Print this page
Saturday, 10 August 2013 11:23

ተናጋሪዋ ምድር

Written by  በኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(4 votes)

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ
‹‹ኧረ ጉድ በዛ ኧረ ጉድ በዛ፤
በጀልባ ተሻግሮ አበሳን ቢገዛ”
ዛሬ የጥበብ ጉዟችን ይጠናቀቃል፤ግን ገና የምናያቸው ድንቅና ታሪካዊ ቦታዎች አሉ። ወደ አክሱም ስንጓዝ ጊዜው በመምሸቱ ምክንያት በይደር ያለፍናት አንድ ገናና ታሪክ የተፈፀመባት ቦታ አለች፡- አድዋ! እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ጥቁር አፍሪካዊ ሁሉ “አድዋ” የሚለው ስም ሲነሳ መንፈሱን የሚነሽጠው አንዳች መግነጢሳዊ ኃይል አለ፡፡ እሱም በ1888 በዕብሪተኞቹ ጣሊያኖች ላይ የደረሰው ዘግናኝ ውድቀት ነው፡፡
አድዋ የአካባቢው ስም ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያንን ከጣሊያን መንጋ ታድገው ዛሬም ከእነ ግርማ ሞገሳቸው የቆሙ ተራሮች ብዙ ናቸው። አቀማመጣቸው በራሱ ዕውቅ ባለሙያ ለውበት ተጨንቆ የቀረፃቸው ይመስላሉ፡፡ አንዳንዶችን ለመጥቀስ ያህል የሰሎዳ ተራራ ቀዳሚው ነው። ቀዳሚ የሚሆንበት ምክንያትም አፄ ምኒሊክ ሰፍረውበት ስለነበር ነው፡፡

“ጊዮርጊስ ጓጓ” ከተባለው ቦታም ንጉሰ ነገስቱ አስቀድሰዋል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒሊክ” በተባለው መፅሀፉ ላይ በወቅቱ የነበረውን አሰላለፍ ሲገልፅ “ራስ መኮንን የሀረርጌን ጦር ይዘው አድዋ ከተማን፣ራስ ሚካኤል የወሎን ጦር ይዘው ሰሎዳ ተራራን፣ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃምን የጦር እየመሩ ከጦርነቱ ፊትለፊት የሚገኘውን እንደ አባገሪማን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ዓዲአቡንን ሲቆጣጠሩ አጤ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ ወሌና ዋግሹም ጓንጉል ሰራዊታቸውን ይዘው የኋላ ደጀን ሆኑ” (ገፅ204) ይላል፡፡ ተክለፃድቅ መኩሪያ ደግሞ እያንዳንዱ የጦር አበጋዝ በስሩ ያሰለፈውን ሰራዊት ከመዘርዘር ውጪ የተሰለፉበትን ቦታ አይገልጡም፡፡
ያም ሆነ ይህ አድዋ ላይ በጣሊያን በኩል 7560 ጣሊያኖች፣ 7100ጥቁር ወታደሮች ያለቁ ሲሆን ከኢትዮጵያ ወገን 7000 ሞተው 10‚000 መቁሰላቸውን ጳውሎስ ጽፎአል (ገፅ 211)፡፡ ቁጥሩን በተመለከተ ከተለያዩ ጸሐፊዎች የሚጠቀሰው አኃዝም የተለያየ ነው፡፡
ለማንኛውም ሰሎዳ፣ እንዳአባ ገሪማ፣ የገሰሰው ተራራ፣ ኪዳነ ምህረት፣ ሰማያታ (ትልቁ ተራራ ነው)፣ “ፎልስ ኪዳነምህረት” ፣ማርያም ሸዊቶ ወዘተ ተራሮች ዛሬም በኩራት ተኮፍሰው ሲታዩ ጠላታቸውን ድባቅ መትቸው ለሀገራቸው ዘብ የቆሙ ጀግኖች ይመስላሉ፡፡ ዛሬም “ሃገሬን አትንኩ!” የሚል የአደራ ቃል የሚያስተላልፉ ባለ ሕያው ታሪክ ግዙፍ የታሪክ ቦታዎች ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ “ፎልስ ኪዳነ ምህረት” የተባለው ጣሊያኖቹ ኪዳነ ምህረት የተባለውን ስትራቴጂክ ቦታ ያዝን ብለው ሌላ ተራራ በመያዛቸው የተሰጠ ስያሜ መሆኑን አቶ ከበደ አማረ ነግረውናል፡፡ የአድዋን ተራሮች የጎበኘናቸው እንደ ሌላው ዝም ብለን አይደለም፡፡ የጀግንነት ግጥሞች በተጓዦች ተነብበዋል፤ቀረርቶም ሰምተናል፤ ግን የገደልነውም ሆነ የማረክነው ጣሊያን አልነበረም፡፡ ምን አልባት የአድዋ ተራሮች “እንዲህ አርጎም ጀግና የለ?” ብለው ታዝበውን ይሆን?
