Saturday, 24 August 2013 10:35

የአሲንባና የአይጋን ታሪካዊ ተራሮች ያቀፈችው አሊቲና

Written by  በዳዊት ንጉሡ ረታ (dawitnegussu@yahoo.com)
Rate this item
(6 votes)

                  አሁን አለን በመኪናችን ውስጥ ሆኖ መንገዱን እየመራን የሚገኘው ጓደኛችን አክሊሉ ጉላይ፡፡ አሁን ዛላንበሳ ከተማ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ ወደ ዋነኛው የጉዞአችን መዳረሻ አሊቴና ለመድረስ ሁለት አማራጭ መንገዶች አሉን፡፡ አንደኛውና የተለመደው መንገድ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የኤርትራን ግዛት አቋርጠን ተመልሰን የምንወጣበት መንገድ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወደ ኤርትራ ሳንገባ ወደፊት በቀጥታ የምንጓዝበት መንገድ ነው፡፡ ይኸኛው የቀጥታ መንገድ በቅርብ ጊዜ ከመሰራቱ በፊት ግን ሁልጊዜ ወደ አሊቲና ሲኬድ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በኤርትራ ክልል ውስጥ ማለፉ የግድ ነበረ ሲልም አከለልን፡፡ “ታዲያ በየትኛው መንገድ ብንሄድ ይሻላል?” ሲልም ምርጫ አቀረበልን፡፡ ለጉዞ በተከራየነው መኪና ውስጥ የነበርነው 8 ተጓዦች እርስ በርሳችን ተያየን፡፡ መቼም በኤርትራ ግዛት ውስጥ አልፈን ጉዞ አድርገናል ብንል ነው የተሻለ የሰው ጆሮ ለማግኘት የሚያስችለን፡፡

ሆኖም ግን ደጋግመን በምንሰማው የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ሳቢያ፣ ከሆነ ቦታ በተወነጨፈ ከባድ መሳሪያ ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳንተርፍ ብናልቅስ፣ የሚል ስጋት አጠቃንና ጎመን በጤና ብለን፣ ከስጋት ነፃ በሆነው ቀጠና ጉዞ ወደፊት፡፡
ምንም እንኳን ከአዲስ አበባ የተነሳንበት የጉዞአችን ዓላማ (ሐምሌ 7/2005 ዓ.ም) የወዳጃችንን የአክሊሉ ጉላይን የሰርግ ስነ-ስርዓት ለማጀብና በሚዜነት ለማገልገል ቢሆንም መዳረሻችን ግን የአዲ ኢሮብ ማህበረሰብ የሚኖርባት አሊቲና ከተማ ነች፡፡ ይህቺ ከተማ የኢህአፓ የትጥቅ ትግል ሲካሄድበት የነበረው የአሲንባ ተራራና የዘመናችን የኢትዮ-ኤርትራ ከባድ ውጊያ የተደረገበት የአይጋ ተራራ መገኛ ናት፡፡ በዚህች ከተማ ከኢህአፓ መስራቾች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ተወልዷል፡፡ በአሊቲና ቆይታችን አንዱ ፕሮግራማችን የሚሆነው የዚህኑ የቀድሞ ታጋይ አባት አቶ ደበሳይን ማግኘትና መተዋወቅ ነው፡፡ ከዚያም ወደ አሲንባና አይጋ ተራሮች ወጥቶ ስለሁለቱም ዘመናት ትዝታዎች የምናውቀውን ያህል ማውጋት! ከነዋሪዎችም ታሪክ መቅዳት! …እጅግ አጓጊ ጉዞ ነው፡፡
የአዲ ኢሮብ ማህበረሰብ ተወላጅ የሆነውንና አሁን ግን በዘላቂነት አዲስ አበባ የሚኖረውን ሙሽራችንን ይዘን እዚያው ተወልዳ ያደገቺውን ሙሽሪትን ከሰርግ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ልናመጣ እተጓዝን ነው፡፡

