Print this page
Saturday, 10 August 2013 11:15

“መንግስት ህጋዊ ባለይዞታ ላልሆኑ ምትክ የመስጠት ግዴታ የለበትም”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

*መጠለያው ሲሰራ ሁሉም ይሰጣቸዋል ማለት አይደለም፤ ይገባቸዋል ያልናቸውን ለይተናል
*ወረዳው ለትራንስፖርት ያወጣውን ገንዘብ ከፍለው እቃቸውን መውሰድ ይችላሉ

ባለፈው ሳምንት “ትራሳቸውን ቤተመንግስት ፤ ግርጌያቸውን ሸራተን ያደረጉ ቤት አልባዎች” በሚል ርዕስ በሸራተን አካባቢ ለመልሶ ማልማት በታጠረው ቤተ-መንግስቱ ሥር ባለው ቦታ በላስቲክ ቤት ውስጥ ስለሚኖሩ 48 አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው አስከፊ ህይወት ሰፋ ያለ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የወረዳውን ሃላፊዎች ማግኘት ባለመቻላችን በጉዳዩ ዙሪያ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡ በዚህ ሳምንት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ተስፋዬ ፣በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስምንት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ት ህይወት ጉግሳን አነጋግራ የሰጡትን ምላሽ አቅርበናል፡፡


በወረዳችሁ 48 አባዎራዎች ከነቤተሰባቸው ቤተመንግሥቱ ሥር በላስቲክ ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ ታውቃላችሁ?
እናውቃለን፡፡ ቁጥራቸው ከ48 አባወራዎች ይበልጣል የሚል ግምትም አለን፡፡
እነዚህ ሰዎች በቀድሞው ቀበሌ 22 ውስጥ ከ17-23 ዓመት መኖራቸውንና ቦታው ለልማት ሲፈለግ ቤት አልባ እንደሆኑ ገልጸውልናል፡፡ የቀበሌ መታወቂያ ያላቸውም አሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች እጣ ፈንታ ምንድን ነው?
በመነሻነት ሁሉም ህጋዊ ባለይዞታዎች አልነበሩም፡፡ ቦታው ለመልሶ ማልማት ሲፈለግ ምትክ የሚሰጠው ባለይዞታ ለነበሩ ሰዎች ነው፡፡ ይህን የመልሶ ማልማት መመሪያን በተከተለ መልኩ ለባለይዞታዎች ምትክ ቦታ ሰጥተን አጠናቀናል፡፡
ታዲያ እነዚህ ነዋሪዎች ለበርካታ ዓመታት የት ነው የኖሩት?
እነዚህ ሰዎች በጥገኝነትና በተከራይነት አብረው የኖሩ ናቸው፤ ለምሳሌ በአንድ ቤት ቁጥር ስሜ ተመዝግቦ ባለይዞታ ከሆንኩ ምትክ ቤቱን የማገኘው እኔ ነኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ያከራየኋቸውንም ሆነ ያስጠጋኋቸውን አብሬ ይዤ መሄድ አለብኝ ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደነገርኩሽ ወረዳው የመልሶ ማልማት ስራ የተከናወነበት እንደመሆኑ ምትክ ለሚሰጣቸው ምትክ ሰጥተን ጨርሰናል፡፡ አሁን በላስቲክ ቤት ውስጥ የሚኖሩት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ልጅ ከቤተሰቡ ይዞታ ጐን ላይ ትንሽ ቤት ይሠራና እዚያው አግብቶ ይወልዳል፣ ከዚያ ለእኔም ቤት ይገባኛል ይላል፤ ይሄ የማይሆን ነገር ነው፡፡ ወረዳው ይህን ሰው የሚያውቀው ከቤተሰቡ ጋር ነው፣ ስለዚህ ቤተሰቡ ቤት ሲያገኝ አብሮ መሄድ ነው ያለበት፡፡
ወረዳው ታዲያ እነዚህ ዜጐች ምን እንዲሆኑ ያስባል?
እኛ ከፖሊስ ጋር ጭምር እየገባን እርምጃ ለመውሰድ ሞክረናል፣ ምክንያቱም ቦታው ለፀጥታ ስጋት እስከመሆን ደርሷል፡፡
ምን አይነት እርምጃ?