ሆኖም አንበሶቹ ራስ መኮንን ፣ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ ሚካኤል፣ ወዘተ ከንጉሰ ነገስታቸው ፊት ዘገራቸውን እየነቀነቁ፣ ጎራዴያቸውን እየሰበቁ ከእሳተ ነበልባል በሚያቃጥል ወኔ ሲፎክሩ፣ግዳያቸውን ሲያስመዝግቡ ደረቱ በትዕቢት ተወጥሮ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቱ ሊያደርግ የመጣ የጣሊያን ጀኔራል በወጥመድ የተያዘች አይጥ መስሎ በፍርሃት ሲንቀጠቀጥ ታየኝና “ምነው በዚያ ዘመን ኖሬ የዚያ ቅዱስ ታሪክ ተሳታፊ በሆንኩ?” ብዬ አሰብሁ፡፡ “ኧረ ጉዱ በዛ፣ ኧረ ጉዱ በዛ፣
በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ” ብለው ያቅራሩትን ጀግኖች በዓይነ ህሊናዬ እያስዋልሁ፡፡ አድዋ ላይ ያየነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃም ሌላው አስደሳች ጉዳይ ነው፤ ግራ ካሱ፣ አብርሃ ወአጽብሃ እና ገረዐልታ ተራሮች ላይ ያየነው የደን ጥበቃና እንክብካቤ አድዋ ተራሮች ላይም ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት፣ ውበት ዳግም እየተፈጠረች መሆኗን ተገንዝበናል፡፡
አድዋ ላይ ባለቁት ወገኖቻችን እያዘንን፤ ደግሞ ባስገኙት ዓለምአቀፍ የጥቁሮች ድል እየተኩራራን በቅርብ ርቀት የምትገኘውን ጥንታዊት ከተማ የሃን ለመጐብኘት ተንቀሳቀስን፡፡ የሃ በ800 ዓመተ ዓለም የተገነባ ቤተመቅደስ ዛሬም በእማኝነት ቆሞ የሚገኝባት ታሪካዊት ከተማ ናት፡፡ ቤተ መቅደሱ የተገነባው ከድንጋይ ብቻ ነው፤ ገንቢዎቹ ጭቃም ሆነ ሲሚንቶ ለማጣበቂያነት አልተጠቀሙም፡፡ የስነ ምድር እና የስነ ህንፃ ተመራማሪዎች በጥናት እንዳረጋገጡት፤ ህንፃው ያረፈው ከአለት ላይ ነው። የገነቡትም ሴማውያን ሲሆኑ ፀሐይ እና ጨረቃን ያመልኩ ነበር፡፡
ቤተመቅደሱ 12 ምሰሶዎች፣ አምስት ክፍሎች፣ ያሉት ባለ ፎቅ ህንጻ እንደነበር አስጐብኝያችን አስረድተውናል፡፡ ቦታው በወቅቱ የአገሪቱ ዋና ከተማ የነበረ ከመሆኑም በላይ 150 ነገሥታት ኖረውበታል፡፡ የመንግሥቱ ሥርወ መንግሥት መጠሪያም “ዳአመት” በመባል ይታወቃል፡፡ ቤተመቅደሱ ከ12-15 ሜትር ከፍታ እንዳለው ከአስጐብኟችን የተረዳን ሲሆን ድንጋይ በድንጋይ ላይ ብቻ በመደራረብ በ800 ዓመተ ዓለም የተሰራ ህንጻ ለ2900 ዓመታት ያለምንም ጥገና መቆየቱ የዚያኔዎቹን ወገኖቻችንን ጥበብ በእጅጉ ተደናቂ ያደርገዋል፡፡ አገራችን “የ3000 ዓመት የሥርዓተ መንግሥት ታሪክ አላት” ሲባል ተረት አለመሆኑንም በእርግጠኝነት ያስረዳል። ለመሆኑ ለህንፃው የተጠቀሙባቸው ድንጋዮችን እንደእንጨት የጠረቡበት መሣሪያ ምን ነበር ይሆን? መቸም ትግራይን የጐበኘ አዕምሮ ሁሉ በተለያዩ ጥያቄዎች መወጠሩ ግድ ነው፡፡
እስከ ሶስት ሜትር የሚረዝሙ ድንጋዮች የተደረደሩበት ህንፃ ለዚያን ያህል ረጅም ዘመን የመቆየቱ ምስጢር በጀርመን ባለሙያዎቹ እየተጠና ከመሆኑም ሌላ ቅርሱ እንዳይጠፋ ጥገና ሊደረግለት ዝግጅት መጀመሩን በጉብኝታችን ወቅት ተመልክተናል፡፡
ቤተመቅዱ ዓድአካውህ ላይ ያየነው አልሙጋህ የተባለው ጣኦትም ይመለክበት ነበር ተብለናል፤ መሥዋዕቱ ይቀርብበት የነበረው፤ ወይም የመሰዊያው ቦታ (ክፍል)፣ የመስዋዕቱ ደም የሚወርድበት ከድንጋይ የተጠረበ ቱቦ በእጅጉ የሚያስደንቁ ናቸው፡፡ ግድግዳው ብቻ ሳይሆን ወለሉ ራሱ በሰፋፊ ጥርብ ድንጋዮች የተስተካከለ ሲሆን ዛሬም ውበቱ አልደበዘዘም፡፡
