Saturday, 24 August 2013 11:27

መሃንዲሱ ኮሜንታተር - ከአርባ ምንጭ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

ዋና ሳጅን ገረመው ታደሰ ይባላል፡፡ በፌደራል ፖሊስ ኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት ውስጥ በምህንድስና ሙያ ይሰራል፡፡ ኮሜንታተርም ነው፡፡ በትርፍ ሰዓቱ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በሞባይሉ ለአርባ ምንጭ ስፖርት አፍቃሪዎች ያስተላልፋል፡፡ የፈጠራ ሃሳቡ የራሱ ነው፡፡ ዋና ሳጅን ገረመው በኮሜንታተርነቱ ባገኘው አድናቆት የአርባ ምንጭ ከነማ የእግር ኳስ ክለብ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን እንዲሰራ ተደርጓል። የስፖርት አድማስ አዘጋጅ ግሩም ሰይፉ፤ ባለትዳርና የ4 ልጆች አባት ከሆነው ዋና ሳጅን ገረመው ጋር እንደሚከተለው አውግቷል፡፡
እኔ የማውቅህ በኮሜንታተርነት ነው፡፡ እስቲ ስለምህንድስናው ንገረኝ?...
በፌደራል ፖሊስ የምህንድስና ክፍል ባለሙያ ነኝ፡፡ በምህንድስና ሙያዬ በተለያዩ የኮንስትራክሽን ስራዎች በህንፃ ፎርማንነት እያገለገልኩ ነው፡፡ በዚህ ሃላፊነቴ በትልቅ ፕሮጀክት ላይ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ፕሮጀክቱ በኮልፌ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ አባላት የመኖርያ ካምፕ ነው፡፡
ዋና ሙያህና ኮሜንታተርነቱ አይጋጭብህም?
የክፍል አባሎቼ ለስፖርቱ ያለኝን ከፍተኛ ፍላጎት እና ዝንባሌ ያውቃሉ፡፡ ትልቅ ደረጃ እንድደርስ ስለሚመኙ ሁሌም ድጋፍ ያደርጉልኛል፡፡ በዚህም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ በተረፈ ግን ብዙ ጊዜ፤ ኮሜንታተርነቱን በእረፍት ሰዓቴ ነው የምሰራው፡፡ እንደምታውቀው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች የሚካሄዱት ከ10 ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ብዙ ጨዋታዎችም ቅዳሜ እና እሁድ ነው የሚደረጉት፡፡ እናም ሁለቱ ሥራዎች የሚጋጩበት ሁኔታ የለም፡፡ እስካሁንም ምንም ችግር ሳይገጥመኝ ሁለቱንም በሙሉ አቅም እና ብቃት ጎን ለጎን እያካሄድኩ ነው፡፡
እንዴት ነው ወደ ኮሜንታተርነት የገባኸው?