ከቦታው እንዲነሱና ወዳስጠጓቸው ወይም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ቀደም ሲል እንደነገርኩሽ፣ አንዳንዶቹ “እኛም ቤት እናገኛለን” በሚል ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው የቀሩ ናቸው፡፡ ቤት ላንሰጣቸው፣ህጋዊ ባለይዞታ ላይሆኑ፣ ላስቲክ ወጥረው መኖርና መስራት እየቻሉ ወደ ልመና ማዘንበል አግባብ ነው ብሎ ወረዳው አያምንም፡፡ አሁን ተጠግቶ ለሚኖርና 18 ዓመት ለሞላው ሁሉ ቤት ለመስጠት የምንችልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ በነገራችን ላይ በፊት በላስቲክ ቤት የሚኖሩት እነዚህ ብቻ አልነበሩም፤ በጣም ከፍተኛ ችግር ላለባቸው፣ የነበሩበት ሁኔታ በነዋሪዎች ኮሚቴና በአስተዳደር አካላት ተጣርቶ በተወሰነ መልኩ እንዲስተናገዱ ተደርጓል፡፡
በምን መልኩ ተስተናገዱ? ቁጥራቸውስ ምን ያህል ነው?
ቁጥራቸውን እርግጠኛ ባልሆንም ከ25 በላይ የሆኑና አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ተብለው የተመረጡ ሰዎች፣ የቀበሌ ቤትና መጠለያ ተሰርቶላቸው መፍትሔ አግኝተዋል፡፡ አሁን ያሉትን ሁሉ ለማስተናገድ ከአቅም በላይ ነው፡፡ በእርግጥ ቦታው ላይ ሆነሽ ስታያቸው፣ ህይወታቸው ሊያሳዝን ይችላል፡፡ ግን ቤተሰብ ስለሆኑ ብቻ ቤት ልስጥ ማለት አይቻልም፡፡ መመሪያ መጠበቅ አለበት፡፡
ባለይዞታ ባይሆኑም በስማቸው ቤት ባይኖራቸውም ቀደም ሲል ግን እዚሁ ቀበሌ ውስጥ የሚኖሩ ነበሩ፡፡ እንደዜግነታቸው መፍትሔ አያሻቸውም?
በነገራችን ላይ ለእነዚህም መፍትሔ እየተፈለገላቸው ነው፡፡ ቦታ ያልተሰጣቸው ህጋዊ ስላልሆኑ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ኖረናል ይላሉ፣ ግን ሲኖሩ የነበረው ቀደም ሲል በነገርኩሽ አግባብ ነው፡፡ ከቤተሰባቸው ቤት ጐን ጠግነው፣ ተከራይተውና ተጠግተው ማለት ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ሁለት ሶስት ጊዜ አጣርተናል፡፡ “ወረዳው ነው የከለከለን፣ ክፍለከተማው ጉዳያችንን ይይልን” ብለው ወደ ክፍለ ከተማ ሄደው፣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩ ታይቷል፡፡ ክፍለከተማውም ያገኘው ከእኛ መረጃ ውጭ አይደለም፡፡ አንድም እናትና አባቱ ሄደው ልጅ ነው የቀረው፡፡ እናም ወልጃለሁ፣ ቤተሰብ አለኝ ቤት ይገባኛል ነው የሚለው፣ አሊያም እንደአቅሜ በ30 ብር ተከራይቼ ረጅም አመት ኖሬያለሁ የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ስራ በመስራት፣ ኑሯቸውን እንዲለውጡ ወርደን እስከማማከር ደርሰናል፡፡ ከዚህ ውጪ ምትክ ቤት የምንሰጥበት አግባብ የለም፡፡ መመሪያውም ህጋዊ ተነሺዎች ስላልሆኑ አይደግፋቸውም፡፡
እነዚህ ሰዎች ግን በጊዜው ወደ ወረዳው እየመጡ አቤቱታ ሲያሰሙ “ቤት እንሰራላችኋለን” እንዳላችኋቸውና ለዚህም የማረጋገጫ ወረቀት እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ እንዴት ነው?
