Saturday, 24 August 2013 10:26

ለአክራሪዎች እጅ እንድንሰጥ የሚገፋፉ 3 ቀዳሚ ምክንያቶች

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(13 votes)

እምዬ ሔዋን፣ እምዬ ኢትዮጵያና እምዬ ሉሲ - 3 ወዶ አይሆንም!
የሃይማኖት አክራሪነትን በለዘብተኛ አስተሳሰብ መከላከልና ማሸነፍ የምንችል ይመስለናል። ግን አንችልም። ለሃይማኖት አክራሪነት… ተቃራኒውና ጠላቱ፣ ሁነኛ ማርከሻውና መድሃኒቱ ለዘብተኛነት አይደለም - ፅኑ የሳይንስ ፍቅር እንጂ። ይህንን አለመገንዘባችንም ነው፣ ቁጥር አንድ ድክመታችን። ተስፋ የጣልንበት ለዘብተኛ አስተሳሰባችን፣ እንደምንመኘው አለኝታና ከለላ ሆኖ አያድነንም። በተቃራኒው፣ አክራሪዎች በቀላሉ የሚያጠቁት ስስ ብልት ይሆንብናል። ውሎ አድሮም ለአክራሪዎች እጅ እንድንሰጥ የሚያደርግ የመጀመሪያው ነጥብ እንደሆነ ለማሳየት እሞክራለሁ።
የመሃል ሰፋሪ ወይም የዘብተኛ ሰው ልዩ ምልክት ምን መሰላችሁ? “ሁላችንም ትክክል ነን”… ለማለት የመቸኮሉ ያህል፤ ይሄ አላዋጣ ሲለው… “ሁላችንም ትክክል አይደለንም” ለማለት ይጣደፋል። ለምን በሉ።
ለዘብተኛው መሃል ሰፋሪ፣ ሁሉንም አይነት አስተሳሰብ እያጣቀሰ (ግን ደግሞ ከየትኛውም ሳይሆን) ለመኖር ይመኝ የለ? እናም የመጣውን ሁሉ ተቀብሎ ያስተናግዳል። “እውነት የሚገኘው ከፈጣሪ ቃል ነው፤ የማንኛውም ነገር መመዘኛችንም ሃይማኖታዊ እምነት መሆን አለበት” የሚል ሰባኪ ሲመጣበት፤ … ለዘብተኛው ሰውዬ አእምሮውን ተጠቅሞ ትንሽ ለማሰብና ለማሰላሰል አይሞክርም። “ትክክል ብለሃል” ብሎ በእንብርክክ ስብከቱን ይቀበላል። ብዙ ኢትዮጵያውያን፣ የጥንቱን ስልጣኔ ረስተው ለሺ አመታት በድቅድቅ ጨለማ የዳከሩት፣ በኋላቀርነት መከራ ውስጥ የተዘፈቁት፣ የአክራሪዎች የክርስትና ስብከት በለዘብተኞች ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ ነው። በግብፅ ደግሞ የመሃመድ ሙርሲ ስብከት!
ይሄም ብቻ አይደለም። “እውነት የሚገኘው ከሕዝባዊ ስሜት ነው፤ የማንኛውም ነገር መለኪያችን ሕዝባዊ ስሜትና ነባሩ ባህል መሆን አለበት” የሚል ካድሬ ወይም የሕዝብ ‘ተቆርቋሪ” ሲመጣበትም፤ ለዘብተኛው ሰውዬ አሻፈረኝ አይልም። “አልተሳሳትክም ጓድ! አልተሳሳትክም የወንዜ ልጅ” ብሎ በፓርቲ መፈክር አልያም በባህላዊ ጭፈራ ያስተናግደዋል። በዚህ ሳቢያ ምን እንደተፈጠረ የምታውቁት ይመስለኛል። “ኢትዮጵያ ትቅደም”፤ “ለጭቁኖች የሚወግን ወዛደራዊ አምባገነንነት ይስፈን”፣ “የሰፊው ሕዝብ ድምፅ የፈጣሪ ድምፅ ነው”፤ “ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ናት”… በሚሉ መፈክሮችና ጭፈራዎች ብዙዎች ተገርፈው ተረሽነዋል፤ ሚሊዮኖች ተርበው አልቀዋል። በግብፅ ደግሞ፣ የጄነራል አሲሲ የአገር አድን መፈክር!
