Saturday, 24 August 2013 10:53

የቀነኒሳ ባለ ብዙ ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(7 votes)

በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው የአትሌቲክ መንደር
አዲስ አበባ በጉም የተሸፈነችበት ዕለት ነበር- ያለፈው ማክሰኞ፡፡ ከአምስቱ የመዲናዋ መውጫ በሮች አንዱ ወደሆነው የሰሜን አቅጣጫ አመራሁ። የሱሉልታ ተራራ አናት በጉም በመሸፈኑ፣ በሶስት እና በአራት ሜትር ሰው ለመተያየት ችግር ነበር። ተራራውን እየወረድን ስንሄድ ጉሙ እየሳሳ ሄዶ “መታጠፊያ” የሚባለው አካባቢ ስንደርስ ከነአካቴው ጠፋ፡፡
ሱሉልታ ከተማ ለመድረስ 10 ኪ.ሜ ያህል ሲቀረኝ የታክሲው ረዳት መኪናውን አስቁሞ “ደርሰዋል” ብሎ አስወረደኝ፡፡ ከዚያም በቀኝም በግራም በእጁ እያመለከተኝ “የእሱ ነው” ብሎኝ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ እኔም የተወሰኑ ሜትሮች ከተጓዝኩ በኋላ፣ ከባለ አንድ ፎቅ ዘመናዊ ሆቴል ሰፊ መመገቢያ አጠገብ “ቀነኒሳ ሪዞርት” የሚል አየሁና ለጥበቃ ሰራተኛው የመጣሁበትን ጉዳይ ነገርኩት። ጥበቃው ከሜዳው ውስጥ ወደሚመጡ ሁለት ሰዎች እያመለከተ “ለእነሱ ንገር፤ ይጠሩልሃል” አለኝ። እኔም እንደተባልኩት አደረግሁና አስጎብኝዬ አቶ ቱሉ እስኪመጡ ወደ ሆቴሉ አመራሁ፡፡
ከጥቂት ቆይታ በኋላ አቶ ቱሉ መጡና የመጣሁበትን ጉዳይ ነግሬያቸው ጉብኝቴን ጀመርኩ፡፡ ከወደሰሜን በኩል የእግር ኳስ ሜዳው አርቴፊሻል ሣር ለብሷል፡፡ አረንጓዴነቱ በጣም ያምራል፡፡ አውሮፓ እንጂ በአዲስ አበባ ዙሪያ በገጠሪቱ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ መሆንዎን ይረሳሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በኳስ ሜዳው ዙሪያ የተነጠፈውን የመሮጫ ትራክ ሲመለከቱ ቀለሙ ቀይ ከመሆኑ በስተቀር ሰሞኑን 14ኛው የዓለም አትሌቲክ ውድድር የተካሄደበትን የሞስኮ ሉዝንስኪ ስታዲየም ያስታውሰናል፡፡ ከስታዲየሙ ግራና ቀኝ የርዝመት ዝላይ፣የምድር ዝላይ፣የመሰናክል መሮጫ….ተገንብቷል፡፡
የስታዲየሙ “ካታንጋ” መቀመጫ የአፈር መደብ ሳር እየተተከለበት ነው፡፡ በትይዩው ደግሞ “ክቡር ትሪቡን” ለመስራት የአፈር ቁፋሮ ተጀምሯል፡፡ ከ “ካታንጋ” በስተሰሜን ምዕራብ ብዙ ክፍሎች ያሉት የመፀዳጃና የሻወር ክፍሎች ተዘጋጅተው ፊኒሺንግ ነው የቀረው፡፡ ክረምቱ እንደወጣ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላ የመዋኛ ገንዳም ይገነባል፡፡ የሚያጠግብ እንጀራ… እንዲሉ፣ የቀነኒሳ በቀለ የአትሌቲክስ መንደር ሥራ ሲጠናቀቅ ምን ሊመስል እንደሚችልና እንዴት እንደሚያምር ከወዲሁ መገመት አያቅትም።
