Saturday, 17 August 2013 12:40

“ድሉን ከቤተሰቤ እና ከወገኖቼ ጋር አከብረዋለሁ”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሀመድ አማን፤ የ800 ሜትር ውድድሩን በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃት አጠናቆ የወርቅ ሜዳልያውን ከወሰደ በኋላ፣ መደበኛው ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥበትን አዳራሽ ያጣበብነው አምስት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና የብሄራዊ ቡድኑ ሃኪም ዶክተር አያሌው ነበርን፡፡ ውድድሩ ተጠናቅቆ ከምሽቱ ለአምስት ሰዓት ምናምን ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በመሃመድ ታሪካዊ ድል ደስታችን ልክ አልነበረውም፡፡

በፕሬስ ኮንፍረንሱ አዳራሽ የተገኘነው ከየትኛውም አገር ጋዜጠኞች ቀድመን ነበር፡፡ መሃመድ አማን በ800 ሜትር ያስመዘገበው የወርቅ ሜዳልያ፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈርቀዳጅ ታሪክ መሆኑን፤ በሻምፒዮናው ታሪክ በ20 ዓመቱ የርቀቱን የወርቅ ሜዳልያ ለመውሰድ የበቃ ድንቅ አትሌት እንደሆነ ጋዜጠኞች ስንነጋገር፣ ዶክተር አያሌው መሃከል ገቡና፣ መሃመድ ለ800 ሜትር እና ለአጭር ርቀት ውድድር የተፈጠረ ምርጥ አትሌት መሆኑን በመጠቆም፣ በስፖርቱ ውጤታማ ለመሆን ባለው የስራ ፍቅርና ትጋት እንደሚያደንቁት ገለፁልን ፡፡ ውይይታችን በስፍራው የነበሩ የሌላ አገር ጋዜጠኞች እና የስፖርት ባለሙያዎችን ትኩረትም ስቦ ነበር፡፡
በፕሬስ ኮንፍረንሱ አዳራሽ ከመሃመድ አማን በፊት መግለጫ የሚሰጡ የሌላ ውድድር አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ የዲስከስ ውርወራ እና የሄፕታትሎን ተወዳዳሪ የነበሩ ናቸው፡፡

የሁለቱ ስፖርቶች አሸናፊዎች መግለጫዎች ሲሰጡ ኢትዮጵያውያኑ ባይተዋር ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ ለነገሩ በረጅም ርቀት እንጂ በ800 ሜትር ኢትዮጵያዊ አትሌት አሸንፎ ለጋዜጣዊ መግለጫ እንበቃለን ብለን አስበንም አልመንም አናውቅም፡፡ የወንዶች ዲስከስ ውርወራ አሸናፊዎች እና የሴቶች ሄፕታተሎን ውድድር ሜዳልያ ተሸላሚዎች መግለጫ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ተራው የእነ መሃመድ አማን ሆነ፡፡ ወደመግለጫው የገቡት የወርቅ ሜዳልያውን የወሰደው መሃመድ አማን፤ የብር እና የነሐስ ሜዳልያውን የወሰዱት የአሜሪካ አትሌቶች ነበሩ፡፡ መሃመድ አማን የወርቅ ሜዳልያውን ያስመዘገበው የሉዝንስኪ ስታድዬም በምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳዳሪዋ ራሽያዊት ዬለና ኢዝንባዬቫ ምክንያት ጥቅጥቅ ብሎ በሞላበት ወቅት ነበር፡፡