ለዘብተኛው መሃል ሰፋሪ ግን ይህንን ሁሉ የማመዛዘንና የማገናዘብ ጣጣ ውስጥ መግባት አይጥመውም። የመጣውን ሁሉ ሸክም ችሎ ማደርን ነው የሚፈልገው።
“እውነት የሚገኘው ከሳይንሳዊ ምርመራ ነው፤ የማንኛውም ነገር መለኪያችንና መመዘኛችን ሳይንሳዊ እውቀት መሆን አለበት” የሚል አስተማሪ ወይም ሃኪም ሲመጣስ? በተለመደው ለዘብተኛ አስተሳሰብ፣ …“ትክክል ብለሃል” ብሎ ስክርቢቶና ደብተር ይዞ ለመማር ወይም መድሃኒት ለመውሰድ እጁን ዘርግቶ ይቀበለዋል። እስከ 1900 ዓ.ም ድረስ ከሰላሳ አመት በታች የነበረው የኢትዮጵያውያን አማካይ የሕይወት ዘመን በእጥፍ የጨመረው ለምን ሆነና? አዳሜ፣ ዛሬ ዛሬ በአማካይ 55 ዓመት ገደማ በሕይወት የመኖር እድል አግኝቷል። ከአምስት ሚሊዮን በታች የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አሁን 90 ሚሊዮን ለመድረስ የተቃረበውም በሌላ ምክንያት አይደለም። በሳይንስ ነው። በሳይንሳዊ እውቀት አማካኝነት የተገኙ ምርቶች፣ በትምህርት ወይም በእርዳታ መልክ ስለደረሱልን ነው። ለዘብተኛው መሃል ሰፋሪ ግን፣ ዝርዝር መረጃዎችንም ሆነ አንኳር ማስረጃዎችን የመመርመርና አፍረጥርጦ የማሰብ ፍላጎት የለውም።
የለዘብተኛ ብልጠት - ብልሃት መሳይ ሞኝነት
በአንድ ጊዜ ሁሉንም አይነት አስተሳሰብ እያስተናገደ፣ ግን ደግሞ አንዳቸውንም በሙሉ ዓይን ሳይመለከትና ሳይመረምር መኖር ነው የለዘብተኛ ሰው ፍላጎት። ይህንን፣ እንደ ብልህነት ወይም እንደ ብልጣብልጥነት ስለሚቆጥረው ነው፤ “ሁላችንም ትክክል ነን፤ ሁላችሁም ትክክል ናችሁ” ለማለት የሚጣደፈው። በቃ! ሁሉንም የሚያስታርቅ፣ በተለይ ደግሞ አክራሪነትን የሚከላከል ምትሃተኛ ፈውስ ከአንደበቱ ያፈለቀ ይመስለዋል። ሞኝነቱ። ለአክራሪዎች ይሁንታውን በመለገስ፣ ራሱን ለጥቃት አመቻችቶ እያጋለጠ መሆኑን አላወቀም።
አሃ! “ሁላችንም ትክክል ነን” ሲልኮ፣ “እናንተም ትክክል ናችሁ” እያላቸው ነው። ከዚያማ ራሱ በጠረገላቸው መንገድ፣ ራሱ በለገሳቸው ይሁንታ ይገባሉ - “ትክክል መሆናችንን ማመንህ ጥሩ ጅምር ነው” በማለት። ግን በዚያ አያቆሙም። “አንተ ግን ትክክል አይደለህም” ብለው ስለት ይሰነዝሩበታል። “ራስህ እንደመሰከርከው፣ ከሁሉም በፊት ሃይማኖታዊ እምነትን ማስቀደም ያስፈልጋል ማለታችን ትክክል ከሆነ፤ ሌሎች አስተሳሰቦችን ማስቀደም ትክክል ሊሆን አይችልም፤ እውነትን