ጉዟችንን በይበልጥ የሰመረ ለማድረግ በአንዳንድ ታሪካዊ ስፍራዎች ለምን ጉብኝት እያደረግን አንሄድም የሚል የተቀደሰ ሃሳብ አመጣንና ባህርዳርን፤ ጎንደርን፤ አክሱምን፤ አድዋን፤ሽሬ እምደስላሴንና አዲግራትን ተራ በተራ እየጎበኘን፣ በቂ ጊዜ ወስደንም ታሪካቸውን እያጠናንና እየተዝናናን፣ አሁን ዛላንበሳ ከተማ ደርሰናል፡፡ እዚህ ጋ ነው እንግዲህ ለአፍታ ወደ ኤርትራ ገባ ብላ በፍጥነት የምትወጣዋ መንገድ ያለችው፡፡
ጉዞአችንን ያሳመረው የሙሽራው የአክሊሉ ጉላይ ወዳጆች የሆንን 8ቱ አጃቢዎቹ በተለያየ ሙያ ላይ የተሰማራን መሆናችን ነበር፡፡ ይህም እርስ-በርሳችን ልምድ እንድንለዋወጥና መንገዳችን አሰልቺ እንዳይሆንብን ማዋዣ ለመፍጠር አግዞናል፡፡ ከዛላአንበሳ ቀጥሎ ወደ አሊቲና ለመድረስ ብዙም ኪሎ ሜትሮች አልቀሩንም፡፡ የበለጠ ግን የሚያስደንቀው አሊቲና ከደረስን በኋላ የ3 ሰዓት ጉዞ ብናደርግ በቀጥታ ወደ ኤርትራ እንደምንገባ መስማታችን ነው፡፡ መቼም የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ስሜት የማይሰጠው አገር ወዳድ የለምና እኛም የእነዚህን አገሮች ጦርነት በትዝታ እያስታወስን፤ ስለወደፊት ዕጣ ፈንታቸውም የመሰለንን እየገመትን ሃዘንና ተስፋ እየተፈራረቁብን፣ ወደ ጉዞአችን ማሳረጊያ አሊቴና ገሰገስን፡፡ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲህ አንድ መሬት አንድ አፈር ተጋርተው እንደኖሩት ሁሉ ወደፊት ተለያይተው እንደማይቀሩ ተነበይን፡፡

ሌሎቻችን ደግሞ ኢትዮጵያና ኤርትራ ቢታረቁ በፍጥነት ኤርትራ ሄደን መጎብኘት እንደምንፈልግ ምኞታችንን ገለፅን፡፡ የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የኤርትራ ጉዳይና የዶ/ር ያዕቆብ አሰብ የማናት የሚሉት መፅሃፍትም በተረዳነው መጠን ለትንታኔ ቀረቡ፡፡ ደስ የሚል ጉዞ ነው፡፡ የባህር ዳር፤ የጎንደርና የአክሱም ጉብኝታችን ለረጅሙ ጉዞአችን አለመሰልቸት ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ስላደረጉልን በጉዞአችን ላይ መሰልቸት የሚባል ነገር ቦታ አልነበረውም፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ይበልጡኑ ያስተዋወቀኝን ዛላንበሳን በመኪና ላቋርጣት ስላልፈለግሁኝ ከመኪናችን ወርጄ በግምት ለ10 ደቂቃ በአስፋልቱ ላይ በሶምሶማ በመሮጥ፣ ባንድ ወቅት እልም ያለ ጦርነት የነበረባት ይህች ዛላንበሳ ከተማ ዛሬ የሰላም አየር እየተነፈሰች የመሆኑዋን ደስታ ተጋራሁ፡፡ መኪናችንም ቀስ እያለ በመከተል አጀበኝ፡፡ እንዲህ እየተዝናናን ወደ ጉዞአችን መዳረሻ አሊቲና ከተማ በሰላምና በጤና ገባን፡፡
እዚህ ጋር የእኔን ጽሁፍ ቆም ለማድረግ እገደድና በቅርቡ ካነበብኩት የአሲንባ ፍቅር ከሚል በደራሲ ካሕሳይ አብር ብስራት ከተፃፈ መፅሃፍ ላይ የአዲ ኢሮብን ማህበረሰብና የአሊቴና ከተማን ጥሩ አድርጎ የሚያስተዋውቀውን ጥቂት አንቀፅ በአስረጂነት በመጥቀስ፣ እናንተ ውድ አንባቢዎቼ በታሪክ አጋጣሚ ስለተገኘሁባት ከተማ ያላችሁን ግንዛቤ በመጠኑ ከፍ ለማድረግ አሰብኩ፡፡
