Saturday, 10 August 2013 12:23

በዛሬው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለድል ይጠበቃሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(11 votes)

ዛሬ የሚጀመረው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመክፈቻ ውድድር በሆነውና የመጀመርያው የሜዳልያ ሽልማት ስነስርዓት በሚደረግበት የሴቶች ማራቶን እንዲሁም በወንዶች 10ሺ ሜትር በሚካሄደው የመጀመርያው የትራክ ፍፃሜ ውድድር፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለቀጣይ ውድድሮች መነቃቂያ የሚሆኑ ድሎችን ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
205 አገራትን የወከሉ ከ2500 በላይ አትሌቶች ይሳተፉበታል የተባለውንና በ200 አገራት በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት የሚተላለፈውን 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ 5 ቢሊዮን የሚደርስ ተመልካች ይከታተለዋል፡፡
ቲኪ ገላና ፤ ማራቶን ልዕልቷ
በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረጉት የኦሎምፒክ፤ የዓለም ሻምፒዮና እና ትልልቅ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያ እና የኬንያ ማራቶኒስቶች ውጤታማ መሆናቸው፣ በሞስኮ የሴቶች ማራቶንም የሜዳልያው ድል ከሁለቱ አገራት አትሌቶች እንደማይወጣ ከፍተኛ ግምት ያሳደረ ሆኗል፡፡ ይሄም ሆኖ በውድድሩ የሞስኮ የአየር ንብረት እስከ 30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይሆናል ተብሎ መጠበቁ፣ ውድድሩን ለአፍሪካውያን አትሌቶች ፈታኝ እንደሚያደርገውና ምናልባትም የራሽያ፤ የጃፓንና አሜሪካ አትሌቶች ሊያሸንፉ የሚችሉበት እድል ሊፈጠር እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
በ29ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ፣ በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው ቲኪ ገላና ከሁሉም ልቃ ልታሸንፍ እንደምትችል ግምት ተሰጥቷታል፡፡ ቲኪ በማራቶን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ክብሯ ላይ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን ከቻለች፣ ይህን ድርብ ድል በመጎናጸፍ ሁለተኛዋ አትሌት ትሆናለች፡፡ በዚህ የውጤት ክብረወሰኗ የምትታወቀው በ1987 እ.ኤ.አ በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን ከሆነች በኋላ በሲኦል ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው ፖርቱጋላዊቷ ሮዛ ሞታ ነበረች፡፡ ከቲኪ ገላና ሌላ ይህን እድል ይዛ ሞስኮ ላይ የምትሮጠው በአቴንስ ኦሎምፒክ 2004 እ.ኤ.አ ላይ የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው የጃፓኗ ሚዚኩ ኒጎቺ ብትሆንም የማሸነፍ እድሏ ጠባብ ነው ተብሏል፡፡
ከ2 ዓመት በፊት በደቡብ ኮርያዋ ከተማ ዳጉ በተደረገው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ የኬንያ ማራቶኒስቶች ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በመግባት የበላይነት ቢይዙም፣ በዘንድሮው ውድድር ግን እምብዛም ግምት አልተሰጣቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት ትልልቅ የማራቶን ውድድሮችን ያሸነፉ ማራቶኒስቶችን በሞስኮ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማሳተፏ ከፍተኛ ግምት አስገኝቶላታል፡፡ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ ቲኪ ገላና፤ ዘንድሮ በተካፈለችበት የለንደን ማራቶን 2 ሰዓት ከ36 ደቂቀቃ ከ55 ሰኮንዶች በማስመዝገቧ ከዓለም ሴት ማራቶኒስቶች በ2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በውድድር ዓመቱ የፍራንክፈርት ማራቶንን ያሸነፈችው መሰለች መልካሙ፤ ከዓለም 10ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ የአምስተርዳም ማራቶንን ያሸነፈችው መሰረት ሃይሉ፤ ከዓለም 12ኛ፣ ከዓለም 13ኛ የሆነችው መሪማ መሃመድ እና የፓሪስ ማራቶንን ያሸነፈችው ፈይሴ ታደሰ በኢትዮጵያ ቡድን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በማራቶን ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ከአንድ በላይ የወርቅ ሜዳልያ አግኝታ አታውቅም፡፡ በ2001 እ.ኤ.አ ገዛኸኝ አበራ ብቸኛው የወርቅ ሜዳልያ ባለ ድል ነበር ፡፡ በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው ያስመዘገበችው ብቸኛው ሜዳልያ በ2009 እ.ኤ.አ አሰለፈች መርጊያ ያስመዘገበችው ነሐስ ብቻ ነው፡፡

