Saturday, 17 August 2013 11:48

ግራኝ ሆኖ የመፈጠር ጣጣ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

አንዳንዴ ለነገሮች የምንሰጠው ትርጓሜ እንደየአካባቢያችን ዓውድ ይወስናል፡፡ በዚህ ዐውድ ውስጥ ደግሞ ባህል፣ ልማድና እምነት የየራሳቸውን ፈንታ ያዋጣሉ፡፡ በተፈጥሮ የተቀበልናቸውን ነገሮች ማህበረሰብ፣ ቤተሰብና አካባቢ እንደልምዳቸውና ዝንባሌያቸው ሞገስ ሊሰጡን፣ ወይም ዝቅ አድርገው ሊፈርጁን የሚችሉበት ቀጥተኛ ያልሆነ ሥልጣን አላቸው፡፡
እኔም ዛሬ ከዓለማችን ፀሐፍት አንደበት ተውሼ፣ አብሬያቸው ተካፍዬ የማስነብበው ርዕሰ ጉዳዩ የዚሁ መነሻ ውጤት ነው፡፡ በተፈጥሮ “ግራኝ” ተብለው ስለሚጠሩት፣ ከቀኝ እጃቸው ይልቅ የግራ እጃቸው ለክፉና ለደግ ስለሚፈጥነው ሰዎች ሕብረተሰቡ ምን ይላል? ዓለማችን ግራኞችን በግራ ዓይን ለምን ማየት አሰኛት? የሚለውን ጥያቄ አንስተው መልሱን ከታሪክ የተቀበሉ ምሁራንን በሮች እያንኳኳሁ ጥቂት ለማለት ፈልጌያለሁ፡፡
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጊዜ ሰጥተው፣ ቀልባቸውን ሰብስበው ያጠኑ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ፤ ብዛታቸው በቁጥር (በፐርሰንት) ሲሰላ ከአጠቃላይ የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር 10% ያህሉን ይይዛሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ በቁጥር ስሌት ከቀኝ እጅ ተጠቃሚዎቹ በቁጥር የሚያንሱ ሰዎች በአብዛኛው በጥሩ ዓይን አይታዩም፤ እንዳልታደለ፣ ወይም ዕድል እንዳልቀናው ይታሰባሉ፡፡ ግራኞች እንደ ግራ መጋባት ይቆጠራሉ፡፡ ይህ አተያይ ደግሞ በእኛ በአፍሪካዊያን ላይ የበለጠ ጫና ይፈጥራል፡፡ ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚያሳየን ታላቁ ቀራፂ ሚካኤል አንጀሎ፣ ጁሊየስ ቄሣር፣ ሌዮናርዶ ዳቪንቺ፣ ቢልክሊንተንናም ባራክ ኦባማ ግራኝ ከሚባሉት ናቸው፡፡
በርግጥም እንደታሪክ ፀሐፍቱ መረጃና አባባል ከሆነ፤ ግራኝ የሆኑ ሰዎች ከእኛ በምንም ነገር አይተናነሱም፡፡ በአእምሮ ብቃት መለኪያም ሆነ በተግባር አንዳች ጉድለት የለባቸውም፡፡ ግን በተለያየ አምልኳዊና ጥንታዊ ልማዶች መነሻነት፤ በሃይማኖታዊ መጽሐፍት ውርስ ግራኝ መሆን ግራ ነው፡፡ ስለዚህም በቀኝ እጅ መጠቀም መልካም ዕጣ፣ ግራኝ መሆን ደግሞ ጣጣ ነው ተብሎ ሺህ ዓመታት ሲታሰብ ኖሯል፡፡
ዛሬም ያ ልክፍት እንደየሕብረተሰቡ የአስተሳሰብ ልቀትና ደረጃ ከፍና ዝቅ ባለ ሁኔታ ይታመናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ፍየሎች በግራ /ተኮናኞች/ሲል፣ በጐች/በቀኝ ፃድቃን ብሎ ስለሚያስቀምጥ፣ በሰይጣን ወገን የሚቆመውን የግራ ዕጣ መልካም ብሎ መቀበል ይከብዳል፡፡ ግን ግራኝ በራሱ ምን ግራ አለበት የሚለውን ጠልቆ ለማሰብ ጊዜና ቦታ ያለው ሰው ብዙ አይደለም፡፡ ስለዚህም ወላጆች ሕፃናት ልጆቻቸው ግራኝ እንዳይሆኑባቸው በማለት በግራ እጃቸው ሲበሉ፣ ወይም ሲሰሩ መከልከልና መቆጣት አለፍ ሲልም እስከዱላ ይደርሳሉ፡፡