መበረዝና ማርከስ ይሆናላ!” በማለት ለዘብተኛውን አጣብቂኝ ውስጥ ያስገቡታል። “የአገር የቁርጥ ቀን ልጆች ነን፤ የሕዝብ ልሳን ነን” የሚሉ የስሜት ካድሬዎችም በተመሳሳይ ዘዴ ነው ለዘብተኛውን መፈናፈኛ የሚያሳጡት። መሃመድ ሙርሲና ጄነራል አሲሲ በለዘብተኛው የግብፅ ሰው ላይ የሚፈራረቁበት በዚህ መንገድ ነው።
መቆሚያ መቀመጫ ያጣ መሃል ሰፋሪ፣ መውጪያ መግቢያ ያጣ ለዘብተኛ ምን ይዋጠው? ሲጨንቀው፤ “እውነት በሞኖፖል የያዘ የለም፤ ሁላችንም ትክክል አይደለንም፤ ሁላችሁም ትክክል አይደላችሁም” በሚል መከራከሪያ ለማምለጥ ይፍጨረጨራል። ራሱን በራሱ ጠልፎ እየጣለ መሆኑን አላወቀም። “ትክክል አይደለሁም ብለህ መናዘዝህ ጥሩ ጅምር ነው” ይሉታል።
በአጭሩ፤ “ሁላችንም ትክክል ነን” ብሎ ሲናገር፣ ለአክራሪዎችና ለካድሬዎች ይሁንታውን ያበረክትላቸዋል። “ሁላችንም ትክክል አይደለንም” ብሎ ሲናገር ደግሞ፣ በጥፋተኝነት እጁን ይሰጣል። የሙርሲና የአሲሲ መጫወቻ ይሆናል። ለዘብተኛነት አያዋጣም። ከሃይማኖትና ከእምነት በፊት ለሳይንስና ለአእምሮ ቅድሚያ የማንሰጥ ከሆነ፤ ከአክራሪዎች ጋር ተስማምተን ይሁንታችንን ሰጥተን ከእግራቸው ስር ለመንበርከክ እንደተዘጋጀን ይቆጠራል። በመሃል ሰፋሪነት ከዚህና ከዚያ እያጣቀሱ መቀጠል አይቻልም። ለምን? መሰረታዊ የሆኑ ተቃራኒ አስተሳሰቦችን አዳብሎና ቀይጦ መያዝ አያዛልቅማ።
ሁለተኛው የድክመታችን ነጥብ እዚህ ላይ ነው - አክራሪነት፣ ከፖለቲካ ጉዳይነት በእጅጉ የሰፋ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ጥያቄ መሆኑን አለመገንዘባችን! መሰረታዊው ግጭት፣ በሳይንሳዊ እውቀት፣ በሃይማኖታዊ እምነት እና በሕዝባዊ ስሜት መካከል ለሺ አመታት የዘለቀ የሶስትዮሽ ግጭት መሆኑን ካላወቅን፣ ለአክራሪዎች እጅ ለመስጠት እንገደዳለን።
ከላይ እንደገለፅኩት፣ ብዙዎቻችን፣ ሶስቱን ተቃራኒ አስተሳሰቦች ቀይጠንና አዋህደን ለማስተናገድ የምንሞክር ለዘብተኞች ነን። ለጊዜው በምሳሌያዊ መጠቆሚያ ልግለፀው። ሃይማኖታዊ እምነትን በመከተል “እምዬ ሔዋን” የሰው ልጆች ሁሉ እናት መሆኗን አምነን እንቀበላለን። ሕዝባዊ ስሜትን በማነፍነፍ፣ “እናት አገር እምዬ ኢትዮጵያ” በሚል ምናባዊ ምስል ተውጠን ሳግ ይተናነቀናል። ሳይንሳዊ ግኝትን በመመርመር ደግሞ፣ “እምዬ ሉሲ” የሰው ዘር ምንጭ እንደሆነች እንገነዘባለን። ከዚያስ?
