Saturday, 03 August 2013 11:00

በስብሐት ላይ የተቃጣው የሚካኤል ዱልዱም ሰይፍ

Written by  ሚልኪ ባሻ
Rate this item
(5 votes)

“መልክአ-ስብሐት” የተሰኘውን እና በደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ህይወት እና ሥራ ዙሪያ የሚያጠነጥነውን ሰሞነኛ መፅሐፍ በትኩሱ አንብቤ ከመጨረሴ በውስጡ ፍንትው እና ቦግ ያለ አርእስት የያዘ አንድ መጣጥፍ ላይ አስተያየት ብጤ ለመከተብ ልቤ ተጣደፈ፡፡ የመጣጥፉ ርዕስ “ስብሐት ገ/እግዚአብሔርን ከሌላ ማዕዘን” ይላል፡፡ የጥድፊያዬ ምክንያት ባለመጣጥፉ አቶ ሚካኤል ሽፈራው፤ ማንኛውንም “ከስሜት ነፃ” የሆነ አስተያየት ለማስተናገድ ክፍት እንደሆኑ በቅድምያ በማሳወቅ ያቀረቡት ግብዣ ነው፡፡ ታዲያ በእንዲህ አይነቱ ልባዊ ግብዣ ልቡ ወከክ የማይል ማን አለ? በተለይ ደግሞ ሙሉ በመሉ ባይሆንም ከእርሳቸው ጋር የሚጋራው ሀሳብ ያለው እንደኔ አይነቱ ሰው! በፀሐፊው ልበሙሉነት እና ተጋፋጭነት ያደረብኝ አድናቆትም የራሱን ድርሻ አዋጥቷል፡፡ እስኪሰለቸን ድረስ በየጋዜጣውና በየመፅሔቱ ስለ ስብሐት አንድ አይነት መወድስ በምንሰማበት ወቅት አለአንዳች ፍርሃት እና ማመንታት የሚሰማቸውን እና የሚያስቡትን የገለጡበት ሁኔታ ያስቀናል፡፡
ብዕር እንዳነሳ ያጣደፉኝ እኒህ ቢሆኑም የፅሁፌ ዓላማ ግን ወዲህ ነወ፡፡

አቶ ሚካኤል የስብሐትን ህይወትና ሥራ ፋይዳ ለማጣጣል እና ለማንኳሰስ የተጠቀሙባቸው ማስረጃዎች አንድም ደካማ አንድም ደግሞ ተጣራሽ ሆነው በማግኘቴ እነዚህን ህፀፆች በተቻለ መጠን በመልቀም ለእሳቸውም ሆነ በስብሐት ላይ ተመሳሳይ ከሆነ “ሌላ ማዕዘን” ለመፃፍ ምኞቱ ላላቸው ጠንከር ያለ ፅሑፍ እንዲፅፉ ለማበረታታት ነው፡፡ ምክንያቱም እኔም ራሴ ምድቤ ስብሐትን በስስት ከሚያዩት ሳይሆን የጐሪጥ ከሚያዩት መካከል ነኝና፡፡ ሦስተኞቹ ቡድኖች የሚያጉረጠርጡበት ናቸው፡፡ ከእነርሱ የለሁበትም፡፡ የአቶ ሚካኤል ፅሁፍ ድካም፣ ስብሐት እና ስብሐታዊ ትኩሳቱ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ለመቸለስ የሚቋምጡ ሁሉ አስቀድመው የባልዲያቸውን ሽንቁር መድፈን እንደሚበጃቸው የሚያስተምር ይመስለኛል፡፡
አንድ… ሁለት እያለ እስከ ሃያ በሚደርሱ (በቆጠራ ስህተት አስራ ዘጠኝ ተብለው ተቆጥረዋል) ንዑስ አርእስቶች የተከፋፈለው የአቶ ሚካኤል ፅሁፍ ውስጥ አምስት ያህሉ በስብሐት የግል ባህሪይ ላይ የሚያተኩሩ፣ አራት ያህሉ ፀሐፊው ከስብሐት ጋር ባሳለፈው ዘመን የገጠመውን የግል ተሞክሮ የሚያትቱ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ፀሐፊው የአቶ ስብሐትን የንባብ እና የሥነ ፅሁፍ ሕይወት ለመዳሰስ እና አቶ ስብሐት በስተርጅናው የልጅ ፊት እንዴት ሊኖረው እንደቻለ በሳይኮአናሊስስ ቲኦሪ መሰረት ለመተንተን የሞከሩባቸው ናቸው። እንግዲህ መጣጥፉ ስነፅሁፋዊ እና ግላዊ ሂስ፣ ኑዛዜ፣ እንዲሁም ስነልቦናዊ ትንታኔ በአንድነት የተደብለበሉበት መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ እኛ ደግሞ ለነገራችን እንዲመቸን ጥቢኛ ጥቢኛ እያደረግን እንፈትሻቸው፡፡
