Saturday, 24 August 2013 10:41

ከ40 ዓመት በፊት በደብረታቦር ከተማ የተነበቡ የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ጽሁፎች...

Written by 
Rate this item
(3 votes)

       ሰሞኑን፣ ወደ ዝግጅት ክፍላችን አንድ በእድሜ ብዛት ንትብ ያለ ባለ 34 ገጽ መጽሔት መጣልን። ክፍለሀገር ከሚኖር፣ የእነ ፈቃደ አዘዘ የቀድሞ ተማሪ እጅ ከ40 ዓመት በላይ የቆየው ‹‹ቴዎድሮስ›› የተሰኘው ይኽ መጽሔት፣ ደብረታቦሩ ከተማ በሚገኘው፣‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት›› በ1964 ዓ.ም. በሰቴንስል ተባዝቶ እንደተሰራጨ ታውቋል፡፡
በወቅቱ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የማስተማር አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ስለነበረባቸው፣ የያኔዬው የ22 ዓመቱ ትንታግ ወጣትፈቃደ አዘዘና ሌሎች 6 ጓደኞቹ፣ በዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የማስተማር ‹‹ሰርቪስ›› ይወጡ ዘንድ፣ የዛሬው የደቡብ ጎንደር መስተዳድር ዞን ዋና ከተማ በሆነው ደብረታቦር፣ ከትመው ነበረ፡፡ እናም፣ መጽሔቱ፣ በዚያ የአንድ ዓመት የማስተማር ቆይታቸው ወቅት ያዘጋጁት ሲሆን፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የቀረቡ መጣጥፎች፣ ዜናዎች፣ ለፈገግታ ያህሎች፣ የአካባቢ ገለጻዎች፣ ግጥሞች፣ የካርቱ ሥዕሎች ወዘተ. ቀርበውበታል፡፡
ታዲያ በመፅሄቱ ላይ በንባብ ከቀረቡ ፅሁፎች መካከል፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስተማርና መመራመር ከጀመሩ፣ ዘንድሮ 40ኛ ዓመታቸውን የደፈኑት የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ፅሁፎችም ይገኙበታል። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” በሚል ርዕስ ያቀረቡት መጣጥፍ፣ በወቅቱ በተማሪዎች ንቅናቄ ሲስተጋባ የነበረው የብሄር/የጎሳ ፖለቲካ የደረሰበት ጫፍና የወደፊት ጦስ አቀንቅኗል፡፡ “ታዲያኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ቀርቶ ‹አጅባሬ ነኝ!›፣ ‹ካሳንችሴ ነኝ!› ወዘተ. ማለት ሊመጣ ነው፡፡ በአባትና ልጅ መሀከል ልዩነት አይፈጠር ብላችሁ ነው? ወይስ ተፈጥሯል? የሚለውን ገለፃ ከዛሬ ነባረ ሁኔታ ጋር በንፅፅር ስናየው የትንቢት ቃልም ይመስላል፡፡
“መቼ ሆን?” በሚል ጥያቄያዊ ርዕስ ለዘብ ብለው የቀረቡ የአስተውሎት ምልከታዎች ፣ስለ ደብረታቦር ከተማና ህዝብ ማህበረ ባህላዊና ኢኮኖሚያዎ ሁኔታ ይጠቁማሉ፡፡ የምልከታዎቹ ዋጋ ግን፣የትናንሽ የገጠር ከተሞችን ጭምር ማህበረ ባህላዊ የኑሮ መልኮች፣የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ክስተቶችን ወዘተ በወቅቱ የመዘገብን አስፈላጊነት ከማመልከታቸውና ከማንቃታቸው ጭምር ሊመዘዝ ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ የደብረታቦር ከተማና ህዝብ የለውጥ ሁኔታን ቃኝቶ ምልከታውን ለሚያከፈለን ፀሐፊም መልካም አጋጣሚ ነው እንላለን፡፡ ለማንኛውም ከመፅሄቱ እንደወረደ የቀረቡትን ፁሁፎች እንደሚከተለው አቅርበናል፤

