Saturday, 17 August 2013 11:12

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህገ-ወጥ ንግድ ላይ እርምጃ ሊወስድ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ህገ-ወጥ የከተማ ንግዶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ማቀዱን ገለፀ፡፡ በከተማዋ በቀላል ባቡር እና በመንገድ ግንባታ ምክንያት ህዝቡ በትራንስፖርት ችግር እየተሰቃየ በመሆኑ የጐዳናና የበረንዳ ንግድ ቅድሚያ እልባት ያገናኛሉ ተብሏል፡፡
ከትላንት በስቲያ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ አዳራሽ የመስተዳድሩ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሀላፊ አቶ ሺሰማ ገ/ስላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ስራ አስኪያጅ ረዳት ኮሚሽነር ሀይሌ አማረና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር ፈቃደ ሀይሌ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በርካታ ህገ-ወጥ ድርጊቶች በከተማዋ የተስፋፉ ቢሆንም፣ አሁን ባለው ሁኔታ በህገ-ወጥ ንግድ የተያዙ የከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች፣ በህገ-ወጥ ግንባታና በሼድ የተያዙ መንገዶች እንዲሁም በረንዳዎች መለቀቅ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

እስካሁን በተካሄው ጥናትም ዘጠኝ ሺህ የበረንዳ ነጋዴዎችና ስምንት ሺህ የጐዳና ላይ ነጋዴዎች ሲነግዱ መመዝገባቸውን ሀላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡
በገበያ ጣልቃ ገብነት፣ በት/ቤቶች ዙሪያ በሚደረጉ አዋኪ ንግዶች፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ በህጋዊ ንግድ ፈቃድ ስም ህገ-ወጥ ንግድ የሚካሄዱና ለትውልድ ስነ-ምግባር እንቅፋት የሆኑ ንግዶችን ለማስቆም እስካሁን ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች እንደተወሰዱ የተገለፀ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ግን አንገብጋቢውና ለከተማው ነዋሪ ፈተና የሆነው የበረንዳና የጐዳና ላይ ንግድ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚሰሩ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይም ከመገናኛ ኡራኤል፣ ከኡራኤል ሜክሲኮና ፒያሳ አካባቢ ያለው የበረንዳና የጐዳና ላይ ንግዶች ቅድሚያ ያገኛሉ፡፡
ይህ ማለት የጐዳና ነጋዴዎች አይስሩ ማለት እንዳልሆነ ሀላፊዎቹ ገልፀው፣ ቢቻል በተለያየ መንገድ ተደራጅተው ቋሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መያዝ፣ አይ እኔ የማውቀው ስራ ይሄ ብቻ ነው ካሉም በተፈቀደ ቦታ፣ በተፈቀደ ሰዓትና በተፈቀደ ቀን መስራት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ስራ አስኪያጅ ረዳት ኮሚሽነር ሀይሌ አማረ በበኩላቸው፤ በ2002 ቢፒአር ሲሰራ ደንብ ማስከበር የተባለው አካል አስፈላጊ አይደለም ተብሎ ደንቦችን ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲያስከብሩ የተወሠነ መሆኑን ገልፀው፣ በሌላ ጥናት ግን ሴክተር መስሪያ ቤቶች ደንብ ማስከበሩን እንዳልሸፈኑት መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ደንብ ማስከበሩ በአዲስ መልክ መቋቋሙንና ለዚህም ስራ የሚሆኑ ከ2000 በላይ ሰዎች በጦላይ ማሰልጠኛ ለሁለት ወራት ስልጠና ወስደው ከግንቦት 1 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን የገለፁት ረዳት ኮሚሽነሩ፣ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በተደጋጋሚ በሚሰጣቸው ትምህርትና ከህገ-ወጥነታቸው ካልታቀቡ ደንብ ማስከበሩ ባለው ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ለየትኛውም ሴክተር መስሪያ ቤት ጉዳዩን ሳያቀርብ እርምጃ የመውሰድ ስልጣን እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ደንብ ማስከበሩ ከንግድ ቢሮው ጋር በትብብር እንደሚሰራም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
በህገ-ወጥ መንገድ የተሰማሩ የጐዳና ላይ ነጋዴዎች የስራ ቦታን በተመለከተ፣ በየወረዳቸው ማመልከት እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
የአገራችን የንግድ ስርዓት ከየት እንደመጣ ይታወቃል ያሉት ሀላፊዎቹ፤ ይህንን ህገ-ወጥነት ለማስቀረት ከቅጣትና ከእርምጃ ከመጀመር በማስገንዘብና በማስተማር መለወጥ ይሻላል በሚል የተለያዩ የምክክር መድረኮችን አመቻችተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ ነጋዴ የሆነና ያልሆነውን ለመለየት ጥናት የተደረገ ሲሆን መረጃውም በአሻራ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አቶ ሺሰማ ተናግረዋል፡፡ አዲስ አበባ ውሰጥ 230ሺህ ነጋዴ አለ ሲባል የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 139ሺህ ብቻ ወደ ህጋዊ ስርዓቱ ገብቶ ቀሪው መስፈርት ባለማሟላት አየር ላይ ቀርቷል ተብሏል፡፡
ያለ ንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የነበሩትን የቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ፣ 86ሺህ ያህሉን ወደ ስርዓቱ ማስገባት ተችሏል ብለዋል፡፡ ነጋዴው በመረጃ ላይ የተደገፈ ስራ እንዲሠራ የመረጃ ኔትወርክ ከወረዳ እስከ ፌደራል መዘርጋቱም ተገልጿል፡፡

Read 22723 times