Print this page
Saturday, 24 August 2013 10:37

ብስጭት የሌለበት ቦታ ናፈቀን!

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(8 votes)

         ገና ከእንቅልፋችን ስንነቃ “ሰላም አውለኝ” ብለን በየእምነታችን መጸለይ የተለመደ ነው፡፡ ግን ጸሎታችን ከፈጣሪ ዘንድ አለመድረሱ ወይም ደርሶ ተቀባይነት በማጣቱ፤ ብቻ በሆነ ምክንያት ልመናችን አይሰምርም፡፡ “ሰላም አውለኝ” ብለን ወጥተን በንዝንዝና በንትርክ ቀኑ ያልፋል፡፡
ብስጭቱ የሚጀምረው ልክ ከቤታችን እንደወጣን ነው፡፡ ታክሲ ለመጠበቅ ረጅም ሰልፍ ውስጥ መቀላቀል አለብን፡፡ ሰልፍ መያዙ ከኪስ መንታፊዎች የሚታደግና የስልጣኔ ምልክት ቢሆንም ጭቃና ዝናብ በበዙበት ቦታ ብዙ መቆም ያበሳጫል። ከእልህ አስጨራሽ ሰልፍ በኋላ የተጠበቀው ታክሲ መጥቶ ገብተን ወንበር ስንይዝ ደግሞ ሌላ የሚያበሳጭ ጉዳይ ይጠብቀናል፡፡

