Saturday, 24 August 2013 10:22

33ቱ ፓርቲዎች የጋራ ህዝባዊ ስብሰባ ነገ ያካሂዳሉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(13 votes)

“ፍርሃትን፣ ሙስናን፣ አፈናን፣ አምባገነንነትን በጋራ በቃ ካልን፣ ያበቃል”
ለአገሪቱ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጥምረት ኮሚቴ አደራጅተው እየሰሩ መሆናቸውን የገለፁት የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ አስራት ጣሴ፤ ፓርቲዎቹ ነገ በመኢአድ ጽሕፈት ቤት “በቃ እንበል” የተሰኘ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያካሄዱ አስታወቁ፡፡
ለህዝባዊ ስብሰባው “በቃ እንበል” የሚል መሪ ቃል ለምን እንደተመረጠ አቶ አስራት ሲያስረዱ፣ ህዝቡ የአገሪቱን ችግሮች የማስቆምና የማስወገድ አቅም እንዳለው የሚያሳይ አባባል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ ምን ቢያደርግ ችግሮችን መፍታት እንደሚችል መወያየትና መላ ማበጀት የስብሰባው አላማ እንደሆነ አቶ አስራት ጠቅሰው፤ ችግሮችን ለማስወገድ “በቃ እንበል” የሚል አቋም እንደያዙ ተናግረዋል፡፡
ገዢዎቻችን ፍርሃት ይፈጥሩብናል፤ ነገር ግን በጋራ “በቃ” ካልን ያበቃል፤ እናም በሰላማዊ ትግል የመብታችን ባለቤት እንሆናለን ብለዋል-አቶ አስራት፡፡ ሙስናን በጋራ በቃ ካልን፣ ሙስና አብቅቶ ጤናማ የስራና የንግድ ውድድር ይፈጠራል በማለትም ስብሰባው የአገሪቱ ዋና ዋና ችግሮችን እንደሚዳስስ አስረድተዋል፡፡
ኢፍትሃዊነትንና ውርደትን በጋራ በቃ ካልን ያበቃል፤ ፍትህ ከመንበሯ ላይ ተቀምጣም ክብራችን ይመለሳል ያሉት አቶ አስራት፤ በእምነት ነፃነት ላይ ጣልቃ መግባትንና በሽብር ስም በሀሰት መወንጀልን በቃ ካልን ያበቃል፤ መብታችን ይከበራል፤ እንደየእምነታችንም በነጻ እናመልካለን ብለዋል፡፡ በጥምረት እየሰሩ ያሉት 33ቱ ፓርቲዎች በጋራ የሚሰሩት ይህን አቋም በመያዝ እንደሆነም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ የገዢውን ፓርቲ የዘረኝነት፣ የመከፋፈልና የማጋጨት ፖሊሲ በቃ ካልን ያበቃል፣ በምትኩም ትብብር ይነግሳል ሲሉ የፓርቲዎቹን አቋም የገለፁት አቶ አስራት፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አጃቢ ማድረግ በቃ ካልን ያበቃል፤ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እውን ይሆናል ብለዋል፡፡ ነፃ ፕሬስ አፈናንና እስርን በጋራ በቃ ካልን፤ በነፃነት እንነጋገራለን፤ አማራጭ የመረጃ ምንጮችን ከእጃችን እናስገባለን ካሉ በኋላ፣ እሁድ እለት ከህዝቡ ጋር በአንድነት “በቃ” የምንልበትን ቀጠሮ ይዘናል ብለዋል፡፡ እነዚህ ሃሳቦች ተግባራዊ ከሆኑ፤ ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም በእኩልነት የሚተዳደሩባትን ሀገር መፍጠር እንችላለን ያሉት አቶ አስራት፤ ዝግጅቱ ላይ ከ1500 በላይ ሰው እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ስብሰባው በፓርቲ ፅ/ቤት ለማድረግ የተወሰነው ፍቃድ ጠይቁ በሚል ሰበብ እንዳይስተጓጎልብን ነው ብለዋል፡፡

Read 37296 times