Saturday, 10 August 2013 12:10

ሚሊየነሩ መቃብር ቆፋሪ

Written by  ዮፍታሔ ካሣ
Rate this item
(25 votes)

የጉልማ መላኩ ሕይወትን የሚቀይር ተአምር የተፈጠረው እንደ ልማዱ በማለዳ ተነስቶ ወደ ሥራው እየሄደ ሳለ ነበር፡፡ ተአምሩ በተከሰተበት ዕለት ባለቤቱ ጐጄ፣ ከውድቅት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በመነዝነዝ፣ እንቅልፍ በዓይኑ ሳይኳል እንዲያድር አድርጋው ነበር፡፡ ከንዝንዟ ለመሸሽ በጠዋት ተነስቶ ወደ ሥራው ሲሄድ ነው ተአምሩ ያጋጠመው፡፡ የሚስቱ ጭቅጭቅ በውኃ ቀጠነ ተልካሻ ምክንያት ተጀምሮ፣ ወደ ኑሯቸው የሚመጣ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡
“ከጓደኞቼ በታች አደረከኝ፡፡ አንተ ስለመሻሻል አስበህ አታውቅ፡፡ ሲፈጥርህ ጅል አድርጐ ነው፡፡ ይኸው መቃብር ቆፋሪ ሆነህ ስንት ዓመት? 28 ዓመት ሙሉ ከመቃብር ቆፋሪነት ሳትሻሻል---- ውይይይይይ” ጐጄ ታማርራለች፣ እንደማልቀስ ይቃጣታል፡፡
“29 ዓመቴ ነው ሟቾችን በማሳረፍ ሙያ ላይ ከተሰማራሁ” ይላታል እያረማት፡፡ ጉልማ ራሱን የመቃብር ቆፋሪ ብሎ አይጠራም፤ “ሟቾችን የማሳረፍ ሥራ” ብሎ ነው ሙያውን የሚገልፀው፡፡ በሙያው ላይ ካሳለፈው ጊዜ ቅንጣት እንዲቀነስበት አይፈልግም፡፡ ጐጄ በሰጣት እርምት ብው ብላ ትጨሳለች!!
“ቁም ነገር ሆኖ ነው አፍህን ሞልተህ 29 ዓመት የምትለው? ኢንጂነር የሆንክ መሰለህ? ወይስ ማዕድን ቆፋሪ ? የሬሳ መቀበሪያ እየቆፈርክ እኔንም ሬሳ አድርገኸኝ ኖርክ፡፡ እንደው የአባቴ አምላክ ይድፋህ---ጅል ጅላንፎ!” የእርግማኗን ዶፍ ታወርድበታለች፡፡
ጉልማ ግን አይናገራትም፡፡ ዝም ይላል፡፡ ዝምታው ይብስ ያናድዳታል፡፡ ሚስቱ ብቻ ሳትሆን የመንደሩ ሰው ሁሉ ነው በጅልነቱ የሚዘባበተው፡፡ የጉልማ ጅልነት ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡
“አይ ጉልማ ጅል እኮ ነህ” ሲሉት ሳቅ ብሎ ከመሄድ ባለፈ ቅርታ አይገባውም፡፡ በሕይወቱ ደስተኛ ነው፡፡ ሁሉን ነገር ይወዳል፡፡ በመቃብር ቁፋሮ ሥራው፣ በሚስቱን መነጫነጭ፣ በጐረቤቶቹን ንቀት ወዘተ--- በሁሉም ነገር ደስተኛ ነው፡፡ ያቺ ሕይወት ለሱ እንደተጣፈች ያምናል፡፡ የሚስቱን ጭቅጭቅ እንደ ሕይወቱ ሙዚቃ ነው የሚቆጥረው፡፡ ለማማረር ጊዜ የለውም፡፡