የአቶ ሚካኤል ኑዛዜ
የመጣጥፍ አቅራቢ አቶ ሚካኤል፤ ከስብሃት ገ/እግዚአብሔር ጋር በወጣትነታቸው ዘመን ስላሳለፉት ዘመን በከፍተኛ ፀፀት እና ቁጭት ይናገራሉ፡፡ በስብሐት እግር ስር ስለባከነው አፍላ ጉልበታቸው እና እድሜያቸው፣ የህልም እንጀራ ስለሆነው ተስፋቸው እና ስለተሰለበው ወኔያቸው ስብሐትን ፍፁም ተጠያቂ አድርገው ይከሱታል፡፡
ምንም እንኳን የአቶ ሚካኤል ኑዛዜ ልባችን ውስጥ ሀዘን ቢጤ ለመጫር አቅም ባያጣም ቅሉ ኑዛዜያቸው ክርክራቸውን አሳማኝ ሊያደርግ ያልቻለበት አንድ ወይም ሁለት ድካሞች እንዳለበት መጠቆም ግን ተገቢ ነው፡፡ አንዱም አቶ ሚካኤል ባከነብኝ ላሉት ወጣትነት ተጠያቂነቱን መቶ በመቶ ከራሳቸው ላይ አውርደው ስብሐት ላይ በመደፍደፍ (Blame Shifting) እንደ ግለሰብ ህይወታቸውን በተመለከተ ያለባቸውን ዋነኛ ተጠያቂነት እና ኃላፊነት በግልፅ መሸሻቸው፣ ኑዛዜያቸው አንጀት በመብላት ለማሳመን ከሚደረግ ሙከራ ብዙም ያልዘለለ አድርጐታል፡፡ አቶ ሚካኤል ይህን ያደረጉት ሆነ ብለው ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ለህይወታቸው መበላሸት እና መኮላሸት ራሳቸው ኃላፊነቱን እና ተጠያቂነቱን በቅድሚያ ቢወስዱ የስብሐት ቀንድ እና ጅራት ይጠፋና ሰው መሆኑ ይታይ ነበር፡፡ እርሳቸው ግን ስብሐትን አንድ ግለሰብ ሳይሆን “መልአከ ሞት” ሊያደርጉት አንዴ ታጠቀው ስለተነሱ ያንን ኃላፊነት መውሰድ አልፈለጉም፡፡

ስለዚህ አስቂኝ አመክንዮ እያስተማሩን ለሂትለር መሳሳት ተጠያቂው ኒቼ ነው፣ ለኒቼ ደግሞ ሾፐንሀወር፣ ለሾፐንሀወር ደግሞ ቡድሃ… ማለት እንደምንችል ይነግሩናል፡፡ በዚህ አካሄድ ዝርዝሩ ማለቂያ ይኖረው ይሆን? አቶ ሚካኤል የሚበጃቸው ከሽሽት ይልቅ ይህ የጥፋት ምንጭ ከሰው ሁሉ ልብ እንደሚፈልቅ በማመን እና ስብሐትም እንደሳቸው ሁሉ የዚህ ምንጭ ተጋሪ እንደሆነ በማወቅ መጀመር ነው እንጂ “የስብሐት መቀነት አደናቀፈኝ” የሚለው ሰበብ ራሳቸውን በራሳቸው ለማፅናናት እና ለማሸንገል ካልሆነ በቀር፣ የስብሐትን ሥራ በአደባባይ ለማጣጣል እምብዛም የሚጠቅማቸው አይሆንም፡፡ ኑዛዜያቸውም የኤድን ገነቱን የመካሰስ ድራማ ያስታውሰናል፡፡
