Saturday, 10 August 2013 11:10

“ዶሮን ሲያታልሏት፣ ውሀው የሚሞቀው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ኢድ-ሙባረክ! “ሃሎ!” “ሄሎ!” “ወ/ሮ በለጡን ነበር!” “ጌታዬ ተሳስተዋል፡፡” “ማን ልበል?” “ወ/ሮ በለጡ የሚባሉ በዚህ ስልክ የሉም!” ይሄ ቁጥር 091143…. አይደለም እንዴ!” “ነው፣ ግን እንደዛ የሚባሉ ሰው በዚህ ቁጥር የሉም፡፡” “እሺ አንተ ማነህ?” እናላችሁ…እንዲህ እንዲህ እያለ፣ ‘ጭቅጭቁ’ ይቀጥላል፡፡ ስሙኝማ…አንዳንዴ ሳስበው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ሰዉ “ተሳስተዋል…” ሲባል የማያምነው የመሸዋወድ ዘመን ስለሆነ ይመስለኛል። ልክ አንድ በኦፊሴል ያልተነገረ የብልጥነት ውድድር ውስጥ የገባን ነው የሚመስለው፡፡ አንድ ወዳጄ ሚኒባስ ውስጥ ያያት ጥቅስ ምን ትላለች መሰላችሁ… “ዶሮን ሲያታልሏት ውሀው የሚሞቀው ለገላሽ ነው አሏት!” አሪፍ አይደለች! እናማ ብዙ ነገር “ውሀው የሚሞቀው ለገላችሁ ነው…” አይነት እየሆነ ነው፡ እናላችሁ…ትክክለኛ መረጃ የሚሰጣችሁ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ከዚህ በፊት ያነሳናት ነገር ትዝ አለችኝማ…በበፊት ጊዜ መሀል አራዳ ውስጥ ‘አራድነትን’ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደረሰ አንድ ሾተላይ ቢጤ ነበር፡፡ እናላችሁ…አውሮፕላን በሰማይ ሲያልፍ “አጎቴ እንዳያየኝ!” ምናምን ብሎ ሲኒማ ኢትዮዽያ ግንብ ላይ ይለጠፍ ነበር፡፡ ታዲያላችሁ…ዘንድሮ “አጎቴ እንዳያየኝ…” አይነት ‘ግንብ ላይ መለጠፍ’ ስለበዛ “ቁጥር ተሳስተዋል…” ሲባል ለመተማመን አስቸጋሪ እየሆነብን ነው፡፡

እናማ…ነገራችን ሁሉ ‘ጥብቅ ምስጢር’ አይነት ነገር ሆኗል፡፡ ምን ይገርመኝ ነበር መሰላችሁ…“ተሳስተዋል…” ሲባሉ የሚቆጡ ሰዎች መብዛት ይገርመኝ ነበር። ስታስቡት ግን ሁሉም ሰው “ተሳስተዋል…” ሲባል ግስላ ነገር የሚያደርገው ሁሉም ‘መጥፎ’ ወይ ‘ምግባረ ብልሹ’ ምናምን ስለሆነ አይደለም። ብዙዎቻችን በአንድም ምክንያት ይሁን በሌላ የውሸት ስም፣ የውሸት ስልክ ቁጥር፣ የውሸት አድራሻ መስጠት…የ‘ኑሮ በዘዴ’ ስትራቴጂ ምናምን ነገር አድርገነዋል፡፡ ነገርዬው…አለ አይደል….“ዋሸ ቢሉኝ እዋሻለሁ፣ ነፋስ በወጥመድ እይዛለሁ…” አይነት ነው፡፡ ከ‘ቦሶች’ እስከ እኛ ተራዎቹ ድረስ እውነት ያልሆነ መረጃ መስጠት እየተካንንበት የመጣ ነገር ነው። የሚያስፈራው ምን መሰላችሁ…ውሸት ሲነገር መሳቀቅ፣ አንደበትን ‘ያዝ፣ ያዝ’ ማድረግ… ምናምን ቀርቶ አንዲት የጸጉራችን ዘለላ ‘ሳትነቃነቅ’ መናገር መልመዳችን! የምር እኮ…እንደ ድሮ “እስቲ እጄን ምታ!” “እስቲ ይሄ ቀን አይንጋልኝ ብለሽ ማይ…” ምናምን አይነት ‘የማጣሪያ ጥያቄም ቀርቷል፡፡ ያውስ ‘መሀላ የምንፈራ’ ብንኖር አይደል! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የስልክ ነገር ካነሳን አይቀር አስቸጋሪ ነገሮች አሉ፡፡ የኤቲክስ ምናምን ነገር “የጠላቶቻችን ሴራ…” ነገር እየመሰለ ነው፡፡ አሀ…ሁሉም ……. (እኔ የምለው…እግረ መንገዴን…እንደው ስትገቡ፣ ስትወጡ የእኛን የአዲስ አበቤዎችን ነገረ ሥራ እያያችሁልኝ ነው! በየእርስ በእርስ መአት ነገር እየተለወጠ አይመስላችሁም። አዲስ አበባ ውስጥ ‘ኢንደስትርያል ሪቮሉሽን’ ተቀልብሶ ወደ ‘አግራርያን ሪቮሉሽን’ እየተለወጠ ነው እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… አሀ…ግራ ሲገባንስ!) እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ስለ ስልክ ካነሳን አይቀር ደግሞ ሌላ አለላችሁ፡፡