የክብር ትሪቡኑ ይሰራበታል ከተባለው ስፍራ ጀርባ በጣም ብዙ ርቀት ከተጓዝን በኋላ የስፖርት መንደሩን ከሌላ የሚለይ የሽቦ አጥር እናገኛለን። አጥሩን አልፈን ስንጓዝ እሳት ማንደጃ ያለው ሰፊ የጋራ ባርና ሬስቶራንት፣ ዘመናዊ ኪችንና ላውንደሪ…ያላቸው አምስት ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያ ቪላዎች እናገኛለን፡፡ ክፍሎቹ ቲቪ፣ቁም ሳጥን፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ ሻወር ቤትና መፀዳጃ….አላቸው፡፡ ከቪላው አረንጓዴ ስፍራ አለፍ ብሎ ሌላ የሽቦ አጥር ታጥሯል። ከአጥሩ ማዶ የማጠናቀቂያ ስራ የቀረው ባለ ሶስት ፎቅ ዘመናዊ የእንግዶች ማረፊያ ህንፃ ይታያል፡፡ ከ80 በላይ ክፍሎች አሉት የተባለው ይህ ህንፃ “በኮንትራክተሩ ድክመት ባይሆን ኖሮ እስካሁን ማለቅ ነበረበት” ብለዋል፤ አስጎብኚዬ አቶ ቱሉ፡፡
የታዋቂው አትሌት የቀነኒሳ የሱሉልታ ኢንቨስትመንት በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ እስካሁን ያየነው ከመንገዱ በስተቀኝ ጠርዝ ያለውን ነው፡፡ ከመንገዱ በስተግራ ጠርዝ ያለውንና ከ3ሺህ ካ.ሜ በላይ ያረፈውን ደግሞ እንቃኝ፡፡
“ቀነኒሳ ሪዞርት” ይላል፤ ባለ አንድ ፎቅ ዘመናዊ ሆቴል መግቢያ በር ላይ የተተከለው ማስታወቂያ። ወጪና ገቢ መኪኖችን በደንብ እንዲያስተላልፍ የተሰራውን ሰፊ በር አልፈው፣ አስፋልቱን ተከትለው ሲሄዱ ወደ ሆቴሉ ይደርሳሉ፡፡ ስላልተመረቀ ብዙ ሰው አላወቀም እንጂ የሪዞርቱ ግንባታ አልቆ ስራ ከጀመረ ሰነባብቷል፤ ስምንት ያህል ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ሪዞርቱ ዘመናዊ ከመሆኑም በላይ ሰፊ ሎቢ ባር፣ ሬስቶራንትና ካፌም አለው፡፡ ትኩስ ነገርም ይገኛል፡፡ የገረመኝ ነገር የምግቦቹ ዋጋ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሬስቶራንቶች ከሚያስከፍሉት ዋጋ አይበልጥም፡፡ ቁርስ እንደየዓይነቱ፣ ሰላጣና አትክልት በ30 ብር ገደማ፣ ምሳና እራት ከ43 እስከ 52 ብር ይገኛል፡፡ ትልቁ ዋጋ 65 ብር ነው፡፡
ሎቢ ባሩን አልፈው ሲዘልቁ እንግዳ መቀበያውና ከፊት ለፊት ደግሞ ሰፊ አዳራሽ ያገኛሉ፡፡ አንደኛ ፎቅ ያሉት የተለያየ መጠንና ዋጋ ያላቸው 17 መኝታ ክፍሎች ናቸው፡፡ 800 ብር የሚከፈልበት ትልቁና ሰፊው ክፍል ከአልጋና ቢፌው በተጨማሪ ሁለት ወንበርና ጠረጴዛ፣ ስልክ፣ ቲቪ፣ ቁምሳጥን፣ የገንዳ መታጠቢያና ሽንት ቤት አለው፡፡ ባለ 500 ብር ክፍሎች ደግሞ ትልቁ ክፍል ያሉት ነገሮች የተሟሉላቸው ሲሆን መታጠቢያው ገንዳ ሳይሆን የቁም ሻወር ነው፡፡
