Saturday, 17 August 2013 11:41

‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…“እኔ ብቻ አዋቂ…” “እኔ ብቻ ልዩ…” “እኔ ብቻ…” ምናምን የሚሉ ነገሮች አልበዙባችሁም! አለ አይደል…በምንም ነገር እኛ ልዩ ሆነን ላይኛው ፎቅ ላይ የተቀመጥንና የተቀረው ሰው ሁሉ ደግሞ ‘ምድር ቤት’ ያለ የምናስመስል እየበዛን ነው፡፡
አንዳንዴ ስታስቡት…“ብሶትና ችግር አውርተን እስከመቼ…” ትላላችሁ፡ ብሶቱና ችግሩ እየበዛ ነዋ! ሁሉ ነገራችን… አለ አይደል… ትንሽ ካፊያ የሚያጥበው የእንትናዬዎቻችንን ‘ኩልና ፋውንዴሽን’ እየሆነ ነው፡፡ ማስመሰል፣ መመሳሰል… አንዲት ስንጥር ሳናነሳ “ዱታው ዘራፍ…” “ግነን በሉኝ…” አይነት ነገሮች ‘ተቀባይነት ያላቸው’ ነገሮች እየሆኑ ነው፡፡
ስሙኝማ…እስቲ ‘ቦተሊካችንን’ ነገሬ ብላችሁ ስሙት…ሁሉም ወገን…አለ አይደል…“ዱታው ዘራፍ…” “ግነን በሉኝ…” ሲል ነው የምትሰሙት፡ አንዳንዴ ምን ይገርመኛል መሰላቸሁ…ሁሉም ወገኖች የሚጠቀሙበት ቋንቋ ተመሳሳይ ከመሆኑ የተነሳ…ይቺን ነገር ማታ ውስኪ ላይ ተመካክረው ነው እንዴ ጠዋት ለእኛ የሚበትኑት ምናምን እንላለን፡፡ አሀ… “ሊበራል ዲሞክራት ነኝ…” የሚለውም፣ “ኒኦ ሊበራል ነህ…” የሚባለውም ልዩነቱ ነጠላ ሰረዝ ላይ ብቻ የሆነ ነገር ሲናገሩ የማንጠረጥርሳ!
እናላችሁ…አንዳንዴ ስታስቡት በ“እኔ ብቻ ትክክል…” የተቃኘው የዚህ አገር ‘ቦተሊካና ቦተሊከኞቹ’ ነገር ግራ አይገባችሁም! አዲስ ሀሳብ ናፈቀን! አሀ…ልክ ነዋ! ዘላለም ‘ሊበራል ቅብጥርስዮ’ ‘ምናምን ሰብሳቢ’ እየሰማን መኖር ሰለቸና! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…አንዳንድ ‘ቦተሊከኞች’…አለ አይደል…ልክ የማርክስን ‘በትረ መንግሥት’ እንደተቀበሉ ነገር ሲያደርጋቸው ስታዩ…በቃ የ‘ቲራቲር’ አገር ሆነን ቀረን ያስብላችኋል፡፡
ስሙኝማ…‘ቦሶቻችን’ ለምን ኮስተር እንደሚሉ ገርሟችሁ አያውቅም! ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በቃ ወንበር ስንይዝ…አለ አይደል…ያቺ የ‘ባላባትነት ሜንታሊቲ’ በእግረ ሙቅ የምትጠፍረን ይመስለኛል። አለ አይደል… ወንበር መያዝን ከሥራ ሀላፊነት ይልቅ በሰው ልጅ ላይ ‘ውሀ እየረጩ’ ለመሄድ የተሰጠ ‘ሊቼንሳ’ ምናምን ነገር እናደርገዋለን፡፡
እናማ…“ውሀ ረጨኸኝ እኮ!” ብትሉ…አለ አይደል… “እና ብትረጭስ ምን ታመጣለህ…” አይነት የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ ነገር እየበዛ ነው፡፡ እንዴት እንደሆነ እንጃ እንጂ…በ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ…‘የተለየን’ የመሆን ስሜት የሚያሳድርብን ሰዎች ቁጥራችን በድምር ሳይሆን በብዜት እየጨመረ ነው፡፡ ጥያቄ አለን አንዳንድ ሰዎች የታርጋቸው መለያ ኮድ ብቻ የትራፊክን ህግ እንደፈለጉ እንዲጥሱ የሚያደርጋቸው …አለ አይደል…በታርጋዋ ብቻ የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ስለሚያድርባቸው አይመስላችሁም!
