Saturday, 24 August 2013 10:56

የቅድመ ካንሰር ምርመራ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(3 votes)

የማህጸን በር ካንሰር ለብዙ ሴቶች ሕይወት ጠንቅ በመሆኑ የክትባቱዋጋ እንዲቀንስ ብቻም ሳይሆን ጥረት በመደረግ ላይ ያለው በነጻ እንዲሰጥም ጭምር ነው፡፡
የማህጸን በር ካንሰር ከማህጸኑ በር አካባቢ ባለው የውስጠኛ ክፍል ይጀምራል፡፡ እዚያ አካባቢ ያሉ ሴሎች ሲፈጠሩ ከነበራቸው ይዘት ወደ ቅድመ ካንሰርነት ተለውጠው በስተመ ጨረሻው ሙሉ ካንሰር ይሆናሉ፡፡ በማህጸን ካንሰር የተያዙ ሴቶች የብልት መድማት ፣ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የወር አበባ መፍሰስ ፣የወር አበባ ከተቀዋረጥ በበሁዋላ በብልት በኩል ደም መፍሰስና ሽታ ያለው ፈሳሽ ከማህጸን መፍሰስ ፣የማህጸን ምርመራ ከተደረገ በሁዋላ መድማትና በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት ሕመም መሰማት ይታይባቸዋል ይላል አንድ መረጃ፡፡ የማህጸን በር ካንሰር ገና በጅምር ደረጃ ላይ እያለ ሊደረግ የሚገባውን ህክምና እና በተለይም ክትባት አሁን ያለበትን ደረጃ በሚመለከት ለዚህ አምድ ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ የአዲስ ሕይወት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር እና በአ.አ ዩኒቨርሲት ህክምና ማእከል ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ትምህርት አስተማሪ ናቸው፡፡
ጥ/ ካንሰር በሴቶች የመራቢያ አካል በየትኞቹ የሰውነት ክፍሎች ላይ ይከሰታል?
መ/ በሴቶች የመራቢያ አካል አካባቢ የሚነሳ የካንሰር አይነት እራሱን የቻለ ትምህርት ያለውና
ባለሙያ የሚያስፈልገው ሲሆን ስርጭቱም ሰፊ ነው፡፡
መጀመሪያ በውጭ አካል ማለትም ወደማህጸን መግቢያው ላይ፣
በብልት አካባቢ ፣
ከማህጸን በር እና ልጅ ከሚያቅፈው ክፍል ፣
ዘር ማፍለቂያው ወይንም ኦቫሪ ከሚባለውም የሚከሰት የካንሰር አይነት ያጋጥማል፡፡
ጥ/ የማህጸን ጫፍ ..በር .. ካንሰር ማለት ምን ማለት ነው?
መ/ የማህጸን ጫፍ ..በር .. ካንሰር ማለት በተለይም በታዳጊ አገሮች በአብዛኛው የሚከሰት ነው፡፡ የማህጸን ጫፍ ወይንም በር ማለት ልጅ የሚወለድበት ወይንም ደግሞ የታችኛውን እና የላይኛውን የማህጸን አካል የሚያገናኝ ክፍል ነው፡፡ይህ አካል ቅድመ ካንሰር ወይንም ካንሰር በሚባል ደረጃ ሊጎዳ የሚችል ሲሆን ሕመሙ ወደካንሰር ሳይለወጥ በቅድመ ካንሰር ደረጃ እያለ ለማከም እጅግ አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ ምክንያቱም ሕመሙ ገና ሲጀምር ባለበት ሁኔታ ምንም ምልክት ስለማያሳይ ነው፡፡ ሕመሙ ገና ከመጀመሪያ ደረጃ ላይ እያለ መኖሩ የሚታወቀው ምርመራ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ በምርመራው ወቅት በሐኪም የሚታይ ወይንም የሚዳሰስ ነገር ባይኖር