ታክሲው ያረጀ/አብዛኞቹ ታክሲዎች ያረጁ ናቸው/ይሆንና ጣራው ሊያፈስ ይችላል፡፡ ታክሲ ውስጥ ደግሞ ጥላ መዘርጋት አይቻልም፤ እናም ብስጭቱ ይቀጥላል፡፡ ወይም በወላለቁ የታክሲው ወንበር ብረቶች ልብሳችን ይቦደስና ሌላ ብስጭት ውስጥ እንገባለን፡፡
ለነገሩ ታክሲው መገኘቱም እንደ ምረቃ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚያ ሁሉ ሰልፍና ጣጣ በኋላ ሥራ ቦታ ሲደረስ ሌላ ብስጭት ይጠብቃልና ነው፡፡ ትንሽ ሰዓት ካለፈ መንግሥት በይፋ ሁለት ሁለት መኪኖችን ለግላቸው የመደበላቸው አለቆች በትር የዋዛ አይሆንም፤ አንድም ደሞዝን ይቆርጣሉ፤ ወይም “ተነሳሽነት ጐድሎታል፤ ፀረ ልማትና ፀረ ትራንስፎርሜሽን ነው” ብለው ከሥራ ሊያፈናቅሉ ይችላሉ፡፡ እነሱና ቤተሰቦቻቸው ግን ከህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ በውድ ዋጋ በተገዙ ዘመናዊ አውቶሞቢሎች ይንፈላሰሳሉ፡፡
ለምንዝሩ ህዝብ ግን “ተሟሙቶ” በጊዜ ከሥራ ቦታ መድረስ ግድ ይሆናል፡፡ በታክሲ ወረፋ፣ በዝናብና በጭቃ መከራውን አይቶ ሥራ ሲገባም ምቹ የሥራ ሁኔታ አይጠብቀውም፡፡ አለቆች ለራሳቸው ምቾት እንጂ ለሥራውና ሠራተኛው እምብዛም ትኩረት ስለሌላቸው የሚጐዳው ያው የፈረደበት ምንዝሩ ይሆናል፡፡ “ልሥራ” ብሎ ሲነሳ ወይ ኮምፒውተር የለም፤ ወይም ወረቀትና እስክብሪቶ አይኖርም፡፡ እንዲሰጠው ሲጠይቅም ጐታታ መልስ እየተሰጠው ጊዜውን በከንቱ ያባክናል፡፡ ግን ደግሞ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ሥራውን አጠናቅቆ እንዲያቀርብ ግዴታ ይጣልበታል፤ በዚህም ሲበሳጭ ይውላል፡፡
ግማሹን ቀን በዚህ ዓይነት ፍሬ አልባ ሁኔታ ያሳልፍና ምሳውን ሊቀምስ በተቋማት ክበቦች አሰሳውን ይቀጥላል፡፡ እዚያም ሌላ ብስጭት ይጠብቀዋል፡፡ ከእሱ የባሱ ምስኪን አስተናጋጆች “የመ/ቤቱ ሠራተኛ ለመሆንህ ቅድሚያ መታወቂያህን አሳይ” ሊሉት ይችላሉ፡፡ ርቦትና በሁኔታዎች አለመሟላት ሲበሳጭ ውሎ ምግብ ፍለጋ ለመጣ ሰው ሌላ ንዝንዝ መፍጠር ስሜትን በእጅጉ ይጐዳል፡፡
ውጣ ውረዱን አልፎ ምግብ ቢቀርብለትም እዚህ ግባ የማይባል መናኛ ይሆንበትና እንደነገሩ ቀማምሶ ዋጋ ሲጠይቅ በሚነገረው የገንዘብ መጠን ይደነግጣል፤ መደንገጥ ብቻ ሳይሆን በአያሌው ይበሳጫል፡፡ የሚያበሳጨው የዋጋው መናር ብቻ ሳይሆን የአቅርቦቱ አለመመጣጠን ነው፡፡ እንጀራው ነፋስ ሽው ቢል ይዞት ሊሄድ የሚችል፤ ወጡም ከእህል የተሰራ የማይመስል ዝባዝንኬ ሲሆንበት ለገንዘቡ ብቻ ሳይሆን ለጤናውም ጭምር በመስጋት ይበሳጫል፡፡
ዋጋው የተወደደበትን ምክንያት ሲያጤን ከጥሬ ዕቃ መወደድ ጋር ተዳምሮ በተጨማሪ ዕሴት ታክስ ሰበብ መሆኑን ይገነዘብና እንደገና ይበሳጫል፤ ከደሞዙ ላይ ለሥራ ግብር 35 በመቶ፣ ከሚመገበውና ከሚጠጣው ሻይ ላይ 15 በመቶ፤ በአጠቃላይ የደሞዙ ሃምሳ በመቶ ለመንግሥት ገቢ እንደሚደረግ ሲገባው ብስጭቱ ይጨምራል፡፡ በህገወጥ መንገድ የሚነግዱና ህጋዊ ሆነውም ለመንግሥት የሚያስገቡትን ገቢ (ግብር) ከራሱ ጋር ሲያነፃፅረው እንደገና ሊበሳጭ ይችላል፤ ህገወጥነትንም ያልማል፡፡
ከ “ምሳ” መልስ ወደ ሥራው ሲመለስም ያው የተለመደው ምቹ ያልሆነ የሥራ ሁኔታ ይጠብቀዋል፡፡ እንደምንም ተፍጨርጭሮ የዕለቱን ተግባር በመከወን ለአለቃው ሲያቀርብም “ጥራቱን አልጠበቀም” ተብሎ ይወረወርለታል፤ ምክንያቱን ግን አይጠየቅም፡፡ የሥልጠና ዕድል ሲገኝም “አቅም የለውም” ለተባለው ሳይሆን ከአለቃ ጋር ለሚሞዳሞዱ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ በአፈጻጸም ድክመት ግን ቀድሞ ይወቀሳል፤ በዚህም ይበሳጫል።