ከዋናው በር በስተቀኝ ራቅ ብሎ ከቀርከሃ የተሰራ ትልቅ ጎጆ ቤት አለ - ባህላዊ የምግብ አዳራሽ ነው። አዳራሹ መኻል ላይ ዘመናዊ መጠጥ ለሚፈልጉ ባር አለ፡፡ ጠጅና ሌሎች ባህላዊ መጠጦችም አሉ። አዳራሹ በተለያዩ ስዕሎችና ጌጣጌጦች አምሯል። ንፁህ አየር እየሳቡ መዝናናት ለሚፈልጉ ሰዎች ከአዳራሹ ውጪ ዙሪያውን ሰፊ ስፍራ አለ፡፡ ከፊትለፊት አነስ አነስ ያሉ ስድሰት ጎጆ ቤቶች አሉ። ከአዳራሹ በስተቀኝ በኩል አግድም የተሰራ ቤት አለ- ሥጋ ቤት፣ ኪችን፣ ላውንደሪ፣ ግምጃ ቤት፣ ይዟል። በጀርባው ደግሞ ሽንት ቤትና የሠራተኞች ሻወር አለ፡፡ ከዚህ ቤት ራቅ ብሎ የተለያየ ዘመናዊ የህፃናት መጫወቻ የተተከለበት ስፍራ ሲኖር ግቢው በሞላ አረንጓዴ ሳር ለብሷል፡፡
ከጓደኞቹና ከቤተሰቡ ጋር እንዴት እንደሆነ አላውቅም እንጂ ቁጥብ ነው፤ ብዙ ጊዜ ፈገግታ አያሳይም፡፡ ነገር ግን ሀሳቡን በትክክል መግለፅ ይችላል-የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና የ10 እና 5ሺህ ሜትሮች ሪከርድ ባለቤት ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፡፡
ቀነኒሳ ወደ ቢዝነስ የገባው ከአራትና ከአምስት ዓመት በፊት እንደሆነ ይናገራል፡፡ “በተወለድኩበት በቆጂ ከተማ ሬስቶራንትና የተወሰኑ መኝታ ክፍሎች ያሉት የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጥ አነስተኛ ሆቴል ሰርቻለሁ፡፡ በአሰላ ከተማም ሱቆች፣ ሬስቶራንትና ባር ያለው መጠነኛ ቤት ሰርቻለሁ፡፡ ሱሉልታ የአትሌቲክስ መንደር መስሪያ ቦታ ወስጄ እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡
ለምንድነው የአትሌቲክስ መንደሩ ግንባታ የዘገየው?
የአትሌቲክስ መንደር ግንባታ ፕሮጀክት በጣም ሰፊ ነው፤ እንዲህ በአጭር ጊዜ የሚያልቅ አይደለም። የእኛ አገር ባንኮች ድጋፍ የሚሰጡት ከተማ ውስጥ ነው እንጂ ወጣ ብለው በጋራ መስራት አልለመዱም። ይህም ፕሮጀክቱን ከባድ ያደርገዋል፡፡ ብዙ ፋይናንስ ስለሚጨርስ በራስ ብቻ በአጭር ጊዜ ለመጨረስ ይከብዳል፡፡ አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው እኔ በምፈልገው መልኩ ተሰርቶ ካለቀ ሁሉንም ስፖርት ያካተተ በአፍሪካ የመጀመርያው የአትሌቲክ መንደር ይሆናል፡፡
ብቻህን መሥራት ከከበደህ እንዴት ነው ለማጠናቀቅ ያሰብከው?