የአዲ ኢሮብ ህዝብ የመቻቻል፤ የእንግዳ ተቀባይነት፤ የህዝብና የታጋይ አንድነት ፍቱን ዓርአያ ነው፡፡ አዲ ኢሮብ በትግራይ ክልል ሰሜን ምስራቅ በአጋሜ አውራጃ ከአዲግራት ከተማ በስተምስራቅ የሚገኝ አብዛኛውን ተራራማ የሆነ ወረዳ ነው፡፡ የአካባቢው ሰዎች እንደሚሉት፣ ኢሮብ የሚለው ቃል የመጣው ኢሮባ ከሚለው ሲሆን ይህም በሳሆ ቋንቋ ወደ ቤት ግቡ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የማህበረሰቡ ስያሜ ምንጭ ኢሮብ ህዝብ እንግዳ ተቀባይ፤ ኑ ግቡ፤ ብሉ፤ ጠጡ የሚል ደግና የዋህ ህብረተሰብ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከአዲ ኢሮብ ተራራዎች ትልቁ ከፍተኛ ቦታ የአሲንባ ተራራ ጫፍ ነው፡፡

አሲንባ ማለት ቀይ አምባ ማለት ሲሆን የዚህ ተራራ ከፍታ 3250 ሜትር ነው፡፡
የኢሮብ ህዝብ ውጊያ የማይፈራ፤ ያገኘውን ተካፍሎ የሚበላ፤ ያመነውን በፍፁም አሳልፎ የማይሰጥ፤ እስከተፈለገው ጊዜ ደብቆና ጠብቆ የሚያቆይ፤ ህዝብ ነው፡፤ የኢሮብ ህዝብ ካመነ አመነ ነው፡፡ የኢሮብ ወረዳ ባህላዊ ከተማ በሆነችው አሊቲና ውስጥ የሚገኘው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተመሰረተው በ1840 ዓ.ም ሲሆን በቤተክርስቲያኑ ስር የተመሰረተ ዘመናዊ ት/ቤትም አለ፡፡ ይህ ት/ቤት ከተመሰረተ ጀምሮ ነፃ የትምህርት ዕድል እየሰጣቸው ወደ ሮም የሄዱ በርካታ የአካባቢው ተማሪዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ተማሪዎች መካከል ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ሄደው በልዩ-ልዩ የሞያ መስኮች ትምህርታቸውን ለመከታተል የቻሉ አሉ፡፡ ከቀደምት የኢትዮጵያ ተማሪዎች መካከል በዚህ የካቶሊክ ሚሽን ት/ቤት ተምረው ከፍተኛ የትምህርት ዕድል ካገኙት አንዱ የኢህአፓ መስራችና የማዕከላዊ ኮሚቴና የፖሊት ቢሮ አባል የነበረው ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ይጠቀሳል፡፡ (የአሲንባ ፍቅር ገፅ 53-56 ከተጠቀሱት ውስጥ የተቀነጨበ)
አሊቲና የደረስነው ከሰርጉ ቀን አንድ ሳምንት ቀደም ብለን ስለነበረ ከከተማው ሰው ጋር የመገናኘቱ፤ ወደ አይጋ ተራራ የመውጣቱንና ወደ አሲንባ ተራራ ቀርበን ፎቶ የመነሳቱን ዕድል አግኝተናል፡፡
በዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ አባት መኖሪ ቤት
