Saturday, 10 August 2013 10:40

አህያ እየነዱ፣ ቅል እየሳቡ፣ ከኋላ ሲከተሉ፣ ወተት ያለቡ ይመስላል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

(ሃርያ ላግድ ጐስያ ጐችድ ጌድዋ ካልዮጌ ዮሳመለቼስ)
ከዕለታት አንድ ቀን አያ አንበሳና ሰው ወዳጅ ሆኑ አሉ፡፡ “እዚህ ከምንቀመጥ ለምን በጫካ ውስጥ ዞር ዞር እያልን እግራችንን አናፍታታም” አለ ሰው፡፡
አንበሳም፤ “እኔ ጫካው ሰልችቶኛል፡፡ መንቀሳቀስ ከሆነ የፈለግከው ወደሚቀጥለው ከተማ እንሂድ”
ሰው፤ “መልካም፡፡ እየተዘዋወርን የከተማውን ሁኔታ እንይ”
በዚህ ተስማምተው መንገድ ጀመሩ፡፡
መንገድ ላይ ጨዋታ አንስተው ሲወያዩ የየራሳቸውን ዝርያ አንስተው ማውራት ጀመሩ፡፡
“እናንተ የሰው ልጆች’ኮ የእኛን የአንበሶችን ያህል ጥንካሬ የላችሁም፡፡ እኛ የዱር አራዊትን ሁሉ አስገብረን በእኛ ሥር እንዲሆኑ አድርገናል፡፡ እናንተ ግን እርስ በርሳችሁ እንኳን መስማማት አቅቷችሁ፤ ጦርነት፣ ዝርፊያና እልቂት ውስጥ ትገኛላችሁ” አለ አንበሳ፡፡
ሰውም፤ “አይደለም፡፡ እኛ የሰው ልጆች፤ የዓለምን ሥልጣኔ ለመምራት ሁልጊዜም ከላይ ታች ስንል፣ ያለውን ሃብት በጋራ ለመጠቀም፣ በእኩል ለመከፋፈል፣ ስንጣጣር ነው ግጭት የሚፈጠረው፡፡ ሌላው ቀርቶ አንተ የምትኖርበትን ጫካና ደን እንዳይጨፈጨፍ ባንታገል ኖሮ ይሄኔ መኖሪያ አጥተህ ነበር” ይለዋል፡፡
አንበሳም፤
“እሱ ለእኛ በማዘን ሳይሆን የራሳችሁን ህይወት ለማራዘም ስትሉ የምታደርጉት ነው፡፡ እኛ የተፈጥሮ ጥንካሬያችን ብቻ ያኖረናል”
ሰው፤ “በሽቦ በታጠረ መናፈሻ ውስጥ እንድትኖሩ የእንስሳት ማቆያም እኮ አዘጋጅተንላችኋል፡፡ አንበሳ፤ “እሱም ቢሆን እኛን ለቱሪስት እያሳያችሁ ገንዘብ የምትሰበስቡበት ነው፡፡ ለእኛ እሥር ቤት ነው”
በዚህ ማህል አንድ አደባባይ ጋ ይደርሳሉ፡፡ አደባባዩ መካከል ሐውልት አለ፡፡ ሐውልቱ አንድ ሰው አንድ አንበሳን ታግሎ ሲጥለው የሚታይበት ስዕል አለው፡፡
ይሄኔ ሰውዬው በአሸናፊነት ስሜት፤
“ተመልከት፤ የሰው ልጅ አንበሳን እንዴት እንደሚያሸንፈው!” አለው፡፡
አንበሳም፤ “ይሄ ያንተ አመለካከት ነው፡፡ ይህንን ሐውልት የሠራነው እኛ አንበሶች ብንሆን ኖሮ፣ አንበሳውን ከላይ፣ የሰውን ልጅ ከታች አድርገን እንቀርፀው ነበር!” አለው፡፡
***
ሁሉ ነገር ሁለት ወገን እንዳለው አንርሳ፡፡ ከማን አቅጣጫ ነው የምንመለከተው ነው፤ ጉዳዩ፡፡ ሁሉም እኔ ነኝ ጠንካራ ይበል እንጂ ጠንካራው በመካያው ይለያል፡፡ ዕውነተኛው፤ የማታ የማታ መለየቱ የታሪክ ሂደት ነው፡፡
“ዳገት ከላይ የሚያዩት ቁልቁለት፣ ቁልቁለት ከታች የሚያዩት ዳገት” እንዳለው ነው ገጣሚው፡፡
መቼ ቁልቁለቱ ዳገት እንደሚሆንብን ካላስተዋልን “ያሰፈሰፈው መዓት” ይጠብቀናል (The impending catastrophe እንዲሉ)፤
ሐውልቱን፤ ጊዜ የሰጠው ይሠራዋል፡፡ አንድ የቀድሞ የደርግ ጄኔራል በሰጡት ኢንተርቪው፤ “ስለደርግ በሚያወራ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በቀዳሚነት የሚታዩት እርሶ ነዎት - ውስኪ ሲጠጡ፡፡ ምን ይሰማዎታል?” ቢባሉ፤ “ይሄ ምንም አይገርምም፡፡ እኛ በጊዜያችን ውስኪ ጠጣን! እነሱም ይሄው በጊዜያቸው ውስኪ እየጠጡ ነው” ብለው መልሰዋል፡፡ ጊዜ ፈራጅ ዳኛ ነው፡፡
