Saturday, 17 August 2013 12:03

ለሙያቸው ያላደሩ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

የህክምና ባለሙያዎች
የአልትራሳውንድና ላብራቶሪ ምርመራ ለወጪ መሸፈኝያ
የህክምና ሙያ ከሌሎች ሙያዎች ሁሉ እጅግ የከበረና የሰውን ልጅ ክቡር ህይወት ለመታደግ የሚያስችል ሙያ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎቹ ለዚህ እጅግ ለተከበረ ሙያቸው ታማኝ በመሆን ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር አክብረው ህብረተሰቡን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ሙያዊ ሥነ ምግባር ጠብቀው በሙያቸውና በዕውቀታቸው ወገኖቻቸውን በመርዳት ተግባር ላይ የተጉ ጥቂት የማይባሉ ሐኪሞች በየሥፍራው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሞያቸውን ለገንዘብ ሸጠው ዓላማቸው ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ሆኖ፣ በተለያዩ የጤና ችግሮች ተይዞ ፈውስ ፍለጋ እነሱ ያሉበት ሥፍራ፣ ደጅ የሚጠናውን ህብረተሰብ ማጉላላትና አግባብ ላልሆኑ ወጪዎች መዳረግ የአንዳንድ ህሊና ቢስ ሐኪሞች ተግባር ነው፡፡
በጤና ተቋማት ውስጥ የሚፈፀሙና የጤና ባለሙያዎች የሥነ ምግባር ጉድለት መገለጫ ናቸው ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱን ዛሬ በዚህች አጠር ያለች ፅሁፍ ለመዳሰስ ወደድኩ፡፡ ጉዳዩ በተለይ በግል የጤና ተቋማት ውስጥ በስፋት የሚታየው ህሙማንን አላስፈላጊ ለሆኑ ወጪዎች መዳረግ ነው፡፡ ይሄንንም የሚያደርጉት ለህሙማን ከአስፈላጊው በላይ ምርመራዎችን በማዘዝና በርካታ ገንዘብ እንዲከፍሉ በማድረግ ነው፡፡
በመሠረቱ ለህሙማን የሚደረጉ የጤና ምርመራዎችን አይነትና ምንነት መወሰን የሚችለው የጤና ባለሙያው ብቻ ነው፡፡ ታማሚው ለምርመራ ወደ ጤና ተቋማት ሲሄድ በሽታው በተለያዩ የምርመራ አይነቶች ታውቆለት ለፈውስ የሚሆን መድሃኒት ወይም ህክምናን አገኛለሁ በሚል ተስፋ ነው፡፡ የጤና ባለሙያው ደግሞ ታማሚሙ ስለገጠመው የጤና ችግር ማወቅ የሚችለው በተለያዩ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ድጋፍ በሚደረጉ ልዩ ልዩ ምርመራዎች ነው፡፡ ሐኪሙ ለበሽተኛው መድሃኒቱን የሚያዘውም በእነዚህ የምርመራ ውጤቶች ላይ ተመርኩዞ መሆኑ አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አሠራር በአንዳንድ ዓላማቸው ከህሙማን ላይ ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ በሆነ ህሊናቢስ የጤና ተቋማት ባለቤቶች ዘንድ በተሣሣተ መንገድ ሥራ ላይ ሲውል ማየቱ የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ለዚህ ፅሁፌ ግብአት የሚሆኑኝን መረጃዎች ለማሰባሰብ በከተማችን ያሉ ስመጥር የግል ሆስፒታሎችንና ክሊኒኮችን በወፍ በረር ቅኝት ተዟዙሬ አይቼአቸው ነበር፡፡ በሆስፒታሎቹ ተቀጥረው የሚሰሩትን የጤና ባለሙያዎች (ዶክተሮች፣ ነርሶችና የላብራቶሪ ባለሙያዎች) ለማነጋገር ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ የጤና ተቋማቱ ሠራተኞች እነሱ ተቀጥረው በሚሰሩበት ሆስፒታል ውስጥ የሚከናወነውን ከሙያው ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ተግባር አውጥተው መናገር አይፈልጉም፡፡ ህክምናውን ለማግኘት ወደ ሆስፒታላቸው የሚመጣው ሰው የሚጠየቀውን ገንዘብ ለማውጣት እስከቻለ ድረስ፣ “ግድ አይሰጠንም፤እሱ ለከፈለው እኛ ምን አገባን” ባይ ናቸው፡፡