የአሲንባ ፍቅር መፅሃፍ ደራሲ ካህሳይ የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን ታሪክ ስሙን ብቻ ከመጥቀስ ውጪ በመፅሃፉ ላይ ቦታ ሰጥቶ አልገለፀውም፡፡ ዶ/ሩ እንዳለመታደል ሆኖም በአሊቴና ነዋሪዎች ዘንድ ታሪኩ በሚፈለገው መልኩ አይታወቅም፡፡ በተለይ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች ስለ ተስፋዬ የሚያውቁት ነገር ከታጋይነቱ ውጪ እምብዛም ሆኖ በማግኘታችን በወጣቶቹ መሪነት ወደ አቶ ደበሳይ ወላጅ አባቱ ቤት አመራን፡፡ እቤት ስንደርስ አንድ ወጣት ልጅ በሳሎን ውስጥ ተቀምጦ የአረብ ዲሽ ሲመለከት አገኘነው፡፡ ከአዲስ አበባ የመጣን ዕንግዶች መሆናችንንና አቦይ ደበሳይን ለማግኘትና ለመተዋወቅ፤ ስለልጃቸው ተስፋዬም የሚነግሩንን ለመስማት የተገኘን መሆኑን ነገርነው፡፡ ወጣቱም አቦይ ደበሳይ ትንሽ አመም አደርጎአቸው በቤቱ ሌላኛው ክፍል መተኛታቸውን ነግሮን፣ እስኪ ከተነሳ ልይላችሁ በማለት ወደ ሌላኛው ክፍል አመራ፡፡
ከትንሽ ቆይታ በኋላም ተመለሰና አባባ ተኝቷል፤ አልተነሳም አለን፡፡

እርሳቸውን በአካል የማየትና ቢቻልም የመተዋወቃችን ጉጉቱ ስላየለብን አንድ ጊዜ በተኙበት ልናያቸው ብንችል፤ ደግሞም ለእርሳቸው ያመጣንላቸው ስጦታ ስላለ እርሱንም ብናበረክትላቸው በማለት አበክረን ስለጠየቅነው ወጣቱ በፍፁም የአክብሮት ስሜት ተከተሉኝ ብሎን ወደ አባባ ደበሳይ መኝታ ክፍል ይዞን ሄደ፡፡
ሁላችንም እዚህ ከመምጣታችን በፊት ማርጀታቸውን ብንሰማም በዚህ ሁናቴ እናገኛቸዋለን ብለን ባለማሰባችን አልጋ ላይ ድንገት ባየነው ነገር በእጅጉ ተደናገጥን፡፡ አቶ ደበሳይ እንካንስ እኛን ተቀብለው ለመተዋወቅና የልጃቸውን ታሪክ ለመንገር ይቅርና ከአንገታቸው እንኳን ቀና ለማለት የማይችሉ፤ ሰውነታቸው እጅግ ከመክሳቱ የተነሳ አልጋው ላይ ብርድ ልብስ እንጂ ሰው ያለበት የማይመስል፤ በሽታው፤ ሃዘንና ዕድሜ ባንድ ላይ አብሮ ያደቀቃቸው ሰው ሆነው አገኘናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ እኒህን ምስኪን ሰው አንዳችም ነገር ለማስቸገር ፍላጎቱ ስላልነበረን ወሬአችን እንዳይረብሻቸው በማሰብ ክፍላቸውን ጥለን ወጣን፡፡

በዚህ ጊዜ ወጣቱ ልጅ ከጎኑ ሆነው አባታቸውን ወደሚያስታምሙት አንዲት ሴት ወይዘሮ ዞር ብሎ የተስፋዬ ታናሽ እህት ናት በማለት አስተዋወቀን፡፡ እኛም በመተዋወቃችን የተሰማንን ደስታ ከገለፅን በኋላ፣ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ከዚያች ትንሽ ከተማ አሊቴና ወጥቶ ኢህአፓ የሚባለውን በታሪክ በእጅጉ የሚታወቀውን ኢህአፓን ከትግል አጋሮቹ ጋር መስርቶ በሞት እስከተለየበት ጊዜ ድረስ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከነበሩት ውስጥ አንዱ የነበረ መሆኑን በማስታወስ፣ የልጅነት ባህሪው እንዴት እንደነበረና ከአሲንባ በኋላ ከቤተሰቡ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ወይዘሮዋን ጠየቅናቸው፡፡
ሴቲቱ የሚናገሩትን የኢሮብ ማህበረሰብ ቋንቋ ለመስማት ባንታደልም ትረካንው በራሳቸው ልሳን ብናደምጠው መልካም እንደነበረ በመጓጓት በወጣቱ አስተርጓሚ አማካኝነት አንዳንድ መረጃዎችን አገኘን፡፡

