Saturday, 17 August 2013 11:24

ያልነው አልቀረም ጥሩዬ፣ ነገር የገባት ሰጐን ነሽ!

Written by  ነ.መ
Rate this item
(2 votes)

(ቁጥር 3)
“አበሻ ፊቱ አይታወቅ፤ ያሸንፍም ይሸነፍም
ፈረንጆቹ ብለው ቢሉም
ለኛ ትታወቂናለሽ፡፡ እፊትሽ ላይ ድል ተጽፏል፡፡
የገጽታሽ ጠይም ብርሃን፣ ልበ ሙሉ ናት ይለናል፡፡
ያልነው አልቀረም ጥሩዬ፤ ነገር የገባት ሰጐን ነሽ፤
ዘንድሮም ተረጋገጠ፣ ክንፍ - ያላት - ሯጭ መሆንሽ፡፡
ብለን ነበር ጐህ ሲቀድ…
“ወትሮም ጀግና ሩቅ ነው ልቡ
ዓለምን እንደጠባብ ቤት፤ በሁለት እግሩ ማሰቡ
ቢሮጥ ነው እንጂ በልቡ
ቢሮጥ ነው እንጂ እንደልቡ
ቢሮጥ ነው እንጂ ከልቡ!!”
ያልነው አልቀረም ጥሩዬ፣ ነገር የገባት ሰጐን ነሽ!
“ንፋስ ሆነሽ ከንፋስ ጋር፣ መሽቀዳደም ሲሆን ዕጣሽ
ከልብ ትርታ ትይዩ፣ ከሥጋት እኩል መሮጥሽ
ከጥላው እንደሚሸሽ ሰው፣ ከባኮው ሾልከሽ መውጣትሽ
ድል - መንገድ በጠዋት ላንቺ፣ የተፃፈ እስኪመስልብሽ
እንደጠይም ብርሃን ንጥቀት፣ ያለኮቴ መመንጠቅሽ”
ያልነው አልቀረም ጥሩዬ፣ ነገር የገባት ሰጐን ነሽ!
ብለን ነበር ጐህ ሲቀድ…
“ባስማት እንዳበሩት ሻማ፣ ተግ ሲል አበሻ ባርቆ
ካጃቢዎች ተፈትልኮ፣ ከባኮው ውስጥ ተመንጭቆ
የቁርጥ ቀን እርምጃ ነው፣ ኮቴው አይሻክርም ደምቆ
ዓለም ምን ያድርግሽ አቦ! ይከተልሽ ቁርጡን አውቆ!
ጥሩዬ ልንገርሽ ዛሬም
“እንኳንስ ተከታይ ሯጭ፣ ተመልካች በዐይኑ አይቀድምሽም፡፡
እግርሽ ካዕምሮሽ ሲፈጥን፣ ያስደነግጣል ጊዜንም፡፡
ሰምበር የበዛው ሜዳ፣ አምስት ሺ ጊዜ ቢዞር
ዥንጉርጉሩ ክብ መንገድ፣ 10ሺ ቀለበት ቢያሥር
ባንቺው እንዝርት - እግር ቀጥኖ፣ እንደድር ተዳውሮ ሲያጥር
ሲጠነጠን እስከድል በር
ይህ እኮ ነው የአገር ኩራት፣ ሁሌም ያሰቡበት ማደር!
ጥሩዬ ልንገርሽ ዛሬም፣ አንቺም ንገሪያት ላገርሽ
“ሩጫችን የወል ጣር ነው፣ ድልም በደቦ ነው ሚያምረው
እርሻ በጅጊ ነው እሚሠምር፤ ጓዛችን አንድ ልብ ነው
ጉዟችን የአገር ልማድ ነው፤
ተናቦ ተቧድኖ መርታት፣ አንድነት ባህላችን ነው!
ዛሬም ንገሪያት ለአገርሽ፣ የሩቅ የሀቅ ወርቅ አንጥረሽ
ድልሽን “እንደድመት ግልገል፣ በጥርስሽ ጫፍ አንጠልጥለሽ”
በዓለም ሰማይ ከዓለም በላይ፣ የባንዲራ ዳስሽን ጥለሽ
ሜዳልሽን፣ ባገርሽ ክብር ውስጥ፣ እንዳራስ ፈገግታ አንጣለሽ
ከሠገነት በላይ ሰንደቅ፣ ከሰው በላይ ድልሽን ሰቅለሽ
የባንዲራችን ነበልባል፣ አየሩን ሸፍኖባቸው
የዓለም ባንድሮች ከመሬት፣ ሰማይ ማየት አቃታቸው፡፡
ጥሩዬ በእኔ ሞት ብለን፣ ገና በጧት ቃል አንቅተን
በገዛ እጅ አካል ዳብሶ፣ ተዘጋጅቶ መንደርደርን
ከቶም ከመሯሯጥ መሮጥ፣ ሺ ጊዜ መብለጥ መላቁን
በትዕግስት መነሳትን፣ በትዕግስት ዳር መድረስን
በትንፋሽ ጉልበት መግዛትን፣ በትንፋሽ ኬላ መስበርን
ዛሬም በእኔ ሞት ጥሩዬ፣ መላውን ለአገር ንገሪ
አንቺ አገር ነሽ፣ የአገር ጠሪ
ጊዜ አይተሽ የምትሰግሪ
ጊዜ አይተሽ የምትበርሪ
አንቺ ጠይም የሰው ጨረር፣ ጠይም ኮከብ ታሪክ ሰሪ
ነገር የገባት ሰጐን ነሽ፣ ጥሩዬ በእኔ ሞት ኩሪ!
ይቻላል በያት አገርሽን፣ አርፎ ተነስቶ መሮጥ
ይቻላል በያት አገርሽን፣ ቦታ ማየት፣ ጊዜ መምረጥ
ተፎካካሪን እያዩ፣ በርቀት፣ በስላች ማምለጥ
ዛሬም በሥራ ንገሪን፣ ላገር ነውና ድካምሽ
ያልነው አልቀረም ጥሩዬ፣ ነገር የገባት ሰጐን ነሽ!!
ነሐሴ 9/2005
(ለጥሩዬ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለልደቴ)

Read 3995 times