የህክምና ሙያ ሥነ ምግባር ጉድለቶች በሙያው ውስጥ ያሉ ሰዎች ሰብዕናን፣ ስለ ሰው ልጆች ያላቸውን አመለካከትና ለሰው ልጆች ያላቸውን ክብር የሚያንፀባርቁ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በህክምና ሙያ ውስጥ ያለ ሰው ክቡር ከሆነው የሰው ልጅ ህይወት ይልቅ ገንዘብን የሚያስቀድም ከሆነ ጭንቀቱ ከታካሚው ስለሚገኘው የገንዘብ መጠን እንጂ ለታካሚው ስለሚደረገው የህክምናና እርዳታ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህ ጉዳይ እንደማሳያ ልጥቀስ፡፡ ሥፍራው እዚሁ አዲስ አበባ አውቶቢስ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ የሠላሣ ሁለት ዓመት ዕድሜ ያላት ወ/ሮ፤ በአንገቷ ላይ ያለውን እንቅርት ለማስወጣት ወደ ሆስፒታሉ ታመራለች፡፡ ሐኪሙ የታካሚዋን ስሜትና ሁኔታዋን እየጠየቁ በካርዷ ላይ ሲሞሉ ከቆዩና ምርመራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ ችግሩ በቀላል ቀዶ ጥገና ሊወገድላት እንደሚችል ነገሯት፡፡ ታካሚዋ በተነገራት እጅግ ተደሰተች፡፡ በሐኪሟ ትእዛዝ መሠረትም ለቀዶ ጥገናው ህክምና ዝግጁ ሆና ትጠባበቅ ጀመር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን የሆስፒታሉን ባለቤት እጅግ አበሳጫቸው፣ ህክምናውን ወደ አደረጉላት ዶክተር ዘንድ በመሄድ “ምን እየተደረገ እንደሆነ አስረዳኝ?” ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ዶክተሩ ግራ ተጋቡ፡፡ “ምን እየተደረገ ነው?” መልሰው ጠየቋቸው፡፡ “ከደቂቃዎች በፊት ለመረመርካት ታካሚ እንዴት የአልትራሳውንድና የላብራቶሪ ምርመራ ሣታዝላት ቀረህ?” አሏቸው፡፡
ዶክተሩ ምርመራው አስፈላጊ እንዳልነበረና ህመምተኛዋ የሚያስፈልጋት ቀላል ቀዶ ህክምና ብቻ መሆኑን ገለፁላቸው፡፡ ይህ ምላሽ ግን የሆስፒታሉ ባለቤት በሆኑት ዶክተር ዘንድ ፈፅሞ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ “ታዲያ ይህ ሁሉ ወጪ በምን ሊሸፈን ነው? አንተ ተረኛ በሆንክ ጊዜ ላብራቶሪውና አልትራሳውንድ ክፍሉ ሥራ ፈቶ ይውላል፡፡ እንደ ሌሎቹ ዶክተሮች ሁሉን ነገር ቶሎ ቶሎ እዘዝ እንጂ” ማሳሰቢያውን ነግረዋቸው ሄዱ፡፡ “ምን ብዬ እንደምመልስለት ሁሉ ጠፋኝ፣ወደ ህክምና ሙያ ስገባ ህመምተኛዬን ልንከባከብ፣ ሚስጢሩን ልጠብቅለት፣ ያለ አግባብ ላላጉላላው የገባሁት ቃል ሁሉ ገደል ሲገባ ታየኝ፡፡ ከዚህ ሰውዬ ጋር አብሬ መዝለቅ እንደማልችል በመረዳቴም ሥራዬን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ የሚገርምሽ ነገር ግን ይህ ሁኔታ በሌሎችም የግል ጤና ተቋማት ውስጥ የገጠመኝ መሆኑ ነው፡፡”
ይሄን ያጫወቱኝ ዶክተር ታረቀኝ ሀብታሙ የተባሉ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ማሳያ ይሆናል ያልኩት ሌላ ታሪክ የተፈፀመው ከጥቂት ዓመታት በፊት በኮሪያ ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡ አንድ የከባድ መኪና መካኒክ፣ በሥራ ላይ እያለ የጭነት መኪናው ጋቢን ድንገት እላዩ ላይ ይወድቅበታል፡፡ አደጋው እጅግ ዘግናኝና አሳዛኝ ነበር፡፡ ሆኖም የሰውየው ነፍስ አልወጣችም፡፡ እንደምንም አንስተው ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ይዘውት በረሩ፡፡ ከሆስፒታሉ ሲደርስ ትንፋሹ ያለ አይመስልም ነበር፡፡