አንዳንዱ ሰው ደግሞ ማንነታችሁን ገና ሳያረጋግጥ ይለቀቅባቸኋል፡፡ ስልኩን ሲጠራ ታነሱታላችሁ… “ሄሎ!” “አንተ ምን የማትረባ ሰው ነህ!” “አቤት፣ ማን ልበል?” “የማትረባ! ባንተ ቤት ብልጥ መሆንህ ነው!” “ጌታዬ የደወሉት ቁጥር…” “ስማ፣ እኔ… አይደለም የአንተ አይነቱን…” እናላችሁ…ፋታ ሳይሰጣችሁ ያለ የሌለውን ያወርድባችኋል፡፡ ታዲያላችሁ…እንደምንም ብላችሁ አንቱታን ወደ አንተ አውርዳችሁ… “ወንድም የተሳሳተ ቦታ የደወልክ መሰለኝ…” ትሉታላችሁ፡፡ “ወንድይፍራው አይደለህም!” “አይደለሁም…” ጥርቅም! ይቅርታ የለ፣ ምን የለ…ይጠረቅመዋል እናማ… እንዲህ አይነት ዘመን ውስጥ ደርሰንላችኋል! መከባበር ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ፣ የሚያስተሳስሩን ማህበራዊ እሴቶች እየተበጣጣሱ አይደለም ታላቅ ሲመጣ ከወንበር ብድግ ማለት… መንገድ ላይ ትከሻ ገጭቶ እንኳን “ይቅርታ!” ለማለት “ኮሚሽን ይከፈለኝ…” የምንል ነው የሚመስለው፡፡

ስሙኝማ…ይሄ ‘ደረት ገልብጦ በአደባባይ የመዋሸት ልማድ’… አለ አይደል… ትውልድን እንዳያበላሽ አያስፈራችሁም! “ልጆች ምን እየሰሙ፣ ምን እያዩ እንደሚያድጉ አያሳስባችሁም! ውሽሚት ዘንድ ከትሞ ቡላ በቅቤውን እየላፈ ለሚስቱ “ፊልድ ለሥራ ሄጃለሁ…” የሚል አይነት ሽወዳ የሚሸውድ አባወራ በበዛበት አገር፣ “የት ይደርሳሉ…” የተባሉ ቤተሰቦች በውሸት ምክንያት እየተሰነጣጠቁ በምናይበት ዘመን…አለ አይደል…ለትውልድ የማንሰጋሳ! የባልና ሚስት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰዉ ለጸሎት ተሰብስቦ ተቀምጧል አሉ። እናማ…ድንገት ዲያብሎስ ፊት ለፊታቸው ድንቅር ይላል፡፡ የዚህን ጊዜ ሰዉ ሁሉ እየተጯጯኸ ወደ ቀረበው አቅጣጫ ይበራል፡፡ በዚህ ሁሉ ትርምስ መሀል ግን አንድ ሰውዬ ምንም ሳይንቀሳቀሱ ዝም ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ዲያብሎስ ሆዬ ሰዉ ሁሉ ፈርቶት ሲራወጥ ሰውየው ምንም እንዳልተፈጠረ ነገር በዝምታ መቀመጣቸው ያበሽቀዋል፡፡ ይቀርባቸውናም… “እኔ ማን እንደሆንኩ አታውቅም እንዴ?” ይላቸዋል፡፡ “በደንብ አበጥሬ ነው የማውቅህ…” ይሉታል፡፡ “እና… እኔን አትፈራኝም ማለት ነው?” “ቅንጣት ታህል አልፈራህም…” ይሉታል፡፡ ይሄኔ ዲያብሎስ ግራ ይገባዋል፡፡ በብሽቀትም… “ዲያብሎስ ሆኜ እንዴት ነው የማትፈራኝ!” ይላቸዋል፡፡

እሳቸው ምን አሉ መሰላችሁ…“አውቅሀለኋ! ላለፉት ሀያ ዓመታት ከእህትህ ጋር በትዳር እየኖርኩ ነው…” አሉት ይባላል፡፡ እናላችሁ…የማወቅ ያለማወቅ፣ የመብሰል ያለመብሰል፣ በሥነ ምግባር የመታነጽ ያለመታነጽ … ምናምን ነገር ቀርቶ…መሀል ላይ ያሉ መስመሮች ሁሉ ጠፍተው…ሁላችንም አንድ ሳጥን ውስጥ ስንገባ አሪፍ አይደለም፡፡ ሴትዮዋ ሰዎችን ለእራት ጋብዛለች፡፡ የተጋበዙትም በምግብ ጠረዼዛ ዙሪያ ይቀመጣሉ፡፡ ሴትዮዋም የስድስት ዓመት ልጇን “ሚሚዬ፣ ጸሎት አድርጊልና…” ትላታለች፡፡ ሚሚም “እማዬ ምን እንደምል አላውቅም…” ትላታላች፡፡ እናትም “እኔ ስጸልይ የነበረውን ሰምተሽ የለ…እሱን በይ…” ትላታለች፡፡ ሚሚም ምን ብላ ጸለየች መሰላችሁ…“ጌታዬ ምን ሲያቀብጠኝ ነው ይሄን ሁሉ ሰዎች የጋበዝኩት!” የህጻናትን ንጹህ አእምሮ ለሁላችን ያድለንማ! ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 4552 times