Print this page
Saturday, 10 August 2013 10:47

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

አንድ ባቡር በአንድ ጉዞ ከ300 በላይ ተጓዦችን ያሳፍራል
. ባቡሩ 80 ኪሎ ሜትር በሠአት የመብረር አቅም ይኖረዋል
. በአፍሪካ የከተማ ባቡር ተጠቃሚዎች ሰባት ብቻ ናቸው

የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን በጠቅላላው 32 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚደርሠው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ፣ በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ ሁለተኛው ዙር ፕሮጀክት፤ የባቡር መስመር ዝርጋታውን ወደ 75 ኪሎ ሜትር የሚያደርስ ሲሆን ይህ የማራዘሚያ ፕሮጀክት የሚከናወነው በ2006 ዓ.ም ነው፡፡ 
አሁን በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የመጀመርያ ምዕራፍ የባቡር መስመር ዝርጋታ መነሻው ሃያት ሲሆን በመገናኛ፣ 22፣ ኡራኤል፣ መስቀል አደባባይ፣ ሜክሲኮና ልደታ አድርጐ ጦር ሃይሎች የሚደርስና የ16.3 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ነው፡፡ ከሠሜን ወደ ደቡብ የሚጓዘው ደግሞ መነሻው ከፒያሣ (ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን) ሆኖ በአዲስ ከተማ፣ አውቶቡስ ተራና 7ኛ አድርጐ፣ ከጦር ሃይሎች ከሚመጣው መስመር ጋር በጥምረት እስከ መስቀል አደባባይ ከመጣ በኋላ እስከ ቃሊቲ ማሠልጠኛ አደባባይ የሚዘልቅና የ17.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢ/ር በሃይሉ ስንታየሁ፤ ስለባቡር መስመር ዝርጋታው፣ ስለባቡሮቹ አቅምና የቴክኖሎጂ ደረጃ፣ እንዲሁም ስለፌርማታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተጠይቀው የሠጡትን ምላሽ ጠቅለል አድርገን በሚከተለው መልኩ አጠናቅረነዋል፡፡

የባቡሮች አቅም እና የአገልግሎት ዘመን
የፕሮጀክቱ ምዕራፍ አንድ ሲጠናቀቅ 41 ባቡሮች ወደ አገልግሎት ይሠማራሉ፡፡ አንድ ባቡር 3ዐ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ይህም ማለት ከሁለት ባለ ተቀጣጣይ የቢሾፍቱ አውቶብሶች ርዝማኔ ላይ 6 ሜትር ብቻ መቀነስ ማለት ነው፡፡ የአንዱ ተቀጣጣይ አውቶቡስ ርዝመት 18 ሜትር ሲሆን የሁለት አውቶብሶች ሲደመር 36 ይሆናል፡፡ በባቡሩ ውስጥ 64 መቀመጫዎች ብቻ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ወንበሮች ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ለረጅም ርቀት ተጓዦች የተሠናዱ ሲሆን አብዛኛው ተጠቃሚ ቆሞ እንዲሄድ ይጠበቃል፡፡ በአንድ ካሬ ሜትር ውስጥ ከ6-8 ሠው ሊቆም ይችላል በሚል ሲሠላ፣ በአጠቃላይ አንድ ባቡር በአንድ ጉዞ ከ268 እስከ 317 ሠዎችን ማጓጓዝ ይችላል ማለት ነው፡፡ በዚህ አይነት በሁለቱ አቅጣጫ የሚጓዙት ባቡሮች፣ በጋራ በሚጠቀሙት ከልደታ እስከ መስቀል አደባባይ ባለው መስመር እስከ 15ሺህ ሠው በአንድ ሠአት ውስጥ ማጓጓዝ የሚቻል ሲሆን በተናጠል በሚጓዙባቸው መስመሮች ቁጥሩ እስከ 7ሺህ ይጠጋል፡፡
የባቡር መሠረት ልማቱ (ሃዲዱ) በየጊዜው ተገቢው ጥገና እየተደረገለት እስከ መቶ አመት ድረስ እንዲያገለግል ታስቦ ነው የሚሰራው፡፡ ከኤሌትክሪፊኬሽንና ሲግናል (ማመላከቻ) እንዲሁም ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር የተያያዙት ደግሞ አስፈላጊው እድሣትና ጥገና እየተደረገላቸው እስከ 40 አመት እንዲያገለግሉ ተደርገው ይሠራሉ፡፡

የባቡር ፌርማታዎች
ከሰሜን ደቡብ፣ ከምስራቅ ምዕራብ በሚዘረጉት እያንዳንዱ መስመር 22 ፌርማታዎች የሚኖሩ ሲሆን በጠቅላላው 39 ፌርማታዎች ይዘጋጃሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አምስቱ ከልደታ እስከ መስቀል አደባባይ በሚዘልቀው የጋራ መስመር ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በየፌርማታዎቹ መካከል በአማካይ እስከ 700 ሜትር ርቀት የሚኖር ሲሆን በአንዳንድ ቦታ እስከ 400፣ ረጅም በሆኑት ለምሣሌ እንደጐተራ ማሳለጫ አካባቢ ደግሞ እስከ 1.2 ኪሎ ሜትር ርቀት ይኖራል፡፡ ተገቢው ፌርማታ ጋ ለመድረስ አንድ ተጠቃሚ ከ300 እስከ 400 ሜትር ብቻ በእግሩ መጓዝ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡
ፌርማታዎቹ ሦስት አይነት ናቸው ይላሉ -ስራ አስኪያጁ፡፡ አንደኛው መሬት ላይ የሚሠራ ፌርማታ ነው፡፡ ሁለተኛው የድልድይ ላይ ፌርማታ ሲሆን ሦስተኛው የመሬት ውስጥ ፌርማታ ናቸው፡፡ የመሬት ላይ ፌርማታ በሚሆንበት ጊዜ፣ ተጠቃሚዎች ለዚሁ አገልግሎት ብቻ በሚሰራ 60 ሜትር በሚረዝም ወለል (ፕላት ፎርም) ላይ ሆነው ይጠብቃሉ፡፡
ጀድልድይ ፌርማታ ደግሞ ከድልድዮቹ በቀጥታ በግራና ቀኝ በኩል ወደ እግረኞች መንገድ ዳር የሚወርዱ የመተላለፊያ ደረጃዎችና ሊፍቶች ይኖራሉ፡፡ አንድ ሰው በድልድዩ ፌርማታዎች መጠቀም ከፈለገ፣ በአስፓልቱ ዜብራዎች በኩል በእግሩ ግራና ቀኝ አስፓልቱን አቋርጦ፣ ደረጃው ጋ ከደረሰ በኋላ ከፈለገ በደረጃው፣ ካሻውም በሊፍቱ ሽቅብ ወደ ድልድዩ መውጣት ይችላል፡፡ በተለይም አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ሊፍቱን እንዲጠቀሙ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡
በመሬት ውስጥ ፌርማታዎችም በሁለቱም አቅጣጫ ወደ ውስጥ የሚያስገቡና የሚያስወጡ ደረጃዎች እና ሊፍቶች ይኖራሉ፡፡ በዚያ መሠረት ሁሉም ሰው የሚመቸውን አማራጭ በመጠቀም ወደ ውስጥ መግባትና መውጣት ይችላል፡፡