ከዚያማ፣ እምዬ ሔዋንን፣ እምዬ ኢትዮጵያንና እምዬ ሉሲን አንዳቸውን መምረጥም ሆነ መጣል ሳይኖርብን ጠቅልለንና አዳብለን አልያም ቀይጠንና አዋህደን ለመያዝ መከራችንን እናያለን። እንዲህ ቅይጥ ለዘብተኛ መሆን ብልህነት ይመስለናል። ነገር ግን እምዬ ሔዋን፣ እምዬ ኢትዮጵያና እምዬ ሉሲ አብረው አይሄዱም። ሊቀየጡና ሊዳበሉ አይችሉም።
ሶስቱ ተቃራኒ አስተሳሰቦች፣ አለማችን ላይ በብቸኝነት የበላይነትን ለመቆጣጠር እየተጋጩ፣ በየዘመኑ አንዱ ሌላውን እየገረሰሰና እያንበረከከ ሲነግሱ እንጂ፣ ተቻችለው አብረው ሲኖሩ ወይም ለዘብተኞች ሲያሸንፉ ታይቶ አይታወቅም።

ሃይማኖታዊ እምነት በሳይንስና በሕዝብ ጫንቃ ላይ
ሃይማኖታዊ እምነት በነገሰበት ዘመን፣ የሔዋን ማንነት በስብከት ጎልቶ ይወጣል። ሳይንሳዊ እውቀትና ሉሲ፣ ህዝባዊ ስሜትና እናት አገር ይቀበራሉ፤ አልያም ምድር ቤት ይወረወራሉ፡፡ የክርስትና እምነትን እናስፋፋለን የሚሉ የሃይማኖት ሰባኪዎችና አማኞች ከ1700 አመታት በፊት በአሌክሳንደሪያና በሮም ከተሞች ውስጥ የበላይነትን ሲይዙ ምን ተፈጠረ? ሃይማኖታዊ እምነት በፍፁም ከሳይንሳዊ እውቀትና ከምርምር ግኝት ጋር ተዳብሎ፤ ወይም ከነባር ባህልና ከሕዝባዊ ስሜት ጋር ተቻችሎ አልተቀመጠም።
የአሌክሳንደሪያ የሳይንስና የፍልስፍና ማዕከል ከነ ምሁራኑና ከነ መፃህፍቱ እንዲቃጠል ተደርጓል። ባህላዊ በዓላትና ጭፈራዎች ተወግዘዋል፤ ሃውልቶችና ቅርሶች ፈራርሰዋል፤ ሕዝብ ቢያጉረመርም እንኳ አዋጅ ተጥሎበታል። የሮም እና የሌሎቹም ተመሳሳይ ናቸው። በአሌክሳንደሪያ ከቃጠሎ የተረፉ መፃህፍት እንደገና ከ1300 በፊት እስልምናን እናስፋፋለን በሚሉ ሰዎች ተቃጥለዋል። በቅርቡም እንዲሁ የሙርሲ ደጋፊ አክራሪዎች የአሌክሳንደሪያ ቅርሶችን ኢላማ አድርገዋል። ከቅርባችን የሶማሊያ አልሸባብንም ማየት እንችላለን። ወይም ደግሞ የአፍጋኒስታንን።
ታሊባኖች አፍጋኒስታንን ሲቆጣጠሩ፣ ሴቶች እንዳይማሩ፣ ወንዶች በቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም እንዳያዩ በመከልከል የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጠላትነታቸውን አስመስክረዋል። ነባር አለባበስንና ጭፈራዎችን ለመከልከል፣ ጥንታዊ ቅርሶችን ለማፍረስና ባህላዊ ስርዓቶችን ለማገድ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በአንድ ሰማይ ላይ ሁለት ወይም ሦስት ፀሐይ አይኖርም እንዲሉ፣ ሃይማኖት የሚነግሰው ሳይንስንና የምርምር ግኝትን በማንበርከክ፣ እንዲሁም ባህልና የህዝብ ስሜትን በማብረክረክ ነው፡፡

የአክራሪነት ማርከሻ ያገኙ የሳይንስ ጀግኖች
