Saturday, 17 August 2013 11:50

የአገር አቀፍ የባቡር ፕሮጀክት ምን ላይ ደረሠ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ለአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር የ41 ባቡሮች ግዢ ኮንትራት ተፈርሟል
የኢትዮጵያ መንግስት ከያዛቸው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች መካከል በመላ ሃገሪቱ የባቡር መስመር ዝርጋታ ማከናወን አንዱ ነው፡፡ በአምስት አመቱ እቅድ ውስጥ በመላ ሃገሪቱ በ8 መስመሮች በጠቅላላ ይዘረጋል ተብሎ ከታሠበው 4744 ኪሎ ሜትር መስመር ውስጥ ከ2000 ኪሎ ሜትር በላይ ዘርግቶ ማጠናቀቅ እንደሚገባም ተመልክቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ለማከናወን ከታሠበው እቅድ ውስጥ በተጨባጭ ወደ ተግባራዊ ስራ ተገብቶ ያለው የአዲስ አበባ (ሠበታ) - ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ ነው፡፡ ሌሎቹም በየደረጃቸው በተለያዩ የቅድመ ግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ይህን እቅድ እንዲያስፋፉም በ2000 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ይገልፃል፡፡ 

ለመሆኑ ፕሮጀክቱ ምን ላይ ደረሠ? እንዴስት እየተከናወነ ነው? ከተጠናቀቀ በኋላስ የሚኖረው ገፅታ ምን ይመስላል? በሚሉት ጉዳዮች ዙርያ ለኮርፖሬሽኑ የኮንትራት አስተዳደር ሃላፊ እና የአዲስ አበባ /ሠበታ/ ጅቡቲ ቺፍ ፕሮጀክት ማናጀር ለሆኑት ኢ/ር ካሣ ታረቀኝ ጥያቄዎችን አቅርበንላቸው የሠጡትን ምላሽ በሚከተለው መልኩ አጠናቅረነዋል፡፡

አጠቃላይ ስለ ፕሮጀክቱ
ፕሮጀክቱ በሁለት ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን በመጀመሪያ ምዕራፍ እና በሁለተኛ ምዕራፍ በ8 የሃገሪቱ አቅጣጫዎች ወይም መስመሮች ግንባታው ይከናወናል፡፡ በስምንቱ መስመሮች በጠቅላላው 4744 ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚሸፈን ሲሆን ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ምዕራፍ 2397 ኪሎ ሜትር ያህሉን ሠርቶ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል፡፡ ስምንቱ መስመሮች፡-
656 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአዲስ አበባ-ሞጆ-አዋሽ-ድሬዳዋ- ደወሌ ወደ ጅቡቲ የሚሄደው
905 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሞጆ-ሻሸመኔ/ሃዋሳ/-ኮንሶ-ወይጦ-ሞያሌ ወደ ኬንያ የሚሄደው
740 እና 115 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው - ከአዲስ አበባ - ኢጃጅ-ጅማ-ጉራፈረዳ-ዲማ-በደሌ ደርሶ ቀጥታ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚራዘም
460 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ኢጃጂ-ነቀምት-አሶሣ-ኩምሩክ የሚደርሠው
757 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-መቀሌ-ሽሬ መስመር
734 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የፍኖተ ሠላም-ባህር ዳር-ወረታ-ወልድያ ሠመራ-ኤልዳር መስመር
244 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የወረታ-አዘዞ-መተማ-ሱዳን መስመር
248 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአዳማ-ኢንደቶ-ጋሠራ መስመር ናቸው፡፡
ከነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል በቀጥታ ወደ ግንባታ ተገብቶ እየተሠራ ያለው የአዲስ አበባ/ሠበታ/ - ጅቡቲ መስመር መሆኑን ኢ/ር ካሣ ይገልፃሉ፡፡ በአሁኑ ሠአት በግንባታ ላይ ያለው ይህ መስመር ለሁለት ተከፍሎ የሚሠራ ሲሆን ከሠበታ እስከ ሜኤሶ ያለውን 317 ኪሎ ሜትር የቻይናው CREC የተባለ ኩባንያ በ1.84 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጨረታውን አሸንፎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ከተያዘለት እቅድም እስካሁን 22 በመቶ የሚሆነው የተከናወነ ሲሆን በ2005 ይሠራል ተብሎ ከታሠበው ደግሞ 95 በመቶው ተሠርቷል፡፡ ከሜኤሶ-ደዋን ሌ/ጅቡቲ የሚዘረጋውን የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ክፍል በአጠቃላይ 339 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ሲሆን ግንባታው በቻይናው CCECC ኩባንያ ይከናወናል፡፡ የተያዘለት በጀትም 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን በአጠቃላይ እስካሁን 20 በመቶ ተከናውኗል፡፡ በ2005 ከተያዘው እቅድ ውስጥ ደግሞ 70 በመቶው ተሠርቷል፡፡
ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ ለማከናወን የገንዘብ ችግር ማነቆ መሆኑን የሚገልፀው ኮርፖሬሽኑ፤ሌሎቹም ጥናታቸው ተጠናቆ ገንዘብ በማፈላለግ ላይ እንዲሁም ውል ተፈርሞ ወደ ግንባታ ለመግባት በመንደርደር ላይ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡
ጥናታቸው ተጠናቆ ገንዘብ በማፈላለግ ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች ኮንትራታቸው ለሩስያ የተሠጠው የሞጆ-ሻሸመኔ-ወይጦ መስመር እና ለብራዚል የተሠጠው የአዲስ አበባ /ሠበታ/-ጅማ- በደሌ መስመር ናቸው፡፡ ውላቸው ተፈርሞ ወደ ግንባታ ሊገቡ ያሉት ደግሞ YAPI Merkezi በተባለ የቱርክ ስራ ተቋራጭ የሚገነባው የ389 ኪሎ ሜትር ሽፋን ያለው የአዋሽ-ወልዲያ /ሀራገያ/ መስመር፣ CCCC ለተባለ የቻይና ኩባንያ የተሠጠው 268 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የወልድያ መቀሌ መስመር እንዲሁም CRI8G እና CGGC በተባሉ የቻይና ስራ ተቋራጮች የሚገነባው 229 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የወልዲያ-አሣይታ መስመር ናቸው፡፡ በጨረታ ሂደት ላይ ያለው ደግሞ 210 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአሣይታ-ታጁራ መስመር መሆኑን ኢ/ር ካሣ ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ መቼ ይጠናቀቃሉ?
የአዲስ አበባ/ሠበታ/ - ሚኤሶ የተያዘለት የግንባታ ዘመን ሶስት አመት ከአምስት ወር ሲሆን እስከ ነሐሴ 2007 ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሠባል፡፡ በተመሣሣይ ከሜኤሶ-ዳዋንሌ/ጅቡቲ/ ያለው መስመርም የሶስት አመት ከ5ወር ጊዜ የተያዘለት ሲሆን በጥቅምት 2007 ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሠባል፡፡ ለሌሎቹ ፕሮጀክቶች የተቀመጠ የመጀመሪያና የመጨረሻ የጊዜ ገደብ የለም፡፡