የባቡሮቹ ፍጥነትና የቴክኖሎጂ ደረጃቸው
የመጀመያው ምዕራፍ ግንባታ በ2007 ዓ.ም ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ አገልግሎት ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁት ባቡሮች፤ በሰአት 80 ኪሎ ሜትር የመብረር አቅም እንዲኖራቸው ተደርገው ዲዛይን የሚደረጉ ሲሆን ወደ አገልግሎት ሲሰማሩ ግን በአማካይ በየ700 ሜትር ርቀት ፌርማታ ስለሚኖር ፍጥነታቸው በሰአት ከ30 እስከ 40 ኪሎ ሜትር ዝግ እንዲል ይደረጋል፡፡ የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ በጀት የባቡሮቹን ዋጋም የሚያጠቃልል ነው፡፡ ኮንትራክተሩ ከመከላከያ ኢንጅነሪንግ ጋር በጋራ የሚገጣጥማቸውን ባቡሮች ጨምሮ ከውጭ ተገዝተው የሚመጡ ባቡሮችም ይኖራሉ፡፡
የቴክኖሎጂ ደረጃቸውን በተመለከተ አሁን የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት በተስፋፋባቸው ሃገሮች ያለውን የሲግናል (ማመላከቻ)፣ የኮሚኒኬሽንና የኤሌክትሪክፊኬሽን ሲስተም ያሟላ እንደሚሆን ኢንጂነር በኃይሉ ይገልፃሉ፡፡ ለምሳሌ የትኬት አገልግሎት ሲስተሙን ስንመለከት፣ ሁለት አይነት ትኬት ይኖራሉ፡፡ የኤሌክትሮኒክስ እና የወረቀት ትኬቶች፡፡ በዋናነት ጥቅም ላይ የሚውለው የኤሌክትሮኒክ ቲኬቱ ሲሆን ማንኛውም ባቡር ተጠቃሚ ያንን ትኬት ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከገዛ በኋላ፣ በየጊዜው ሂሣብ እያስሞላ መጠቀም ይችላል፡፡ በየቦታው የተዘጋጁ የሂሳብ መሙያ ጣቢያዎችም ይኖራሉ፡፡ ተጠቃሚው ልክ ወደ ባቡሩ ሲገባ፣ በሩ ላይ ወደሚገኘው ትኬት አንባቢ መሣሪያ (SVT Reader) ቲኬቱን በማስጠጋት እንዲነበብለት ያደርጋል፡፡ በቂ ሂሣብ ካለው እንዲገባ ይፈቀድለታል፡፡ ይህን ሂደት የሚቆጣጠሩ መኮንኖችም በባቡሩ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ተጠቃሚው መውረጃው ጋ ሲደርስ በድጋሚ የኤሌክትሮኒክስ ትኬቱን በሩ ጋ ወዳለው አንባቢ መሣሪያ በማስጠጋት እንዲነበብና ለተጓዘባት ኪሎ ሜትር ተገቢው ክፍያ እንዲቆረጥ ያደርጋል፡፡ አንባቢ መሣሪያውም ተጠቃሚው የተጓዘበትን ርቀት አስልቶ ሂሣቡን ይቆርጣል፡፡ አንድ ተሣፋሪ ይህን ሳያደርግ ከወረደ፣ መሣሪያው እስከ መጨረሻው ፌርማታ ድረስ ያለውን ታሪፍ አስልቶ ይቆርጥበታል፡፡ በዚህ ሂደት የባቡሩ ሠራተኞች (መኮንኖች) የት ኬት ማንበቢያ መሣሪያውን በእጃቸው ይዘው ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋሉ፡፡
የወረቀት ትኬቱ በአብዛኛው ከክፍለ ሀገር ለሚመጡና የአጭር ጊዜ ቆይታ ላላቸው የአንድ ጊዜ ተጓዦች የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡ የጉዞ ታሪፍ በተመለከተ አሁን የተወሰነ ነገር ባይኖርም የአብዛኛውን ህብረተሰብ አቅም ያገናዘበ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡
ባቡሩ ከትኬት አቆራረጥ ዘመናዊነቱ ባሻገር፣ የባቡሩን መነሻና መድረሻ እንዲሁም እያንዳንዱን የሚቆምበትን ፌርማታ ለተሳፋሪዎች በድምጽና በጽሑፍ ያሳውቃል፡፡
ለዚሁ በተዘጋጀው ስክሪን ላይ ቀጣይ ፌርማታ የቱ እንደሆነም ይገልፃል፡፡ በድምጽም ጭምር፡፡ በአሁኑ ወቅት የባቡር ኦፕሬተሮች፣ ቲኬተሮች፣ የቁጥጥር ባለሙያዎችና የመሳሰሉትን ለማሰልጠንም ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የባቡሩና የመኪኖች መንገድ አጠቃቀም