ዛሬም የሀገራችን ቁልፍ ጉዳይ መቻቻል ነው፡፡ መቻቻል ብስለትንና ዕውቀትን አጣምሮ የያዘና ጊዜን በቅጡ ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባ ዕሳቤ ነው፡፡ መልካም ባሕል ያለው ህዝብ የታደለ ነው፡፡ የባህሉ ጥንካሬ ለመቻቻሉ ብርቱ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደዚያ ነው፡፡ እኔ ብቻ ነኝ ጠንካራ የሚል አመለካከት ከመቻቻል ጋር ግንባር ለግንባር ይጋጫል፡፡ “እኔ ነኝ የበላይ” የሚል አስተሳሰብን ያመላክታልና፡፡ መካረርና ማክረር ከጽንፈኛና ከፅንፈኝነት ጐራ መክተቱ እውን ነው፡፡ መጭው ነገር አስቀድሞ ጥላውን ይጥላል፡፡ (Coming events cast their shadows) እንደሚሉት ፈረንጆች) (ለላመት የሚቆስል እግር ዘንድሮ ዝምብ ይወረዋል፤ እንዳለውም አበሻ)
የሩቁን ያላስተዋለ አለቃ፣ ኃላፊ ወይም መሪ፣ አስተውሎም ያላመዛዘነ፤ አመዛዝኖም በጊዜ እርምጃ ያልወሰደ ከሆነ፤ በአደጋው ውስብስብ መረብ ውስጥ ገብቶ መተብተቡ አይቀሬ ነው፡፡ ብርቱ ጥንቃቄ ያሻል፡፡ ስለዲሞክራሲ መጠንቀቅ ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ስለሃይማኖት መጠንቀቅ የበለጠ ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጐረቤት አይኖርምና ሁሉም ወገን ሊያስብበት የሚገባ ጥልቅና ጥብቅ ጉዳይ ነው፡፡
እንደተጣደ ወተት መቼ ሊገነፍሉ እንደሚችሉ የማናውቃቸውን ነገሮች በዐይነ-ቁራኛ ማየት፤ ተገቢውን ማርከሻ ማወቅና መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ እንደ ሙስና፣ ኢፍትሐዊነት፣ የዕምነት - ሽፋን ሂደቶች… ወዘተ ጉዳዮች በትኩረት መጤን ያለባቸው ናቸው፡፡
ሬዲዮው ያወራል በተግባር ምንም የለም፡፡ ቴሌቪዥኑ ያሳያል በተግባር የለም፡፡ ጋዜጣ ይፅፋል በግብር ምንም የለም፡፡
The rottener the time the easier it is to get promoted ይላል ሔልሙት ክሪስት የተባለ ፀሐፊ፡፡ (ጊዜው ወይም ዘመኑ እየተበሳበሰ ሲሄድ የሥራ ዕድገትና ሹመት በሽበሽ ይሆናል እንደማለት ነው፡፡) የተሾምንበት፣ የአደግንበት ሥራ ተግባርን ግድ እንደሚል ደጋግመን እናስብ፡፡ ምን አልሠራንም የምንለውን ያህል የሠራነው ተገቢ ነወይ? ብለንም ለመጠየቅ እንትጋ!
የትውልድ ዝቅጠትና መበስበስ (decadence) የፖለቲካውና የሶሺዮ ኢኮኖሚው ድቀት የሚያመጡት ክስተት ነው፡፡ እጅግ በከፋ ገፁ ሲታይ ከሀገራችን ከውይይት ይልቅ ግጭት፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነት ይዘወተራል፡፡ በእንዲህ ያለው ዘመን አፍ ይበዛል፡፡ አዕምሮ ይደርቃል፡፡ አንድ ደራሲ እንደሚለው verbal diahria and mental constipation በይፋ ይታያል፡፡ (የአፍ - ተቅማጥና የአዕምሮ - ድርቀት ይንሰራፋል እንደማለት ነው፡፡ መለፍለፋ፣ መለፍለፋ፣ መለፍለፋ ብቻ፡፡ ሐሳብ የለም፡፡ ዕውቀት የለም፡፡ ጥበብ (wisdom) የለም፡፡ ተግባር - አልባ ልፍለፋ! ለዚህ ነው ከልኩ በላይ የተመኘነው ለውጥ በቀላሉ የማይመጣው፡፡ የአፍ መብዛት፣ የስብሰባ መብዛት… የግምገማ መብዛት ብቻውን ፍሬ እንደማያፈራ ደጋግመን ተናግረናል፡፡ የሚሰማ አለመኖሩ ነው ምላሹ፡፡
“የምንለውን ብለናል የምናደርገውን እንጀምር!” አሉ አሉ የቀድሞው መሪ፡፡ ስላልን የሠራን እንዳይመስለን ነው ነገሩ፡፡
“አህያ እየነዱ፣ ቅል እየሳቡ፣ ከኋላ ሲከተሉ፤ ወተት ያለቡ ይመስላል” የሚለው የወላይታ ተረት ሁኔታውን የበለጠ ይገልፀዋል፡፡

Read 5880 times