ብዙ ሚሊየን ብር ባፈስም ያንን ፕሮጀክት ብቻውን ይጨርሳል ተብሎ መታሰብ የለበትም፡፡ ይህ የስፖርት መንደር የአገር ቅርስ ነው፤ ባንክ ገብቶበት መሥራት አለበት፡፡ ማንኛውንም ፕሮጀክት በራሱ ብር ብቻ የሠራ የለም - የተወሰነ ያህል ከግለሰቡ ወይም ከድርጅቱ፣ አብዛኛው ደግሞ ከባንክ በሚገኝ ብድር (ድጋፍ) ነው፡፡ ስለዚህ ያለው ነው፤ የሌለው ነው ተብሎ መታየት የለበትም፡፡ ሚሊየነርም ቢሆን ከባንክ ጋር አብሮ ነው የሚሠራው፡፡ እኔ ብዙ ብር አውጥቻለሁ፤ አሁን ደግሞ ፕሮጀክቱን ለፍፃሜ ለማብቃት አብረውኝ የሚሰሩ ባንኮች መኖር አለባቸው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ይኼ ስፖርት ነው፤ ስፖርት ደግሞ መሰረተ ልማት ነው፡፡ ይህ የስፖርት ማዘውተሪያ ተሰራ ማለት ለአገር የሚጠቅሙና የአገራቸውን ስም በአደባባይ የሚያስጠሩ ምርጥና ብቁ ስፖርተኞች ይፈልቁበታል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡
አትሌቲክ መንደሩ ምን ምን ይዟል?
መሰረታዊ የሚባሉ የስፖርት ነገሮች በሙሉ አሉት፡፡ ባስኬትቦል፣ ዋና፣ የተለያዩ የሩጫ ዓይነቶች፣ ጎልፍ፣ የሜዳ ቴኒስ መጫወቻ፣ የልጆች መጫወቻ፣ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል…አካትቷል፡፡
እንዴት ነው በአፍሪካ ደረጃ ያወዳደርከው?
እኔ እንግዲህ በአፍሪካ ውስጥ በመንግሥት ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በግለሰብ ደረጃ በስፖርተኛ የተሰራ የለም፣አላየሁም፡፡ የዚህን ዓይነት የአትሌቲክ መንደር በአፍሪካ ቀርቶ በዓለምም በኦሎምፒክ ነው እንጂ በአንድ ስፖርተኛ የተሰራ የለም፡፡ በሌላ ኢንቨስትመንት ሊሳተፉ ይችላሉ እንጂ እንዲህ ለትውልድ በሚተላለፍ የስፖርት መንደር በዓለም ላይ ኢንቨስት ያደረገ ማንም የለም፡፡ ምናልባት በመንግሥት ደረጃ መጠነኛ የስፖርት ማዕከላት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ይህን የመሰለ ማዕከል የመገንባት ሐሳብ ከየት መጣ?
በአፍሪካ ለመወዳደር ፈልጌ ሳይሆን በዓለም ላይ በአውሮፓና በአሜሪካ ስዘዋወር ሆቴል ያለው፣ ብዙ የስፖርቶች ዓይነት ማስተናገድ የሚችል የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በማየት ነው እዚህ ውስጥ የገባሁት፡፡
በዚህ ቦታ የተለያዩ ስፖርተኞች ሊሰሩ ይችላሉ። ለስፖርተኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሰው በሳምንት መጨረሻ ስፖርት እየሰራ የሚዝናናበት ቦታ በአገራችን ብዙም አልተለመደም፡፡ ስፖርት በሁሉም የዕድሜ ክልል ላለ ሰው አስፈላጊ ስለሆነ የሚቆም አይደለም፤ ከትውልድ ትውልድ እየተቀጣጠለ የሚሄድ ነው፡፡ በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉትን ማሳተፍ በጣም ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም ነገሮች በማሰብ ነው ወደዚህ ኢንቨስትመንት የገባሁት፡፡
አሁን’ኮ በየክልሉ ብዙ ስታዲየሞች መሰራት ጀምረዋል?
አዎ! በሌላ አገር በስፖርት ላይ የሚታየው ነገር በእኛ አገር የለም፡፡ አውሮፓ ለውድድር በምሄድባቸው የተለያዩ አገራት መሮጫ ትራክ በየቀበሌው አለ ማለት ይቻላል፡፡ በውጪው ዓለም የእግር ኳስ መጫወቻና መሮጫ ሜዳ በቅርብ ርቀት ይገኛሉ፡፡ በእኛ አገር ገና አሁን ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት እንጂ ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የመሮጫ ትራክ ነበር ያለው፡፡ ይህ ደግሞ ለሁሉም በቂ አይደለም፡፡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰው ለሚኖርባት አዲስ አበባ፣ ከአራት በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ሊኖራት ይገባል። ያለበለዚያ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው መጠቀም የሚችሉት፡፡ ብዙ ሰው የሚጠቀምበት ከሆነ የስፖርት ማዘውተሪያው ስፍራ ቶሎ ሊበላሽ፣ ቶሎ ሊያረጅ ... ይችላል፡፡
አንድ ሰው በግልም ሆነ በቡድን በሱሉልታው የስፖርት ማዘውተሪያ ለመጠቀም ምን ማሟላት አለበት?