ደብዳቤ ተሰጥቶናል የሚሉት ፍፁም እውነት ያልሆነና የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ እንሰራላችኋለን ብሎ ቃል የገባላቸው ወይም ለዚህ ማረጋገጫ ደብዳቤ የሰጣቸው አካል የለም፡፡ በእርግጥ በአንድ ወቅት “ስራ አጥ ስለመሆናችን ደብዳቤ ስጡን” ብለው የተሰጣቸው ደብዳቤ እጃቸው ላይ አለ፡፡
የቤት እቃቸው፣ የልጆቻቸው ልብስ ሳይቀር ተጭኖ መጥቶ ወረዳው ግቢ ውስጥ ዝናብ እያበሰበሰው እንደሆነ እነዚህ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ እኛም የተወሰነ እቃ እዚሁ ግቢ ውስጥ ተመልክተናል፡፡ የልጆች ልብስና የመመገቢያ እቃ አጥተው መቸገራቸውን ገልፀውልናል፡፡ ይሄስ እውነት ነው?
እቃቸውን በተመለከተ ትክክል ናቸው፣ እዚህ ቀበሌ ግቢ ውስጥ አለ፡፡ ግን ተነጥቀው አይደለም የመጣው፡፡ አሁንም እንወስዳለን ካሉ የሚከለክላቸው የለም፡፡ እቃቸው የተጫነበት ምክንያት በቦታው ሰፊ የፀጥታ ችግር ነበር፡፡ መነሻውም ቤት ካልተሰጠን አንለቅም የሚል ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማርገብ፣ ከፖሊስ ጋር በትብብር ቦታው ድረስ ወርደን አነጋገርናቸው፡፡ “ህጋዊ ባለይዞታ ባልሆናችሁበት አግባብ ምትክ ይሰጠን ማለት አትችሉም፣ እንደማንኛውም ችግረኛ መጠየቅ ካለባችሁ በረብሻ ሳይሆን ወጥታችሁ ነው መጠየቅ ያለባችሁ” የሚል አቅጣጫ ሰጠናቸው፣ ነገር ግን ከችግራቸው በመነሳት “ቤት ካልሰጣችሁን፣ እንዲህ ካላደረጋችሁልን፣ ከእቃችን ጋር እዚሁ አጥፉን፣ አንቀሳቀስም” የሚል ጫፍ ያዙ፡፡ አሁን እንኳን ሄደን ብናናግራቸው ከዚህ የተለየ ነገር አይሉም፡፡
እኮ ከዚህ ወጥተው የት ይሂዱ? ወረዳውስ ምን አማራጭ አስቀመጠላቸው?
ወረዳው ህጋዊ ባለይዞታ ላልሆኑ አማራጭ የማስቀመጥ ግዴታ የለበትም፡፡ መመሪያውም ይህን አይፈቅድም፡፡ በዚህ የተነሳ እቃ ሊያነሱ አልቻሉም፡፡ ጭራሽኑ የበለጠ ያደራጁ ጀመር፡፡ እኛ ደግሞ መሬቱን ለመሬት ልማት ባንክ ማስረከብ ነበረብን፡፡ ምክንያቱም ቦታው ለገዛው ባለሀብት ስለሚውል ማለት ነው፡፡ እነሱ ግን ብዙ ቤተሰብና እቃ በመሰብሰብ ቤት እናገኛለን የሚል ወደ የዋህነት ያዘነበለ አስተሳሰብ ይዘዋል፡፡ ይህ ደግሞ የትም አያደርሳቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት እቃቸውን ጭነን ወስደናል፡፡
ቀደም ሲል መውሰድ ከፈለጉ አሁንም መውሰድ ይችላሉ ብለሻል፡፡ መጀመርያ ለምን ተወሰደ? ይውሰዱ ከተባለስ--- “ውሃ ቅዳ ውሀ መልስ” ለምን አስፈለገ?
እንደነገርኩሽ ቦታውን ማስለቀቅ ነበረብን፡፡ እቃቸው ሲወሰድ ይነሳሉ በሚል ነበር የተጫነው፡፡ እነሱ ሊለቁ አልቻሉም፡፡ ሆኖም በጣም አስፈላጊ አስፈላጊ እቃዎችን፣ አንገብጋቢ ለሆነ ችግር የሚፈልጉትን እየመጡ እንዲወስዱ ነገርናቸው፣ እየወሰዱም ነው፡፡ ሙሉ እቃቸውን መውሰድ ከፈለጉ ግን ወረዳው ለትራንስፖርት ያወጣውን ወጪ ከፍለው መውሰድ ይችላሉ፡፡ የመጫኛ ጉልበት ራሳቸው ስለጫኑ አናስከፍላቸውም፡፡
እቃቸው ተጭኖ መወሰዱ ምን መፍትሄ አመጣ?