“እኔኮ እንደሌላው ወንድ ቢሰድበኝ፣ ቢመታኝ በማን ዕድሌ?” ትላለች፣ባለቤቱ ጐጄ ዝምታው ሊያሳብዳት ሲደርስ፡፡
ጠጅ የጠጣ ቀን ብቻ ረጋ ብሎ የመቃብር ቆፋሪነትን (በሱ አጠራር ሟቾችን የማሳረፍ ሙያ) ክብር ሊያስረዳት ይሞክራል፡፡ “አየሽ ጐጄ፤ በምድር ላይ መቃብር የመቆፈርን ያህል የተከበረ ሙያ የለም፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ የኛ ደንበኞች ናቸው፤ እስቲ ምድር ላይ ካለ ሰው ወደኛ የማይመጣ ጥሪልኝ”
ከባድ ጥያቄ እንደጠየቃት በማመን ያፈጥባታል፡፡
“ደሞ ሙያ ይልልኛል ---- ምን የረባ ሙያ ሆኖ ነው?” መልስ ሲመልስላት ደስ ስለሚላት ረጋ ትላለች፡፡
“ብዙ ሙያ ብዙ ጥበብ አለው እንጂ---- እይው መጀመሪያ አፈር መምረጥ አለብሽ፤ ካህናት የሚቀበሩበት አፈር ልል መሆን አለበት፤ ይኼ ደለል እንዳመጣው ዓይነት፤ ጀግና የሆነ እንደሆን መረሬ አፈር መምረጥ አለብሽ…ምንም ያላገባች ሴት ከሆነች ደግሞ በዛፍ መካከል፤ ሀብታም የሆነ እንደሆነ ደግሞ ለምለም ሳር ያለው ቦታ ላይ ነው መቀበሪያው፡፡ መቃብሩ ሲቆፈር ደግሞ እንደው ዝም ብሎ መሬቱን ድርምስ እያደረጉ አይደለም፤ ከላይ እንደ እርከን እያደረግሽ በየደረጃው ትወርጅና እያጠበብሽ እያጠበብሽ…” ጉልማ ማስረዳቱን ይቀጥላል፡፡ ባለቤቱ ጐጄ የተናገረ ቀን ጭቅጭቋ ይቀንሳል፡፡ ክፋቱ ግን ጉልማ ብዙ የመናገር ፍላጐት የለውም፡፡ ዝምታው የሕይወቱ ዋሻ ነው፤ ራሱን የሚደብቅበት፡፡ ዝምታውን ተከትላ ጐጄ ቤቱን ስታምሰው ታመሻለች፡፡
የጐጄን ንዝነዛ ለማምለጥ በጠዋት በወጣበት ማለዳ ነበር ተአምሩ ያጋጠመው፡፡ ጐጄን ምንም ሳይናግራት ወደ መቃብር ቁፋሮ ሥራው እየሄደ ሳለ፤ ከቤተክርስትያኑ መግቢያ ላይ ሊደርስ ትንሽ ሲቀረው፤ ከቀጭኗ አስፋልት ዳር ላይ አንድ የሆነ ሻንጣ የመሰለ ነገር ያየ መሰለው፡፡ መጀመሪያ የወደቀውን ሻንጣ እንዳላየ ሆኖ ሊያልፈው ነበር፡፡ አንዳች የማያውቀው ውስጣዊ ስሜቱ ግን እግሮቹን አስሮ እንዳይንቀሳቀስ አደረገው፡፡ በቆመበት አፍታ ከራሱ ጋ ትንሽ ተሟገተ፡፡
“ምን ሊሆን ይችላል?” የሚል ዓይን ያወጣ ጉጉት በአንድ በኩል፤ “አንድ ሰው ጥሎት ይሆናል፡፡ አንስቼ ለፖሊስ ባስረክበው” የሚል ትሁት ጉጉት በሌላ በኩል ገፋፉት፡፡