ምንም የተለየ መስፈርት የለውም፡፡ ሰው እዚያ ሄዶ በግልም ሆነ ከልጆቹና ከቤተሰቦቹ ጋር አልጋ ይዞ አርፎ ስፖርቱን ሰርቶ፣ የገጠሩን ንፁህ አየር እየሳበ ሳምንቱን ሙሉ በሥራ የተጨናነቀ አዕምሮውንና አካሉን ዘና ማድረግ ይችላል፡፡ ማንኛውን ሰው እዚያ ሄዶ ሻይ እየጠጣ፣ ንፁህ አየር እየሳበ መዝናናት ይችላል፡፡
ሪዞርቱ በአሁኑ ወቅት ስንት አልጋዎች አሉት?
በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 25 ክፍሎች ናቸው፡፡ አሁን ፊኒሽንግ ብቻ የቀረው ባለ ሶስት ፎቅ ህንፃ አለ፡፡ እሱ ተጠናቆ አገልግሎት ሲጀምር 150 ያህል አልጋዎች ይኖሩናል፡፡
ይህን የስፖርት ማዘውተሪያና ሪዞርት ለመስራት ያነሳሳህ ምንድነው?
ማንም ሰው አቅም ካለውና ማድረግ ከቻለ አንድ ነገር መስራት አለበት፡፡ እኔም አትሌቲክስ ላይ ብቻ መሳተፍ የለብኝም፡፡ ሌላ ነገር ላይ በመሳተፍ ለአገሬ የሚጠበቅብኝን ማድረግ አለብኝ፡፡ ለአገሪቱ ትልቅ ገፅታ የሚገነባና ለወገኖቼም የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነገር መስራት አለብኝ፡፡ ይኼ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በሩጫ ያገኘሁትን ገንዘብ ዝም ብሎ ማስቀመጥ ሳይሆን ኢንቨስት ማድረግና ማባዛት አለብኝ፡፡ አንድ ሰው ባንክ አስቀምጦ ቢቆጥብም ያው አንድ እንጀራ ነው የሚበላው፤ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት አያጣም፡፡ በአንድ ካፌም መኖር ይችላል፡፡ የእኔ ግን ከዚያ በላይ ነው፤ የአገር ገፅታ መገንባትና ለወገኖቼ የሥራ ዕድል መፍጠር፡፡
እስካሁን ድረስ ምን ያህል ብር ኢንቨስት አድርገሃል?
ስላልደመርኩት እስካሁን ይህን ያህል ብር ኢንቨስት አድርጌአለሁ ማለት አልችልም፡፡ በአገር ቤት (በቆጂ)፣ በአሰላ፣ በአዲስ አበባና በሱሉልታ ኢንቨስት ያደረግሁት ቢቆጠር በመቶ ሚሊዮን የሚገመት ብር ነው፡፡
ለምን ያህል ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረሃል?
ስራው ገና አላለቀም፤ ሲያልቅ ብዙ ሰራኞች ያስፈልጋሉ፡፡ እስካሁን በክልል፣ በአዲስ አበባና በሱሉልታ ያሉ 300 ይሆናሉ፡፡
ባለ 4 ኮከቡን ሰው መክሮህ ነው ወይስ ምን አይተህ ጀመርክ?
ማንንም አላማከርኩም፡፡ በኢንቨስትመንት መሳተፍ ደስ ይለኛል፡፡ አዕምሮዬ ያዘዘኝን ለማድረግ ፈልጌ ነው፡፡
ለወደፊት ያሰብካቸው ኢንቨስትመንቶች አሉ?