ከጥንቱ የሮምና የአሌክሳንድርያ ታሪክ እስከ ዘመናችን የአልሸባብና የታሊባን ወቅታዊ ዜና… ሁሉም ላይ በግልፅ እንደሚታየው፣ ለዘብተኞች የአክራሪዎችን ዘመቻ ማስቆም አልቻሉም። የሃይማኖት አክራሪነት ሽንፈትን የቀመሰው፣ በለዘብተኞች አማካኝነት ሳይሆን፣ በፅኑ የሳይንስ አፍቃሪዎች ጥረት ነው። ሃይማኖታዊ እምነት ከዙፋን ወርዶ በቦታው ሳይንሳዊ እውቀት የበላይነት ያገኘ ጊዜ ነው፡፡ ያኔ አእምሮ ይከበራል፤ የሉሲ ማንነት በትምህርት እየተዳረሰ ሳይንሳዊ እውቀት ይስፋፋል። ወቅቱ፣ The Age of Reason “የአእምሮ ዘመን”፣ Enlightenment Age “የእውቀት-ፋና ዘመን” ተብሎ ይታወቃል። በዚሁ ወቅት እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ድረስ ሲስፋፋ በቆየው ሳይንሳዊ አስተሳሰብ አማካኝነት አሜሪካ እንዴት እንደተመሰረተች ማየት ይቻላል።
አሜሪካ ውስጥ በ18ኛው ክፍለዘመን አክራሪዎችን ለመቋቋምና ለመከላከል የተቻለው በለዘብተኞች ሳይሆን በሳይንስ አፍቃሪዎች ነው። “ሃይማኖታዊ እምነት ምንም ሆነ ምን፣ በአእምሮና በሳይንስ መመርመር አለበት” በሚሉ ብልሆች ናቸው አሜሪካን የመሰረቷት። እዚህ ላይም በግልፅ የሚታይ ነገር ቢኖር፣ ተቃራኒዎቹ አስተሳሰቦች በጋራ መግዘፍና መንገስ እንደማይችሉ ነው። አእምሮ እና ሳይንስ የሚነግሱት፤ በሃይማኖታዊ እምነትና በህዝባዊ ስሜት ላይ የበላይነትን በመቀዳጀት ነው፡፡
የአሜሪካ መስራቾች ይህንን እውነታ ስለሚያውቁ ነው፤ ከለዘብተኛነት ይልቅ ፅኑ የሳይንስ አፍቃሪ በመሆን ሰፊ ዘመቻ ያካሄዱት፡፡ እምነትንና አእምሮን አቻችለው ለመቀየጥ አልሞከሩም፤ አእምሮን ነው የመረጡት፡፡ ሃይማኖትንና ሳይንስን አስማምተው ለማዳበል አልጣሩም፡፡ ሳይንስን ነው የመረጡት። ለአእምሮና ለሳይንስ ምን ያህል ክብር እንደነበራቸው ለማሳየት ያህል፣ የአንዳንዶቹን አባባል ልጥቀስላችሁ። ቤንጃሚን ፍራንክሊን፣ የእምነትንና የአእምሮን ተቃራኒነት ከመጥቀስ አልፈው፣ ለየትኛው ቅድሚያ እንደሚሰጡ እንዲህ በማለት ገልፀዋል፡ “The way to see by faith is to shut the eye of reason.” በእምነት መመራት፣ የአእምሮን አይን መዝጋት ነው።
የዚያን ዘመን ዝነኛ ፀሃፊ ቶማስ ፔን ደግሞ፣ ሃሳቡን ጠጠር ባለ ቋንቋ ይገልፃል፡ “I do not believe in the creed professed by … any church that I know of. My own mind is my own church.” … “በማናቸውም የሃይማኖት ቤተ መቅደስ ቀኖና አላምንም፤ አእምሮዬ ነው ቤተ መቅደሴ”።
“ሰባኪዎች በሳይንስ ግስጋሴ ይርዳሉ” በማለት የፃፉት ቶማስ ጄፈርሰን በበኩላቸው፣ አክራሪነትን ለመከላከልና በስልጣኔ ጎዳና ለመራመድ ምን ማድረግ እንደሚያስፈለግ ያብራራሉ፡ “Shake off all the fears of servile prejudices, under which weak minds are servilely crouched. Fix reason firmly in her seat, and call on her tribunal for every fact, every opinion. Question with boldness even the existence of a God; because, if there be one, he must more approve of the homage of reason than that of blindfolded fear.