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር
በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ አንድ ሰው ብቻውን ኢምንት ነው፡፡ ሀይል የለውም፡፡ ስርዓት አይኖረውም፡፡ አላማውም ግላዊ ነው፡፡ ብቻውን ከመቶ ኪሎ ጤፍ እንደ አንዲቱ የጤፍ ቅንጣት ነው። ጤፍ ብቻዋን አታጠግብም፡፡ ሰውም ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ከሰው ከተባበረ ግን እራሱን ሊያሻሽልና ሊጠብቅ፣ ባላንጋራውን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ሥራውም እንደ አንዷ ጤፍ ሳይሆን እንደምንበላው እንጀራ አንጀት አርስ ይሆናል፡፡
ታድያ ምነው የሰው ልጆች ልብ ተራራቀ? ምነው ተከፋፈለ? ምነው ሕብረትን ጠላ? ለምንስ በጠቅላላው በሰው ልጅ ወንድማማችነት እንደመመስረት የጎሳ ዝምድና ይመሰረታል? ለምን ወገን ይለያል? ሀገር የጋራ ነው ተብሏል፡፡ ታዲያኮ ዝምድናውም የጋራ ነው ማለት ነው፡፡ ፍቅሩ የሁሉ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የሚታየው ድርጊት ህሊናን የማያስደስትና አንጎልን የሚያናውጥ ነው፡፡
ጠለቅ ብለን ስንመለከት ብዙ ጅል ነገር እናገኛለን፡፡ አማራና ትግሬ ወገን መርጦ፣ ና ጉራጌ ተከፋፍሎ፣ ጋምቤላና ኩናማው ተለያይቶ ደም እንዳየች ውሻ በተገናኘ ቁጥር (‹‹ሲጣላ››) ሥራው እንዴት ይሠራ? እንዴት ለትምህርት እናስብ? እንዴት ለአንዲቷ ለመከረኛዪቱ እናት እናስብላት? ልባችን ለየብቻ ሆነ፡፡ ሥራችን ለየብቻ ሆነ፡፡ በመሀከል ግን ተጎዳን፡፡ እሷንም እንደማቀቀች ጎባጣ አሮጊት፣ ቀንታ (ቀና ብላ) ዓለሟን እንዳታይ ዓይኗን አጠፋነው፡፡
የሚገርመው ደግሞ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ልዩነቱ እየጠበበ ነው የሚሄደው፡፡ አማራው እንደገና ጋይንት፣ ቡልጋ፣ እስቴ፣ ደብረማርቆስ ወዘተ. እያለ ወገን ይለያል፡፡ ጋላውም አሩሲ፣ ሰላሌ፣ በቾና ወለጋ ወዘተ. እያለ ይከፋፈላል፡፡ ትገሬውም እንደዛው፡፡ ሌላውም እንደዛው፡፡ ካፍንጫችን እርቀን ስናስብ ደግሞ ቀስ እያለ በትውልድ መንደር የሚደረግ ልዩነት ሊመጣ ሞቆብቆቡን እንረዳለን፡፡ የአጅባርና የአስፋው ግራር፣ የአራት ኪሎና የስድስት ኪሎ ወዘተ. ልጆችስ እየተፈላለጉ ይጣሉ የለ? ታዲያኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ቀርቶ ‹‹አጅባሬ ነኝ!››፣ ‹‹ካሳንችሴ ነኝ!›› ወዘተ. ማለት ሊመጣ ነው፡፡ በአባትና ልጅ መሀከል ልዩነት አይፈጠር ብላችሁ ነው? ወይስ ተፈጥሯል?
ይህ ሁሉ የሚመጣው የስልጣኔን ጮራ፣ የትምህርትን ውጋገን ካለማገኘትና ከዚህም በላይ እውነተኛ የሀገር ፍቅር ከማጣት ነው፡፡ ስለዚህ ያገሬ ሰው ስማኝ፣ ተባበር፡፡ አትበታተን፡፡ ጠላትህን አታስደስት፡፡ ከተባበርክ እንኳን ረሃብን፣ ድንቁርናን እና ሌሎች ልዩ ልዩ በሽታዎችን ማጥፋት ትችላለህ፡፡
ተራራውን ብትገፋው ይገፋልሃል፡፡ ወደመሬት ማውረድ ወደሰማይ ማውጣት፣ ማስጠምም ማዳንም ያንተው ይሆናሉ፡፡ አትፍራ ሁሉም የሚፈልግ ህብረት ነው፡፡ አንድነትህን የሚጠላ የለም፡፡ ልብህን ይክፈተው፡፡ ብርታቱን ይስጥህ፡፡
ፈቃደ አዘዘ
የሰርቪስ መምህር
(በግል ምክንያት ሆሄ አልተጠበቀም)
መቼ ይሆን?
የደብረ ታቦር ሕዝብ መኪና በበጋ ሲመጣ በእልልታ መቀበሉ የሚቀረው?
ደብረ ታቦር መብራትና መንገድ ውሃና በቂ የሕክምና ጣቢያ የሚኖራት?
አንድ ብልህ ነጋዴ በላመነት የሚሰሩ ቦርሳዎችና ሻንጣዎች ኢንዱስትሪ የሚያያቋቁመው?
የደብረ ታቦር ጠላና ጠጅ የሚበላሸው?
የሚሲዎን ሀኪም ቤት አዋቂ ዶክቶሮች አስመጥቶ ሀብታም ደኃ ሳይል በትክክል የሚያክመው?
የደብረ ታቦር የ‹‹ቴዎድሮስ›› ቡድን (የእግር ኳስ) የቤጌምድር አሸናፊ (ሻምፒዎን) ሆኖ አዲስ አበባ የሚመጣው?
ፍርድ ቤት የሚመላለሰው ተሟጋች ቁጥር የሚቀንሰው?
እማማ የኔ ገላ የሚወፍሩት?!!!!!!!!
ተማሪዎችና መምህራን በጓድ ተከፋፍለው በትርፍ ጊዜያቸው ሕዝቡን በየቤቱ ሄደው የሚያስተምሩት?
የበኣል ቀናት ተቀንሰው የሥራ ቀናት የሚጨመሩት?
‹‹ፋርጣ ብር ቢያጣ ነገር አያጣ›› የሚባለው አነጋገር ዋጋ የሚያጣ?
በየመንገዱ፣ በየሜዳው፣ በየአጥር ጥጉና በየዱሩ መጸዳዳት የሚቀረው?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጭነት መጫኛ አውሮፕላን ሰው ማመላለሱን የሚተወው?
የደብረ ታቦር ተማሪዎች ለኮርስ መስገብገባቸውን ትተው በትምህርታቸው ለመግፋት የሚያስቡት?
አዝማሪዎች በቀን በቀን ብር አምጡ ማለት የሚተዉት?
የሰርቪስ መምህር - ፈቃደ አዘዘ
1964፣ ደብረ ታቦር

 

Read 4006 times