Saturday, 10 August 2013 11:42

ሸዋ ሃይፐርማርኬት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

ፈር ቀዳጁ የገበያ ማዕከል

የውጭ ገንዘብ መመንዘሪያ (ፎረክስ ቢሮ)
በየሳምንቱ ሰርፕራይዝ አለ
የንፅህና መስጫ (ላውንደሪ)
ብዙ መሸመት ያሸልማል
የሕፃናት ማቆያ

 ዴፓርትመንት ስቶር፡- የተለያዩ ምርቶችና ሸቀጦች በዓይነት ዓይነታቸው ተለይተውና የራሳቸው ስፍራ ተሰጥቷቸው ለሸማቾች የሚቀርቡበት በጣም ትልቅ የችርቻሮ ገበያ ማዕከል ነው፡፡ የገበያ ማዕከሉ እስከ መቶ ዴፓርትመንት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለምሳሌ፣ ራሱን የቻለ የልብስ፣ የምግብ፣ የእርሻ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የቤት ዕቃዎች፣ ዴፓርትመንት (ክፍል) ሊኖረው ይችላል። 

ሱፐርማርኬት፡- ተገልጋዩ ራሱ የሚፈልገውን ዕቃ በመምረጥ (ለምሳሌ የምግብ፣ የቤት ዕቃ፣ የሕፃናት መገልገያ፣ …) የሚገዛበት የችርቻሮ ገበያ ማዕከል ነው፡፡
ሃይፐርማርኬት፡- ዴፓርትመንት ስቶርንና ሱፐርማርኬትን አጠቃሎ የያዘ በጣም ግዙፍ (ሱፐር ስቶር) የገበያ ማዕከል ማለት ነው፡፡
* * *
በአገራችን ዴፓርትመንት ስቶር ለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሱፐርማርኬት ግን ሸዋ ሱፐር ማርኬት “ሱማሌ ተራ” ከተከፈተበት ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 50 ዓመታት ያህል ይታወቃል፡፡ ሸዋ ሱፐርማርኬት፣ አምስት የገበያ ማዕከላትን በቦሌ፣ በጦር ኃይሎች፣ በሳር ቤት፣ በሲኤምሲ አካባቢ ከፍቶ ሲሠራ ከቆየ በኋላ፣ ሰሞኑን ደግሞ መገናኛ አካባቢ ከቤተልሔም ፕላዛ ፊት ለፊት በዘፍመሽ ግራንድ ሞል (ትልቅ የገበያ ማዕከል) ስድስተኛ ቅርንጫፉን ከፍቷል - “ሸዋ ሃይፐርማርኬት” በሚል፡፡ የሸዋ ሱፐርማርኬት መስራችና ባለቤት ማን እንደሆኑና ከምን ተነስተው እንደከፈቱት ወደ ኋላ ላይ እመለስበታለሁ፡፡
በ3ሺ ካ.ሜ ላይ ባረፈው ሸዋ ሃይፐርማርኬት ሲገቡ፣ መገረምዎና መደነቅዎ አይቀርም፡፡
የዕቃዎች ዓይነት፣ ብዛትና ጥራት አጃኢብ ያሰኛል፡፡ በገበያ ማዕከሉ ፈልገው የሚያጡት ነገር የለም፡፡ “ደንበኞቻችን የሚፈልጉትንና መርካቶም ሆነ ሌላ ቦታ ሄደው የሚገዙትን ማንኛውንም ነገር (ምግብ፣ የቤት ዕቃ፣ የሕፃናት መገልገያ …) እዚሁ በአንድ ቦታ እንዲያገኙ አድርገናል” ይላሉ የሸዋ ሃይፐርማርኬት ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማይ ዓለማየሁ፡፡
አሁን በምሥራቅ በር እንግባና እንጐብኝ። የነገው አገር ተረካቢ ሕፃናት ጤናማ ሆነው፣ ምቾትና ፍላጐታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ከተወለዱበት ዕለት ጀምሮ የሚያስፈልጋቸው ነገር በዘርፍ በዘርፉ ተዘጋጅቷል። ምግብ፣ የገላ ማጠቢያ፣ መታቀፊያ፣ ልብስ፣ ጡጦ፣ ቅባቶች፣ ሻምፑዎች፣ የንፅህና መጠበቂያ ዳይፐር፣ የገላ መጥረጊያ ዋይፐር፣ ከፍ ሲሉ ደግሞ እንደ የዕድሜያቸው ጫማና ነጠላ ጫማ፣ የተለያዩ መጫወቻዎች፣ አሻንጉሊቶች፣ መኪኖች፣ የተለያየ መጠን ያላቸው አልጋዎች፣ የመመገቢያ ጠረጴዛ፣ ዳዴ ከማለታቸው በፊት የሚጠቀሙበት ጋሪ፣ ግራውንድ ፕላስ ዋን መጫወቻ ቤት፣ … ኧረ ስንቱ! ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ “አራት መደርደሪያ ሙሉ፣ (ከፊትና ከጀርባ ስምንት) ሸቀጦች መዘጋጀታቸው ለሕፃናት የተሰጠውን ትኩረት ያመለክታል” ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡
ከሕፃናት መደብር ቀጥሎ የጽሕፈት መሳሪያዎች ናቸው ያሉት፡፡ ከትንሿ ነገር እስከ ትልቁ የፋይል ማቀፊያ 300 ዓይነት የጽሕፈት መሳሪያዎች አሉ፡፡ በዳር በኩል በስተግራ ኮስሞቲክስና ሽቶ፣ ጥራት ያላቸው ሞባይሎችና መለዋወጫዎች፣ ልዩ ልዩ የወርቅና የብር ጌጣጌጦች ይታያሉ፡፡ ሸሚዞች፣ የአዲዳስ ጫማዎች፣ ቱታዎችና የስፖርት ትጥቆች፣ … የሚሸጡበት ቡቲክ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚያ ፊት ለፊት ደግሞ የተለያየ ዓይነትና መጠን ያላቸው የጉዞ ሻንጣዎች (ላጌጅስ)፣ በፀሐይ ኃይል (ሶላር ሲስተም) የሚሠሩ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ አምፑሎችና ኮምፒዩተር አክሰሰሪዎች (ሃርድ ዌርና ሶፍት ዌር) … በወግ በወጉ ተሰትረዋል፡፡
ከቡቲክ ቀጥሎ የዲኤስቲቪ ዕቃዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው ቴሌቪዥኖች፣ ምድጃዎች፣ ፍሪጆች፣ ማይክሮዌቭ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ ውሃ ማሞቂያ፣ ጁስ መጭመቂያ፣ ፔርሙሶች፣ ሽንኩርት መፍጫ፣ … ከፊትና ከጀርባ 10 መደርደሪያ ሞልተዋል፡፡ ከዚያ በታች ያሉት የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ የንፅህና መስጫ ዱቄትና ፈሳሽ ሳሙናዎች (ዲትሬጀንቶች) ናቸው፡፡
ስንዴና ጤፍም ሃይፐር ማርኬት ገብተዋል። ነጭ ጤፍ፣ ማኛ፣ ሠርገኛ፣ ቀይ ጤፍና የስንዴ ዱቄት በ50 ኪሎ እየሆኑ ተሰናድተዋል፡፡ ሌላው የሚገርመው “ትንሿን መርካቶ” የሚመስለው የጥራጥሬና የቅመማ ቅመም ገበያ ነው፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ለውዝ፣ ተልባ፣ የተለያየ ዓይነት ቦሎቄ፣ ፈንዲሻ፣ ማኛ (ማሽ) ምስር፣ ሽንብራ ዱቤ፣ ባቄላ፣ ቡና፣ ምስርና አተር ክክ፣ የቅንጬ እህሎች፣ የተፈጨ ጐመን ዘር፣ አብሽ፣ ዘለላ ሚጥሚጣ፣ ከሙን፣ ኮረሪማ፣ ሄል፣ ቀረፋ … ኧረ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ብቻ 70 ዓይነት ጥራጥሬና ቅመማ ቅመም ንፅህናቸው ተጠብቆ በመስተዋት ቤት ተቀምጠው፣ በዲጂታል ሚዛን እየተመዘኑ ይሸጣሉ፡፡