ሻንጣውን በማንሳት ወስኖ የቀጭኗን አስፋልት ግራና ቀኝ ቃኘ፡፡ የሰው ዘር አይታይም፡፡ ሻንጣውን ቀስ ብሎ አነሳው፡፡ ከበድ ያለ ነበር፡፡ “ምን ቢኖርበት ነው እንዲህ የከበደው” እያለ የመቃብር ቁፋሮ ወደሚሠራበት ቤተክርስቲያን መጣደፍ ጀመረ፡፡ ትንሽ እንደሄደ ሦስት ቱታ የለበሱ ወጣቶች ከፊት ለፊቱ እየሮጡ ሲመጡ አያቸው፡፡ አንዳች ቦታ ሊደበቅ ቢፈልግም ከመደበቁ በፊት ወጣቶቹ በሶምሶማ ዱብ ዱብ እያሉ አልፈውት ቁልቁል ሄዱ፡፡ በእፎይታ ተንፍሶ ወደ ደጀ ሰላሙ ገባ፡፡
በቤተክርስትያኑ ውስጥ የተወሰኑ ምዕመናን የቅዳሴ መግቢያ ሰዓት እንዳያልፍባቸው ወደ መቅደሱ ይቻኮላሉ፡፡ ሻንጣውን እንደያዘ ከቤተክርስትያኑ ጀርባ ወዳለው መቃብር ሥፍራ እየተጣደፈ ሄደ፡፡ የመቃብር ቦታው ጭር ብሏል፡፡ የመቃብር ሥፍራው ፀጥታ ሁሌም ይማርከዋል፡፡ በሀውልቶቹ ላይ እየተረማመደ ወዲያና ወዲህ ሲል ፍፁም ሀሴት ያደርጋል፡፡
ዓለምን ሲያንቀጠቅጡ የነበሩ ሰዎች በሙሉ በእግሩ ሥር ናቸው፣ እሱ ብቻ ነው ሕያው፤ እሱ ብቻ ነው የማለዳዋን ፀሐይ መምጣት በናፍቆት መጠበቅ የሚችለው፡፡ የመቃብር ቦታው ፍቅር አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ገብቷል፡፡ አሁን ግን ቀልቡ ሁሉ ሻንጣው ላይ ነው፡፡ የወትሮ ልማዱን ትቶ ሻንጣውን ለመክፈት ቦታ መምረጥ ጀመረ፡፡ “ሻንጣው ውስጥ ምን ይሆን ያለው” የሚለው የጉጉት ስሜቱ አእምሮውን ሊያፈነዳው ሲደርስ ወደ አንደኛው መቃብር ቤት ተንደርድሮ ገባ፡፡ መቃብር ቤቱን ከውስጥ ዘጋው እና ሻንጣውን ከፈተው፡፡ ሻንጣው ውስጥ ያለውን ነገር ሲያይ ሳይታወቀው ኡኡታውን ለቀቀው፡፡ ትንሽ ቆይቶ አእምሮውን የሚስት ሁሉ መሰለው፡፡ ሻንጣውን ዘግቶ በድጋሚ ከፈተው፡፡ ዓይኑን ማመን አልቻለም፡፡ ሻንጣው በአዳዲስ የኢትዮጵያ ብር እና የአሜሪካ ዶላሮች የተሞላ ነበር፡፡ ጉልማ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ፣ አፉ ደረቀበት፡፡ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጣ፡፡ በሕልም እና በእውን መካከል የሚቃዥ መሰለው፡፡
“ምንድነው-- ምንድነው--- ምንድነው…?” አለ ሳይታወቀው፡፡
“አምላኬ ሆይ-- ይህን ያህል ዘመን በመቃብር ቆፋሪነት ሕይወቴን እንድገፋ ያደረከኝ ይኼንን ቀን አስበህልኝ ነው ለካ” ያለልቡ በጉልበቱ ተንበረከከ፡፡