እንኩዋን ፈሳሽ ተወስዶ በሚደረገው የላቦራቶሪ ፍተሻ ካልሆነ በስተቀር ሴቶች ምንም ምልክት አያዩም፡፡ነገር ግን ወደካንሰር ከተለወጠ በሁዋላ የራሱ ደረጃ ስላለው በዚያ ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ካንሰር ጊዜ ከወሰደ በሁዋላ ከሆነ ሕመም ፣ፈሳሽ ፣ቁስል የመሳሰሉት ነገሮች ስለሚኖሩ ታማሚዋ ልታውቀው ትችላለች፡፡ ቅድመ ካንሰር ባለበት ደረጃ ሕክምናው ከተሰጠ ጭርሱንም ሊድን የሚችል በሽታ ሲሆን ጊዜ ወስዶ ሕመሙ እየተስፋፋ ከመጣ በሁዋላ ከሆነ ግን ማከም ቢቻልም በሽታውን ጭርሱንም ማጥፋት ግን ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ካንሰር ምርመራ የሚባለው ካንሰር የሚከሰትበት ሁኔታን የሚያሳይ ምልክት የሚታይበትና ሙሉ በሙሉ ወደካንሰር በሽታነት ከመለወጡ በፊት ለሕክምና ዝግጁ መሆን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛዋም ሴት ከ25-30አመት እድሜዋ በሁዋላ በየአመቱ ምርመራ ማድረግ እንዳለባት ሁኔታዎች ያስገድዳሉ፡፡ ምናልባትም የምርመራው ውጤት ደህና ከሆነ እድሜያቸው 60 /አመት እስኪሞላ ድረስ በየሶስት አመት ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ እውነታዎች ያረጋግጣሉ፡፡
ጥ / ካንሰርን ለመከላከል የሚያስችለው ክትባት ከምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
መ/ የማህጸን በር ካንሰር የሚመጣው በቫይረስ ነው፡፡ ቫይረሱም ..ሃበቂሮቃ ቅሮቅሽቁቁቄቂሮ ባሽቈበቋ .. ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ሲሆን በዚህ ስያሜ የተንተቱት የቫይረስ አይነቶች ወደ 120/ ይደርሳሉ፡፡ ከነዚህም ወደ 30/ የሚሆኑት ፊንጢጣና ማህጸን አካባቢቃስ የሚያጠቁ ናቸው፡፡ ከነዚህም ካንሰር የሚያመጡና የማያመጡ ተብለው የሚከፈሉ ሲሆን ካንሰር የሚያመጡት በቁጥር ከ15-17/ ድረስ የተለዩት ናቸው፡፡ ስለዚህ ክትባቱ የተገኘው ለአ ራቱ ሲሆን ካንሰር ከሚያመጡት ውስጥ ለ16/ እና 17/ እንዲሁም ካንሰር ከማያመ ጡት ማለትም እንደኪንታሮት ላሉት ሕመ ሞች ለሚያጋልጡት ለ6/ እና 11/ ለተባሉት ቫይረ ሶች ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የክትባቱን አገልግሎት ስንመለከት በአብዛኛው ካንሰርን ለሚ ያመጡት ለ16 እና 17 ክትባቱ መገኘቱ ከ 75 ኀበላይ የማህጸን በር ካንሰርን ለመከ ላከል የሚያስችል ክትባት አለ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ባለንበት ደረጃ ካንሰሩን መቶ በመቶ መከላከል ባይቻልም ለሌሎች ዘጠኝ ለሚሆኑ የቫይረስ አይነቶችም ክትባት በመዘ ጋጀት ላይ በመሆኑ ጥሩ ተስፋን የሚሰጥ ነው፡፡ በእርግጥ ካንሰሩን መቶ በመቶ ለመከ ላከል ካንሰር አምጪ ለሆኑት ከ30/በላይ ለሚሆኑት ቫይረሶች ክትባት መዘጋጀት እንዳ ለበት ይታመናል፡፡
ጥ/ የማህጸን በር ካንሰር ክትባት በሀገራችን አገልግሎቱ ምን ይመስላል?