በአዲስ አበባ ታዋቂ የሆኑት የሙልሙል ዳቦ ሠራተኞች፣ እዚያው በገበያ ማዕከሉ የድርጅቱን መሳሪያ በመጠቀም ትኩስ ዳቦና ኬክ በመጋገር ለደንበኞች ያቀርባሉ፡፡ ክሬም ኬክ ግን ሌላ ቦታ ተጋግሮ ይቀርባል፡፡ ሃይፐርማርኬቱን ልዩ የሚያደርገው ጣፋጭ የሶሪያ ኬኮችን እዚያው ጋግሮ ማቅረቡ ነው፡፡ ባቅላባና ኩኪስን ጨምሮ 22 ዓይነት ጣፋጭ ምግቦች ያሰናዳል፡፡ ከዚያው ጐን ደግሞ ትኩስ ፒዛና በርገር ይጋገራል፡፡ በደንበኛው ፍላጐት መሠረት፣ የዶሮ፣ የበሬ፣ የበግ፣ የአትክልት፣ … 26 ዓይነት በርገሮችና ፒዛ ማግኘት ይችላል፡፡ ዓሳም አለ፡፡ ደንበኛው ከፈለገ በቋንጣ፣ ካልፈለገ ትኩሱን “ፊሌቶ አውጡልኝ” ብሎ መውሰድ ይችላል፡፡ የወተት ተዋጽኦዎችም በርካታ ናቸው። የሚያስጐመጅ የሥጋ ዓይነትም አለ፡፡ እንደ ደንበኛው ፍላጐት፣ ንቅል፣ የክትፎ፣ የወጥ፣ የጭቅና፣ የበርገር፣ … ማግኘት ይቻላል፡፡
ዝቅ ሲሉ፣ ፒያሳ አትክልት ተራ የገቡ ይመስልዎታል፡፡ ፒያሳ የሚገኘው አትክልትና ፍራፍሬ በሙሉ፣ በንፅህና ታሽጐ ቀርቧል፡፡ በኪሎ በኪሎ ተመዝነው ተፈጥሮዊ መልክና ጣዕማቸውን ይዘው እንዲቆዩ ፍሪጅ ውስጥና መደርደሪያ ላይ ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡
ሃይፐርማኬቱን ልዩ የሚያደርገው ሌላው ነገር ዘመናዊ የሕፃናት ማቆያው ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው ዕቃ ፍለጋ የገበያ ማዕከሉን ሲዞሩ፣ ልጆች ሊደክማቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ፣ ሞግዚቷ ልጆቹን ተቀብላ፣ መጫወቻ ወደተሟሉለት ማቆያ በመውሰድ እንደየዕድሜያቸው ታዝናናቸዋለች። “ወላጅ ልጆቹን ይዞ ከሠራተኛው ጋር ሊመጣ ይችላል፡፡ ያኔ ልጆቹ እየተጫወቱና እየተዝናኑ እንዲቆዩም ይደረጋል” ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡ በማቆያው ሲጫወት ያገኘነው ዳኒ ቦጃ 7 ዓመቱ ነው። የ11 ዓመቷ እህቱ ሳሮኒያም አብራው ነበረች፡፡ ልጆቹ ማቆያውን በጣም ወደውታል። “ለልጆች በጣም ጥሩ መጫወቻ ስለሆነ በጣም ደስ ይላል” ብላለች - ሳሮኒያ፡፡ እቃ ለመግዛት ከወንድ ጓደኛዋ ጋር መጥታ በሃይፐርማርኬቱ ውስጥ ያገኘናት ራሔል ግርማም ስለ ገበያ ማዕከሉ ጠይቄአት፤ “በጣም ደስ ብሎኛል፤ ከጠበቅነው በላይ ነው ያገኘነው፡፡ የምንፈልገው ዕቃ በሙሉ አለ። ከእንግዲህ ወዲያ ዕቃ መግዛት ስንፈልግ ወደዚህ እንመጣለን” ብላለች፡፡ ራሔል ዋጋውም ተመጣጣኝ መሆኑን ተናግራለች፡፡ “ስለ ዋጋው ጉዳይ ከእሱ ጋር (የወንድ ጓደኛዋን ማለቷ ነው) እየተወያየን ነበር፡፡ በሌላ ሱፐርማርኬቶች የምናውቃቸው ዕቃዎች በዚያው ዋጋ እዚህ አሉ፡፡ ስለዚህ ጥሩ ዕድል ነው፤ ብዙ ሳንለፋ ሁሉንም እዚሁ እንገበያለን ማለት ነው፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል” በማለት አስተያየቷን ገልጻለች፡፡
እዚያው ያገኘነው ሌላው አስተያየት ሰጪ ማንደፍሮ “የአገራችንም ሆኑ የውጭ እንግዶች ይህን የገበያ ማዕከል በማግኘታቸው በጣም ደስ ብሎኛል። ለአገራችንም ክብር ነው” ብሏል፡፡
የገበያ ማዕከሉ ባንክ ቤት አለው፣ በቅርቡ ደግሞ የንፅህና መስጫው ላውንደሪ ሥራ እንደሚጀምር አቶ ግርማይ ተናግረዋል፡፡ “ሌላው ለየት የሚያደርገን ባንካችን ሸዋ ፎሬክስ ቢሮ ነው፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን፣ የውጭ እንግዶችና ቱሪስቶች ይመጣሉ፡፡ እነዚህ የውጭ አገር ደንበኞቻችን ወደዚህ ሲመጡ ዕቃ መግዛት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ምንዛሪ በማጣት ይቸገራሉ። መመንዘሪያ ባንክ ፍለጋ እንዳይንከራተቱ ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር በመተባበር ሸዋ ፎሬክስ ቢሮ ከፍተናል፡፡
