Print this page
Saturday, 10 August 2013 11:39

የተፈጥሮ ፍልውሃዎችና ፈዋሽነታቸው

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ማንኛውም ጤናማ ሰው ቢያንስ በሣምንት አንድ ቀን በፍልውሃ መታጠብ ይገባዋል

እርጅና የተጫጫናቸው ክፍሎች፣ የወላለቁ የቧንቧ መክፈቻና መዝጊያዎች፣ የተላላጡ ግድግዳዎች፣ ያረጁ ፎጣዎች፣ የተንሻፈፉ ነጠላ ጫማዎች፣ እድሜ የተጫናቸው ሠራተኞችና ተራ ጠባቂ ደንበኞች በብዛት የሚገኙበት ሥፍራ ነው-ፍልውሃ፡፡ ከህመማቸው ለመፈወስና፣ የሻወር አገልግሎት ለማግኘት ከፍቅረኞቻቸው፣ ከባለቤቶቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመታጠብ በርካቶች ወደ ፍልውሃ ይሄዳሉ፡፡ ድርጅቱ የሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም ሥፍራው ሁልጊዜም በደንበኞች እንደተጨናነቀ ነው፡፡
በንጉሡ ዘመን ተሰርተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ክፍሎች፤ እርጅና ተጫጭኗቸውና እድሣት ናፍቋቸው ዛሬም ድረስ ደንበኞቻቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ሥፍራው ለአዲስ አበባ ከተማ ምሥረታም ያበረከተው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ቤተመንግስታቸው ተነስተው ወደእዚህ ሥፍራ ለመውረዳቸው ምክንያታቸው በአካባቢው የተፈጥሮ ፍልውሃ መገኘት ነበር፡፡ እቴጌይቱ በፍልውሃ አካባቢ ውበት ተማርከው ጊዜያዊ ማረፊያቸው ካደረጉት በኋላ፣ በሥፍራው በሚገኘው የተፈጥሮ ፍልውሃ መታጠብ የየዕለት ተግባራቸው ሆነ፡፡ አካባቢውን ወደዱት፡፡ በፍልውሃው ፍቅር ወደቁ፡፡ ይህ ደግሞ ባላቸውን (አፄ ሚኒሊክን) አሣምነው የአገሪቱን መናገሻ ከተማ እስፍራው ላይ ለመቆርቆፍ እንዲችሉ ማድረጉን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፍልውሃዎችን በብዛት ከታደሉት አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የምሥራቅ አፍሪካው ታላቁ ስምጥ ሸለቆ የአገሪቱን አብዛኛውን ክፍሎች አቋርጦ የሚያልፍ በመሆኑ ነው፡፡ የአዲስ አበባው ፍልውሃ፣ የሶደሬው አባድር፣ ወንዶገነት፣ ወሊሶና አምቦ ኢትዮጵያ ሆቴል የተፈጥሮ ፍልውሃ ከሚገኝባቸው የአገራችን አካባቢዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ የተፈጥሮ ፀጋዎችም ከቱሪዝም መስህብነታቸው እና ከገቢ ማስገኛ ምንጭነታቸው በተጨማሪ ለፈውስ አገልግሎት እየዋሉ ነው፡፡ በፍልውሃው አማካኝነት በርካቶች ከያዛቸው ደዌ እንደሚፈወሱ እንሰማለን፡፡ የጥንት አባቶቻችን ለዘመናት ያለ ሳይንሳዊ ዕውቀት ሲጠቀሙበት የኖሩት ይኸው የተፈጥሮ ፍልውሃ፤ አሁን ዘመናዊና ሣይንሣዊ በሆነ መንገድ ጥናትና ምርምር እየተደረገበት ይገኛል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃን በማጥናት ሥራ ላይ ተጠምደው የሚውሉ ተመራማዎች አሁን አዲዲስ የጥናትና የምርምር ውጤቶችን ይፋ እያደረጉ ነው፡፡ በቅርቡ በአሜሪካ የሚገኙ ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጓቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከ37°C (ከሰላሣ ሰባት ድግሪ ሴንትግሬድ) እስከ 39°C ድረስ ሙቀት ያለው የተፈጥሮ ፍልውሃ ለጤና እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ማንኛውም ጤናማ ሰው ቢያንስ በሣምንት አንድ ቀን በዚህ የሙቀት መጠን ውስጥ ባለ የፍልውሃ መታጠብ ወይም መዘፍዘፍ ይኖርበታል፡፡ ይህም በምግብ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ልናገኛቸው የማንችላቸውን ንጥረ ማዕድናትንና የተለያዩ ለሰውነት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ማግኒዚየም፣ ሶዲየምና ካልሲየም የተባሉ ማዕድናትን ለማግኘት ያስችለናል፡፡ እነዚህ ማዕድናት ደግሞ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ እንደሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃዎች እንደሚገኙበት ሥፍራ በማዕድን ይዞታቸው መጠንና በአሲዳምነታቸው እንደሚለያዩ የጠቆመው ይኸው ጥናት፤ በውሃው ውስጥ የሚገኙት ማዕድናት የሚሰጡትም የፈውስ አገልግሎት እንደየሁኔታው ሊለያይ እንደሚችል አረጋግጧል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃን ፈዋሽነት በሚያጠናው ባላኒዮሎጂ (Balaneyology) በተሰኘው የጥናትና ምርምር ዘርፍ የተሰማሩ የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ባደረጉት መረጃ፤ ፍልውሃ በሁለት የተለያዩ መንገዶች ሊገኝ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው (Filtrate hot spring) የተባለውና በመሬት ስንጥቅ አማካይነት ወደ ከርሰ ምድር ውስጥ የገባው የዝናብ ውሃ እጅግ ሞቃታማ በሆነው የመሬት ክፍል ውስጥ ደርሶ፣ በውስጡ ከሚገኙ የከርሰ ምድር ማዕድናት የያዘው ሞቃት ውሃ፣ በመሬት ውስጣዊ ግፊት አማካኝነት ወደ መሬት ገፅ በመውጣት በፍል ውሃነት ይከሰታል፡፡ ሌላው የተፈጥሮ ፍልውሃ (Primary hot spring) የተባለው ሲሆን ይህ ውሃ የሚፈጠረው በተፈጥሮ በከርሰ ምድር ውስጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በከርሰ ምድር ውስጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ አማካኝነት በርካታ ማዕድናትና ንጥረ ነገሮች ከውሃው ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ በመሬት ግፊትም ውሃው ወደ ገፀ ምድር ሲወጣ በርከት ያሉ ለጤና እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ማዕድናትንና ንጥረ ነገሮችን ይዞ ይወጣል፡፡ በሁለቱ የተለያዩ መንገዶች የሚገኘው ፍልውሃ፤ የተለያዩ የማዕድንና የጋዝ መጠኖች ያሉት ሲሆን የሶዲየም ክሎራይድ ይዘትም አለው፡፡ ከ3-5% የሚደርስ የሶዲየም ክሎራይድ ይዘት ያለው የተፈጥሮ ፍልውሃ፤ ለመገጣጠሚያ ብግነት፣ ለቁርጥማት ለነርቭ በሽታ፣ ለአጥንት መሳሳት፣ ለጡንቻ መተሳሰር እና መሰል የጤና ችግሮች መድሃኒት መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃ ከዚህ በተጨማሪ ለቆዳ በሽታዎች፣ ለመተንፈሻ አካላት ችግሮች እፎይታን ይሰጣል፡፡ የአዕምሮን የማሰብ ችሎታ ከፍ ለማድረግ፣ ድብርት ሲጫጫነን፣ ጤናማ የልብ ምት እንዲኖረን፣ ሰውነታችን ውስጥ የሚፈጠሩ መርዛም ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድና የሆርሞን ስርዓታችንን ለማስተካከል የተፈጥሮ ፍልውሃዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡
ከከርሰ ምድር የሚገኙት የተፈጥሮ ፍልውሃዎች በሚኖራቸው የሙቀት መጠን እንደሚለያዩ መረጃው ጠቁሞ፤ በዚሁ የሙቀት መጠናቸው ልክም በአራት የተለያዩ መደቦች እንደሚከፈሉ ገልጿል፡፡ የሙቀት መጠናቸው ከ25°C በታች የሆኑና ከከርሰ ምድር የሚገኙት ቀዝቃዛ የምንጭ ውሃ (Cold Spring water) ሲባሉ፣ የሙቀት መጠናቸው ከ25-34°C ድረስ ያሉት ደግሞ ለብ ያለ (Tepid Spoizing Spring water) ይባላሉ፡፡ ከ34-42°C ድረስ ያሉት የገፀ ምድር ውሃ ሞቃታማ (Warm Spring water) በሚል መጠሪያ ሲታወቁ ከ42°C በላይ ያሉት ደግሞ ፍልውሃ (hot Spring water) ተብለው ይጠራሉ፡፡
ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው እነዚህ የተለያየ የሙቀት መጠን ያላቸው የተፈጥሮ ፍልውሃዎች፤ እንደሙቀት መጠናቸውና እንደማዕድን ይዘታቸው የሚሰጡት የፈውስ አገልግሎትም ይለያያል፡፡ የሙቀት መጠናቸው ከፍ ያለ ፍልውሃዎች እንፋሎታቸው ከባድ በመሆኑ የደም ግፊት፣ የልብ ድካም፣ የካንሰር፣ የጉበትና የኩላሊት ህሙማንና ነፍሰጡር ሴቶች ባይጠቀሙ ተመራጭ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

Read 6698 times
Administrator

Latest from Administrator