ታዲያላችሁ… ይቺ የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ በተለይ በስነ ጥበቡ አካባቢ ግንኙነቶችን እያበላሸ ነው፡፡ አሥር ሰው ባጨበጨበ ‘ኤጓቸው’ በአሥር እጥፍ እየናረ ባልሆነ አቅጣጫ ‘የሚታጠፉ’ ሰዎች እያየን ነው፡፡
እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ሴሌብሪቲዎቻችን’ ስሙኝማ…ምን የምትል ነገር አለች መሰላችሁ…“ገንፎ እፍ እፍ ቢሉሽ ሊውጡሽ ነው፤ እውነት አይምሰልሽ፣” የሚሏት ነገር አለች፡፡ እናማ… ጭብጨባ ሁሉ የእርፍና መለኪያ እንዳልሆነ ልብ በሉልንማ! አሀ ልክ ነዋ…አብዛኞቹ ነገሮች በ‘ቲፎዞ’ ብዛት እየተሠሩ ባሉበት ዘመን…ከልብ ያልሆነ የይሉኝታ ጭብጨባ ብዙ ልጆችን እያሳሳታቸው ነው፡፡ (እግረ መንገዴን…አብዛኛው በየአዳራሹ የምናሰማው ጭብጨባ የ‘ይሉኝታ’ እንጂ ‘ቦሱ’…አለ አይደል… “ትምህርት ለአንድ አገር እድገት አስፈላጊ…” መሆኑን ስለነገሩን በ‘አስተሳሰባቸው ምጥቀት’ ተመስጠን እንዳልሆነ ይጻፍልንማ! ቂ…ቂ…ቂ…)
እናላችሁ…ተዋናያኖቻችን ወይ በፊልም፣ ወይ በድራማ ትንሽ ሲታወቁ…የአራዶቹን ቋንቋ ለመጠቀም ‘መነስነስ’ ያበዛሉ ይባላል፡፡ እንዲህ ነዋ የሚባለው! ታዲያላችሁ…የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ውስጥ ይገቡና ለሥራ የሚጠይቁትም ዋጋ የመለስተኛ ድርጅት ዓመታዊ ገቢ ወደመሆኑ እየተቃረበ ነው አሉ፡፡
ነገርየው… አለ አይደል…
“አይታ የማታውቀውን የሰው ጃኖ ለብሳ፣
ተመለሺ ቢሏት መቼ ተመልሳ…”
አይነት እየሆነላችሁ ነው፡፡ ትንሽ ማበረታቻ እንደ ‘ፍጹምነት’ ማረጋገጫ እየታየ…አለ አይደል… “የት ይደርሳሉ…” የተባሉ ሰዎች ባቡራቸው መሀል ላይ እየተሰናከለ ነው፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ኳስ ተጫዋቾቻችን ‘ተዘዋወሩባቸው የሚባለውን የገንዘብ መጠን እየሰማን…“ጉድ!” እያልን እንደሆነ ይመዝገብልንማ፡፡ ብቻ…ያንን ያህል ገንዘብ የሚያወጡ ክለቦች የየራሳቸውን ሜዳ መቼ ሊሠሩ እንዳሰቡ ይንገሩንማ… ‘ለመሥራት ካሰቡ’ ማለታችን ነው፡፡ በነገራችን ላይ…አንዳንዴ “በኳስ ክለቦቹ መሀል የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ አለ እንዴ!” የምንል መአት ነን፡፡ ልክ ነዋ…ከክለቦች ጀርባ ገንዘብ… ከገንዘብ ጀርባ ሰዎች… ከሰዎች ጀርባ ‘ኤጎ’…ምናምን እያለ የሚቀጥል ነገር ሊኖር ይችላል ብሎ መጠርጠር ክፋት የለውማ!”)
እናላችሁ…የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ለብዙ ነገሮች መሰናክል ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ ጓደኝነቶች፣ ወዳጅነቶች፣ ውህደቶች…ምናምን ሁሉ ‘እንዳማረባቸው የማይዘልቁት’…በመሀል የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ዘልቆ ስለሚገባ አይመስላችሁም!