የዕለቱ የሥራ ሰዓት በዚህ መልኩ ይገባደድና ወደ ቤቱ ለመሄድ የተለመደውን የታክሲ ወረፋ ይይዛል፤ በዚህ ጊዜ ከጥዋቱ የተለየ መስተንግዶ ይጠብቀዋል፡፡ ለሁለት ሰዎች በተዘጋጀው ወንበር ላይ ሶስትና አራት ሰዎች እንዲቀመጡ ግድ ይባላሉ፡፡ በተለይ እንደ አጋጣሚ ወፋፍራም ሰዎች ጐን ለጐን ከተቀመጡ ያለው ጣጣ በቀላሉ የሚገለጽ አይሆንም፡፡ ከቦታው ጥበት በላይ ከጐኑ የሚቀመጡት ሰዎች ወይ ድብን አርገው የጠጡ፣ አለዚያም ንጽህናቸው የተጓደለ ይሆንና እንደ ኦሪታዊው ኢዮብ በመፈጠሩ ሊያዝን ይችላል፡፡
ከዚህ ሌላ ባለ ታክሲው ከመጠን በላይ ትርፍ ሰው በመጫኑ ከትራፊክ ፖሊስ ለመሰወር ሲል በአልባሌ መንገድ መጓዝ ይጀምራል፤ “ለምን በተገቢው መንገድ አትጓዝም” ብሎ የሚጠይቅም የለም፡፡ የሚጠይቁ አንዳንድ ሰዎች ቢኖሩም ወያላው ክብራቸውን ከፍና ዝቅ አርጐ ያዋርዳቸዋል፡፡
የከተማው የትራንስፖርት መ/ቤት በወሰነው መንገድ ሳይሆን የታክሲ ወያላና ሹፌር በመረጡት “አቋራጭ” መንገድ መጓዝ ሌላው የብስጭት መነሻ ነው፡፡ ታክሲ አሽከርካሪዎች አቋራጩን መንገድ የሚመርጡት ትርፍ ሰው በመጫን በአቋራጭ ለመክበር አስበው ነው፡፡ በመደበኛው መንገድ ቢጓዙ የትራፊክ ፖሊሶች ሊይዟቸው ይችላሉ። ስለዚህ ትራንስፖርት መ/ቤቱ በወሰነው ሳይሆን ለእነሱ ህገወጥ አሠራር በሚያመች አቋራጭ መንገድ ሰውን ያለፍላጐቱ እየወሰዱ ህገወጥ ክፍያ ይጠይቁታል፡፡
በዚህ ዓይነቱ ውስብስብ ውሎ ቀኑን የገፋ ሰው በጊዜ ከደሳሳ ጐጆው ገብቶ ማረፍ ቢፈልግም ከቤቱም ብስጭት ቀድሞ ይጠብቀዋል፡፡ ገና ከቤቱ በር ሲደርስ መብራቱ ሁሉ ድርግምግም ብሎ ወንበዴ የወረረው ሰፈር መስሎ ይጠብቀዋል፤ የረባ ምሳ ባለመብላቱ ሲበሳጭ ውሎ ከቤቱ ሲደርስም ያገኘውን አብስሎ እንዳይቀምስ ሁኔታዎች ይዘጋጉበታል፡፡
በመጣበት እግሩ ተመልሶ በመሄድ እንጀራ ለመግዛት በየሱቁ ይንከራተትና የሚያገኘው እንጀራም ያው ነፋስ ሊወስደው የሚችል ሆኖበት ይበሳጫል፡፡ የሚያበሳጨው የእንጀራው መሳሳት ብቻ ሳይሆን ዋጋውም ጭምር ነው፡፡ ድሮ አንድ ክትፎ ይበላበት በነበረው ዋጋ አንድ ስሙ ብቻ እንጀራ የሆነ ነገር ሲገዛ በእርግጥም ቢናደድ የሚያስፈርድ አይሆንም፡፡
ሰውየው ላጤ ከሆነ ይህም ላያስደንቅ ይችላል። ትዳርና ልጆች ካሉት ግን ጣጣውና ኃላፊነቱ እጅግ ከባድ ይሆናል፡፡ እንጀራ ብቻ ሳይሆን ሻማ መግዛትም ግድ ነው፤ የሻማው ዋጋም ድሮ አንድ ወደል ወሰራ ዶሮ ይገዛበት የነበረው መሆኑን ሲያውቅ ብስጭቱ ይጨምራል፡፡
ይህን ሁሉ ከውኖ እንደገና ወደቤቱ ሲመለስም ሌላ ጣጣ አይኑን አፍጥጦ ይጠብቀዋል፡፡ ልክ እንደመብራቱ ውሃውም “የውሃ ሽታ” ይሆንበታል። በሐምሌና ነሐሴ ውሃ ማጣት ማለት አስገራሚም አሳዛኝም ጉዳይ ነው፡፡
መብራቱ “ ወደ ሱዳንና ጅቡቲ ተልኮ ነው” ይባላል፤ ግን ውሃው ደግሞ ወዴት ተልኮ ይሆን ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡
“የታህሳስን ራብ የሐምሌን ውሃ ጥም እናት አታውቀውም” የሚባለውን ብሂል መገንዘብ የሚያሻው እንዲህ ዓይነት ግራ አጋቢ ገጠመኞች ሲኖሩ ይመስለኛል፡፡ መብራት ከጠፋ የነዳጅና የማገዶ አቅርቦት ሊኖር ይገባል፤ እሱም ከዘመኑ ኑሮ ጋር ሊሄድ አይችልም፡፡ ብዙ ቤቶች ወደ ፎቅነት እየተቀየሩ ናቸው፡፡ ፎቅ ላይ ደግሞ እሳት ማንደድም ሆነ ከሰል ማቀጣጠል አይመችም፤ ተገቢም አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ከሚያስደስቱ ጉዳዮች ይልቅ የሚያበሳጩት የሚያይሉት፡፡
እናም ሀገራችን፤ በተለይም ከተማችን በብስጭት ውለን፣ በብስጭት ተጉዘን፣ በብስጭት የምናድርባት፤ በአጠቃላይም የብስጭት ፋብሪካዎች የተገነቡባትና ብስጭት ይመረትባት ይመስል የብስጭት ጐተራዋ አድርጋናለች፡፡ ደስታችን ከውስጣችን ሙጥጥ ብሎ ወጥቶ የገባበት ጐሬ ጠፍቶናል፡፡
ይህ ሁሉ ጣጣ መድረሻ ሲያሳጣን ለችግሮች ሁሉ፣ በተለይ “በውሃና በመብራት እንዲሁም በቴሌ አገልግሎት ድክመት ላይ ለውጥ እናመጣለን” እያሉ በምርጫ ሰሞን ሲያሰለቹን የነበሩት የፌዴራልና የከተማዋ ባለሥልጣናት የት ገብተው ይሆን? ወይስ ቃልአባይ ሆኑ?

Read 5755 times