ኮሜንታተር የሆንኩት ለእግር ኳስ ባለኝ ከፍተኛ ፍቅር ነው፡፡ በተለይ የደምሴ ዳምጤን አርዓያ ለመከተል ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ደምሴ ዳምጤ በጣም የማደንቀው ኮሜንታተር ነበር፡፡ ጨዋታዎችን በቀጥታ የሚያስተላልፍበት መንገድ፤ የሚሰጠው መረጃ፣ የአገላለፅ ችሎታው ፤ የእግር ኳስ ስሜቱ እና ድምፁ ሁሉ ያስደስተኛል፡፡ ይገርምሃል ደምሴ ዳምጤ በኮሜንታተርነት የሚያስተላልፈውን ጨዋታ ለመስማትና ለማየት ብዬ ለእስር ተዳርጌአለሁ፡፡ የዛሬ 26 ዓመት ነው፡፡ ኢትዮጵያ፤ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድርን አዘጋጅ ነበረች፡፡ ያኔ እኔ ለምረቃ እየተዘጋጀሁ ያለው ምልምል ፖሊስ ነበርኩ፡፡ ፖሊስ ለመሆን አንድ አመት ከሁለት ወር በለገዳዲ የፖሊስ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መሰልጠን ያስፈልጋል፡፡ አንድ ወሩ ግን የልምምድ ጊዜ ነው፡፡ እኔ እና ሌሎች ባልደረቦቼ ለመመረቅ የልምምድ ስራ ላይ ነበርን፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ የተመደብነው ደግሞ ስቴዲየም ነው፡፡ ክፋቱ ግን እኔ የነበርኩት ውጭ ነው፤ 7 ቁጥር በር አካባቢ፡፡ በጣም አዘንኩ፤ አለቀስኩ፡፡ ጓደኞቼ እንዲቀይሩኝ ጠየቅኋቸው፡፡ እነሱም ጨዋታውን መመልከት ስለፈለጉ ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ከዚያ ምን አደረግሁ መሰለህ? የተመደብኩበትን ስራ ትቼ ጂንስ ጃኬት አስመጣሁና ለብሼ ወደ ስታዲየም ውስጥ በመግባት፣ ህዝብ መሃል ቁጭ አልኩ፡፡ በካታንጋ በኩል ነበር፡፡ አለቃዬ ፈልገውኝ ስታዲየም መግባቴን ሲሰሙ ስሜ እንዲመዘገብ አደረጉ፡፡ እኔ ግን ደስ ብሎኛል፡፡ የተመደብኩበትን ሥራ ጥዬ ስቴዲየም በመግባቴ ምን እንደሚከተለኝ እንኳ አላሰብኩም፡፡
ጨዋታው ተጀመረ፡፡ እዚያው ካታንጋ መሃል ከጎኔ የነበረ አንድ ሰውዬ ትንሽዬ ሬድዮ ይዞ ነበር፤ “ስጠኝ” አልኩት፤ ሰጠኝ፡፡ ጨዋታውን እያየሁ በሬድዮ ደምሴ ጨዋታውን ሲያስተላልፍ፣ ለመስማት ፈልጌ ነው፡፡ ደምሴ የብሔራዊ ቡድናችንን ብርቅዬ ተጨዋቾች አሰላለፍ በሬዲዮ ሲያስተላልፍ በዓይኔ መመልከቴ ልዩ ስሜት ፈጠረብኝ፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ ነው ኮሜንታተር ለመሆን የወሰንኩት፡፡ ቤቴ ውስጥ ቁጭ ብዬ ድምፄን እየቀዳሁ ኮሜንታተር ለመሆን መለማመመድ ጀመርኩ፡፡ ያደረግሁትን ሁሉ ለጓደኞቼ እነግራቸው ነበር፡፡ ድምፄንም ሲሰሙ ጥሩ ነው ብለው አበረታቱኝ፡፡ በዚያው ቀጠልኩበት፡፡
አለቃህ ምን አሉ… ስቴዲዬም በመግባትህ?
አለቃዬ ሲጠይቁኝ፤ “ጌታዬ፤ ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም፤ ጨዋታውን ማየት ነበረብኝ፡፡ ጓደኞቼን ቀይሩኝ ብላቸው እምቢ ሲሉኝ ነው የገባሁት” አልኳቸው፡፡ ጥፋተኛ ነህ ተብዬ ኮልፌ ለአምስት ቀን ታሰርኩ፡፡ የሚገርምህ ከደምሴ ብዙ ተምርያለሁ፡፡ ዋናው ነገር ግን አንድ ሰው ለ90 ደቂቃ ጨዋታውን በተሟላ አቅም እና በሚያጓጓ ስሜት ተከታትሎ ማስተላለፍ እንደሚችል ማወቄ ነው፡፡ ደምሴን የማደንቀው በዚህ ነው፡፡ ለ90 ደቂቃ ጨዋታ ማስተላለፍ የለመድኩትም ከሱ በወሰድኩት አርዓያነት ነው፡፡ ከ65 ደቂቃ በኋላ ማንኛውንም ጨዋታ ስታስተላልፍ ይደክምሃል፡፡ ድምፅህ ሃይሉ ሊቀንስ ይችላል፡፡ እኔ ግን በልምምድ ጨዋታዎች 90 ደቂቃ ሙሉ ለብቻዬ የማስተላለፍ ብቃት አዳብሬያለሁ፡፡ ጨዋታዎችን በማስተላለፍበት ጊዜ አንድ በእግር ኳስ ህይወት እንግዳ ይኖረኛል፡፡ በተለይ ከደቡብ ክልል የሆነ ስፖርተኛ አቀርባለሁ፡፡
የአርባምንጭ ክለብ ኮሜንታተርነትን እንዴት እንደጀመርከው ንገረኝ…
በአንድ ወቅት ከአርባ ምንጭ እግር ኳስ ክለብ አመራሮች ጋር ሆነን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአርባምንጭ ጨዋታን ለማስተላለፍ ፈለግን፡፡ የአርባምንጭ ስፖርት አፍቃሪ ክለቡ በአዲስ አበባ የሚያደርገው ጨዋታ እንዲተላለፍለት ጠይቆ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የአርባምንጭ ደጋፊዎች የአዲስ አበባ አስተባባሪ ስለነበርኩ፣ ከክለቡ ሃላፊዎች ጋር ሆነን በዛሚ ኤፍኤም ጨዋታውን በቀጥታ ለማስተላለፍ ጠየቅን፡፡ የተጠየቅነው ገንዘብ ከፍተኛ ነው -13ሺ ብር፡፡ ያልጠበቅነው ነበር፡፡
የክለቡ አመራሮች “ሳጅን ምን ታስባለህ” አሉኝ። እኔ ይሄ ሁሉ ገንዘብ ሊከፈል አይገባም አልኳቸው። ከዛም ጨዋታውን ማስተላለፍ የምችልበት ዘዴ እንዳለኝ ገለፅኩላቸው፡፡ “እንዴት አድርገህ” አሉኝ፡፡ አርባምንጭ ከምታውቁት ሙዚቃ ቤት ጋር አገናኙኝ አልኳቸው፡፡ ቀደም ሲል ጨዋታውን ስታዲየም ሆኜ በስልክ ማስተላለፍ እንደሚቻል ያደረግኋቸው ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ነገሩ እንደሚሳካ ጥርጥር አልነበረኝም፡፡ ኖኪያ የስልክ ቀፎ አለኝ፤ በሄድፎን ጆሮዬ ላይ እሰካዋለሁ፡፡ ከዚያም አርባምንጭ ከተማ ከሚገኘው ሙዚቃ ቤት ጋር በቀጥታ ስልክ በመደወል እገናኛለሁ፡፡ ሙዚቃ ቤቱ በስልኩ የማስተላልፈውን የእኔን ድምፅ በጃክ በመቀጠል በሞንታርጎ ያሳልፈዋል። እናም “ብርሃን ፀረ ኤድስ ማህበር” ከሚባል ሙዚቃ ቤት ጋር በመተባበር ጨዋታዎችን ማስተላለፍ ጀመርኩ - በኮሜንታተርነት ነው፡፡ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ በረከት አርባምንጭ ሆነው በቴክኒክ ተቆጣጣሪነት ይሰሩልኛል፡፡
ስፖርት አፍቃሪው የት ሆኖ ነው ጨዋታውን የሚከታተለው?
ጨዋታው በአርባምንጭ መናኸርያ ነው የሚተላለፈው፡፡ መናኸርያው በጣም ሰፊ ነው። በዚያው አካባቢ አምስትና እና ስድስት ሞንታርጎ ስፒከሮች በ4 ሜትር ልዩነት ተራርቀው በተለያዩ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ፡፡
ጨዋታውን ስታስተላልፍ ምን ያህል ሰው ይከታተልሃል?
ስጀምር በአንድ ጨዋታ እስከ 20ሺ ሰው ይከታተለኝ ነበር፡፡ አሁን እስከ 30ሺ የሚደርስ ይመስለኛል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ያስተላለፍኩት ጨዋታ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ያደረጉት ነበር፡፡
“አድማጮቻችን መስመራችን ከአሁን ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ከአዲስ አበባ ስታዲየም 505 ኪሎ ሜትር ተጉዞ አርባምንጭ ከተማ ይደርሳል። በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ 26ኛ ሳምንት፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአርባምንጭ ከነማ ጨዋታን እናስተላልፋለን፡፡ አሁን የአርባምንጭ ከተማ አሰላለፍ ደርሶኛል፤ እንደሚከተለው እገልፃለሁ፡፡ 1 አንተነህ መሳይ፤ 2 አንተነህ ተስፋዬ፤ 3 እምሻው ካሱ፤ 4 ታገል አበበ፤ 5 አብዮት ወንድይፍራው፤…” እያልኩ አስተዋውቃለሁ፡፡ በመጀመርያ የየክለቦቹን የተጨዋቾች አሰላለፍ ዝርዝር እገልፃለሁ፡፡ የተጨዋቾችን ስም ዝርዝር ከቡድን መሪዎች አገኛለሁ። የማላገኝ ሲሆን ከማሊያቸው እያየሁ አስተላልፋለሁ፡፡ የማውቃቸውን በስም እጠቅሳለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ በግራ ጥላ ፎቅ፤ የጊዮርጊስ ደጋፊዎች በሚቀመጡበት አካባቢ ሆኜ ነው ጨዋታዎችን የማስተላልፈው፡፡
በደጋፊ መሃል ሆኖ ጨዋታውን ማስተላለፍ አይቸግርም? ለምን ለኮሜንታተሮች በተመደበው የትሪቡኑ ክፍል ወይም መሐል ሜዳ ትራኩ አካባቢ ወርደህ አታስተላልፍም?
ይህን ብዙ አላሳብኩበትም፡፡ ፌደሬሽኑ ካልከው ሥፍራ እንዳስተላልፍ ይፈቅድልኛል ብዬ አስባለሁ። የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች የምሰራውን ስራ የሚያደንቁ ይመስለኛል፡፡ እስካሁን ማንም አልከለከለኝም፡፡ በፈጠራዬ ከብዙ አካላት አድናቆት አትርፌያለሁ። ጋዜጠኞች ስለእኔ ተግባር በአድናቆት ዘግበዋል ፅፈዋል፡፡ ለእኔም ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ሆኖኛል፡፡ በአዲሱ የውድድር ዘመን ይህን ስራዬን እንዳልከው ፈቃድ አግኝቼ በትሪቡን ለመስራት ሃሳብ አለኝ፡፡ ኮሜንታተርነት ስሜታዊ ቢያደርግም ሚዛናዊ ሆነህ ጨዋታውን ማስተላለፍ አለብህ ብዬ አምናለሁ፡፡ በኮሜንታተርነቴ በአርባምንጭ በመደነቄ፣ የክለቡን የህዝብ ግንኙነት ስራዎች እንድሰራ አድርጎኛል፡፡ እስካሁን በስራዬ ያገኘሁት ሽልማት ባይኖርም ከህዝቡ የማገኘው ፍቅር ትልቅ ብርታት ነው፡፡
እስከዛሬ በዚህ መንገድ ስንት ጨዋታ አስተላለፍክ?
ሁለት ዓመት ሰርቼያለሁ፡፡ የአርባምንጭ ክለብ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ከሜዳው ውጭ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ አስተላልፌያለሁ፡፡ ከአርባምንጭ ስታዲየም ደግሞ በአዲስ አበባ ኮልፌ ፤ ሽሮሜዳ እና አስኮ ለሚኖሩ የክለቡ ደጋፊዎች ለበርካታ ጊዜያት ጨዋታዎችን አስተላልፌያለሁ፡፡ በአዲስ አበባ 20ሺ የሚደርሱ የክለቡ ደጋፊዎች እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ ከአርባምንጭ ስታዲየም የምንደግፈው ክለብ ጨዋታ ይተላለፍ ብለው ይጠይቁኛል፡፡ ዘንድሮ የአርባምንጭ ክለብ ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ 18 ጨዋታዎችን ሰርቻለሁ፡፡ ከሜዳው ውጭ ያደረጋቸውን ሁሉንም 13 ጨዋታዎች አስተላልፌያለሁ፡፡ ካስተላለፍኳቸው ጨዋታዎች ምርጥ የምለው፣ የዘንድሮው ሻምፒዮን ደደቢት እና አርባምንጭ ተገናኝተው 1ለ1 የተለያዩበት ጨዋታ ነው፡፡