“አምላኬ ሆይ ተመስገን! ተመስገን! የባለቤቴን ጭቅጭቅ ሰምተህ መሆን አለበት ይኼንን በረከት የላከልኝ” የሚስቱ ጐጄ ጦር ምላስ፣ ወደ ወጥ መቅመሻ እና መላሻነት ሲለወጥ፣ የሚኖረውን ሕይወት ለአፍታ በሰመመን ቃኘው፡፡ ምርጊቱ የፈራረሰው የቀበሌ ቤቱ ተቀይሮ ቪላ ቤት ውስጥ ሲኖር፣ በመቃብር ቁፋሮ የቆረፈዱ እጆቹን በወይራ ዘይት እየታሸ ሲዝናና፣ በብርድ የተቆራመደ ገላው በሙቅ ውኃ እየረሰረሰ ሲቀማጠል …እነዚህን ሁሉ ነገሮች ሲያስብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳለፈው ሕይወት ምን ያህል አስከፊ እንደነበረ ወለል ብሎ ታየው፡፡
“ጐጄ ልክ ነበረችና! ምን ዓይነት አስከፊ ሕይወት ውስጥ ነው የምንኖረው!” ኑሮው አንገሸገሸው፡፡
የሕይወቱን ከግማሽ በላይ ዓመታት በመቃብር ቁፋሮ ማሳለፉን ሊያምን አልቻለም፤ ሙያው፣ አብረውት የሚሰሩት ሰዎች፣ ጐረቤቶቹ፣ የሚኖርበት ሰፈር…አስከፊነት ወለል ብሎ ታየው…ወደፊት የሚኖረውን ህይወት ሲያስብ ልቡ በደስታ ይዘል ጀመር፡፡ በተመስጦ ከተቀመጠበት ስሙ ከውጪ ሲጠራ የሰማ መሰለው፡፡
“ጉልማ --- ጉልማ!!!...” ድንጋጤ መላ አካሉን ወረረው፡፡ ማን ነው ሊጠራው የሚችለው? ሻንጣውን ይዞ ሲገባ ያየው ሰው ይኖር ይሆን? ጥርጣሬ እንደ ግሪሳ ወፍ ወረረው፡፡
“ጉልማ ጉልማ!!!...” ስሙ ተደጋግሞ ተጠራ፡፡
ሻንጣውን ወደ ጥግ አስቀምጦ ድንጋይ ጫነበት፡፡ ግራ ቀኙን በጥርጣሬ እየቃኘ የመቃብር ቤቱን በር ከፍቶ ወጣ፡፡ የቤተክርስትያኑ ዘበኛ ነበር የሚጣራው፡፡ ጉልማን እንዳየው ወደሱ መምጣት ጀመረ፡፡ ከኋላው ሁለት ሰዎች አሉ፡፡ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት፡፡
“አላልኳችሁም--- የፈለገ ተአምር ቢፈጠር ይህ ጅላጅል መቃብር ቆፋሪ፣ ከዚህ አይጠፋም” እያለ ዘበኛው ወደ ጉልማ ቀረበ፡፡
“ይኼ ጅላጅል ነው ያልከው አንተ” አለ ጉልማ፣ በደምፍላት ስሜት ተሞልቶ፡፡
ዘበኛው በግርምት እና በድንጋጤ ጉልማን አፍጥጦ አየው፡፡ ጉልማ ሲቆጣ አይደለም ተሳስቶ እንኳን ኃይለ ቃል ሲናገር ሰማሁ የሚል ሰው ታይቶ አይታወቅም፡፡ የጅል ምሳሌ ተደርጐ ቢቀርብ፣ የሞኝ መለያ ተደርጐ ቢጠራ ምንም ቅር የማይለው ፍጡር ነበር ጉልማ፡፡ ዘበኛው በጉልማ ላይ ባየው ድንገተኛ ለውጥ ግራ ተጋብቶ ለአፍታ ዝም ካለ በኋላ፣ ተከትለውት ወደመጡት ሰዎች እያመለከተ መናገር ጀመረ፡፡
“ሥራ ይዤልህ ነው የመጣሁት” አለ ረጋ ብሎ፡፡ “እ…ሟች ከአውሮፓ ነው ሬሳው የሚመጣው--- ጥሩ ቦታ ፈልገህ የመቃብሩን ጉድጓድ እንድታዘጋጅለት ነው የሚፈልጉት--- ያው ዋጋ ተደራደሩ” አለ ለድርድር በሚጋብዝ ሁኔታ እጆቹን ወደ ጉልማና ወደ ሰዎቹ እየዘረጋ፡፡ ጉልማ ግን መልስ ያለው አይመስልም፡፡ ዘበኛውን በንቀት ተመለከተው፡፡ ዘበኛው በጉልማ ሁኔታ ግራ መጋባቱ በግልጽ ያስታውቃል፡፡