ዞግቦ፣ የሚባሉ ፀሐፊና ተመራማሪ እንደሚሉት፤ በምንኖርባት ዓለም ግራኝ መሆን ከወንጀለኝነት አመፀኝነትና ከጥንቆላ ጋር ሳይቀር ይዛመዳል፡፡ ነገር ግን ግራኞች ከሌሎቻችን የተለየ የወንጀልና የዓመጽ ድርጊት ስለመፈፀማቸው የሚጠቁም አንዳች ጥናታዊ ማስረጃ የለም፡፡ ይልቅስ በሁሉም ነገራቸው እኛን መሰል ናቸው፡፡
አውሮፓውያኑ፣ በአጠቃላይ ምዕራባዊያኑ “You are right!” በማለት ቀኝን የትክክለኝነት ማሳያ አድርገው እንደተቀበሉ ሁሉ፤ እንዲያውም ከዚያ እጅግ ባለፈ ሁኔታ አፍሪካዊያኑ በቀኝ እጅ ያመልካሉ፡፡ ለቀኝ ይገዛሉ፡፡
በአፍሪካ ውስጥ ከምዕራብ አፍሪካ እስከመካከለኛው አፍሪካ፣ ግራኝ መሆን እንደ ክፉ ዕጣ የሚታይ ፍርጃ ነው፡፡ ከዳካር አንስቶ እስከ ኪንሻሳ በግራ እጅ መብላት፣ በግራ እጅ የቱንም እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ወይም ለተግባቦት መጠቀም በእጅጉ የተወገዘችና ለሌሎች ሰዎች አክብሮት እንደመንፈግ የሚቆጠር ድርጊት ነው፤ ከዚያም በላይ እንደስድብ ይቆጠራል፡፡
ለምሳሌ ኒጀር ውስጥ በሰሜናዊ ሣንጋይና ሃውስ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በግራ እጃቸው በፍፁም ሰላምታ አይለዋወጡም፡፡ ምናልባት በቀኝ እጃቸው አንዳች ዕቃ ጨብጠው ቢሆን፣ ወይም በሌላ ጉዳይ መጠቀም ባይችሉ ቀኝ ክንዳቸውን ለሠላምታ ይዘረጋሉ እንጂ በግራ እጃቸው ሰላም ማለትን አይሞክሩትም፡፡ በግራ እጅ ሠላምታ ቀኑን ሸቃባ እንደማድረግ ይቆጠራል፡፡ ኮትዲቯር ውስጥ ቤቴ በሚባል አካባቢ ሴት ልጅ በግራ እጅዋ ምግብ ካበሰለች ነገር ተበላሸ፣ አገር ጠፋ! አሻፈረኝ ብላ ምናልባት እንኳ ብታበስል እንትን የነካው እንጨት ነው ምግቡ፡፡ እዚሁ ሥፍራ ካህን ይሁን ቄስ አሊያም መጋቢ የግራ እጁን አንስቶ ቃሉን ቢያስተምር ወይም ቢሰብክ ምዕመኑ ጉባኤውን እየተወ ሹልክ ብሎ ይወጣል፡፡ ምክንያቱም በግራ እጅ እርግማን እንጂ ባርኮት አይሰጥም፡፡ ታዲያ ማን ሞኝ አለ ከካህኑ እጅ እርግማንን የሚቀበል፡፡
በዚህችው ኮትዲቯር ውስጥ ዲያስ በምትባል ሥፍራ አንድ ሰው የሌላውን ሰው የትውልድ መንደር በግራ እጁ ጣት ከጠቆመ ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡ ትርጓሜውም ያ በግራ እጅ የሚያመለክት ሰው እዚያ ለሚያሳየው መንደር ተወላጅ ያለው ከበሬታ ዝቅ ያለ ነው የሚል ነው፡፡
በቶጐም ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢነት ያለው የግራ ትርጔሜ አለ፡፡ ቶጐ/ጋንጋም/ ውስጥ አንድ ልጅ በግራ እግር ለምታት መሞከር የንቀት ንቀት ነው፡፡ ስለ ግራኞች ትንሽ ለየት ያለ ትርጓሜ የሚሰጠው ካሜሩን ውስጥ ግባያ የሚባል አካባቢ ነው፡፡ እዚያ ሀገር ላይ “ግራኝ አይስትም” የሚል ከአነጣጣሪነት ወይም ከጦረኝነት ጋር የሚዛመድ ትርጓሜ ይሰጣል፡፡
ቤኒን ውስጥ ባታናም በሚባል አካባቢም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ያለው እምነት አለ፡፡ ግራኞች ጀግና፣ አዋቂ፣ ተዐምረኛም ተደርገው ይታሰባሉ፡፡ ስለዚህም ሕዝቡ ባንድ ወገን ያከብራቸዋል፤ በሌላ ወገን ደግሞ ይፈራቸዋል፡፡ ምክንያቱም የተለየ ገድል እንደሚፈጽሙ ስለሚያስብ በጥንቃቄ ያያቸዋል፡፡