አዎ! በአዳማ ከተማ ሲኒማ ቤትና የተለያዩ ሱቆች ያሉት የገበያ ማዕከል ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ከኮንትራክተሩ ጋር ስላልተግባባን ስራው ቆሟል፡፡ የተፈጠረው ችግር ሲወገድ ግንባታው ይቀጥላል፡፡ ሁለት ትላልቅ ፕሮጀክቶች አልተጠናቀቁም፤ ጅምር ላይ ነው ያሉት፡፡
አንተ አትሌት ነህ፡፡ ልምምድ አለ፣ ውድድር አለ፤ ከኢንቨስትመንቱ ጋር ሲሆን አያስቸግርህም?
ማንኛውም ሥራ አልጋ በአልጋ ሆኖ የምትመራው አይደለም፡፡ ሥራ ከተባለ የራሱን ጊዜ ሰጥተኸው አስበህ ነው መስራት ያለብህ፡፡ ሁሉም ስራ ለሌላው ሰው ሰጥተህ የምትተወው አይደለም። ገንዘብ እስከወጣበት ድረስ ተቆጣጣሪ ቢኖረውም መከታተል ግድ ይላል፡፡ ሥራውን እንዲመሩ እውቀትና ልምድ፣ የተማሩና አቅም ያላቸውን ሰዎች ነው ያሰማራሁት፡፡ በእርግጥ ቀላል አይደለም። ግን ያስቸግረኛል ብዬ የምሰጋበት ነገር የለም፡፡ በየትኛውም ዘርፍ ውጣ ውረዶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይኼ ደግሞ በጥረትና በብልጠት ይታለፋል፡፡
እስካሁን በጣም ፈታኝ ነው የምትለው ችግር (ቻሌንጅ) ምንድነው?
የአዲስ አበባውን ሆቴል ስሰራ በጣም ፈታኝ የሆኑ ችግሮች አጋጥመውኛል፡፡ በግንባታው ላይ ባለመግባባት ብዙ ኮንትራክተሮች ተቀያይረውበታል፡፡ ይህ ስራ እንዳሰብኩት አለመሄዱ ትልቅ ችግር ነበር፡፡ የሆቴሉ ግንባታ አምስት ዓመት ስለፈጀ ቶሎ ስራ ለመጀመር ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል፡፡ ምክንያቱም አንድ ኢንቨስትመንት በተፈለገው ጊዜ አልቆ ስራ ካልተጀመረ ኪሳራ ነው። ብዙ ገንዘብ አንቆ ስለሚቀመጥ ወጪው ይበዛል፡፡
ከኮንትራክተሮቹ ጋር ያለው ችግር ምንድነው?
አብዛኛውን ጊዜ ከእነሱ ጋር ያለው ችግር ያሉትን ሆነው ያለመገኘት ነው፡፡ ምናልባት ከመጀመሪያውኑ አስበው የሚገቡበት ነገር ይኖራል፡፡ ያ ነገር ሳይሳካላቸው ሲቀር፣ ተስፋ ቆርጠው (ዲስከሬጅ በመሆን) ስራውን ማጓተት፡ እልህ መጋባት ይፈጠራል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ጥሩ የሚሠሩ ኮንትራክተሮች የመኖራቸውን ያህል እንጀራችን ነው ብለው ለፕሮፌሽኑ ተጨንቀው የማይሰሩ ሰዎች ይኖራሉ፡፡
በቀረበው መስፈርት መሰረት ከተዋዋለና ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ፤ ኃላፊነቱን ይተውና ሌላ አነስተኛ ችሎታ ያለው ሰው ቀጥሮ ስራውን ይሰጠዋል። ችሎታ የሌለው ሰው ስራህን ሲያበላሽብህ ዝም ብለህ አትመለከተውም-ታስቆመዋለህ፡፡ የችሎታ ማነስም አለ፡፡ “እንችላለን” ብለው ይገባሉ፤ስራው ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ “ለምን እንዲህ አደረክ?” ተብለው ሲጠየቁ፣ ስህተትና ድክመታቸውን አይቀበሉም፤ አውቀውም ወይም ሳያውቁም ሊሆን ይችላል፤ ራሳቸውን ትክክለኛ አድርገው ይከራከራሉ፡፡ “ጥፋተኛ ነኝ ካልኩ ኪሳራ ይደርስብኛል” በማለት ስህተታቸውን ይክዳሉ። ጥቂት ለፕሮፌሽኑ ያደሩ ደግሞ ስህተታቸውን አምነው ተቀብለው ያርማሉ፡፡
እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥምህ እንዴት ነው የምትፈታው? ፍርድቤት ትሄዳለህ?