እንዲህ ልተርጉመው፡
“ነፈዞች በታዛዥነት የሚንበረከኩለት የጭፍን እምነት ፍርሃታችሁን ከላያችሁ ላይ አራግፉ። አእምሮን በጠንካራ መሰረት ላይ በማኖር፣ በሁሉም ነገርና በሁሉም ሃሳብ ላይ ዳኝነት እንዲሰጥ አቅርቡለት። የፈጣሪ መኖርና አለመኖርንም ጭምር በድፍረት መርምሩ። ምክንያቱም ፈጣሪ ቢኖር፣ ከጭፍን ፍርሃት ይልቅ የአእምሮ ክብርን እንደሚያስበልጥ አያጠራጥርም…” የቶማስ ጄፈርሰን ንግግር ነው - የአሜሪካ ሶስተኛው ፕሬዚዳንት።
አእምሮውን በፅኑ መሰረት ላይ ያላኖረና ሁሉንም ነገር በአእምሮው የማይመረምር ለዘብተኛ ሰውስ ምን ይጠብቀዋል? መጫወቻ ይሆናላ።
“ሰው፣ አእምሮውን ለሌላ ነገር በምርኮ አሳልፎ የሰጠ ጊዜ፣ ጭራና ቀንዳቸው የማይታወቁና የተቃወሱ የጥፋት ሃሳቦችን የሚከላከልበት መመከቻ አይኖረውም። የአቅጣጫ መቆጣጠሪያ እንደሌለው ጀልባ፣ የነፋስ መጫወቻ ይሆናል” ብለዋል ጄፈርሰን። (Man once surrendering his reason, has no remaining guard against absurdities the most monstrous, and like a ship without rudder, is the sport of every wind.) አንዴ የሙርሲ፣ አንዴ የአሲሲ መጫወቻ ይሆናል!
በአእምሮ እና በሳይንስ ላይ ለዘብተኛ መሆን አያዋጣም ነው ነገሩ። ጄፈርሰን የሳይንስ አፍቃሪ በመሆናቸው፤ እምነትም ሆነ ባህል፣ የሃይማኖት ቀኖናም ሆነ የሕዝብ ስሜት፣ ሁሉም በአእምሮ መመርመርና መመዘን እንዳለበት በመናገር ብቻ አላበቁም። በሃይማኖታዊ መፃህፍት ውስጥ የተካተቱና ሳይንሳዊ እውቀትን የሚቃረኑ “ተአምራት”፣ ፈፅሞ ተቀባይነት ሊኖራቸው አይገባም ብለው በመሰረዝ ቀሪውን በግላቸው ለማሰራጨት ጥረዋል።
እንግዲህ አስተውሉ። የአሜሪካ መስራች አባቶች፣ ከእምነት ይልቅ ለአእምሮ፣ ከሃይማኖት ይልቅ ለሳይንስ ቅድሚያ በመስጠት፣ ጠንካራና የጠራ የአስተሳሰብ መሰረት በመያዝ፣ በዚህም የአክራሪነትን ስረ መሠረት በመናድ ነው ወደ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የተሸጋገሩት።
እነ ጄፈርሰን፣ ከመሰረታዊዎቹ ሶስት ተቃራኒ አስተሳሰቦች መካከል ሳይንሳዊ የእውቀት መንገድን መርጠው በፅናት ስለያዙ፣ ፖለቲካው ብዙ አላስቸገራቸውም። ፖለቲካዊ ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙትና መንግስት የሚመሰረተው፣ ከሃይማኖት በፀዳ ሳይንሳዊ መንገድና በአእምሮ እየተፈተሸ መሆን እንዳለበት ገለፁ። አብዛኞቹ የአሜሪካ ሕገመንግስት አርቃቂዎችና አፅዳቂዎች በዚህ ሃሳብ ይስማሙበታል። “The United States of America should have a foundation free from the influence of clergy.” አሜሪካ ከሰባኪዎች ተፅእኖ የፀዳ መሰረት ሊኖራት ይገባል - የአሜሪካ ሁለተኛ ፕሬዚዳንት ጆን አዳም የተናገሩት ነው።
የሃይማኖት ተቋማት በማህበረሰብ ውስጥ ያመጡት ውጤት ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ሌላኛው ታዋቂ ፓለቲከኛ ጄምስ ማዲሰን ምላሽ ሲሰጡ፣ “አልፎ አልፎ በሲቪል አስተዳደር መቃብር ላይ መንፈሳዊ አምባገነንነት ሲገነቡ ይታያሉ፤ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ የዘውድ አምባገነንነትን ሲደግፉ ይታያሉ። ለሰው ነፃነት አለኝታ የሆኑበት ጊዜ ግን የለም” በማለት ለዘብተኛ ያልሆነ አቋማቸውን ገልፀዋል … In some instances they have been seen to erect a spiritual tyranny on the ruins of the civil authority; on many instances they have been seen upholding the thrones of political tyranny; in no instance have they been the guardians of the liberties of the people. ከአሜሪካ መስራቾች መካከል አንዱ የሆኑት ጄምስ ማዲሰን የአገሪቱን ህገመንግስት በማርቀቅ ትልቁን ድርሻ የተወጡ ከመሆናቸውም በላይ የአሜሪካ አራተኛ ፕሬዚዳንት ናቸው።
ጆን አዳምስ፣ ቶማስ ጄፈርሰን፣ ጄምስ ማዲሰን እና ሌሎቹ የአሜሪካ ታላላቅ መስራቾች፤ በአለማችን ስር ሰድዶ ለሺ ዘመናት የዘለቀውን አክራሪነት ለመከላከልና ለማሸነፍ የቻሉት፣ በአእምሮና በሳይንስ የበላይነት ላይ ፅኑ አቋም በመያዝ እንጂ በለዘብተኛነት አይደለም።
ይህም ብቻ አይደለም። የሳይንስ አፍቃሪ እንደመሆናቸው፣ ህዝባዊነትንም በፅናት ተቃውመዋል፡፡ አንድ ሃሳብ፣ በብዙ ተከታታይ ትውልዶች በውርስ እየተላለፈ የመጣ ቢሆን እንኳ፣ ትክክለኛ ሃሳብ ላይሆን ይችላል በማለት የባህል የበላይነትን ተቃውመዋል፡፡
የሰዎች ቁጥር፣ የእውነት ማረጋገጫ እንዳልሆነ በመግለፅ የተከራከሩት እነ ጄፈርሰን፣ የእውነት ምንጭ እውኑ ተፈጥሮ እንደሆነ፣ ብያኔ ሰጪው ደግሞ አእምሮ እንደሆነ በግልፅ ተናግረዋል - ሳያለዝቡ። ሕዝባዊ ስሜት የእውነት መመዘኛ አይደለም። ከህዝቡ ውስጥ 99 በመቶ ያህሎቹ፤ ንጉስ እንዲገዛቸውና የፖለቲካ ምርጫ እንዲታገድ ድምፅ ሰጥተውና ተስማምተው ውሳኔ ቢያስተላልፉ እንኳ፣ ውሳኔያቸው ትክክል ይሆናል ማለት አይደለም በማለት ህዝባዊነትን ውድቅ አድርገዋል - እነ ጄፈርሰን፡፡ ለዚህም ነው የአሜሪካ መስራች አባቶች፣ ከህዝብ ስሜት ጋር የማይዋዥቅ፣ በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ ህገመንግስታዊ ስርዓት ያቋቋሙት፡፡
