Saturday, 10 August 2013 10:30

የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊት ማህበር ለ22 አመት በአቤቱታ ተንገላታሁ አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

        የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊት ማህበር፤ የአባላት መዋጮ ታግዶበትና የጡረታ መብት ሳይከበር ለሃያ አመታት በአቤቱታ እንደተንገላታ የገለፁት ም/ዋና ፀሃፊ ኮ/ል አለማየሁ ንጉሴ፤ ማህበሩ እንዲፈርስም ተደርጐብናል ሲሉ አማረሩ፡፡ ለመረዳጃ እድር ከእያንዳንዱ አባል በየወሩ 1 ብር እየተዋጣ የተጠራቀመና በባንክ የተቀመጠ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያለ አግባብ ታግዶብናል የሚሉት ኮ/ል አለማየሁ፤ ገንዘቡ ከንጉሡ ስርአት ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ፣ በችግርና በሞት ጊዜ ለመረዳዳት ከአባላት ደሞዝ የተዋጣ ነው ብለዋል፡፡ በህጋዊ መንገድ በባንክ የተቀመጠው የእድር ገንዘብ ባልታወቀ ምክንያት ታግዶ ከቆየ በኋላ፣ በፍ/ቤት የክርክር አፈፃፀም ለማህበሩ እንዲለቀቅ ቢታዘዝም ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም ብለዋል፤ ኮ/ል አለማየሁ፡፡

ገንዘቡ ለምን አላማ እንደሚውል በባለሙያ አስጠንታችሁ እቅድ አቅርቡ ስለተባልን፣ 7ሺ ብር ከፍለን አስጠንተናል ያሉት ኮ/ል አለማየሁ፤ ለችግረኛ አባላት አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክና የመዝናኛ ክበብ ለመገንባት እቅድ አውጥተን ብናቀርብም ምላሽ አልተሠጠንም ብለዋል፡፡ በሃገሪቱ ህግ መሠረት ካገለገልንበት መስሪያ ቤት ጡረታ እንዲፈቀድልን ለበርካታ ዓመታት ያቀረብነው አቤቱታ ሰሚ በማጣቱም፣ በኑሮ ውድነቱ እና በሌሎች ጫናዎች የማህበሩ አባላት ህይወት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

ምላሽ ሳናገኝ እንድንገላታ መደረጉ፣ የቀድሞ አባቶችን ውለታ መዘንጋት ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ይሄ አልበቃ ብሎ ዘንድሮ ማህበሩ ፍቃዱን እንዳያሣድስ ተከልክሏል ብለዋል፡፡ “የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊትና ሲቪል ሠራተኞች ማህበር” የሚለውን ስያሜ ትታችሁ በበጐ አድራጐት ድርጅት ስም ተደራጅታችሁ ኑ ተብለናል ይላሉ - ኮ/ል አለማየሁ፡፡ ማህበሩ ለአመታት ከከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ድረስ በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያደርስም ምላሽ አለማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

Read 26978 times