Saturday, 17 August 2013 12:36

“በሚቀጥለው ዓመት በእርግጠኝነት ማራቶን እሮጣለሁ”

Written by  ግሩም ሠይፉ (ከሞስኮ)
Rate this item
(5 votes)

­አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ባለፈው እሁድ በሞስኮ 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በ10ሺ ሜትር ውድድር የወርቅ ሜዳልያ ካጠለቀች በኋላ፣ በሉዝንስኪ ስታዲየም የልምምድ ስፍራ አካባቢ ባለው መናፈሻ ያደረግነው አጭር ቃለምልልስ እነሆ፡-

በዓለም ሻምፒዮናው ስንተኛው የወርቅ ሜዳልያሽ ነው? (በእጇ የያዘችውን የወርቅ ሜዳልያ እየተመለከትኩ)
አምስተኛው ነው፡፡
በሁሉም ርቀት ማለትሽ ነው? ማለቴ… በ10ሺም በ5ሺም፡፡ በ10ሺ 3ኛሽ ነው አይደለም?
አዎ
ከሳምንት በፊት ሞስኮ ስንገባ፣ በዴሜዶቮ አየር ማረፊያ “ሞስኮ ላይ ስንተኛው ወርቅሽ ነው?” ስልሽ እንዲሁ አምስተኛው ብለሽኝ ነበር፡፡
(ሳቅ) አምስተኛ አልኩ እንዴ፤ ለአምስተኛ ጊዜ ነው የምሮጠው ማለቴ ነው
ያው ነው ብዙም ልዩነት የለውም፡፡ ግን ከውድድሩ በፊት የተበላ ወርቅ አደረግሽው፡፡ ለመሆኑ ከትልልቅ ውድድር በፊት እንደምታሸንፊ ሁሌም እርግጠኛ ነሽ እንዴ?
ህመም ካላጋጠመኝ በስተቀር አዎ፡፡
በዓለም ሻምፒዮና እስከ ዛሬ ካገኘሻቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ያስደሰተሽ የትኛው ነው?
በ2007 እ.ኤ.አ በኦሳካው የዓለም ሻምፒዮና ያገኘሁት ነው፡፡ በወቅቱ ታምሜ ብዙ ርቀት ከለቀቅኩኝ በኋላ ያገኘሁት የወርቅ ሜዳልያ ድል በመሆኑ በጣም ያስደስተኛል፡፡ ያኔ በውድድሩ ወቅት ሆዴን አሞኝ ነበር፡፡ እየሮጥኩኝ ልክ አምስት ዙር ካጠናቀቅሁ በኋላ ነው የጀመረኝ፡፡ ውድድሩ ሰባት ዙር ሲቀረው ህመሙ ለቀቀኝ፡፡ ሌሎች አትሌቶች ጥለውኝ ከሄዱ በኋላ ደርሼባቸው ውድድሩን በማሸነፌ ልዩ ደስታ ነበር የተሰማኝ፡፡
በሞስኮው ሉዝንስኪ ስታድዬም በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያውን ለመውሰድ የመጨረሻውን ዙር ስትከንፊ ፊትሽ ገፅታ ላይ ልዩ ደስታ ይነበብ ነበር፡፡ ምንድነው ነገሩ?
ወርቁን እንደማገኝ እርግጠኝነት ተሰምቶኝ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አንቺ በምታስመዘግቢው ውጤት ሁሌም ከመጠን በላይ ይፈነድቃል፡፡ አንቺስ ምንድነው የሚሰማሽ?
ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሌም በድጋፍ ከእኛው ጋር ናቸው፡፡ እናም የምሮጠው የህዝቡን ደስታ እያሰብኩ ነው፡፡ እንደዚያ በመሆኑም ሁሌም ከፍተኛ ሞራልና ክብር ነው የሚሰማኝ፡፡
የ10ሺ ሜትር ንግስት ነሽ ማለት አይቻልም?