እንደሁኔታው ነው፡፡ ፍ/ቤት ሄጄ የማገኘው ጥቅምና ጉዳት ምንድው? ብለህ ታስባለህ፡፡ ፍ/ቤት መቆም ካለብህ ትቆማለህ፡፡ አለመግባባት ተፈጥሮ ያንን መወጣት ካልቻለ፣ ውል ማፍረስ ስለሚቻል ጥሎ ይሄዳል፤አንተም ሌላ ሰው መቀየር ትችላለህ። “በገባው የጊዜ ገደብ ውስጥ ጨርሶ አላስረከበኝም” ብለህ ፍ/ቤት ብትሄድ ተጨማሪ ወጪ ታወጣለህ፤ ጊዜ ታባክናለሁ፤ ራስ ነህ የምትጎዳው፡፡ ስለዚህ እርቅ ወይስ ፍ/ቤት መሄድ ይሻላል? ብለን አስበን ነው የምንወስነው፡፡
የአዲስ አበባውን ሆቴልና የሱሉልታውን ሪዞርት በስምህ ነው የሰየምከው፡፡ ስምህን ብራንድ ለማድረግ ፈልገህ ነው?
አዎ! ሰው መጠቀም ያለበት ባለው ነወ፡፡ እኔም በስፖርቱ (በሩጫው) ያፈራሁት ዝና አለ፡፡ ብዙ ደጋፊዎች፤ በሰራሁት ሥራ የሚደሰቱ ብዙ ሰዎች ስላሉ ይህንን ስም ብጠቀም ብዙ ማስታወቂያ መሥራት ሳያስፈልገኝና ሳልጨናነቅ በእነዚህ ሰዎች መተዋወቅ እችላለሁ፡፡ አንድን ሥራ በስምህ ማድረግ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው እንጂ መጥፎ አይደለም፡፡ በስምህ ስታደርገው ታሪክ ነው የምታስቀምጠው። የሰው ልጅ ያልፋል፡፡ በስምህ የተከልከው ግን ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ይኖራል፡፡
ይኼ ባለ 4 ኮከብ ሆቴል ምን ምን አለው?
በሆቴሎችና ቱሪዝም መስፈርት መሰረት፣ ለእንግዶች አስፈላጊ የሆኑና መሟላት ያለባቸውን መሰረታዊ ነገሮች አሟልቶ ይዟል፡፡
ባለ 4 ኮከብ ሆቴል መዋኛ፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው አዳራሾች፣ የቤት ውስጥና ከቤት ውጭ ስፖርቶች… ሊኖሩት ይገባው ይመስለኛል፡፡ እነዚህን ነገሮች ሳያሟላ ባለ 4 ኮከብ ማለት ይቻላል?
5 ኮከብ ሲሆን ነው እንጂ 4 ኮከብ ላይ እነዚህን ነገሮች ማካተት ግዴታ አይደለም፡፡ 4 ኮከብ ሆቴል የስፖርት ማዘውተሪያ ይኑረው የሚል ሕግ የለም። መዋኛ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ደግሞ በማስፋፊያ እናካትታለን፡፡ የተባሉትን ነገሮች በሙሉ ብናሟላ ወደ 5 ኮከብ ከመሄድ የሚያግደን ነገር የለም፡፡ የሚጨምረውም ወጪ ይህን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ቦታው በቂ አይደለም። በ3ሺ ካ.ሜ ላይ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ማካተት በጣም ማጨናነቅ ነው የሚሆነው፡፡
በማስፋፊያው ምንድነው የሚጨመረው?