እናላችሁ…‘ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል’ ይባልና ስትገቡ አርባ ምናምን የምግብ አይነት ከፍተኛ ‘ሽብር’ በተካሄደበት ‘ስፔሊንግ’ የተጻፈበት የምግብ ዝርዝር ይቀረብላችኋል፡፡ ታዲያ ምን መሰላችሁ…ሠላሳ ዘጠኙ የምግብ አይነት አይኖርም። ግን ይቺ “ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል…”፣ “እጅ የሚያስቆረጥም …እንሠራለን…” ነገሮች ከጀርባቸው “ከሌሎች የተሻልን ነን… አይነት የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ ነገር አለባቸው፡፡
ከመደበኛዋ ስምንት የሥራ ሰዓት ሦስቷን እንኳን በስነ ስርአት የማይሠሩ ድርጅቶች “የሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት እንሰጣለን…” ሲሉ ብዙ ጊዜ ከጀርባ ያቺ ባህል ነገር የሆነችው የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ አለች፡፡
ብዙ ማስታወቂያዎች ላይ የሚጠቀሙባቸውን ቃላት ነገሬ ካላችሁ…“ማን እንደ እኛ!” አይነት የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው፡፡
የእኔ ቢጤዎች ደግሞ አለንላችሁ…አንድ መጽሐፍ ስለተረጎምን፣ አንዲት የግጥም መጽሐፍ ስላስመረቅን የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ እያደረብን “ምን ተርጓሚ አለና ነው…” “አሁን እዚህ አገር ገጣሚ አለ!...” የምንል፡፡
እግረ መንገድ…ይቺን ስሙኝማ…ይሄ የፌስቡክ ዘመን ጣጣ…ትንሽዬው ልጀ እናቱን “እማዬ ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ‘ዳውንሎድ’ ተደርጌ ነው እንዴ?” ብሎ ይጠይቃታል.፡ እናቱ ምን ብላ መለሰችለት መሰላችሁ…“አይ ‘ዳውንሎድ’ ተደርገህ አይደለም፡ ተወልደህ ነው፡፡” አሪፍ ምሳሌ አይደል!
እናላችሁ… ነገሮች አሁኑኑ በብልጠት ካልተያዙ ነገና ተነገ ወዲያ…“እማዬ ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ‘ዳውንሎድ’ ተደርጌ ነው እንዴ?” የሚሉ ልጆች የማይበዙበት ምክንያት የለም፡፡ ነገርዬው ምን መሰላችሁ… ዘንድሮ ብዙ ወላጆች በ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ‘ከሌሎች ለመለየት’ ልጆቻቸውን ዕድሜያቸው ለማይመጥናቸው ነገሮች እያጋለጧቸው ነው፡፡ አንዳንዴ እኮ…እዚቹ ከተማችን ውስጥ ብቻ እየተፈጠሩ ያሉትን ነገሮች ስታስቡ ከአንድና ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ ነገሮች ሊደርሱበት የሚችሉበት ደረጃ ያሳስባችኋል።
ቢ.ኤምደብልዩ ያለው እንትና ስለያዘች ብቻ የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አይነት ነገር የሚጠፍራት መአት አለች፡፡ በአንድ ቡና በወተት አምስት ሰዓት ሙሉ ‘ወንበር ስታግል’ እንዳልዋለች ሁሉ ‘መኪና ላይ ስትወጣ’… “በእናታችሁ፣ ማኪያቶ፣ ቡና በወተት ምናምን አይሰለቻችሁም!” አይነት ‘ዘጠነኛው ደመና’ ላይ መንጠላጠል ትጀምራለች፡፡
እግረ መንገዴን…አንዱ ምን አለ ይባላል መሰላችሁ… “ሴቶች አስቸጋሪ ፍጡራን ናቸው፡፡ ዕድሜያቸውን ስትጠይቃቸው ኮረንቲ ሊጨብጡ ይደርሳሉ፡፡ የልደት ቀናቸውን ስትረሳ ግን ዘልዝለው ቢበሉህ ደስ ይላቸዋል፡፡” ደግነቱ ዘንድሮ ልደት ላይ “ለመሆኑ ዕድሜሽ ስንት ደረሰ?” እያሉ ቁጥር መጠያያቅ ‘ጎጂ ልማድ’ ስለሆነ… እየቀረልን ነው፡፡
ከዚህ በፊት ያወራናትን እንድገማትማ…ሰውየው ዕድሜውን ሲጠየቅ ወደ ሀያ ምናምኑን ይገነድስና “ሠላሳ…” ምናምን ይላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ የእሱን ዕድሜ ሲጠየቅ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“በእሱ ስሌት ከሆነ እኔ ገና አልተወለድኩም!” ቂ…ቂ…ቂ…በዛሬው ቀን በራሳቸው የዕድሜ ስሌት ‘ሳይወለዱ ልደታቸውን ለሚያከብሩ’ ሁሉ… መልካም ልደት ብለናል፡፡
እናላችሁ…የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ…(እንደውም በቋፍ ነን!) ነገሮችን በ“አንተ ትብስ አንቺ…” እንዳንሠራ እያደረገን ነው እላችኋለሁ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3309 times