እስቲ ስለ አርባምንጭ ስታዲየም ንገረኝ…? የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በርካታ ተመልካች ከሚያገኙባቸው የአገሪቱ ስታዲየሞች አንዱ ነው…
የአርባምንጭ ስታዲየዬም ተራራ አጠገብ ነው። ከተራራው ስር ሜዳው አለ፡፡ በጥላ ፎቁ በኩል እስከ 25 ሜትር ከፍ ባለው እና ወደ ጎን ረጅም በሆነው ጋራ እርከን ተሰርቶለታል፡፡ በኮረብታው ላይ በሲሚንቶ መቀመጫ ተሰርቷል፡፡ በካታንጋ በኩል ደግሞ በሽቦ ታጥሮ ተመልካች ይገባበታል፡፡ ብዙ ጨዋታዎች ሲደረጉ 70ሺ ያህል የስፖርት አፍቃሪ ይገኛል፡፡ በአንድ ጨዋታ በአማካይ እስከ 55ሺ ተመልካች አይጠፋም። 3ብር፤ 5ብር እና 10 ብር ነው መግቢያው፡፡ በርግጥ ሳይከፍል የሚገባም ይኖራል፡፡ ከፍሎ ባይገባም ከስታዲየሙ ክልል ራቅ ብሎ እስከ 15ሺ የሚደርስ ተመልካች ጨዋታውን ሲታደም ትመለከታለህ። እንዴት ደንበኛ ስታድዬም አልተሰራም ልትል ትችላለህ፡፡ በቅርቡ እንደሚገነባ አልጠራጠርም፡፡ አርባምንጭ ከነማ ክለብ፤ ፕሪሚዬር ሊግ በገባበት በዚህ አመት ይህን ተፈጥሯዊ ስታዲየም ለማሳደስ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል፡፡ የፕሪሚዬር ሊግ ስታንዳርድ እንዲኖረው አፈር የነበረው ሜዳ ሳር ለብሷል፡፡ መቀመጫ አልነበረውም፤ ተሰርቶለታል። ሻወር ቤት፤ ሽንት ቤት… ሁሉም አስፈላጊ ነገሮች ተሰርተውለታል፡፡
በኮሜንታተርነት የምታገኘው ክፍያ አለህ? የምሰራው ለእግር ኳስ ፍቅር ብዬ ነው፡፡ ምንም የምጠይቀው ክፍያ የለም፡፡ ያው ጨዋታውን የማስተላልፈው በስልክ እንደመሆኑ፣ በአንድ ጨዋታ እስከ 200 ብር ካርድ እሞላለሁ፡፡ ስፖንሰሮቼ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ስልኬ ላይ እየደወሉ “ጨዋታ ለምታስተላልፍበት ካርድ እንሞላለን” ብለው ይረዱኛል፡፡ የስታዲየም መግቢያ የሚከፍሉልኝም እነዚህ ስፖርት አፍቃሪዎች ናቸው፡፡
በቋሚነት ስፖንሰር ከሚያደርጉህ ኩባንያዎች ጋር ለምን አትሰራም?
የምሰራው ለማትረፍ ብዬ አይደለም፡፡ የእኔ ዋና ትኩረት ስፖርት አፍቃሪው ቤተሰብ የሚደግፈውን ክለብ ውጤት በትኩሱ ማግኘት አለበት የሚል ነው። በአርባምንጭ ከህፃን እስከ አዛውንት ስታዲየማም ገብቶ ክለቡን ሲደግፍ ማየት ያስደስተኛል፡፡ ወደፊት አርባምንጭ በሚገኘው ኤፍኤም ሬድዮ ለማስተላለፍ የክለቡ ቦርድ እየጣረ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ያን ጊዜ ከቋሚ ስፖንሰር ኩባንያዎች ጋር እንሰራለን ብዬ አስባለሁ፡፡
የደቡብ ክልል እግር ኳስ ጥሩ እድገት እያሳየ ነው። አሁን ፕሪሚዬር ሊግ የገቡ ክለቦች ብዛት አራት ደርሷል። በሌላ በኩል ከአርባምንጭ የሚወጡ ተጫዋቾች በውጤታማነታቸው እየታወቁ መጥተዋል። የደቡብ ክልል እግር ኳስ የስኬት ምስጢር ምን ይመስልሃል?