እንግዲህ እኔ አላውቅም፡፡ እንደዚህ ነኝ ማለት አልችልም፡፡
በ10ሺ ሜትር በጥሩ ሁኔታ ሮጠሽ የወርቅ ሜዳልያውን ከወሰድሽ በኋላ ብዙ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በ5ሺም መድገም አለባት እያሉ ነው፡፡ አንቺ ምን ትያለሽ?
እንግዲህ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ በሁለቱም ርቀቶች ደርቤ የመወዳደር ልማዱ ነበረኝ፡፡ ውጤታማም ሆኛለሁ፡፡ ዘንድሮ በ10ሺ ሜትር ብቻ በመወሰኔ የሮጥኩም አልመሰለኝ፡፡ ማጣርያ አድርጌ ገና የፍፃሜ ውድድር ቀርቶኛል ብዬ ነው ሳስብ የነበረው፡፡ ሁለቱንም ርቀቶች መሮጥ ስለለመድኩ ነው፡፡ ፌደሬሽኑ በጠየቀኝ መሰረት፤ ለአዳዲስ አትሌቶች እድል ለመስጠት የሚለውን ሃሳብ ተቀብዬ ነው ላለመወዳደር የወሰንኩት፡፡
በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ ያገኘሻቸው ሜዳልያዎች ስብስብ እኮ ከምርጦቹ ወንድ አትሌቶች ጋር እየተስተካከለ ነው፡፡ በሁለቱ ርቀቶች በኦሎምፒክ ኃይሌን በልጠሽዋል፡፡ ከቀነኒሳም ተስተካክለሻል፡፡ በ10ሺ ግን በአንድ የዓለም ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳልያ ማግኘት ይኖርብሻል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በቤጂንግ ይደረጋል፡፡ ያኔ ምን እንጠብቅ?
በዓለም ሻምፒዮና የሜዳልያ ስብስብ በ5ሺ ሜትር ሁለቱንም እበልጣለሁ፡፡ በ10ሺ አንድ ሜዳልያ ይቀርሻል ያልከው ልክ ነህ፡፡ እንግዲህ የዛሬ ሁለት ዓመት እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው፡፡
በአትሌቲክስ ስፖርት በረጅም ርቀት ውድድሮች ከፍተኛ ስኬት ካላቸው የዓለም ሴት አትሌቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆነሻል፡፡ ለመሆኑ በስፖርቱ ያገኘሽው ስኬትና ክብር ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥርብሻል?
በአትሌቲክሱ የተቀዳጀኋቸው ውጤቶች እና ክብሮች በአገሬ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስገኙልኝ ክብር እና ዝና ከፍተኛ ደስታ አጐናፅፎኛል፡፡ ድሮ በአገር ቤት ነበርኩ፡፡ ከትንሽ የገጠር ከተማ ነው የወጣሁት፡፡ እዚህ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሼ ይህን ክብር በማየቴ እና በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ወደ ማራቶን እገባለሁ የምትይው ነገር ከምር ነው?
በሚቀጥለው ዓመት በእርግጠኝነት ማራቶን እሮጣለሁ፡፡ ግን ሙሉ በሙሉ ወደ ማራቶን አልሄድም፡፡ በዓመት ውስጥ አንድ ማራቶን ብቻ ነው ለመሮጥ የወሰንኩት፡፡

