Saturday, 10 August 2013 10:31

በፀረሽብር አዋጁ ላይ የፓርቲዎች ክርክር መራዘሙን ተቃዋሚዎች አልተቀበሉትም

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “የፀረ ሽብር አዋጅና የፓርቲዎች አቋም” በሚል ርዕስ ለዛሬ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረውን ክርክር ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለፁ። የክርክር ፕሮግራሙ የተራዘመው ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን በመግለፁ ተቃውሟቸውን የገለፁት፣ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት)፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መድረክ (መድረክ) እና ሠማያዊ ፓርቲ ናቸው፡፡ በፀረሽብር አዋጅ ዙሪያ ህብረተሰቡ ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖረው ማክሰኞ ውይይት ይካሄዳል የሚል የደብዳቤ ጥሪ ደርሷቸው እንደነበር ፓርቲዎቹ አስታውሰው፤ ውይይቱ ወደ ቅዳሜ የተላለፈው አንዳንድ ፓርቲዎች ተጨማሪ የዝግጅት ጊዜ በመጠየቃቸው ነው ተብለን ነበር ብለዋል፡፡ እንደገና በትላንትናው ዕለት ኢቴቪ ውይይቱን ለሁለተኛ ጊዜ አዝራሞታል በማለት ቅሬታቸውን የገለፁት ፓርቲዎቹ፣ በፕሮግራም መደራረብ ምክንያት ውይይቱ ተሰርዞ ለሌላ ቀን እንደተራዘመ የተነገረን በስልክ ነው ብለዋል፡፡ የፕሮግራሙን መሰረዝ አስመልክቶ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤ ፕሮግራሙ የተሰረዘው “ኢህአዴግ ሃሳብን እንደጦር ስለሚፈራ ነው” ብለዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የአቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው፤ ኢቴቪ ፕሮግራሙን ማራዘሙንም ይሁን መሰረዙን በደብዳቤ እንዳላሳወቀ ጠቅሰው፣ አንድ ሰው ደውሎ ተሰረዘ ወይም ተራዘመ ማለቱ አግባብ ባለመሆኑ አንቀበለውም” ብለዋል፡፡ ለውይይቱ ተወካይ መድበን ነበር የሚሉት የመድረክ ሊ/መንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ ለተወካያቸው ተደውሎ ፕሮግራሙ ላልተወሰነ ቀን መራዘሙ እንደተነገራቸው ገልፀዋል፡፡ “የመንግስት ሚዲያዎች ብዙ ጫና እንዳለባቸው እናውቃለን” ያሉት የመድረክ ሊቀመንበር፤ አሁንም ከበላይ አካላት በተላለፈ ክልከላ ፕሮግራሙ ሊሰረዝ እንደቻለ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር በበኩላቸው፤ የፀረ ሽብር አዋጁ ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ያገኘው አንድነት ፓርቲ “የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት” በሚል አዋጁን ለማሰረዝ እንቅስቃሴ ከጀመረ ወዲህ ነው ብለዋል፡፡ ፓርቲዎችን በደብዳቤ ለውይይት የጋበዙት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝን፣ በስልክ አግኝተናቸው “ምን አይነት መረጃ እንደፈለጋችሁ ከባልደረባዬ ሰምቻለሁ፤ ከ30 ደቂቃ በኋላ ደውሉ፤ አሁን ስራ ላይ ነኝ” የሚል ምላሽ የሰጡን ቢሆንም ከዚያ በኋላ ስልካቸው ስለማይነሳ ሳናገኛቸው ቀርተናል፡፡

Read 28901 times