ከቤተመቅደሱ ምስራቃዊ አቅጣጫ የቆመው የአቡነ አፍጼ ቤተክርስቲያንም ሌላው ግዙፍ ሃብት ነው፡፡ አቡነ አፍጼ በ6ኛው መቶ ክፍለዘመን ከሮምና ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ወደ አገራችን ከመጡ ዘጠኝ ቅዱሳን አንዱ ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያኑ የተገነባው በጥንታዊ ህንፃ ላይ መሆኑን፣ እንዲያውም ከየሃ ቤተመቅደስ ላይ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦችን ወስደው ቤተክርስቲያኑን እንዳስጌጡበት በጉብኝታችን ተገንዝበናል፡፡ በገዳሙ ወስጥ እጅግ ጥንታዊ የሆኑና ከቤተመቅደሱና ከአካባቢው የህንፃ ፍርስራሾች የተገኙ በሳባ፣ በግዕዝና በግሪክ ቋንቋዎች የተፃፉባቸው ድንጋዮች፣ የብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎችና ልዩ ልዩ ንዋየቅድሳት ይገኛሉ፤ ግን አቀማመጣቸው አንዱ በሌላው ላይ የተደራረበ ስለሆነ ለልዩ ልዩ ጉዳቶች ሊዳርጓቸው ይችላልና ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡
ከአቡነ አፍጼ ቤተክርስቲያን ምስራቃዊ አቅጣጫ በቅርብ ርቀት ላይም ሌላ አስደናቂ ነገር ተገኝቷል። ስፋቱ 24 በ24 የሆነ ሰፊ ቤተመንግሥት፡፡ ስሙ “ግራት በዓል ገብሪ” የሚባል ሲሆን ከየሃ ምኩራብ በፊት አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ከአስጐብኛችን ተረድተናል፡፡ ምንም እንኳ በጀርመንና በሃገራችን ባለሙያዎች እየተጠና ቢሆንም ህንጻው ከ5-6 ፎቆች እንደነበሩት ተረጋግጧል፡፡
በተከታታይ ጽሑፎቼ ለመጠቆም እንደ ሞከርኩት ሃገራችንን እንኖርባታለን እንጂ አናውቃትም፤ እናማርራታለን እንጂ አንመረምራትም፤ ከፈረንጆች ማረጋገጫ ካላገኘን ስለ እኛ የምናየውን አናምንም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ዘመናዊ ትምህርት በአገራችን ሲጀመር በፈረንጅ ሥርዓትና በፈረንጅ አስተማሪ መቀረጹ ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ሌላ ስለ ቱሪዝም ያለን አመለካከት በእጅጉ ደካማ ነው፤ እስራኤላውያን ኢየሱስን ሰቅለው ሌላ ኢየሱስን (መሲሕ) ይጠብቃሉ፡፡ ግን ገቢያቸዉን ለማሳደግ ሲሉ ኢየሱስ የሄደበትን፣ የተቀመጠበትን፣ የተገረፈ፣ የተገፈፈበትን፣ የተሰቀለበትንና የተነሳበትን ቦታ ሁሉ በሥርዓት ያስጐበኛሉ፡፡ በዚህም የትየለሌ ዶላር ዓመት ሙሉ ይዝቃሉ፡፡ ግብጾችም ሙሴን በቅርጫት አድርገው እንደ ቆሻሻ ዓባይ ወንዝ ውስጥ እንዳልጣሉት ሁሉ ዛሬ ካይሮ በርባራ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በሚገኝ ቦታ የአይሁድ ቤተ መቅደስ ገንብተው “ሙሴ የተጣለው በዚህ ቅርጫት ነበር” እያሉ ያስጐበኛሉ፡፡ ፎቶግራፍ ማንሳት እየከለከሉም በጉቦ የፖሊሶቻቸውን ኪስ ያደልባሉ፡፡ እኛ ግን ዛሬም እንደተኛን ነን፡፡ ምንአልባት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት እንደ ተፈጥሮ ጥበቃው