በወቅቱ መፍትሄዎችን አግኝተናል፡፡ ለምሳሌ እቃቸውን በማንሳታችን ምክንያት ቦታውን ለማስረከብ ስንነሳ፣ የወጠሩትን ላስቲክ ብቻ ለማፍረስ ቀላል ሆኖልናል፡፡
ማፍረስ ብቻ ሳይሆን ለስምንት ጊዜ ያህል ላስቲክ ቤቱን አቃጥላችኋል፣ ስታቃጥሉም ከሌሊቱ ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት እየሄዳችሁ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ያንን ስታደርጉ ህይወት ቢጠፋ ንብረት ቢወድም ተጠያቂው ማን ነበር?
የላስቲክ ቤት ቃጠሎው የተካሄደው እነሱ ላይ ጉዳት በሚያደርስ መልኩ አይደለም፡፡ ከሌሊቱ ስምንት ዘጠኝ ሰዓት አቃጠሉብን የሚለው የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግስት የስራ ሰዓትም አይደለም፡፡ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ 11፡30 ባለው ነው የምንሰራው፡፡ ሌላው ቀርቶ 12 ሠዓት ላይ እንኳን ሄደን አናስጨንቃቸውም፡፡ ሶስት አራት ጊዜ ወርደን አቃጥለናል፡፡ ትክክል ነው፡፡ በትክክል ካሰብነው ያሉበት ቦታ ለራሳቸው ለጤናቸውም አስቸጋሪ ነው፡፡
ግን እኮ ወደው አይመስለኝም ፡፡ አማራጭ ስላጡ ነው፡፡ ድሮ እነዚህ ሰዎች በ30 ብር ቤት ኪራይ ያገኙ ነበር፡፡ አሁን በ400 ብርም የለም፡፡ እንዴት ይሁኑ?
ልክ ነው ግን ከላስቲክ ቤቱ ቃጠሎ ለመጀመር፣ መጀመሪያ በአግባቡ ተነግሯቸዋል፣ ህጋዊ ባለይዞታ ስላልሆኑና እንዲህ አይነት ድርድርም ውስጥ መግባት ስለሌለብን፣ አስጠንቅቀን ጉዳት ሳይደርስባቸው ነው ያደረግነው፡፡ ይሄ በህግና በመመሪያ የሚተዳደር አገር ነው፣ ነገ ሌሎች የልማት ቦታዎች ላይ ሄደው ሰፍረው “አንወጣም ግደሉን” ማለት ይመጣል፡፡ ስለዚህ ቃጠሎው ከመምጣቱ በፊት ሶስትና አራት ጊዜ መድረክ ተመቻችቶ በደንብ ተነግሯቸዋል፡፡ ግን ሊሠሙ አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሳ ቃጠሎውን አከናውነናል፡፡ በሌሊት የተባለው ውሸት ነው፡፡ በሰው ላይ ጉዳት አላደረስንም፤ እኛ እንደውም ይህን ስናደርግ አማራጭ ዕድሎችን ይፈልጋሉ በሚል ነበር፡፡
ምን አይነት አማራጮችን?
ለምሳሌ አብዛኛው ወጣት ነው፤ የጉልበት ስራ፣ ኮብልስቶን፣ የብሎኬት ምርት ስራና በመሳሰሉት ተደራጅተው መስራትና የልመናን አስተሳሰብ ያስወግዳሉ፤ ከዚያም እንደየአቅማቸው ቤት ይከራያሉ ብለን ነበር፤ግን አልሆነም፡፡
መስራት የማይችሉ አቅመ ደካሞችና ህሙማን ጉዳይስ እንዴት ይታያል?
አቅመ ደካሞች ማለትም 70 እና 80 አመት የሆናቸው በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሌላው ሰርቶ ለመኖር የሚያስችል አቅም አለው የሚል እምነት አለን፡፡ ይህን የፈጠረው ለስራ ያላቸው የወረደ አመለካከት ነው፡፡
ታዲያ ይህን የተዛባ አመለካከት የመቀየርና ህብረተሠቡን የማንቃት ሀላፊነት የማን ነው?