የአቶ ሚካኤል ኑዛዜን እንዳንቀበል የሚያሰናክለን ሌላው ምክንያት ደግሞ “ስብሐት አይኔን ገለጠልኝ፣ እርሱን ያወቅሁበት ቀን የተባረከች ትሁን” የሚሉና ከእርሱ ጋር የነበራቸውን ቆይታ እና ቁርኝት በናፍቆት የሚያወሱ ጥቂት የማይባሉ ታዋቂ ሰዎች የመኖራቸው እውነታ ነው፡፡ ይሄም እውነታ “መልክዐ-ስብሐት” ውስጥ በሰፊው ተንፀባርቋል፡፡ ግዙፍ ስም ባላቸው አያሌ ፀሐፊያን እና ገጣምያን በቀረበው “በመፅሐፍህ የምትኖር፤ ስብሐታችን ሆይ፣ ስምህ ትቀደስ” አይነት የውዳሴ ጋጋታ መካከል የስንጥር ያክል የተሰነቀረችው የአቶ ሚካኤል ኑዛዜ፤ የስብሐትን “ቅዱስ” ስም እውን ማርከስ ትችል ይሆን? መፅሐፉ አቶ ሚካኤልን በአሳ ነባሪው የተዋጠውን ነብዩ ዮናስን አስመስሏቸዋል፡፡ አቶ ሚካኤል መጣጥፋቸው እንዲካተት ባያደርጉ እና በሌላ መንገድ ቢያወጡት ይሻል ነበር፡፡ እንግዲህ አንዴ አሳ ነባሪው ውጧቸዋልና መልአኩ ሚካኤል ይርዳቸው ከማለት ውጪ ምን ይባላል?
ባህርይ እና የህይወት ዘይቤ ላይ ያነጣጠረው ትችት
አቶ ሚካኤል ምርር እርር ብለው ስብሐትን ከሚነቅፉበት ነገር አንዱና ዋነኛው ፈንጣዥነቱ እና ተድላዊነቱ (Hedonism) ነው፡፡ እኔም ራሴ የስብሐት ልቅ የህይወት ዘይቤ በመነቀፉ ቅር የምሰኝ ሰው ባልሆንም አቶ ሚካኤል ይህንን የስብሐትን ደስታ አሳሽነት እና ተድላዊነት ሲነቅፉ ቆመው የተንጠራሩበት እና ከፍታን ያገኙበት መሰረት የሆነው ቡድሂዝም (ፍልስምና (2) እና መልክዐ ስብሐትን ማየት ይቻላል) ስብሐትን ለመኮርኮም የተመኙትን ያህል ቁመታቸውን እንዳላስረዘመላቸው ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም የቡድሂዝምም ሆነ የሄዶኒዝም አስተሳሰቦች ዋንኛ አላማ እና ግብ በህልውና ውስጥ የሚገጥሙትን መከራዎች እና ስቃዮች በማምለጥ ደስተኛ እና ሰላማዊ ኑሮን መኖር በመሆኑ ነው። እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች የሚለያዩት ግባቸውን ለማሳካት ይበጀናል ባሉት መንገድ ብቻ ነው። የቡድሂዝም አላማ እና መንገድ ዝነኛ በሆነው እና ገራገር መስሎ አብዛኛው ሰው ሳያውቀው በሚናገረው ቅኔ ውስጥ ደምቆ ይታያል፡፡
ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም
ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም
የስብሐት ሄዶኒዝም ደግሞ እኔው ራሴ በፈጠርኳት ግጥም እንዲህ ተሸብልላለች፡-
ፅድቅና ኩነኔ ከሌለ ከሌለ
ስጋዬን ባስደስት ምናለ ምናለ
ታዲያ በአንድ አምላክ የፍርድ ወንበር ስር የሚበየን የፅድቅና የኩነኔን ብያኔ የሚክድ እምነት የሚያራምድ ሰው “ፈራጁ አምላክ ከሌለማ ደስ ያለኝን እንዳረግሁ ብኖር ምናለበት!!” ብሎ ለሚጠይቀው ሰው የሚሰጠው አጥጋቢ ምላሽ ከየት ይመጣል? ተድላዊነት እንደ ቡድሂዝም ያሉ ሁሉ አምላክ እምነቶች (Pantheistic) ወይም እንደ ቁስ አካላዊነት ያሉ ኢ-አማኒ አስተሳሰቦች ጭምቅ (Logical conclusion) በመሆኑ ከነዚህ አስተሳሰቦች ተነስተን ለመሞገት አቅም ያንሰናል፡፡