ከበቆጂ ከተማ እስከ የዓለም ማማ
ከ10 ዓመት በፊት ጥሩነሽ ዲባባ በ18 ዓመቷ በዓለም ሻምፒዮና ተሳትፋ ፓሪስ ላይ የመጀመርያ የወርቅ ሜዳልያዋን ስትወስድ በአገሯ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ገና ዝነኛ መሆን መጀመሯ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የጥሩነሽ ዝና በዓለማችን ታላላቅ ከተሞች እየገነነ የመጣው፡፡ በሄልሲንኪ፣ ኦሳካ ፣ ቤጂንግ፣ አቴንስ፣ ለንደን፣ ሉዛን፣ ኤደንብራ፣ ፉካካ፣ ደብሊን፣ ብሩክሰልስ፣ ቦስተን፣ ኦስሎና ሌሎች የዓለማችን ግዙፍ ከተሞች የጥሩነሽን አስደናቂ የሩጫ ገድሎች በየተራ አስተናግደዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ከተጎናፀፈች በኋላ የጥሩነሽ ዲባባ ስምና ክብር በሞስኮ ደምቋል፡፡ ከሳምንት በፊት በተደረገው የ10ሺሜትር የፍፃሜ ውድድር በሞስኮው ሉዚንስኪ ስታድዬም የተገኙ ስፖርት አፍቃሪዎች፣ ጥሩነሽ ዲባባ ካሸነፈች በኋላ ከመቀመጫቸው ተነስተው በደስታ አጨብጭበውላታል፡፡ የወርቅ ሜዳልያዋን ባለፈው ሰኞ ከተረከበች በኋላም በሞስኮው ሉዝንስኪ ስታድዬም ዙርያ በርካታ የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪዎች እና ጀግና ወዳዶች አብረዋት ፎቶ ለመነሳት ሲሻሙ እና ሲጋፉ በአይኑ ለተመለከተ ሰው፣ ጥሩነሽ ዲባባ ምን ያህል ዓለም አቀፍ ጀግና እንደሆነች ለመገንዘብ አያዳግተውም፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አትሌቷን አሞጋግሰዋታል፡፡
ዲባባ በትእግስቷ ድል አደረገች ብሏል ሮይተርስ በዘገባው፡፡ ቢቢሲ በበኩሉ፤ ንግስቲቱ ዲባባ ለ5ኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ሆነች ሲል፤ ዴይሊ ኒውስ፤ ዲባባ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮና ሃትሪክ መስራቷን፤ ራነርስ ዎርልድ፤ በረጅም ርቀት በበላይነት መቀጠሏን፣ ሌትስራን ደግሞ፤ በ10ሺ ሜትር ተሸንፋ እንደማታውቅ፣ በመግለፅ በአድናቆት ዘግበዋል፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ፤ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ከተጎናፀፈች በኋላ በረጅም ርቀት “የምንግዜም ምርጥ አትሌት” መሆኗ በከፍተኛ ሁኔታ ጎልቶ ተስተጋብቷል፡፡ በ10ሺ ሜትር በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ የተጎናፀፈቻቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ብዛት 5 በመድረሱ ብቸኛዋ አትሌት ለመሆን የበቃች ሲሆን ይህን ክብረወሰን ሊጋራት የሚችለው ብቸኛው አትሌት ጃማይካዊው ዩሴያን ቦልት ሆኗል፡፡
በዓለም ሻምፒዮና በ10ሺሜትር ብቻ የወሰደቻቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ብዛት 3 የደረሱ ሲሆን ከታዋቂ አትሌቶቹ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ በአንድ የወርቅ ሜዳልያ ነው የምታንሰው፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር እያንዳንዳቸው አራት አራት የወርቅ ሜዳልያዎች ማግኘታቸው ይታወቃል፡፡ በጉዳት ሳቢያ በ2009 እ.ኤ.አ በርሊን ላይ እና በ2011 ዳጉ ላይ በተደረጉ የዓለም ሻምፒዮናዎች ባለመሳተፏ እንጂ ኃይሌንና ቀነኒሳን ጥላ ታልፍ ነበር፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር ትላልቅ ውድድሮች ከኃይሌ እና ከቀነኒሳ ጋር እኩል ለመሆንና ለመብለጥ የቀራት የአንድ የዓለም ሻምፒዮና ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺሜትር የትራክ ውድድርና በጎዳና ላይ ሩጫ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ይዛ የምትገኝ አትሌት ስትሆን በ5ሺ ሜትር ውድድር 2ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ በሩጫ ዘመኗ በ10ሺ ሜትር ተሸንፋ አታውቅም፡፡ አስራ አንድ ውድድሮች አድርጋ አስራ አንዱንም አሸንፋለች፡፡ 3ቱ የዓለም ሻምፒዮን ሲሆን 2ቱ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ናቸው፡፡
ኃይሌ፣ ቀነኒሳና ጥሩነሽ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች
በዓለም ሻምፒዮና በ10ሺ
ኃይሌ 4 የወርቅ፤ 1 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች
ቀነኒሳ 4 የወርቅ ሜዳልያዎች
ጥሩነሽ 3 የወርቅ ሜዳልያዎች
በ5ሺ
ጥሩነሽ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች
ቀነኒሳ 1 የወርቅ እና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች
ኃይሌ 1 የብር ሜዳልያ
በኦሎምፒክ በ10ሺ
ኃይሌ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች
ቀነኒሳ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች
ጥሩነሽ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች
በ5ሺ
ጥሩነሽ 1 የወርቅና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች
ቀነኒሳ 1 የወርቅ እና 1 ብር ሜዳልያዎች
ኃይሌ 0 ሜዳልያ

Read 3260 times