እኛ ብዙ ጊዜ ልናስተምራናቸው ሞክረናል ግን ወደ ልመና ያዘነብላሉ፡፡ ድሮም ተከራይተውና ተጠግተው ሲኖሩ ይሠሩ ነበር፤ አሁን እንደውም ከላይ የገለፅኳቸው አማራጭ ስራዎች አሉ፡፡ ከእነሱ መካከል ምክራችንን ሰምተው በብሎኬት ምርትና በኮብልስቶን የተሰማሩ አሉ፡፡ ወደፊትም አመለካከታቸውን ለመለወጥ ጥረታችንን አናቆምም፡፡
ቁርጥ ያለውን ንገሪኝ ፤ በአጭሩ ወረዳው እንደመፍትሔ የያዘው ሃሳብ አለው ?
አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ማንም ጐዳና እንዲወጣ አያበረታታም፤ እስከመጨረሻው የምንመክራቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሊገቡ የሚችሉበት እድል ስላለ እሱን መጠቀም አለባቸው፡፡ ይህን በተጨባጭ ያውቃሉ፡፡ እኛም እናስተምራቸዋለን፡፡ ይሄ አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው፤አሁን መሬት ያልረገጠ ነገር ማውራት ጥሩ አይደለም እንጂ ጊዜያዊ ማረፊያ የማዘጋጀት ጉዳይ ለክፍለ ከተማው አቅርበን ሃሳቡ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ሃሳቡ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን እየታየ ነው፡፡ ወረዳው እንደ አጠቃላይ ሃሳብ ያየው ነገር፤ ህጋዊ ባለይዞታ አይደሉም፣ አዎ አይደሉም፣ ነገር ግን በቦታው ላይ በምንም መልኩ ቢሆን ልጅ ወልደው ቤተሰብ መስርተው በመኖራቸው ለማህበራዊ ቀውስ ተዳርገዋል ያላቸውን ሰዎች ለይቷል፣ በነገራችን ላይ ከነዚህ ሰዎች ጋር ቤት አገኛለሁ ብለው ከጐዳና ገብተው የተቀላቀሉም አሉ፡፡ የመፍትሔ ሃሳብ ስናዘጋጅ፣ በወረዳችን ክፍት የሆነ ቦታ እና ለጊዜያዊ መጠለያ ግንባታ ሊሆን ይችላል ያልነውን አየንና መነሻ ሃሳቡን ለክፍለከተማው አቀረብን፡፡ ክፍለከተማው፣ ወረዳው ያየበት አግባብ ጥሩ ነው በሚል ተቀብሎታል፡፡ ይህም ቢሆን በዜግነታቸው እንጂ በአሁኑ ወቅት መጠለያ የሚመከር ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህ ደረጃ ነው ያለው፡፡ ቦታው በመሀንዲሶች ይታያል፣ የግንባታው አይነትና ሁኔታ ምን ይምሰል የሚለው ይወሰናል፣ መሬቱ የሚፀድቅበት መንገድና አጠቃላይ ነገሮች ታይተው የሚሆነው ይሆናል፡፡
እነዚህ ሰዎች በዚህ ሁኔታ ህይወታቸውን መግፋት ከጀመሩ አምስተኛ አመታቸውን ይዘዋል፡፡ መጠለያውን ለማግኘትስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድ ይሆን?
ቦታው ለልማት በአስቸኳይ ይፈለጋል፡፡ ቦታውን ለማስረከብ ደግሞ እነዚህን ሰዎች ቦታ ማስያዝ አለብን፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ረጅም ጊዜ ይወስዳል ብዬ አላስብም፡፡ እዚህ ላይ ማስመር የምንፈልገው፣ ነገሩ እውን ሆኖ ጊዜያዊ መጠለያው ሲሰራ፣ እዚያ ያሉት ሰዎች ሁሉ ያገኛሉ ማለት አይደለም፣ ይገባቸዋል ያልነውን ለይተን አስቀምጠናል፡፡

Read 2088 times
Administrator

Latest from Administrator