Saturday, 17 August 2013 11:10

ነዋሪዎች በውሃ እጦት ተሰቃየን አሉ

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(1 Vote)

በሳምንት አንድ ቀን ውሃ ማግኘት ብርቅ የሆነባቸው ሰፈሮች፣ በውሃ እጦት አካባቢያቸውን በመጥፎ ጠረን የሚበክሉ የኮንዶሚኒየም መኖሪያዎች፣ ለተደጋጋሚ አቤቱታ ምላሽ ሳያገኙ በርካታ ወራት እየተቆጠሩ የሚማረሩ ነዋሪዎች የአዲስ አበባ የዘመኑ ገጽታ ሆነዋል፡፡
በቂ ውሃ ስለሌለ በራሽን ለማከፋፈል እየሞከረ መሆኑን የሚልፀው የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ፤ የኤሌክትሪክ መቆራረጥና የአንዳንድ ሰራተኞች እንዝህላልነት፣ ለመንገድ ግንባታ የሚቆፈሩ ቧንቧዎች እንዲሁም በከንቱ የሚባክን ውሃ መብዛቱ የውሃ እጥረትን እንዳባባሱ ይናገራል፡፡
የአገሪቱ እንዲሁም የአህጉሪቱ መዲና በሆነችው ከተማ፣ ለዚያውም በሰለጠነ ዘመን በርካታ ነዋሪዎች የዝናብ ውሃን ደቅኖ ለማጠራቀም ሲሯሯጡና በጀሪካን ተሸክመው ውሃ ሲያመላልሱና የፎቅ ደረጃዎችን ለመውጣት ሲውተረተሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
በገርጂ፣ አየር ጤና፣ ጀሞ፣ እንቁላል ፋብሪካ፣ አዲሱ ገበያ፣ እንዲሁም በየአቅጣጫው የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞችን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ሰፈሮች፣ በውሃ እጥረት የተቸገሩ ነዋሪዎች “አወይ ስልጣኔ” በማለት መላ እንደጠፋባቸው ይገልፃሉ፡፡
የፉሪ አካባቢ ነዋሪ ወ/ሮ አልማዝ ሞገስ፣ ቀድሞም ቢሆን በሁለት በሶስት ቀን ነበር ውሃ የምናገኘው ይላሉ፡፡ አሁን ግን ብሶበታል፣ ይሄውና በሰፈሩ ውሃ ካገኘን ከሳምንት በላይ ሆኖናል የሚሉት ወ/ሮ አልማዝ፤ ውሃ የምናገኘው ጀሪካን ተሸክመን ሰፈር አቆራርጠን ነው ብለዋል፡፡
ብዙ ጊዜ አቤቱታ አቅርበን ደከመን፤ ምንም መልስ አላገኘንም ብለዋል - ወ/ሮ አልማዝ፡፡
በጀሞ ቁጥር 1 መኖር ከጀመረች ሁለት አመት የሆናት ሰናይት ፈቃደ በበኩሏ፣ የውሃ ችግር የጠናብኝ ዛሬና ትላንት አይደለም፣ በጣም ቆይቷል ትላለች፡፡ ድሮ ድሮ ሌሊት ላይ ብቅ ይል የነበረው ውሃ፤ ዛሬ ሽታውም የለም የምትለው ሰናይት፣ የኮንዶሚኒየም ቤት ያለ ውሃ የስቃይ ቤት ማለት ነው ብላለች፡፡ የመጀመሪያ ፎቅ ነዋሪዎች የዝናብ ውሃ ደቅነው ለማጠራቀም ይሞክራሉ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ፎቅ ግን አይሞከርም፡፡ ቧንቧ በየቤታችን አለ፤ ውሃ የምናመጣው ግን እንደ ጥንቱ የገጠር አኗኗር ነው የምትለው ሰናይት፤ ለውሃና ፍሳሽ አመልክተናል፡፡ ውሃውን ወደ ላይ ለመሳብ የፓምፕ ሃይል ስለሚያስፈልግ ነው ይሉናል፤ ይህንን እንደ በቂ ምላሽ ይቆጥሩታል በማለት ግራ መጋባቷን ትገልፃለች፡፡