እንደ ወይዘሮዋ አባባል ተስፋዬ ደበሳይ ገና በልጅነቱ በካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት የተማረና እዚያው ያደገ በመሆኑ ከቤተሰቡ ጋር ብዙ እንዳልኖረ፣ ከፍ ሲልም ውጪ ሄዶ ተምሮ እንደመጣና ከዚያ በአሲንባና በሌሎችም ስፍራዎች በትግል ውስጥ ያሳለፈ በመሆኑ ከእርሳቸው ጋር ብዙም አይተዋወቁም፡፡ ሆኖም ግን አባታቸው አቦይ ደበሳይ ተስፋዬ አሲንባ በነበረበት ጊዜ በተደጋጋሚ በድብቅ እየሄዱ እንደጎበኙትና አንዳንድ ጨዋታዎችን እንደተጫወቱ አስረዱን፡፡ የአቦይ ታሞ ከአልጋ ላይ መውደቅ ይበልጡኑ የሚያስቆጨው የዚህን ጊዜ ነው፡፡ ታሪክ የመዘገብና ቢያንስ እንኳን ጫር ጫር አድርጎ የማስቀመጡ ልማድ የሌለን ህዝቦች ነንና የእነዚህ አባትና ልጅ የበረሃ የአንዳንድ ነገሮች ጨዋታ ምን እንደነበር ሳይከተብ እንደዚሁ ተድበስብሶ መቅረቱ በእጅጉ ያስቆጫል፡፡ የሆነው ሆኖ የተስፋዬን በትልቁ የታጠቡ ፎቶዎች ይዘን ከእህቱ ጋር የመታሰቢያ ፎቶ ከተነሳን በኋላ ተሰነባብተን ተለያየን፡፡ በዚህ አጋጣሚ አቦይ ደበሳይ ተገቢውን የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ዘመድ ወዳጆቻቸው አንዳች ነገር ማድረግ ቢችሉ መልካም ነው እላለሁ፡፡
አሲንባ/አይጋ
አሲንባና አይጋ እነዚህ ሁለት ተራሮች የጦርነትም ቢሆን በታሪክ ያላቸው ትውስታ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የአሲንባ ፍቅር በሚለው መፅሃፍ ላይ ታሪኩ በስፋት እንደተገለፀው፣ የአሲንባ ትግል ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ደደቢት እንደሚባለው የእግር ካስ ቡድን አሲንባ የሚባልም ይኖረን እንደነበር እሙን ነው፡፡ አሲንባ የኢህአፓ ጓዶች በርካታ የአይዲዮሎጂ ፉክቻ ያደረጉበትና የትጥቅ ትግላቸውንም ያደራጁበት እንደመሆኑ ለአሊቲና ነዋሪዎች ያለው ትዝታ በደብዛዛውም ቢሆን ለረጅም ዓመታት አብሮአቸው የሚኖር ነው፡፡ ለእነርሱ ግን የቅርብ ጊዜ ዘግናኝ ትዝታቸው በአይጋ ተራራ ላይ የተደረገው የኢትዮ ኤርትራ ከባድ ጦርነት ነው፡፡ ለሙሽራው ክብር ከሰርጉ ቀደም ብሎ አቶ ግደይ በተባሉ የቅርብ ዘመዱ በተዘጋጀ የምሳ ግብዣ ላይ ለመገኘት ሙሽራውን አጅበን የአቦይ ግደይ መኖሪያ አቅራቢያ አካባቢ ወደሚገኘው አይጋ ተራራ ወጥተናል፡፡
ስፍራው ስንደርስ በአቦይ ግደይ ቤት ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሆኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ የግብዣው ተካፋይ ሆነው ሲበሉና ሲጠጡ አገኘናቸው፡፡ በሁኔታው ግራ ተጋብተን ምንድነው ነገሩ ብለን ስንጠይቅ፣ ድንበር ጠባቂዎች መሆናቸውንና ሁልጊዜ የአካባቢው ሰው እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም ሲያዘጋጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱን ታሳቢ አድርጎ ሰፋ ያለ ድግስ እንደሚያዘጋጅ ተነገረን፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ሃሳብ ወደ አእምሮዬ ከተፍ አለ፡፡ ስለድንበር ጠባቂዎች!