አርባምንጭ በየሰፈሩ ሜዳ ነው፡፡ ከ5 ዓመትህ ጀምሮ ኳስ ትጫወታለህ፡፡ በ1970ዎቹ የታዳጊ ቡድን ውድድሮች ነበሩ፡፡ የስፖርት መምህራኖች ናቸው የታዳጊ ውድድሮችን የጀመሩት፡፡ አሁን ሃይሌ ደጋጋ በሚባል ትምህርት ቤት ሰለሞን ውሹ የሚባል የስፖርት መምህር ነበር፡፡ እኔን ሁሉ አሰልጥኖኛል፡፡ ይህ አይነቱ የታዳጊዎች ውድድር አሁን ብዙ የለም። ይህ መመለስ አለበት፡፡ አርባ ምንጭ ካፈራቻቸው ታዋቂ ተጨዋቾች መካከል ከድሮው ተስፋዬ ፈጠነ ይጠቀሳል፡፡ ከአሁኑ የብሄራዊ ቡድን አባላት ደግሞ ደጉ ደበበና አበባው ቡጣቆ ከዚያው የወጡ ናቸው፡፡ ደጉ እና አበባው የሲቃላ ልጆች ናቸው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ አውቃቸዋለሁ፡፡ ስፖርት ይወዳሉ፣ በጠዋት ተነስተው በልዩ ስሜት እና ፍቅር ሲሰሩ አያቸው ነበር። አርባምንጭ ምግቡም ልጆቹን የሚያጠነክር፡፡ የዚያ ከተማ ልጆች በአሳ ፤ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በስጋ ያደጉ ናቸው፡፡ አሳ አዘውትረው መብላታቸው በሳል አድርጓቸዋል፡፡ ስጋው፤ አትክልቱ እና ፍራፍሬው ደግሞ ጠንካራ ተክለሰውነት አዳብሮላቸዋል፡፡ በአርባምንጭ በየዓመቱ በወረዳዎች መካከል ብዙ ስፖርቶችን የሚያካትት ውድድሮች ይደረጋሉ። በሁለት እና ሶስት ዓመት ለፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች እና ለብሄራዊ ቡድን የሚበቁ ምርጥ ተጨዋቾች መውጣታቸው አይቀርም፡፡ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በከተማው የታዳጊ ፕሮጀክት እየሰራ መሆኑ በአርባምንጭ ያለውን አቅም ያሳያል፡፡ የፕሪሚዬር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ከደቡብ ክልል ጨምረዋል፡፡ ሃዋሳ ከነማ አለ፤ ሲዳማ ቡና፤ አርባምንጭ እና አሁን ደግሞ ወላይታ ዲቻ፡፡ በብቃታቸው አነፃፅር ብትለኝ… ጠንካራው እና ልምድ ያለው ሃዋሳ ቀዳሚ ነው፡፡ ከዚያ አርባምንጭ እና ሲዳማ ቡና፤ ቀጥሎ ገና በፕሪሚዬር ሊጉ ብቃቱ የሚፈተነው ወላይታ ዲቻ ብዬ በደረጃ አስቀምጣቸዋለሁ፡፡
ለወደፊቱ ምን አቅደሃል?
ምን መሰለህ ፍላጎቴ? የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታን በቀጥታ በማስተላለፍ ብቃቴን ማሳየት ነው። መነሻዬን ክለብ አድርጌያለሁ፡፡ ወደፊት ግን የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ማስተላለፍ ነው የምፈልገው፡፡ ግብዣው ይኑር እንጂ ብሄራዊ ቡድን በሴካፋ እና በሌሎች ውድድሮች ሲጫወት ባስተላልፍ ምኞቴ ነው፡፡ አሁን ያለው ብሄራዊ ቡድን ባለው ፍቅር እና አንድነት በጣም ነው የምኮራበት፡፡ ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ ብሄራዊ ቡድኑ በፍፁም ታታሪነት እና ጀግንነት ያስመዘገበው ውጤት፣ በጣም የምደነቅበት እና የምኩራራበት ነው፡፡ አሁንም ጳጉሜ አራት ከሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 3ለ1 አሸንፎ፣ ለቀጣዩ ውድድር እንደሚበቃ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሁለቱን ጎሎች ጌታነህ ከበደ፣ አንዱን ሽመልስ በቀለ ያገባሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡

Read 4599 times