“ይኼ ጅል ዛሬ ምን ነካው” አለ ለራሱ፡፡
“እ---የተለመደ ዋጋው 300 መቶ ብር ነው---ባላችሁት ሰዓት ያደርሳል” አለ ዘበኛው፣ ወደ ሰዎቹ እያየ፡፡
“ዋጋው ላይ ችግር የለም፡፡ ጥሩ ቦታ መርጦ በደንብ ያዘጋጅልን፡፡ 1000 ብር እንከፍላለን…ከመንገድ ብዙ ባይገባ ደስ ይለናል” አለች ሴትየዋ፡፡
“ሌላ መቃብር ቆፋሪ ፈልጉ--- እኔ ለመቆፈር ፈቃደኛ አይደለሁም” አለ ጉልማ ጀነን ብሎ፡፡ ዘበኛው በንዴት ጦፈ፡፡ “ጉልማ ዛሬ ጤነኛ አልመሰልከኝም--- ከሶስት እጥፍ በላይ ዋጋ ሰጥተውህ ከዚህ በላይ አምጡ ነው--- ኧረ ተው እናንተ መቃብር ቆፋሪዎች ግን እግዜርን ፍሩ፤ ኧረ ተው” አለ ዘበኛው እያማተበ፡፡
“ለገንዘቡ ችግር የለም--- 2000 ብርም ቢሆን ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ብቻ ጥሩ ቦታ እና ከመንገድ ብዙ ያልገባ--- ደህና ሰው መቃብር አጠገብ ይሁን” አለች ሴትየዋ፡፡ ለገንዘብ ብዙ ጭንቅ የለባትም፡፡ በቅርቡ የሞተው ሽማግሌ ባሏ ትቶላት የሄደው በቂ ሀብት አላት፡፡ ከሁኔታዋ ባለቤቷ ዳግም እንዳይነሳ አርቃ ልታስቀብረው የፈለገች ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብቃት ያለው ቆፋሪ ያስፈልጋል፡፡
“ኧረ ተባረኪ ተባረኪ እንዴት ያለ መቃብር ቆፋሪ መሰለሽ? በሙያው ስለሚተማመን ነው እኮ ትንሽ እንትን ያለው…” አለ ዘበኛው ሥራውን በማምጣቱ የሚያገኘውን ኮሚሽን እያሰበ ተደስቶ፡፡
“እኔ ፈቃደኛ አይደለሁም” አለ ጉልማ በስጨት ብሎ
“ብር ከሆነ ችግር የለውም 3ሺህ ብርም ቢሆን…” ሴትየዋ እልህ የተጋባች ትመስላለች፡፡
“ጉልማ ኧረ ተው እግዜር አይወደውም--- 3ሺህ ብር ለአንድ ክንድ መሬት” ዘበኛው ንዴት ገብቶታል፡፡
“የብሩ ጉዳይ አይደለም--- እኔ መቃብር ቆፋሪነቱን ትቼዋለሁ ---ይኼንን ቀፋፊ ሥራ እስከዘላለሙ ትቻለሁ” አለ ጉልማ ረጋ ብሎ፡፡
“እኮ አንተ መቃብር ቆፋሪነቱን ተውከው?” ዘበኛው ባለማመን ጉልማን እየተመለከተው፡፡
“መቃብር ቆፋሪነትህን ትተህ ምን ልትሆን ነው ነው? አንተ ራስህ ልትሞት አሰብክ?” ዘበኛው ግራ ገብቶት እንደብራቅ ጮኸበት፡፡