በአጭሩ ለሳይንሳዊ እውቀትና ለአእምሮ፣ ከሁሉም የላቀ ክብር የሚሰጥ አስተሳሰብ የበላይነት የሚይዘው፣ ስልጣኔና ነፃነት የሚሰፍነው፣ ሃይማኖታዊ እምነትንና ህዝባዊ ስሜትን በማሸነፍ ነው፡፡ እንደገና ለመድገም ያህል፣ ሶስቱ መሠረታዊ የአስተሳሰብ መንገዶች ተቃራኒ ስለሆኑ፣ መሸናነፍና የበላይነት መያዝ እንጂ ተዳብለውና ተቀይጠው መኖር አይችሉም። አሳዛኙ ነገር፣ ከሁሉም በላይ ለሳንሳዊ እውቀትና ለአእምሮ ዋጋ በመስጠት የሚሟገት ምሁር ወይም ፖለቲከኛ በኛ አገር ብዙም የለም። ሦስተኛው የድክመታችን ነጥብ ይሄው ነው።

በሳይንስ ቦታ ሕዝባዊነት፣ በነፃነት ፋንታ ሂትለርና ስታሊን
አገራዊ ባህል እና ሕዝባዊ ስሜት በ20ኛ ክፍለ ዘመን ገንነው የወጡትም በለዘብተኛነት አይደለም። ሳይንስንና አእምሮን ከንግስና በመገልበጥ፣ ሃይማኖትንና እምነትን በመድፈቅ አልያም በማንበርከክ ነው፡፡
“ስዩመ እግዚአብሔር” የሚለው የእምነት ፈሊጥ በመገርሰስ ነው፣ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል ሕዝባዊ የፋሺዝም መፈክር የበላይነትን የተቀዳጀው። የብሔር ብሔረሰብ ታርጋ የለጠፉ ሕዝባዊ ቡድኖች ጎልተው የወጡትም በተመሳሳይ መንገድ ነው። የወዛደሩ አምባገንነትን እናሰፍናለን፤ የጭቁኖችን መንግስት እንመሰርታለን የሚሉ ሶሻሊስቶች የነገሱትም፣ በተመሳሳይ መንገድ ሃይማኖታዊ እምነትንና ሳይንሳዊ እውቀትን በማንበርከክ ነው። እናም፣ የሂትለርና የሞሶሎኒ፣ የሌኒንና የስታሊን፣ የማኦ እና የቼጉቬራ ዘመን ተፈጠረ፡፡
የህዝባዊ ስሜት አቀንቃኞች በሃይማኖታዊ እምነት ላይ ብቻ ሳይሆን በሳይንሳዊ እውቀት ላይም ነው የበላይነት የተቀዳጁት፡፡ እንዴት በሉ፡፡ “የራሳችንን ባህል ንቀን የምዕራባዊያንን ሳይንስ ቀድተን መውሰድ የለብንም” ሲባል ሰምታችኋል? የአውሮፓ ሳይንስ፣ የአይሁድ ሳይንስ፣ የኤስያ ሳይንስ፣ የአፍሪካ ሳይንስ… የሚሉ ስያሜዎችን በመለጠፍ ነው፣ እነ ሂትለር የሳይንስን ትርጉም የሸረሸሩት። ሳይንስ በሕዝባዊ ስሜት ስር እንዲንበረከክ ያደረጉት። እነ ሌኒን ደግሞ፣ የቡርዧ ሳይንስና የወዛደር ሳይንስ፣ የበዝባዦች ሳይንስና የጭቁኖች ሳይንስ እያሉ ሳይንስን አራከሱት።
በዚህም ተባለ በዚያ፣ በሦስቱ መሰረታዊ አስተሳሰቦች መካከል መቻቻልና አብሮ መኖር የለም፡፡ ተዳቅሎና ተቀይጦ በጋራ መጓዝ የለም። ከዚያ በኋላ እነማን ቀሩ? የቀረነውማ ቁጥራችን ቢበዛም ከቁጥር የማንገባ ለዘብተኞች ነን። የአቅጣጫ መቆጣጠሪያ እንደሌለው ጀልባ፣ የነፋስ መጫወቻ ነን! ከነፈሰው ጋር መሄድ ብቻ! አንዱን አስተሳሰብ የመመከት ወይም ሌላኛውን አስተሳሰብ የማራመድ አቅም የለንም። ከነፈሰው ጋር እንደገለባ እየተበጠርንና እየተላጋን ለመንጐድ ከፈለግን፤ ለዘብተኛ መሆን “ትክክለኛ” ምርጫ ነው፡፡ በአክራሪነት ማዕበል ተጠራርገን እንዳንሄድ ከፈለግን ግን፣ ለዘብተኛነት አያዋጣም፡፡ የጠራ የነጠረ የሳይንስ አፍቃሪ መሆን ይኖርብናል፡፡

Read 5532 times