መሃመድ አማን በ800 ሜትር ያሸነፈው በጣም ጠንካራ አትሌቶች በተሳተፉበት የ800 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ሲሆን ርቀቱን የሸፈነበት 1ደቂቃ ከ43.31 ሰኮንዶች የውድድር ዘመኑ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ መሃመድ አማን በ5ሺ፤በ10ሺ እና በማራቶን ውድድሮች ስኬታማ አትሌቶች ከበዙባት ኢትዮጵያ መውጣቱ እያነጋገረ ሲሆን ከአጭር ርቀት ሯጭነት ወደ መካከለኛ ርቀት ምርጥ አትሌትነት መሻገሩም ያልተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡
ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ መሃመድ አማን መግለጫውን የሰጠው በእንግሊዘኛ መሆኑ ነው፡፡ ይሄም ሌላ ያልተጠበቀ ነገር ሆኗል፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በአስተርጓሚ ነበር ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡት፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታውን ፊልሞች በመመልከት እና በማንበብ ነው ያዳበረው፡፡ ለመሃመድ የቀረበለት የመጀመርያው ጥያቄ ከመግለጫው መሪ የአይኤኤኤፍ ጋዜጠኛ ነበር፡፡
“መሃመድ ውድድሩ አስቸጋሪ ነበር፤ በሩጫው መሃል ወደ ኋላ ቀርተህ ከዚያ በኋላ ነው አፈትልከህ የወጣኸው፡፡ ስትራቴጂው ምን ነበር?” ሲል ጠየቀው፡፡
“የፍፃሜ ውድድር ነው፡፡ ስለዚህም ለማሸነፍ የተከተልኩት ስትራቴጂ ተገቢ ነው፡፡ በፍፃሜ ውድድር የሚሳተፉት ሁሉም አትሌቶች ምርጥ ብቃት እንዳላቸውና የማሸነፍ እድል እንደሚኖራቸው ግምቱ ነበረኝ፡፡ እስከመጨረሻዎቹ ሜትሮች ሁኔታውን እያጠናሁ በትዕግስት ተጠባብቄያለሁ፡፡ ከዚያም በአስፈላጊው ጊዜ አፈትልኬ ወጥቻለሁ፡፡›› በማለት መሃመድ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ቀጣዩ ጥያቄ ከፕሬስ ኮንፍረንሱ የመድረክ መሪ የቀረበ ሲሆን ያሸንፋል የሚል ግምት ለተሰጠው አሜሪካዊው ኒክ ሳይመንድስ እና ለነሐስ ሜዳልያው ባለድል የጅቡቲ አትሌት ነበር፡፡ “ኒክ ሳይመንድስ” በብር ሜዳልያው መወሰንህ ምን ስሜት ፈጠረብህ?” ተብሎ ለተጠየቀው ሲመልስ፤
‹‹በብር ሜዳልያው በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ውድድሩ ሜትር እስኪቀረው ቀጣዩ የዓለም ሻምፒዮን መሆኔን እያሰብኩ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ባገኘሁት የብር ሜዳሊያ ብዙም አልተከፋሁም›› ያለ ሲሆን የነሐስ ሜዳልያ ባለቤቱ ጅቡቲያዊ በበኩሉ፤ ‹‹ደስተኛ ነኝ፤ ለአገሬ የተገኘ ብቸኛ እና የመጀመርያው ሜዳልያ ነው፡፡ ውጤቱ በጠንካራ ፉክክር የተገኘ በመሆኑም አኩርቶኛል›› በማለት መልሷል፡፡
ለመሃመድ አማን “በአገርህ ለወርቅ ሜዳልያ መጠበቅህ የፈጠረብህ ጫና ነበር ወይ” የሚል ጥያቄ ከኢንተር ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና የአትሌቲክስ ዘጋቢ ብዙአየሁ ዋጋው ቀርቦለት ነበር፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት እና በማራቶን ውድድሮች ውጤታማ በሆኑ በርካታ አትሌቶቿ ትታወቅ ነበር፡፡ እኔ በአጭር ርቀት ውጤታማ በመሆኔ ብዙ ጫና አልነበረብኝም፡፡ እንዴት እንደሆነ አላውቀውም፡፡ ከፍተኛ በራስ የመተማመን ስሜት አለኝ፡፡ አራት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን ማሸነፍ መቻሌ በጣም ልበ ሙሉ አድርጎኛል፡፡ የዓለም ሻምፒዮና ጠንካራ ፉክክር ያለበት ነው፡፡ በጥንቃቄ መሮጥ ያስፈልግ ነበር፡፡