በዚህም ፋና ወጊ ተግባር አከናውኖ ማየት ይናፍቀኛል፡፡ ሌላውና ከአገራችን ይልቅ ባዕድ ናፋቂ እንድንሆን ያደረገን ምክንያት የነገሥታቱ ከንቱ አስተሳሰብ ይመስለኛል፡፡ ይህም ድምሩን ህዝብ በማታለል “ከመለኮት ዘር አለን” ለማለትና ራሳቸውን ከኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ፤ በዘራቸው ለመግዛት ብቻ የፈጣሪ ፈቃድ የታደላቸው አድርገው ለማጭበርበር ሲሉ “ሞዐ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ” የሚል ቅጽል ከስማቸው በፊት ያስቀድማሉ እንጂ “ዘእምነገደ አክሱም” አይሉም፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊ አንበሣነታቸው እንደሚያሳፍራቸው መረዳት ይቻላል፡፡
የአክሱም ዘራቸውን ሳይጠቅሱ ከሰሎሞን ቤተመንግሥት ውስጥ ራሳቸውን እንዴት እንደሚያገኙ ግን ለኔ እንቆቅልሽ ነው፡፡ መሪዎች የተጸየፉትን አገር ህዝቡ ቢጠላው ታዲያ ምኑ ያስገርማል? ከሰሎሞን መወለድ ማለት ዲቃላነትን መቀበል ነው፤ ዲቃሎች ያልሆኑት የላሊበላ ነገሥታትና የቅርብ ጊዜው ዳግማዊ ቴዎድሮስ በግልባጩ “ዲቃሎች” ተብለው ሲወገዙ መኖራቸው ራሱ ታሪካችንን ክፉኛ በክሎታል ባይ ነኝ፡፡
ታሪክን መበከል ባይሆን ኖሮ ነገሥታት “ከሰለሞን ዘር መጣን ከማለት ይልቅ “ከታላቋ አክሱም የተገኘን” ቢሉ ምንኛ ያኮራቸው ነበር! ለማንኛውም አገራችንን በደንብ እንዳናውቃት ካደረጉን ሰበቦች አንዱ የእነሱው የዘር ቅልውጥ ይመስለኛል፡፡
ወደተነሳሁበት ነጥቤ ልመለስና ጉዟችንን እያጠናቀቅቅ ነው፤ ግን በጉብኝታችን ወቅት ራትና ምሳ እየጋበዙ የላቀ የክብር እንግድነት አቀባበል ያደረጉልን የመላዋ ትግራይ ከተሞች፣ የክልሉ መንግሥት፣ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ጽ/ቤት በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ደሴ ገብተናል፤ ጉዟችን የተቋጨው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ደሴ ቅርንጫፍ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ደማቅ የሥነ-ጽሑፍ ምሽትና የራት ግብዣ ነው፡፡
በዚህም የቅርንጫፍ ማኅበሩ መሪዎችንና ወሎ ዩኒቨርስቲን አድንቀናል፡፡ በአጠቃላይ የመልስ ጉዞአችን እንደ መጀመሪያው ደማቅ አልነበረም፤ በእያንዳንዱ ተጓዥ ፊት ላይ ቅሬታና የመከፋት ስሜት ይነበብ ነበር፡፡ እንደኔ ከሆነ ለዚህ ምክንያቱ “ያንን የመሰለ ታላቅ ስልጣኔ ምን በላው? እኛስ ምንድን ነን? ወደየትስ እያመራን ነው?” የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ አንድ ቤተሰብ በፍቅር ቆይቶ መለያየቱም ሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
ለማንኛውም ያን የመሰለ ድንቅ የጥበብ ጉዞ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርና ወጭውን የሸፈነው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምስጋናውን ብኩርና መውሰድ ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሰላም!

 

Read 3887 times