አሁን ያለን አነስ ያለ አዳራሽ ነው፡፡ ወደፊት ትልቅ አዳራሽ ይኖረናል፡፡ የመዋኛ ገንዳ፣ ተጨማሪ ክፍሎችና የቅርፃ ቅርፅ መሸጫ ሱቆች… ናቸው፡፡
በዓለም ደረጃ ታዋቂ የሆኑ አትሌቶች በአገራቸው ኢንቨስት ያደርጋሉ?
ኬንያዊያን ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዶቹም ጓደኞቼ ስለሆኑ በእርሻ፣ በስፖርት ካምፕ፣ በሆቴል ቱሪዝም ላይ ሲሳተፉ አያለሁ፡፡ ስለሌሎች አገር አትሌቶችን ግን ምንም መረጃ የለኝም፡፡ ይሳተፉ ይሆናል፣ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
ዓለም አቀፍ ታዋቂ አትሌት ነህ፡፡ እንዳንተ ያሉ አትሌቶች ደግሞ ስፖንሰር አላቸው፡፡ ያንተ ማን ነው?
ናይክ ነው፡፡
ለምን ያህል ጊዜ?
የ10ሺ እና የ5ሺ ሜትር የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ክብረወሰን በእጄ ነው ያለው፡፡ በ10ሺ ሜትር ከ10 ዓመት በላይ፣ በ5ሺሜ ደግሞ ከ7 ዓመት በላይ ናይክ ስፖንሰር አድርጐኛል፡፡ እነሱ የሚያተኩሩት ወቅታዊ ብቃት ላይ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከሦስት ዓመት በላይ እግሬን ታምሜ ብቃቴ ቀንሷል። ናይክ ከእኔ ጋር ይቀጥል አይቀጥል እንደሆነ ወደፊት እናያለን፡፡
ስፖንሰርሺፕ የሚያስገኘው ጥቅም አለ እንዴ?
አይ! የለም፡፡ ስም ብቻ ነው፡፡
ቀነኒሳ ምን አይነት ሰው ነው? ምን ይወዳል? ምን ይጠላል?
እንግዲህ ስለእኔ ባህርይ መናገር የሚችለው የሚያውቀኝና የሚቀርበኝ ሰው ነው፡፡ እኔ እንደዚህ ነኝ ብዬ መናገር ይከብደኛል፡፡ ጥሩ ነገሮችን እወዳለሁ፤ መጥፎ ነገሮችን እጠላለሁ፡፡ ያለኝን አካፍዬ መኖር የምፈልግ ሰው ነኝ፡፡
ከምግቦችስ?
የሰው ልጅ ለምግብነት የሚጠቀማቸውን አልጠላም፡፡ ሁሉንም አይነት ባይሆንም አብዛኛውን እጠቀማለሁ - የምጠላው ነገር የለም፡፡ የሰው ልጅ ዛሬ የሚፈልገውን ምግብ ሲያገኝ ነገ ደግሞ ሊያጣ ይችላል፡፡ የምፈልገውን ሳላገኝ ስቀር “ገንዘብ ስላለኝ ይህንን አልበላም” ማለት የለብኝም፡፡ የተገኘውን አክብሬ መቀበል አለብኝ፡፡ ተገልዬ መኖር አልችልም።
ስንት ዓመትህ ነው?
አሁን 31 ዓመቴ ነው፡፡
ስንት ልጆች አሉህ?
ሦስት ልጆች አሉኝ፡፡
ከባለቤትህ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? ሠራተኛ ናት ወይስ የቤት እመቤት?
የምናደርገውን ነገር ተመካክረንና ተነጋግረን ነው የምንሠራው፡፡ ልጆቹንም ታሳድጋለች፤ መሥራት ያለባትንም ነገር ትሰራለች፡፡ ልጆች የማሳደግ ሥራ ከባድ ነው፡፡ የቤት ውስጥና የውጭ ሥራ ቀላል ነገር አይደለም - ከባድ ነው፡፡ በሁሉም ነገር ትደግፈኛለች፤ አብራኝም ትሳተፋለች፡፡ ስለዚህ የጀርባዬ አጥንት ናት ማለት እችላለሁ፡፡

 

Read 5805 times