ስለውድድሩ ላለመጨነቅ ስል ብዙ ሃሳብ ውስጥ አልገባሁም፡፡ ለጥ ብዬ እንቅልፌን ተኛሁ፡፡ አሰልጣኜ ስልክ ደውሎ ምን እየሰራህ ነው አለኝ፡፡ ስለ ውድድሩ ከማሰብ ጥሩ እረፍት እንደሚያስፈልገኝ አምኜበት መተኛቴን ነገርኩት” በማለት ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የኢቴቪ ስፖርት ጋዜጠኛ እና የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዮናስ ተሾመ በበኩሉ፤ “ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ አዲስ ታሪክ ሰርተሃል፡፡ በአጭር ርቀት በአለም ሻምፒዮና የተመዘገበ ብቸኛ ድል ነው፡፡ ምን ተሰማህ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦለታል፤ ለአትሌቱ፡፡
መሃመድ ሲመልስም፤ ‹‹ምንም የማይቻል ነገር የለም፡፡ ድል እንደማደርግ እምነት ነበረኝ፡፡ ያስመዘገብኩት ውጤት ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት የመጀመርያው በመሆኔም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ልምምዴን የምሰራው በኢትዮጵያ ነው፡፡ በእንጦጦ፣ በሰንዳፋና በአዲስ አበባ ዙርያ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ በርካታ የብሄራዊ ቡድን አትሌቶች ጋር ነው የምሰራው፤ አሰልጣኜም ኢትዮጵያዊ ንጉሴ ጌቻሞ ነው፡፡ ›› በማለት አስረድቷል፡፡
እኔ ደግሞ እንዲህ ስል ጠየቅሁት፤ “በ800 ሜትር የዓለም ሪከርድ የያዘው፤ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነው ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ ቢኖር የወርቅ ሜዳልያው እድል የጠበበ ይሆን ነበር ብለህ አላሰብክም?”
‹‹በመጀመርያ እኔ ልምምድ ስሰራ የቆየሁት ለዴቪድ ሩዲሻ ብቻ አልነበረም፤ሩዲሻ ባለመኖሩ አዝኛለሁ፡፡ ጉዳት ለብዙ አትሌቶች ፈተና እየሆነ ነው፡፡ እሱ ባይኖር እንኳን ለፍፃሜ የደረሱት ሌሎቹ ሰባት አትሌቶች እጅግ ጠንካሮች ነበሩ፡፡ እነሱን በማሸነፌ ውጤቴን አስደሳች አድርጎታል፡፡› ሲል መለሰልኝ፡፡
በመጨረሻም ወደ አገሩ ሲመለስ ደስታውን እንዴት እንደሚያከብር ነበር የተጠየቀው፡፡ አማን ወደ ትውልድ ቀዬው አሰላ ለመሄድ የሚፈልገው በመስከረም ወር ዋዜማ በብራሰልስ ከሚያደርገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በኋላ ነው፡፡ ከብራሰልስ በኋላ በቀጥታ ወደ እናቱ ቤት ለመሄድ እቅድ ይዟል፡፡ ቤተሰቡ በዳጉ የዓለም ሻምፒዮና እና በለንዶን ኦሎምፒክ ሲሮጥ ተመልክተውታል፡፡ በሁለቱም ውድድሮች እንዲያሸንፍ ጠብቀው አልተሳካለትም፡፡ አሁን ግን የልባቸውን አድርሶላቸዋል፡፡ የቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያንን፡፡ ከብራሰልስ መልስ የዓለም ሻምፒዮና ድሉን ከወላጆቹ እና ከመላው ቤተሰቡ ጋር በፌሽታ እንደሚያከብር አማን በፈገግታ ተሞልቶ ገልፆልናል፡፡ አንድ ፌሽታ ሳይሆን ሺ ፌሽታ ይገባዋል፡፡

Read 4606 times