10ሺ ሜትርና የኢትዮጵያ ያልተደፈረ ክብር ፤ የርቀቱ ንጉስ በሌለበት
በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር የምንግዜም ምርጥ ሯጭ የሆነው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አለመሳተፍ ያልተጠበቀ ክስተት ሆኖ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ በርካታ የአትሌቲክስ ሚዲያዎች፣ ቀነኒሳ በቀለ በ10ሺ ሜትር የኢትዮጵያ ቡድን በተጠባባቂነት በመያዙ እና በ5ሺ ሜትር ባለመመረጡ ግራ ተጋብተዋል፡፡
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር በተጠባባቂነት መያዙ የመወዳደር እድሉን እንደሚያጠብበውና በሙሉ ብቃት ለመወዳዳር እንደማይችል በመረዳት ወደ ውድድሩ ላለማቅናት መወሰኑን ተናግሯል፡፡ ይህ ችግር ሊፈጠር የቻለው ለ3 ዓመታት ከዘለቀበት ጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ባለማገገሙ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
በዛሬው 10ሺ ሜትር ውድድር ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ግምቱን የጠየቅነው ቀነኒሳ፤ በርቀቱ የሚካሄደው ውድድር በወቅታዊ ብቃት ላይ የሚወሰን እንደሆነ ገልፆ፣ ከሁሉም የትራክ ውድድሮች ለግምት የሚያስቸግረው 10ሺ ሜትር ነው ብሏል፡፡ በፈታኝነቱ በሚታወቀው በዚህ ውድድር፤ ቀነኒሳ በቀለ አለመሳተፉን ተከትሎ የወርቅ ሜዳልያው ግምት በዋናነት ለእንግሊዛዊው ሞፋራህ ተሰጥቷል፡፡ በወንዶች የ10ሺ ሜትር ቡድን ከ2 ዓመት በፊት በዴጉ የዓለም ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበውና በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆነውን ኢብራሂም ጃይላን ጨምሮ ደጀን ገብረመስቀል፣ አበራ ኩማና ኢማና መርጋ ኢትዮጵያን ይወክላሉ፡፡
ቀነኒሳ በ10ሺ ሜትር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አራት የወርቅ ሜዳልያዎች፤ በኦሎምፒክ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች የወሰደ ብቸኛ አትሌት ነው፡፡ በርቀቱ የዓለም ሪከርድ እና የዓለም ሻምፒዮና ሪከርድም በእጁ ይገኛል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን ከያዘ 10 ዓመት እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን ከያዘ 7 ዓመት ሆኖታል፡፡ በሞስኮ የዓለም ሻምፒዮና ባይሳተፍም በሪከርዶቹ ሳቢያ ከሁለቱም ርቀቶች ውድደሮች ጋር ስሙ መነሳቱ እንደሚያፅናናው የሚናገረው ቀነኒሳ ይህን ታሪኩን ቢኩራራበትም ምንም ገቢ እንደማያገኝበት አብራርቷል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ቀነኒሳ በቀለ፤ 6 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ እና 1 የነሐስ) በማስመዝገብ፣ ከዓለም 6ኛ ከኢትዮጵያ 2ኛ ነው፡፡ በ2011 እ.ኤ.አ በ12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ሲጎናፀፍ 26 ደቂቃ ከ46.31 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዱ ነው፡፡በ10 ሺ ሜትር ወንዶች ከ1983 እ.ኤ.አ ጀምሮ በተካሄዱ 13 የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ 9 የወርቅ ሜዳልያዎች ወስዳለች፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ፤ 9 የወርቅ፣ 4 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡

Read 4572 times