ድንበር አስከባሪዎች፤ ኬላ ጠባቂዎች ወዘተ---እነዚህ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በአካባቢው አንድ ዓይነት ፀብ ሲነሳ የመጀመሪያዎቹ ገፈት ቀማሽ የሚሆኑት እነሱ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ እነርሱ ወደሰፈሩበት አካባቢ የሚመጣ ሰው የለምና ሰው ይናፍቃቸዋል መሰለኝ በተለይ ከመሃል አገር የመጣ ሰው ሲያገኙ በከፍተኛ አክብሮት ሊያጫውቱት ይፈልጋሉ፡፡ የዕለት ተልዕኮአችንን አሳክተን እኛ በየቤታችን ተረጋግተን ስንተኛ፣ በህይወት አጋጣሚ ድንበር ጠባቂ የሆኑ ወታደሮች ግን ቀን ተሌት ተግተው ድንበራችንን የማስከበር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

አብዛኞቹ ሲጋራ ያጨሳሉ፡፡ ወጣቶች ቢሆኑም ሰውነታቸው ግን የፈረጠመ ነው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች እንደ አንዱ ብሆንስ ብዬ ራሴን ላፍታ በጀግንነት ልመዝነው አሰብኩና ፈፅሞ ሊሆንልኝ የማይችል ቅዠት ነገር ሲሆንብኝ ጊዜ ተውኩት፡፡
ደጉ የኢሮብ ማህበረሰብ መቼም ተበልቶና ተጠጥቶ የሚጠገብ አይመስለውምና ከዚህ በፊት አይቼው በማላውቀው አይነት እየተጠበሰ የሚቀርብ አስገራሚ የስጋ ጥብስ እየጋበዘን፣ ማወራረጃውንም ጠጅ እንደ ጉድ እያቀረበልን ስንጫወት ቆይተን፣ የሁላችንም ጉጉት ነበረና በአይጋ ተራራ ላይ ስለተደረገው የኢትዮ-ኤርትራ ከባድ ጦርነት ወሬ ተጀመረ፡፡ ሁሉም የድንበር ጠባቂዎች ስለዚህ ቦታ ልዩ ትዝታ አላቸው፡፡ በወቅቱ በስፍራው ያልነበሩትም ቢሆኑ በአካባቢው የነበረውን ከባድ ጦርነት በታሪክ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ አመጣጣችን ለሰርግ ቢሆንም እነሆይ ጦርነቱም የታሪካችን አንዱ አካልና መጥፎም ጠባሳችንም ነውና በርካታ ሰዎች ስላለቁበት የእጅ በእጅ ውጊያ ፊልም በሚመስል ሁኔታ የተተረከልንን አደመጥን፡፡ ከዚህ ካለንበት የአይጋ ተራራ ሆነን ፊት ለፊት ስንመለከት ደግሞ የአሲንባ ተራራ ቁልል ብሎ ገዝፎ እርሱም የራሱን የታሪክ ትዝታ እያስነበበን እንመለከተዋለን፡፡ ይህንን ጊዜ ስለዚህ መከራ ቻይና ደግ ማህበረሰብ በጥልቀት ሳያስቡ መቅረት ፈፅሞ የማይቻል ነገር ነው፡፡
189 አባወራዎችን ድንገት የተነጠቁት አዲ ኢሮቦች
ከማህበረሰቡ አባላትና ያገር ሽማግሌዎች ጋር ሰፊ ውይይት ሳደርግና በተለይም በጋዜጠኝነት ዓለም ውስጥ ያለሁ መሆኔን ሲረዱ፣አፅንኦት ሰጥተው የነገሩኝ ነገር በእጅጉ ስሜቴን ነክቶታል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ይህቺ የአሊቲና ከተማ በኤርትራ ቁጥጥር ስር ውላ ስለነበረ ከከተማዋና ከአጎራባች አካባቢዎች 189 አባወራዎች ከቤታቸው እየተጠሩ በኤርትራ ወታደሮች ተወስደዋል፡፡ ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ቢደመደምም እነኚህ ከቤታቸው ተጠርተው የተወሰዱ ሰዎች እስካሁን ድረስ የት እንደገቡ ሳይታወቅ ቀርቷ፡፡ እንደ አገር ሽማግሌዎቹ አባባል፣ ወገኖቻቸው ሞተውም ከሆነ ቁርጣቸውን አውቀው እርም ለማውጣት እንኳን አልተቻለም፡፡ የእነዚሁ የት እንደገቡ ያልታወቁ ሰዎች ስም ዝርዝርን ይዘው