ጀሞ ብቻ አይደለም፡፡ የጐሮ ነዋሪ ናርዶስ አስማረ አንድ ቀን ውሃ ከመጣ ለሁለትና ለሶስት ቀን ይጠፋል፤ ቅዳሜና እሁድ ውሃ ያገኘንበት ጊዜ የለም ትላለች፡፡ በየሳምንቱ አቤቱታ ስናቀርብ የምናገኘው ምላሽ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ነው የምትለው ናርዶስ፤ አሁን ይስተካከላል ይሉናል፤ ግን ተስተካክሎ አያውቅም ትላለች፡፡
ውሃ የሚጠፋበትን ቀን ዘርዝሮ ከመናገር ይልቅ ውሃ የሚመጣበትን ቀን መናገር ይቀላል የሚለው የአዲሱ ገበያ ነዋሪ ልዩነህ አያሌው፤ ውሃ ይግባልን ብንል ይሻላል፤ በሳምንት አንዴ ውሃ ከመጣ ፌሽታ ነው፤ ብርቅ ይሆንብናል ሲል ይናገራል፡፡
አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ወ/ሮ እፀገነት ተስፋ ምላሽ ሲሰጡ፤ በአዲስ አበባ የውሃ ችግር አለ በማለት ነው የሚጀምሩት፡፡ ዋናው ምክንያት የውሃ እጥረት ነው የሚሉት ወ/ሮ እፀገነት፤ ከነእጥረቱም ቢሆን ውሃውን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ደግሞ የተለያዩ መሰናክሎች እንደሚገጥሙ ገልፀዋል፡፡
ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ከፍታ ቦታ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በፓምፕ ውሃ ማድረስ አንችልም ይላሉ፡፡ ሌላው ችግር በራሳችን ሰራተኞች የሚፈጠር ነው የሚሉት ሃላፊዋ፣ የውሃ ቧንቧ ተበላሽቷል ተብሎ ሲነገራቸው አንዳንድ ሰራተኞች ብልሽቱን እንደመጠገን ውሃውን ዘግተውት ይመጣሉ ብለዋል፡፡ በመንገድ ስራና የተለያዩ ግንባታዎች የውሃ ቧንቧ እንደሚሰበር ሲያስረዱ፣ ለምሳሌ በሃያ ሁለት አካባቢ፣ በመንገድ ግንባታ ምክንያት ዋናው የውሃ ቧንቧ በመቋረጡ አሁን በተዘረጋ ጊዜያዊ ቧንቧ የምናቀርበው ውሃ በአስር እጥፍ ያነሰ ነው ብለዋል፡፡ በዚያ ላይ ለከተማዋ ከሚቀርበው ጠቅላላ የውሃ መጠን ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጠው በከንቱ ይባክናል ብለዋል ሃላፊዋ፡፡ የከተማዋን የውሃ ችግር ለማቃለል 11 የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው 10 ስራ መጀመራቸውን ወ/ሮ እፀገነት ጠቅሰው፤ ከለገዳዲ ይቀርብ የነበረውን 165ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ፣ ወደ 195ሺ ሜትር ኪዩብ ለማሳደግ እየሰራን ነን ብለዋል፡፡ በገርጂ አካባቢ በ2.5 ቢሊዮን ብር ወጪ 100ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ለማቅረብ ግንባታው በ2006 ይጀመራል፤ በሁለት እና ሦስት አመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ችግሩ እንደሚፈታ እርግጠኛ ነኝ ያሉት ሃላፊዋ፣ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን በ906 በመደወል እንዲሁም በአመት 3 ጊዜ በምናካሂደው የደንበኞች ፎረም ማሰማት ይችላሉ ብለዋል፡፡

Read 18911 times