“አንተ ሰውዬ አፍህን ብትዘጋ ይሻላል--- አትጩህ” አለ ጉልማ፤ አካፋ የሚያህል እጁን በማስጠንቀቅ ወደ ሰማይ እያነሳ፡፡
ዘበኛው ክፉኛ ደነገጠ፡፡ ጉልማ አንዴ በጥፊ ቢለው መጋኛ አጠናግሮት ከሚደርስበት ጉዳት አስር ጊዜ የበለጠ ጉዳት እንደሚደርስበት እርግጠኛ ነበር፡፡
“አይ…እኔኮ 3ሺ ብር ብዙ ነው ብዬ ነው ጉሌ…አስበው እስቲ 3ሺህ ብር!” ዘበኛው በጉጉት ምራቁን ዋጠ፡፡
“አትሰማኝም?! እኔ መቃብር ቆፋሪ አይደለሁም!!” አለ ጉልማ ወደ ሁሉም በየተራ እያፈጠጠ፡፡
ዘበኛው ጉልማ ያበደ መሰለው፡፡ ሌላ መቃብር ቆፋሪ ማናገር አለበት፡፡ ሰዎቹን እያቻኮለ ወደ መቃብሩ መውጫ ወሰዳቸው፡፡ ጉልማ ግራ ቀኙን እያየ በጥንቃቄ ወደ መቃብር ቤቱ ተመለሰ፡፡ አንድ ሰው በመቃብሮቹ ተከልሎ የሚያየው መሰለው፡፡ ምናልባትም እሱ እስኪርቅ ጠብቆ ገንዘቡን ማንሳት የሚፈልግ ሰው እንዳለ እየጠረጠረ፣ ቀስ ብሎ ወደ መቃብር ቤቱ ተመለሰ፡፡ ሻንጣው መኖሩን አረጋግጦ በእፎይታ ተነፈሰ፡፡
“ሴትየዋ ግን 3ሺ ብር ለመክፈል እንዴት ፈቃደኛ ሆነች?” በአእምሮው ውስጥ ጥርጣሬ ሽው አለበት፡፡ እሱን መቃብር እያስቆፈረች ብሩን ይዛ ልትሞጨለፍ? መጠርጠር ደግ ነው …
“እግዜር ነው ይኼን ብር የላከልኝ! እስካሁን ፍጡሮቹ በቅንነት ሳገለግል መኖሬን ተመልክቶ ሊከሰኝ ነው!” ወደ ሰማይ ቀና ብሎ አመሰገነ፡፡ የመቃብሩ ቤት በደንብ መዘጋቱን ካረጋገጠ በኋላ፣ ሻንጣው ውስጥ ያለውን ብር መቁጠር ጀመረ፡፡ ለሁለት ሰዓት ሳይወጣ መቁጠሩን ቀጠለ …
“ሁለት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ …” ቆጠራውን እንደቀጠለ ነው፣ ከውጪ ስሙ ሲጠራ የሰማ መሰለው፡፡
“ጉልማ! ጉልማ! …” የሴት ድምፅ ነው፡፡ ብሽቅ አለ፡፡ ሚስቱ ጎጄ ናት፡፡ እንደሁልጊዜው ረፈድ ሲል ለቁርስ የሚቀማምሰውን ይዛለት መጥታ ነው፡፡ ምን ብትነዘንዘው በጉልማ የሚጨክን አንጀት የላትም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎጄ መምጣት ብስጭት አለ፡፡ እንደሌለ መስሎ ዝም ሊላት ፈለገ፡፡ ዝም ካላት ደግሞ የት ገባ ብላ ችግር መፍጠሯ አይቀርም፡፡ የቆጠረውን ገንዘብ ካልቆጠረው ለመለየት በመሀል ድንጋይ ካስቀመጠ በኋላ የመቃብር ቤቱን በር ከፍቶ ወጣ፡፡
“የት ገባህ ደግሞ ዛሬ? መቼም መርመጥመጥ ነው በየመቃብሩ ሥር!” አለች ጎጄ ወደሱ እየቀረበች፡፡
“ጤና የለሽም እንዴ አንቺ ሴትዮ!” አላት ንግግሯ ብስጭት አድርጎት፡፡
