡፡ የሁለተኛ አልበም ቀረፃችንን ለመጨረስ ውጥረት ውስጥ ነበርን፡፡
ከኢዮብ ጋር ባወራንባቸው ጥቂት ጊዜያት ሃቀኛ ነፍስ እንደነበረውና ሲበዛ ደግ መሆኑን ለመገመት አልቸገረኝም፡፡ የግጥሞቹ ትርጉም ባይገባኝም ድምፁና አዘፋፈኑ ውብና አይረሴ ነበር፡፡ ሙዚቃ ክልልና ድንበር ተሻጋሪ ለመሆኑ ይሄም ተጨማሪ አብነት ነው፡፡ በዚህ ሰዓት በጣም አዝኛለሁ፡፡ ለባለቤቱና ቤተሰቦቹ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ። በዚህ የሀዘን ጊዜ በፀሎት ከጐናችሁ መሆኔን ለመግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
ክሪስ ኤሊስ (ኦሬንጅ ካንቲ፣ ዩኤስኤ)

==============
ድምጻዊ እዮብ መኮንን ዘውዴ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ዘውዴ ይመኑ እና ከእናቱ ወ/ሮ አማረች ተፈራ የምሩ ጥቅምት 12 ቀን 1967 ዓ.ም በጭናቅሰን ገብርኤል ጅጅጋ ከተማ ተወለደ፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጅጅጋ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ከፊል የሁለተኛ ደርጃ ትምህርቱን ደግሞ ከወላጅ አባቱ ጋር ወደ አስመራ በመሄድ የተከታተለ ሲሆን፤ቀሪውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ወደ ጅጅጋ በመመለስ ተምሯል፡፡ በ1991 ዓ.ም. በአጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ የሚያመጡ ፈቃደኛ ሰዎች በማግኘቱ እራሱን ያስተዳድርበት የነበረውን የፎቶግራፍ አንሺነት ሥራን ትቶ፣ በ24 ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የያኔው ፋልከን ክለብ ድምጻዊነቱን “ሀ” ብሎ ጀመረ።
ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ አልበሙን እስካወጣበት 2000 ዓ.ም ድረስ የሌሎች ድምጻውያንን ሥራዎች፣በዋነኝነት የአሊ ቢራን እና የቦብማርሊን ዘፈኖችን ሲያቀነቅን የቆየ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ውጭ ወደ ዱባይም በመመላለስ በድምጻዊነቱ ሰርቷል፡፡ በጥቅምት 2000 ዓ.ም በአብዛኛው በሬጌ ስልት የተዘጋጀው “እንደቃል” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበሙ ከተለቀቀ አጭር ጊዜ በኋላ፣ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማትረፍ እስካሁን ድረስ በከፍተኛ መጠን በመደመጥ ላይ ይገኛል፡፡ በአዲስ ጣዕም የመጣው “እንደቃል” አልበም በኢትዮጵያ ውስጥ የሬጌ ሙዚቃ ይበልጥ ይወደድ ዘንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል።
ከዚህ አልበሙ በኋላ በሀገር ውስጥ እና ከሃገር ውጪ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እያቀረበ ቆይቷል፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ የሙዚቃ ቦታዎች ላይም ለረጅም ጊዜያት በቋሚነት የራሱን ዘፈኖች ለአድናቂዎቹ በመድረክ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ሁለተኛ አልበሙንም በመሥራት ላይ የነበረ ሲሆን በድንገት እስኪታመም ድረስ ሙሉ ትኩረቱ በዚሁ ሥራው ላይ ነበር፡፡ ድምጻዊ እዮብ መኮንን ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በድንገተኛ የስትሮክ ህመም መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ላይ የወደቀ ሲሆን፤ህመሙ ጠንቶ እራሱን ሳያውቅ በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሲደረግለት ቆይቶ በወዳጅ ዘመዶቹ ርብርብ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ናይሮቢ ኬንያ ሄዶ፣ በአጋካን ሆስፒታል ሕይወቱን ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም በታመመ በአምስተኛ ቀኑ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ምሽት በ38 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል፡፡
ድምጻዊ እዮብ መኮንን ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ነበር። የድምጻዊ እዮብ መኮንን የቀብር ስነ-ስርዓት ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም ቤተሰቦቹ፣ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

Read 7653 times