ወደተለያዩ የመንግስት አካላት ዘንድ ሄደው አቤት ቢሉም እንዲህ ነው ነገሩ የሚላቸው አላገኙም፡፡ በዚህም የማህበረሰቡ አባላት እስካሁንም ድረስ በከፍተኛ ሃዘን ላይ መሆናቸውን በምሬት ነግረውኛል፡፡ አሁንም ቢሆን መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት አንድ ነገር በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሚያደርጉላቸው በተስፋ ይጠባበቃሉ፡፡ በነገራችን ላይ አሊቲና ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን ጨምሮ በልዩ-ልዩ ትምህርቶች ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ከ10 የማያንሱ ዶክተሮችንም አፍርታለች፡፡ እነማን እንደሆኑም ያገር ሽማግሌዎች በስሜት ተውጠው አጫውተውኛል፡፡
እንደተፃፈላት ያገኘሁዋት ከተማ አሊቴና
የአሲንባ ፍቅር መፅሃፍ ሰፋ ያለ ገፅ ሰጥቶ (ከገፅ 55 እስከ 57 ድረስ) በዝርዝር ፅፎ ያስተዋወቀኝን ታሪክ በዓይኔ ለማየት ታድያለሁ፡፡ እነዚህ የማህበረሰብ አካላት በእርግጥም እጅግ ደግና ጨዋዎች ናቸው፡፡ በከተማዋ ያለው ነዋሪ አብዛኛውን የካቶሊክ ዕምነት ተከታይ ሲሆን በስፍራው ቡና ቤትም ሆነ በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ሴቶች የሉም፡፡ ከተማዋ ውስጥ ፈፅሞ ጫት አይቃምም፡፡ ጫት መሸጫም የለም፡፡ ጠላ ቤቶችና ጠጅ ቤቶች ግን በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም አግኝተናል፡፡
በእርግጥ ከአሲንባ ጊዜ ጀምሮ እስከ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ድረስ ወታደር አዘወትሮ የሚጎበኛት ከተማ ናትና አሊቲና በሲጋራ አጫሾች ቁጥር አትታማም፡፡ በርካታ ወጣትና አዛውንት ሲጋራ አጫሾች በብዛት በከተማዋ አሉ፡፡ ወጣቶቹ በእጅጉ ሰው ወዳዶች ሲሆኑ ቀን-በቀን የበለስ ግብዣ በማድረግ ሲንከባከቡን ሰንብተዋል፡፡ ለምለም የተባለች አንዲት እንደ ካፌ ነገር ያላት ሴት ከባለቤትዋ ዕቁባይ ጋር ስጋ ሲሰለቸን እጅግ የሚጣፍጥ መኮረኒና ፓስታ ትሰራልን ነበረ፡፡ የአዲ ኢሮብ ማህበረሰብ የጥህሎና የስጋ ስፔሻሊስት ነው፡፡ ጥህሎ ሲሰሩና ስጋ ሲጠብሱ እጅ የሚያስቆረጥም አድርገው ነው፡፡ የሰርግም ሆነ የሃዘን ስነ-ስርዓታቸው በጋራ የሚከወን ነው፡፡ ማርና ቅቤያቸውም የተለየ ነው፡፡ ኢሮብ ውስጥ ማርና ቅቤ ግን አይሸጥም፡፡ ማህበረሰቡ ራሱ ነው በስጦታ የሚያቀርብልህ እንጂ!
ቢግ ብራዘር አሊቲና
በአሊቲና ሆቴል የሚባል ነገር የለምና ያረፍነው የማህበረሰቡ ተወላጅ ከሆነውና የሙሽራው የቅርብ ዘመድ ከሆነው ከዳንኤል እናት ቤት ሲሆን ወ/ሮ አብረኸት ቤታቸውን ለቅቀው ከ10 ቀን በላይ እጅግ ሊነገር ከሚችለው በላይ በሆነ መስተንግዶ ሲንከባከቡን ከርመዋል፡፡ 8 ከተለያየ ሞያዎች የመጣን በተለያየ የዕድሜና የኑሮ ደረጃ ላይም የምንገኝ የሙሽራው ወዳጆች እኛ ቢግ ብራዘር አሊቲና ብለን የጠራነው የነዳንኤል/የእነ ወ/ሮ አብርሃት ቤት በርካታ ትዝታዎችን በውስጣችን ቀርፆብናል፡፡ መብራት ካልጠፋ ዕንቅልፍ አይወስደንም የሚሉ፤ ፕሮፌሽናል ሰዎች 4 ሰዓት ብቻ ነው የሚተኙት በሚል የግል ፍልስፍና እንቅልፍ የማይተኙና ሲያነቡ የሚያድሩ፤ በሌሊት ለዎክ ካልወጣን ብለው የሚያስቸግሩ፤ የአይፓድ ፊልም ሱስ የተጠናወታቸው፤ ጠጥተው ሞቅ ሲላቸው ሌላውን አላስተኛ የሚሉ፤ የልጅነት ትዝታቸውን ሲያወሩ በዕንባ የሚታጠቡ፤ ወዘተ እነዚህ ሁሉ የቢግ ብራዘር አሊቲና ዋና ዋና ትዝታዎቻችን ናቸው፡፡ ለእኛም የዩኒቨርሲቲን ዶርሜተሪ የሚያስታውስ ከ10 ያላነሱ ተከታታይ ቀናትን በመቻቻል ያሳለፍንበት የአዲ ኢሮብ ትዝታችን ብዙ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ወደ ወንዝ እየወረድን ገላችንን ተለቃልቀናል፡፡ በግ አርደን በጫካ ውስጥ ካምፕፋየር አድርገናል፡፡ ተራራ በእግራችን መውጣት ተለማምደናል፡፡ የኢሮብና የትግሬኛ ቋንቋ ለመስማት ከሳምንት በላይ ልምምድ አድርገናል፡፡

ከማህበረሰቡ አባላት ጋር በጠላና ጠጅ ቤቶች ለረጅም ሰዓት አብረን ተቀምጠን ወግ ጠርቀናል፡፡ ከነዋሪ ወጣቶች ጋር ጠዋትና አመሻሹ ላይ የእግር ካስ ግጥሚያ አድርገን በሰፊ ውጤት ተሸንፈናል፡፡ በእነ ፀጋ ቤት የቡና ጠጡ ፕሮግራም አካሂደናል፡፡ የኢህአፓ አባል እንደነበሩ ካጫወቱን ከመምህር ተስፋዬ ጋር (እሳቸው ያገቡት የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን ሌላ እህት ነው) ተራራ ላይ ቁጭ ብለን ጣፋጭ የህይወት ታሪካቸውን አድምጠናል፡፡ የኢሮብ ዋና ከተማ በሆነችው ዳውሃን ተገኝተን በቀዝቃዛ ቢራ አንጀታችንን አርሰናል፡፡ ብቻ አሊቲናን ድምቅ አድርገናት ተመልሰናል፡፡ ጉዟችን ደግሞ እጅግ አዝናኝ እንዲሆን የሳቅ ምንጫችን የነበረው የቀድሞ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ወጋ-ወጋ በፈገግታ ዓምድ ፀሃፊ ጀቤሳ/ ቢኒያም እሸቱ የነበረው አስተዋፅኦ ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡
በነገራችን ላይ እዚያ በቆየንበት ወቅትም እንደ አጋጣሚ ሆኖ በአንድ የቀብር ስነ-ስርዓትም ላይ ለመገኘት በቅተን ነበረ፡፡ ይህንን አስደናቂ ቀብርና የወዳጃችንን የሰርግ ስነ-ስርዓት በተመለከተ እንደዚሁም በጉዞአችን ላይ በአዲግራት ከተማ ስለተመለከትኩት የኦርቶዶክስ፤ የሙስሊምና የካቶሊክ ሃይማኖቶች ጥምረት የሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ በሰላም ዙሪያ ስለሚሰራው አስደናቂ ስራዎች በወደፊት ፅሁፌ በስፋት የምመለስበት ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ግብዣ!
የአዲ ኢሮብ ማህበረሰብ በአሊቲና ከተማ የመስቀል በዓልን በየዓመቱ እጅግ ደማቅ በሆነ ስነ-ስርዓት እንደሚያከብር የአገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ተወላጆች ነግረውኛል፡፡ በመሆኑም እንግዶች ከየአካባቢው በመገኘት ማህበረሰቡን እንዲያውቁትና ታሪኩንና ባህሉንም እንዲገነዘቡለት ማህበረሰቡ በደግነት ግብዣውን እንዳቀርብ አዞኛል፡፡ እኔም ትዕዛዙን አክብሬ እነሆ አስታውቄአለሁ፡፡ ለመጪው መስቀል ወደዚያው በድጋሚ ማምራቴ አይቀርምና የጉዞው ሃሳብ ያላችሁ ሰዎች ለምን አንገናኝም? መልካም ቅዳሜ!

Read 5095 times Last modified on Saturday, 24 August 2013 10:41