መኪናዎችና ባቡሩ በመስቀለኛ መንገዶች ላይ እንዴት ይተላለፋሉ ብለን የጠየቅናቸው ኢንጂነር በሃይሉ፤ የባቡሩ መስመር አይነት በከፊል የተዘጋ የሚባለው ሲሆን ራሱን ችሎ ከመኪና መንገድ ጋር ሳይገናኝ የመጓዙን ያህል በሌላ በኩል ከመኪኖች ጋርም መንገድ የሚጋራባቸው ጥቂት ቦታዎች እንደሚኖሩ ይናገራሉ፡፡ ባቡሩ ከመኪኖች ጋር ሊገናኝ የሚችለው ወደ ኋላ በሚመለስበት ጊዜና በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው፡፡ ባቡሩ ከመኪናዎች ጋር በሚቆራረጥባቸው የተወሰኑ ቦታዎች አካባቢ ሲደርስ፣ ከርቀት የሲግናል ማመላከቻዎች በመጠቀም መኪኖች በቀይ መብራት እንዲቆሙ ይደረጋል፡፡ ባቡሩ በፍጥነት ሲያልፍ ወዲያው መኪኖቹ ይለቀቃሉ፡፡
የአፍሪካ ሃገራት ልምድ ምን ይመስላል?
በአፍሪካ ውስጥ የቀላል ባቡር አገልግሎት የተስፋፋ አይደለም ይላሉ - ኢንጂነሩ፡፡ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት መካከል የከተማ ባቡር ተጠቃሚ የሆኑትና ለመሆን እየሰሩ ያሉት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት ሀገራት ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም የሰሜን አፍሪካ ሀገራት እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡ ከሰሜን አፍሪካ የካይሮ ሜትሮ ባቡር ተጠቃሽ ነው፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ልምድ የወሰደችበት የቱኒዚያ ቀላል ባቡር አገልግሎትም ተጠቃሽ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአልጄሪያ፣ ሞሮኮ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ፣ ፕሪቶሪያ እና ኬፕታውን የተለያየ አይነት የከተማ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አለ፡፡ በግንባታ ላይ ካሉት ደግሞ በናይጄሪያ ሌጐስ እና አዲስ አበባ ላይ የተዘረጉት ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ የአዲስ አበባው ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት ቀዳሚው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የባቡር መስመር ግንባታው ሂደት
በመሬት ላይ የሚገነባውና በድልድይ የሚገነባው የባቡር መስመር በጥሩ ሂደት ላይ ሲሆኑ እንደሆነ የሚናገሩት ኢንጂነር በኃይሉ፤ ከሁሉም የላቀ ስራ የተከናወነው በመሬት ውስጥ በሚገነባው የባቡር መስመር ነው ይላሉ፡፡
በድልድይ የሚገነባው መስመር ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ አንዳንድ ችግሮች እንዳጋጠሙት ግን አልሸሸጉም፡፡ በተለይ ከመስቀል አደባባይ እስከ ለገሃር ባለው መስመር ባለቤቱ የማይታወቅ ምናልባትም ጣልያን ሳያሰራው አይቀርም ተብሎ የተገመተ የውሃ ማስወገጃ ቦይ በግንባታው ላይ ጫና ፈጥሯል፤ ሌላው አካባቢ ግን በጥሩ ሂደት ላይ ነው ብለዋል - ኢንጂነር በኃይሉ፡፡
21 ኪሎ ሜትር በሚሆነው የፕሮጀክቱ አካል ላይ ሁሉም አይነት የግንባታ ክንውኖች እየተተገበሩ ሲሆን፤ አብዛኛው የግንባታ ስራ በ2006 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡
የሃዲድ ማንጠፍ ስራዎችም በዚያው አመት ይጠናቀቃሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ የኤሌክትሪፊኬሽን ስራዎችም በብዛት ይሰራሉ፡፡
በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ በቻይናው የባቡር መንገድ ግንባታ ድርጅት የሚከናወን ሲሆን የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ 475 ሚ.ዶላር ነው፡

 

 

Read 9609 times
Administrator

Latest from Administrator