“ይህን ቢሮ የከፈትነው እኛ የውጭ ምንዛሪ (ዶላር) መቀበል ስለማንችል ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ደንበኞች ቼክ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ቼኩን አንቀበልም ብለን ደንበኛውን ከምንመልስ፣ “ሸዋ ፎሬክስ” ቼኩን ተቀብሎ ገንዘብ ያለውና የሌለው መሆኑን አረጋግጦ፣ ፈርሞ ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ ቼክ ይዘው የሚመጡ ደንበኞችም ይስተናገዳሉ ማለት ነው፡፡ ሌላው አዲስ ነገር ላውንደሪያችን ነው፡፡ ደንበኛው ወደኛ ሲመጣ ልብሶቹ እንዲታጠብለት ይሰጣል፡፡ በቀጠሮው ወይም በሌላ ጊዜ ሲመጣ ደግሞ ልብሶቹን ይዞ ይሄዳል፡፡ ይህ ለየት ያደርገናል” በማለት አስረድተዋል፡፡
ሸዋ ሃይፐርማርኬት ለ350 ሰዎች የመኪና ማቆሚያ አዘጋጅቷል፡፡ የገበያ ማዕከሉ 220 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ሠራተኞቹ ደንበኛ ማለት ምንድነው? ከእኛ ምን ይፈልጋል? እንዴት ነው ማስተናገድ የሚገባን? … በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ ስልጠና እንደተሰጣቸው አቶ ግርማይ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ንብረታቸውን ከሌባ ለመጠበቅና የደንበኞቻቸውን ደህንነት ለማረጋገጥ 58 ካሜራዎችና አንድ የሴኩሪቲ መከታተያ ካሜራ አለ፡፡
ለሸዋ ሃይፐርማርኬት መመሥረት መነሻ የሆኑት ሐጂ ቡሰር አህመድ ናቸው፡፡ ሐጂ ቡሰር፤ ፒያሳ፣ ወደ ሸዋ ዳቦ በሚያወጣው መንገድ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ይተዳዳሩ እንደነበር አቶ ግርማይ ይናገራሉ። ከዚያም በ1958 ዓ.ም “ሱማሌ ተራ” አካባቢ የመጀመሪያውን ሸዋ ሱፐርማርኬት ከፈቱ፡፡ ከብዙ ጊዜ ጥረትና ትግል በኋላ ሁለተኛውን ቦሌ አካባቢ “ሸዋ ሾፒንግ ሴንተር”፣ ሦስተኛውን ጦር ኃይሎች አካባቢ፣ ሳር ቤትና ሲኤምሲ አካባቢ ከፈቱ፡፡
ሐጂ ቡሰር በአሁኑ ወቅት በሕይወት የሉም፤ ከስድስት ወር በፊት በሞት ተለይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሸዋ ሃይፐርማርኬትን የሚመራው ልጃቸው አቶ ሐሰን ቡሰር ሲሆኑ የታዘዙ ዕቃዎችን ለማስጫን ውጭ አገር ስለሄዱ ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡
“በኢትዮጵያ የመጀመያ የሆነ በ3ሺህ ካ.ሜ ላይ ያረፈ ሃይፔርማርኬት (የተሟላ የገበያ ማዕከል) ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረትና ብዙ ሚሊዮን ብሮች የጠየቀን ቢሆንም፤ የሕዝቡን ፍላጐት ለማርካት ቆርጠን ተነስተናል” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ አሁንም ህብረተሰቡ “ይኼ ቀረ፣ ይኼ ጐደለ” ካላቸው ለማሟላት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዓላማችን የሕዝቡን ፍላጐት ማርካት ነው፤ ትልቅ የገበያ ማዕከል እስከሆነ ድረስ ሁሉንም ነገር ማሟላት አለበት ብለዋል፡፡ አንዳንድ ዕቃዎች ለምሳሌ የአሳማ ሥጋ፣ መጠጥና ሲጋራ የለም ተብለው የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፤ “ለጊዜው እነዚህ ነገሮች የሉም። ነገር ግን በምን መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ከዚያም በጥናቱ መሠረት ተፈጻሚነት ያገኛል” ብለዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉ ባለፈው ማክሰኞ ተከፍቷል። በዕለቱ የ1,500 ብር ዕቃ ለገዙ ወይም በዕለቱ መጥተው ባይገዙም በቅርቡ ለመግዛት ላቀዱ 250 ደንበኞች የ30 በመቶ ቅናሽ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በየሳምንቱ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ የ “ሰርፕራይዝ” ፕሮግራም መኖሩን ተናግረዋል፡፡ “ለምሳሌ ካሁን ቀደም ያደረግነው ስኳር 20 ብር በሚሸጥበት ወቅት እኛ ግማሽ በግማሽ ቀንሰን በዘጠኝ ብር ሸጠናል።
ዘይትም በጣም በተወደደበት ጊዜ እንደዚሁ አድርገናል፡፡ ሰርፕራይዝ የምናደርገውን ነገር አንገልጽም፡፡ “ለምሳሌ ካሁን ቀደም ያደረግነው ስኳር 20 ብር በሚሸጥበት ወቅት እኛ ግማሽ በግማሽ ቀንሰን በዘጠኝ ብር ሸጠናል፡፡ ዘይትም በጣም በተወደደበት ጊዜ እንደዚሁ አድርገናል። ሰርፕራይዝ የምናደርገውን ነገር አንገልጽም፡፡ ‘ዛሬ ይኼ አልፏችኋል፡፡ ለሳምንት ደግሞ?’ ብለን በጥያቄ ምልክት በመተው፣ በሳምንቱ ውስጥ ለኅብረተሰቡ በጣም አስፈላጊ ነው ያልነውን ነገር ሰርፕራይዝ እናደርጋለን” በማለት አስረድተዋል፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የመጀመሪያዎቹ 10 ከፍተኛ ሸማቾች የሚሸለሙበትም ፕሮግራምም አለ፡፡ “ለደንበኛው አንድ ካርድ ተዘጋጅቶለት ይዞ ይሄዳል፡፡ በየወሩ የገዛቸውን ሸቀጦች ዋጋ እዚያ ላይ ይሞላል፡፡ ያ ይደመርና በወሩ ከፍተኛ ሸማች ለሆኑ 10 ደንበኞች እንሸልማለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሼባ ማይልስ ጋር ተነጋግረን የውጭ ጉዞ ሽልማት አዘጋጅተናል፡፡ ደንበኛችን በየጊዜው በሚገዛው እቃ ዋጋ መጠን ነጥብ ይያዝለትና ተጠራቅሞ ዱባይ ወይም ሌላ ቦታ መሄድ ከፈለገ እኛ ወጪውን እንሸፍንለታለን፡፡ ይኼ ደንበኛውን ለማበረታታትና ስለገዛ ብቻ የምንሸልምበት ፕሮግራም ነው፡፡
ሌላው ደግሞ በክፍያ ወቅት ደንበኞቻችን በወረፋ ብዛት እንዳይጨናነቁ 14 የኤሌክትሮኒክስ መክፈያ ቦታ አዘጋጅተናል፡፡ መክፈያዎቹ በኔትወርክ ስለተያያዙ ደንበኛው ሰው ወዳልበዛበት ሄዶ መስተናገድ ይችላል” በማለት አቶ ግርማይ ዓለማየሁ አስረድተናል፡፡በማስፋፊያው ሁለት ተመሳሳይ ሃይፐር ማርኬት ለማቋቋም ታቅዷል፡፡

Read 6781 times