ስለ ባቡሮች
በ2018 ይጠናቀቃል ተብሎ ለሚታሠበው የአ.አ/ሠበታ/-ጅቡቲ መስመር በጠቅላላው 41 ባቡሮች እንዲሠማሩ እቅድ ተይዟል፡፡ ለባቡሮቹ ግዢም 259 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተመድቧል፡፡ ባቡሮቹ በአብዛኛው ከቻይና የሚመጡ ሲሆን የግዥ ኮንትራታቸውም ከወዲሁ ተፈርሟል፣የመከላከያ ኢንጅነሪንግ የተወሰኑትን የፉርጐ ግንባታዎችን እንደሚያከናውን ተመልክቷል፡፡
ባቡሮቹ ሁለት አይነት ሲሆኑ በኤሌክትሪክ የሚሠራው HXDIC/7200 ኪሎ ዋት ሲሆን በነዳጅ የሚሠሩት DF7G/2200 ኪሎ ዋት ይባላሉ፡፡ ቴክኖሎጂያቸውም ባለ 1435 ስታንዳርድ ስምንት እጅ የአውሮፓ እና የቻይና ተዳቃይ ነው፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከሚገቡት 41 ባቡሮች 35 ያህሉ የኤሌክትሪክ ሲሆኑ 6 የነዳጅ ባቡሮች ይኖራሉ፡፡ በነዳጅ የሚሠሩት አገልግሎታቸው ወደብ አካባቢ ላይ ያሉ እቃዎችን ወደ ዋናው መስመር ማጓጓዝ ይሆናል፡፡ የትራንስፖርቱን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ የሚሠጡት የኤሌክትሪኮቹ ናቸው፡፡ ከ35ቱ የኤሌክትሪክ ባቡሮች ከ3-5 የሚደርሡት ለሠው ትራንስፖርት ሲውሉ ቀሪዎቹ እቃ ማጓጓዝ ተቀዳሚ ስራቸው ይሆናል፡፡ አርባ አንዱ ባቡሮች በአጠቃላይ 1130 ተጐታቾች (ፉርጐዎች) ይኖራቸዋል፡፡ ሠው የማጓጓዝ አቅማቸውን ስንመለከት አንድ ሎኮምቲቭ 10 ኮችዎች (ፉርጐዎች) እንዲጐትት ይደረጋል፡፡ አንዱ ኮች በአንደኛ ማዕረግ 56 ሰዎችን፣ በሁለተኛ ማዕረግ 80 ሰዎችን ይይዛል፡፡ አስሩ በጠቅላላው 560 እና 800 ሰዎችን ይይዛሉ፡፡
የእቃ ባቡሮቹ ስንመለከት 30 ዋገኖችን (ፉርጐዎች) እንዲጐትት የሚደረግ ሲሆን ከ3500-4000 ቶን እቃ እንዲጭን ይደረጋል፡፡
የባቡሮቹን ፍጥነት ስንመለከት፣ ለሠው የሚመደቡት በሠአት 120 ኪሎ ሜትር ሲፈጥኑ፣ ለእቃ የሚመደቡት 80 ኪሎ ሜትር በሠአት ፍጥነት ይኖራቸዋል፡፡ የምልልስ ብዛታቸው አገልግሎቱ ሲጀመር ፍላጐትን መሠረት አድርጐ የሚወሠን ይሆናል፡፡
ባቡሮቹ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ እንደመሆናቸው ድንገት ኤሌክትሪክ ቢቋረጥ ምን ይሆናሉ ለሚለው ስጋት ሁሌም እስከ ቀጣይ ጣቢያ ሊያደርስ የሚችል በቂ የሆነ በትርፍነት የሚጠራቀም ሃይል ይኖራቸዋል ብለዋል ኢ/ር ካሣ፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ላይም በተመሣሣይ እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ባቡሮች ወደ ስራ እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡

ባቡር ነጂዎችን በተመለከተ
እስካሁን ሠልጣኞች የሚመረጡበት መስፈርት የተዘጋጀ ሲሆን ከባቡሮቹ ግዢ ጋር በኮንትራቱ ተካቶ በእቅድ ተይዟል፡፡ በቀጣይ ባለሙያዎች በተዘጋጁት መስፈርቶች መሠረት ተመልምለው እንዲሠለጥኑ ይደረጋል፡፡

Read 5268 times