ይሁንና በዚህ ምድር ግራኝ ሰው ለሥልጣንና ለንግሥና ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ የጦረኝነት መንፈስ አለበት ተብሎ ስለሚታሰብ የሕዝቡ ልብ አይተማመንባቸውም፡፡ እንደ ዓይነ ስውር፤ አካል ጉዳተኛ የሚታዩበትም አጋጣሚ አለ፡፡
በአፍሪካዊቷ ቡርኪናፋሶም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ጀግንነታቸውን ከጦር ሜዳ ወደ አልጋ ይወስደዋል፡፡ ጉርማንቼ በምትባል አካባቢ ግራኝ፤ ከሚስቱ ጋር ፍቅርን ሲጋራ የተሳካለት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
ምክንያቱም በአልጋ ፍቅር ዋነኛው ተዋናይ ግራ እጅ ነው ተብሎ ስለሚገመት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እስካሁን ዘመን ድረስ ወንዶች ሲሞቱ መቃብራቸው ጉድጓድ ውስጥ የሚጋደሙት በግራ በኩል ወደ ምስራቅ ዞረው ነው፤ እዚያም ፍቅር መሥራት ይኖራል ብለው ስለሚያስቡ፡፡
ኮትዲቯር ውስጥ ኒያራፎሎ ደግሞ ወንዶች ሲቀበሩ በግራ ነው፤ ይህ የሚደረገው የቀኝ እጃቸው ባርኮት ለመስጠት ነፃ እንዲሆን ነው፡፡ ይህ ማለት ቀኝ ለባርኮት፣ ግራ ለእርግማን እንደማለት ነው፡፡
ሰሜን ቶጐ ጋንጋም ውስጥ ማንም ሰው በመኖሪያ ቤቱ ግራ ማዕዘን ላይ አይቀመጥም፤ ያ ግራ ሥፍራ ለሟች መቀበሪያ ነው፤ ትርጉሙም ግራ ከሞት ጋር የሚያጣምር ነው፡፡ እዚያ አካባቢ ክፉ ሞት ሞቷል የሚባልን ሰው በቀኝ እጁም ሆነ በቀኝ እግሩ እንዲህች ብሎ የሚነካው የለም፡፡ መቃብር ቆፋሪዎች በግራ እግራቸው ነው የሚነኩት፡፡
ግራ እጅ መንፈሳዊ መስዋዕት ለማድረግም አይመረጥም፤ ለሹመትም ሲሆን በቀኝ እጅ ተሿሚው ጭንቅላት ላይ እጅ ተጭኖ ወይም በቀኝ እጅ ወደ እርሱ እያመለከቱ ባርኮትና ሹመት ይሰጣል እንጂ በግራ አይሞከርም፡፡ የግራና ቀኝ ጉዳይ በቋንቋና ሥነ ልሳንም ውስጥ የተሳሳተተ ትርጓሜ ይሰጠዋል፡፡ ይሁንና በአብዛኛው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚታየው የግራና የቀኝ ትርጓሜ በተለይም የብሉይ ኪዳን አዋቂዎች እንደሚሉት፤ አመጣጡ በጥንት ዘመን ዕብራዊያን ከጐረቤቶቻቸው የወረሱት ነው፡፡ በተለይ ከትንሿ እስያ፡፡ የቀኝን ሞገስ ማግኘትና ጥንካሬን በተመለከተ ከላይ የጠቀስኳቸው ፀሐፊ ያስቀመጡት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ለምሳሌ ኢራቅ ውስጥ ከኖራ ድንጋይ የተሰራው ሃውልት የአምር ቀኝ እጅ ወደሌላው ንጉሥ ተዘርግቶ ይታያል፤ ይህ ቀኝ እጅ ስምምነትን ያሳያል፡፡ በሌላ ቦታ የግብፁ ፈርኦን (ከ1345-1318) ከክ/ል/በፊት ሆረስ ከሚባለው አምላክ ቀኝ ተቀምጦ ይታያል፡፡ ይህ ክብር ነው፡፡ በነዚህ ምሣሌዎች/መታሰቢያ ሃውልቶች/ ትርጓሜ ቀኝ ስምምነት፣ ስኬትና ባለአለኝታ መሆን ናቸው፡፡
እነዚህ ደግሞ በዕብራዊያን ታሪክ ገቡ፤ ከዚያም አደጉ፡፡ ተዘሩ፡፡ ኖሩና እንደ እንጀራ ክብ እየሰሩ ቀጥለዋል፡፡ ተደጋግመዋል፡፡ በማለት ጠቢባኑ አትተውልናል፡፡ ምሥጋና ይግባቸው!

Read 5184 times