ጎጄ በግርምት ሀውልት ሆና መቆም እስኪቀራት ድረስ ተደንቃ አየችው፡፡ ሌላ ሰው መሰላት፣ ጉልማ ሲቆጣ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጉልማ ስትጠብቅ ስንት ዓመት ኖራለች? የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ አልፏል፤ እያለ የሌለው፣ ለምንም ነገር ግድ የማይሰጠው፣ በስድብ እና በሙገሳ መካከል ያለው ልዩነት የማይገባው፣ በዝምታ ካባ ውስጥ ያደፈጠው ጉልማ፣ ነገ የሚባል ነገር በዓይኖቹ ውስጥ የሌሉት ጉልማ! ያ እንደኩሬ የረጋው ጉልማ --- ምን አገኘ?”
“በል ተወው--- ቁርስ ቢጤ አምጥቻለሁ--- አረፍ በልና ቀማምስ!” አለች ጎጄ ለስለስ ብላ፡፡
እንደወትሮው ከአንዱ የመቃብር ሀውልት ላይ ቁጭ ብለው ያመጣችውን ሰሀን አቀበለችው፡፡ ሰሀኑን ከፈተው፣ ሚጥሚጣ እና ቁራሽ ዳቦ ተቀምጧል፡፡ ወሽመጡ ቁርጥ አለ፡፡
“የምትወዳትን ቁርስ ነው ያመጣሁልህ!” አለች ጎጄ ሳቅ እያለች፡፡
“ይኼን መናኛ ቁርስ ነው የምወደው? … በይ ይኼ ቅራቅንቦሽን ይዘሽ ወደምትሄጅበት ሂጅልኝ!” አለ ጉልማ ቁጣ ቁጣ እያለው፡፡
“ይቺን ትወዳለች ጎጄ?! … ጥሩ ቁርስ ከዚህ በላይ ከየት ይምጣልህ? አበዛኸው! ይኼ አፈር ፈንቅለህ የምታመጣው ገንዘብ ቁም ነገር ኖሮት ነው! በዛ ላይ መቅኖ የሌለው!” ጎጄ መንጣጣት ስትጀምር ጉልማ አቋረጣት፡፡
“ይኼ ልቅ አፍሽን ካልሰበሰብሽ ዛሬውኑ ከቤቴ ውጪልኝ! እኔኮ የሚገርመኝ እስካሁን ድረስ እንዴት ችዬሽ እንደኖርኩ ነው!” አለ ጉልማ ኮስተር ብሎ፡፡
“ከቤት ሲወጣ ያልነበረውን ጸባይ ከየት አመጣው?” ብላ ግራ ተጋባች፡፡
ፍርሀት ሰውነቷን ወረረው፡፡ ቃል ሳትተነፍስ ዕቃዋን ሰብስባ ተነስታ ሔደች፡፡ ጎጄን ከኋላዋ አስተዋላት፡፡ ከዚች ሴት ጋር 29 ዓመት ሙሉ መኖሩን ሊያምን አልቻለም፡፡ ፊቷ የተጠባበሰ፣ የተቆረጠ ነጠላ ጫማ የምታደርግ፣ የተቀደደ ቆሻሻ ቀሚስ የለበሰች፣ በዛ ላይ ምላሳም … ከዚህች ሴት ጋር ከአሁን በኋላ መኖር የለበትም፤ ሌላ ሚስት ያስፈልገዋል፡፡ ምናልባትም ልጅ፣ ሰውነቷ እንደ እስፖንጅ የሚለሰልስ፣ ምላሳም ያልሆነች …
ድንገት ዞር ሲል አንበሉ አጠገቧ ቆሟል፡፡
“አጅሬ ---ማታ ጠጅ አበዛህ እንዴ? እኛ ስድስት መቃብር ስንቆፍር አንተ ምንም አልሠራህም አሉ! ለማንኛውም የጠዋት ደንባችንን አድርሰን እንምጣ! … ሁለት ብርሌ ልጋብዝህ!”