መ/ ከሶስት አመት ወዲህ የማህጸን በር ካንሰር ክትባት በአገራችን እንዲሰጥ ሁኔታዎች የፈቀዱ ሲሆን ነገር ግን ክትባቱ በመሰጠት ላይ ያለው በአንዳንድ የግል የህክምና ተቋማት ነው፡፡ እስከአሁን ድረስ ክትባቱ በኢትዮጵያ በፕሮግራም ደረጃ ሰፋ ብሎ በመንግስት መርሀ ግብር ተካትቶ ለህብረተሰብ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል አገልግሎት በመሰጠት ላይ ነው ሊባል የሚችለው ክትባቱ በመንግስት መርሀ ግብር ተካትቶ በእድሜያቸው ከ9-26 አመት ለሚሆኑ ሴቶች ሲሰጥ ነው፡፡ ይህ የእድሜ መመዘኛ ከወሲብ ድርጊት ጋር የሚያያዝበት ሁኔታ አለ፡፡ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰርን ክትባት ወሲብ መፈጸም ከመጀመራቸው በፊት ቢወስዱት የሚመረጥ ሲሆን ነገር ግን በብዛት ለካንሰሩ ያልተጋለጡ እስከሆኑ ድረስ ክትባቱን ቢወስዱ እስከ 75ኀ ድረስ ከካንሰሩ እራሳቸውን መከላከል ይችላሉ፡፡
ጥ/ ክትባቱ በግል አስመጪዎችና በግለሰብ ተጠቃሚዎች መወሰኑ ለምንድነው?
መ/ አሁን ባለበት ሁኔታ ክትባቱን እንደልብ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ለማድረግ አስቸጋሪ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል የክትባቱ ዋጋ ውድ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ክትባቱ በሶስት ጊዜ በወራት ተከፋፍሎ የሚሰጥ ሲሆን ግዢው ለአንድ ሰው እስከአምስት ሺህ ብር ይደር ሳል፡፡ አንድ ሰው ሁለት እና ሶስት ሴት ልጆች ቢኖሩት እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር ሊደርስ የሚችል ዋጋ ስለሚያስወጣ አቅምን የሚፈታተን ይሆናል፡፡ ይህንን ክትባት እንደአገልግሎት ለመስጠት የሚቻልበት መርህ በመንግስት ካልተዘረጋ ብዙሀኑ ሊጠ ቀምበት የሚችልበት መንገድ የለም፡፡ ስለዚህም በአለም የጤና ድርጅት በኩል በሚደረግ ንግግር መድሀኒቱ ወደአገር ውስጥ ሲገባ ከአምስት ዶላር በታች እንዲሆንና በተቻለ መጠን እንዲቀንስ የሚቻልበት መንገድ እየተሞከረ ነው፡፡ የማህጸን በር ካንሰር ለብዙ ሴቶች ሕይወት ጠንቅ በመሆኑ የክትባቱዋጋ እንዲቀንስ ብቻም ሳይሆን ጥረት በመደረግ ላይ ያለው በነጻ እንዲሰጥም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ክትባቱ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን መንግስትም የሚያምንበት በመሆኑ አሰራሩ በምን መንገድ ይሁን የሚለውን በቀጣይ መፍትሔ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡
ጥ/ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር እንዳይይዛቸው መከላከል የሚችሉበት መንገድ አለ?
መ/ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር እንዳይይዛቸው ለማድረግ ዋና መከላከያቸው ክትባት መውሰድ ነው፡፡ ክትባቱ ለጊዜው በመንግስት አሰራር በፕሮግራም ታቅፎ በስፋት እና በነጻ እስካልተሰጠ ድረስ ግን እራስን መከላከል ግድ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን፡-
ንጽህናን መጠበቅ፣
በአንድ መወሰን፣
እድሜ ከ25 አመት በላይ ከሆነ በየአመቱ ቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ፣
እራስን ከአባላዘር በሽታ መከላከል፣
ሲጋራ እና የመሳሰሉትን ሱስ አስያዥ እጾች አለመጠቀም ፣
በወሲባዊ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶም መጠቀም...ወዘተ የመሳሰሉት ለቫይረሱ የሚያጋልጡ በመሆናቸው በተቻለ መጠን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠቅማል፡፡
በአጠቃላይ ያለው ሁኔታ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ የካንሰር አይነቱ ጥንቃቄ ከተደረገና በጊዜው አስፈላጊው ሕክምና ቢደረግ የሚድን ሲሆን ነገር ግን ለሕክምና ወደሆስፒታል የሚመጡት ታማሚዎች ግን ጊዜ ፈጅተው ካንሰሩ ከተሰራጨ በሁዋላ ሰለሚሆን ማዳን አይቻልም፡፡ ስለዚህ እኔ የምመክረው ማንኛዋም ሴት ሌላውን የጤና ምርመራ እንደምታደርገው ሁሉ በማህጸን ካንሰርም እንደዚሁ ቅድመ ካንሰር ምርመራን በማድረግ አስቀድሞ መከላከል ይቻላል ብለዋል ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት፡፡

Read 6749 times