በአስቸኳይ ወደ ኦፕሬሽን ክፍል እንዲገባ ታዘዘ፡፡ የቤተሰቦቹ ሃሳብ በሁለት ተከፍሏል፣ ገሚሱ ተስፋ እንደሌለው በመገመት ወደ ቤት ይዘውት ለመሄድ ሃሳብ ሲያቀርቡ፣ ገሚሶቹ ደግሞ የእግዚአብሔር ነገር ምን ይታወቃል ይሞከር አሉና ወደ ቀዶ ጥገናው ክፍል እንዲገባ ፈቀዱ፡፡ ቅድሚያ 10ሺህ ብር እንዲያሲዙ ተጠይቀው አስያዙ፡፡ ሰዓታት ነጐዱ፣ ሰውየው ግን ከቀዶ ጥገናው ክፍል አልወጣም፡፡ ከበድ ያለ የቀዶ ህክምና እየተደረገለት እንደሆነ የጠረጠሩት ቤተሰቦቹ፣ እዛው ሆስፒታሉ ውስጥ ሲንቆራጠጡ ቆዩ፡፡ ከሰዓታት በኋላ ሰውየውን ማዳን እንዳልቻሉና ህይወቱ እንዳለፈች ተነገራቸው፡፡ ሁኔታው እጅግ አሳዘናቸው፡፡ አስከሬኑን ለማውጣትና የከፈሉትን ገንዘብ ለማስመለስ ጥያቄ ያቀረቡት የሟች ቤተሰቦች፣ ካስያዙት ገንዘብ ተመላሽ የተደረገላቸዉ ከአንድ ሺህ ብር የማይበልጥ ገንዘብ ነበር፡፡ አገር ይያዝ አሉ- ቤተሰቦች፡፡
“አስከሬኑንም አናወጣም፣ ከሃላፊዎች ጋር እንነጋገራለን” አሉ፡፡ ትችላላችሁ ተባሉ፡፡ ጊዜው መሸ፡፡ ኃላፊዎቹን አነጋግረው አስከሬኑን ጠዋት ለማውጣት ይወስኑና ይሄዳሉ፡፡ በማግስቱ ኃላፊ ከተባሉት ሰዎች ጋር ቢነጋገሩም ምንም መፍትሔ አልተገኘም፡፡ ጭራሽ አስከሬኑን ሲረከቡ ለተጨማሪ አንድ ቀን በሆስፒታሉ ላደረበት 300 ብር እንዲከፍሉ ተደረጉ፡፡
ሌላው ገጠመኝ በቤቴል ቲቺንግ ሆስፒታል ውስጥ የደረሰ ነው፡፡ ሴትየዋ በሆስፒታሉ አልጋ ይዛ ስትታከም ትቆይና ህክምናዋን አጠናቅቃ፣ ከሆስፒታሉ ለመውጣት ባለቤቷ ሂሣብ ያሰራል፡፡ በዚህ ወቅትም ያስያዙት ገንዘብ አልቆ ተጨማሪ 2ሺህ ብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ይነገረዋል፡፡ ባል ጉዳዩ አስደነገጠው፡፡ በእጁ ገንዘብ እንደሌለው ተናገረ፡፡ “ሄደህ ማምጣት ትችላለህ ፤እሷ ግን ከዚህ መውጣት አትችልም” አሉት፡፡ አማራጭ አልነበረውና ህመምተኛ ሚስቱን በመያዣነት አስይዞ፤ አለብህ የተባለውን ገንዘብ ለማምጣት ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቤቱ ከአዲስ አበባ ውጪ አሰላ የሚባል ከተማ ውስጥ በመሆኑ በዕለቱ መመለስ አልቻለም፡፡ አደረና በማግስቱ ተጨማሪ የአንድ ቀን ሂሣቡን ከፍሎ ሚስቱን ከታገተችበት አስለቅቆ ወጣ፡፡
እንዲህ እንዲህ ያሉ አሣዛኝና ከህክምናው ሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ታሪኮችን መስማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህ የሙያውን ስነ ምግባር ጥሰው በወገኖቻቸው ላይ በደል የሚፈፅሙ ህሊና ቢስ የጤና ባለሙያዎች ተግባር እንጂ በህክምና ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሁሉ ተግባር እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የህመምተኛቸውን አቅም ተረድተው ከኪሣቸው ገንዘብ እየከፈሉ ምርመራና ህክምና የሚያደርጉ፣ የህመምተኛቸውን ችግር ለመስማት ጆሮአቸውን የሚሰጡ፣ አላስፈላጊ ከሆኑ ወጪዎች ህመምተኛቸውን የሚጠብቁ በርካታ የህክምና ባለሙያዎች እዚሁ አገራችን ውስጥ አሉ፡፡ እነዚህ ዓይነቶቹ ምስጋናና አድናቆት ይገባቸዋል፡፡ እነዛኞቹ ደግሞ ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ወገኖቻቸውን በታማኝነት ለማገልገል እንዲችሉ ምክርና ተግሳፅ፡፡

Read 2870 times