አምበሉ አብሮት መቃብር በመቆፈር የሚተዳደር ባልደረባው ነው፡፡ መልኩ ጥቁር ነው፡፡ በዛ ላይ ግዙፍ፡፡ እንደዚህ ሰይጣን ከመሰለ ሰው ጋር ጓደኛ ሆኖ መኖሩ በውስጡ ግርምት ፈጠረበት፡፡
“ሒድ! እኔ ትንሽ ልቆይ!” አለ ጉልማ
“አቤት--- በጠጅ ጨክነህ? ግዴለህም ና እጋብዝሀለው!” አለ አንበሉ ፍርጥም ብሎ
“አልሔድም አልኩህ!” አለ ጉልማ ቆጣ ብሎ፡፡
አንበሉ በግርምት ለአፍታ አየውና ትከሻውን በምን ቸገረኝ ወደ ላይ ሰብቆ “በጠጅ ጨከንክ? ተመስገን! ተመስገን!” እያለ ወደ ጠጁ ተቻኮለ፡፡
የአንበሉን መሔድ ተከትሎ ስሙ ሲጠራ ሰማ፡፡
“ጉልማ! ጉልማ!...” የቤተክርስቲያኑ ጥበቃ ሌሎች ሰዎችን አስከትሎ ወደሱ ሲመጣ ተመለከተው፡፡
“ይኼ ሰውዬ መቃብር ቆፋሪነቴን አቁሜያለሁ ማለት አይገባውም?” ንድድ አለው፡፡
“መቃብር ቆፋሪነቴን አቁሜያለሁ! አይገባህም?” አለ ጉልማ በንዴት ፀጉሩን እየነጨ፡፡
ሰዎቹ ወደሱ ሲቀርቡ በቸልታ ቆሞ ጠበቃቸው፡፡
“ጉልማ እሱ ነው!” አለ ዘበኛው ወደ ጉልማ እየጠቆመ፡፡
“አቶ ጉልማ አንተ ነህ?” አለ ከዘበኛው ጀርባ ከቆሙት ሰዎች መካከል አንደኛው፡፡
ጉልማ ከዘበኛው ጀርባ የቆሙትን ሰዎች አስተዋላቸው፡፡ ሻንጣውን ካገኘ በኋላ፣ ቱታ ለብሰው ስፖርት ሲሠሩ የነበሩት ወጣቶች ናቸው፡፡ ከኋላቸው ፖሊሶች አሉ፡፡
“አቶ ጉልማ ጠዋት ወድቆ ያገኙት ገንዘብ …” ፖሊስ ንግግሩን ሳይጨርስ ጉልማ ራሱን ስቶ ወደቀ፡፡
ከአዘጋጁ - (ከላይ የሰፈረው ታሪክ “በአራጣ የተያዘ ጭን” ከሚለው በቅርቡ ለንባብ የበቃ የአጭር ልብወለድ መድበል የተወሰደ ሲሆን በዝግጅት ክፍሉ መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበት የቀረበ ነው)

Read 3532 times