አቶ ሚካኤል ግን “ቡድሃ” ሳያንሳቸው የማህበረሰቡ ጠባቂ እና መንገድ ጠቋሚ ነቢይ አድርገው በሚቆጥሩት በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ግዙፍ ቁመና ላይ በመንጠላጠል ሎሬቱ ለስብሐት እና ለብጤዎቹ በዘመኑ ያደረገውን የንሰሐ ጥሪ “ከትንቢት መፅሐፍ” ውስጥ እየጠቀሱ በከንቱ የሚሞግቱበት የባከኑ ገፆችም አሉ፡፡ ይሔም ሙከራቸው ሎሬቱ ራሳቸው በመሞታቸው ሰሞን የገቡት ሌላ “ንሰሐ” እንደነበር እንደማያውቁ፣ ካወቁ ደግሞ እንዳላወቁ ለማስመሰል እንደሞከሩ ያስነቃባቸዋል፡፡ ባለቅኔው ዛሬ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ለስብሐትና ለጓደኞቹ የሚያቀርቡት የንሰሐ ጥሪ አቶ ሚካኤል እንዳሉት ማህበራዊ እና አገራዊ መልክ ሳይሆን መንፈሳዊ መልክ ይኖረው እንደነበር የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡
አቶ ሚካኤል ስብሐትን ለማንኳሰስ ብዕራቸውን አለመጠን እንዳተጉ የሚያስነቃባቸውን ፍንጭ መጣጥፋቸው ውስጥ በየቦታው ትተውልናል፡፡ ከሁሉም ባስ ያለው እና አሁንስ አበዙት የሚያሰኘው ግን ስብሐት በባህል፣ በሐይማኖት እና በልማድ ሰንሰለት ተተብትቦ ከነበረው ማህበረሰብ ጋር የነበረውን ያፈጠጠ ግጭት እና ተቃርኖ ለማድበስበስ የሞከሩበት ሙከራ ነው፡፡ በገፅ 146 ላይ እንዲህ ብለዋል “ያለ ማህበራዊና ቤተሰባዊ ኃላፊነት በዝሙት እና በአልኮል ተነክሮ ለመኖር ከነበረው የማያወላውል አቋሙ ከሚመነጭና በዚሁ ሰበብ ከሚታይ የአኗኗር እና የአስተሳሰብ ልዩነት በስተቀር ከማህበረሰቡ ጋር ምንም አይነት ማህበራዊ ተቃርኖ አልነበረውም፡፡
ስብሐት ልክ በግሪክ ትራጄዲ ውስጥ እንዳሉት ገፀ-ባህርያት በሁለት ማህበረሰባዊ ህግጋት መካከል ተወጥሮ ከገባበት አጣብቂኝ የተነሳ ራሱን መጉዳት በመምረጡ ህብረተሰቡ የሚያጨበጭብለት ትራጂክ ሄሮ ባይሆንም፣ ህይወቱ ግን ትራጂክ እንደነበር መካድ የሚቻል አይመስለኝም። ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ቅራኔ እና ግጭት የገለፀበት መንገድ ሳይንሳዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ፍልስፍናዊ ሳይሆን ይልቁኑ ስነውበታዊ (Aesthetical) እና ህልውናዊ (Existential) መሆኑ ቅራኔ አልባ ነበር አያስብለውም፡፡ እንደውም ከአለቃ ገብረሃና በመቀጠል ከማህበረሰቡ ጋር በፈጠረው ከፍተኛ ግጭት እና ቅራኔ በጥሩም በመጥፎም ዝነኛ የሆነ ሰው ስብሃት ብቻ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በገፅ (146-147) የስብሐት የድህነት ህይወት ዘይቤ፣ ፍልስፍናዊ ማዕቀፍ የጐደለው ይልቁንስ ከስንፍና እና ራስን መግዛት ካለመቻል የመጣ እንደሆነ የሚነግሩን አቶ ሚካኤል፤ በገፅ (157) ላይ ደግሞ ድህነቱ የፍልስፍናው ውጤት እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ዥዋዥዌ የሚጫወቱት ፀሐፊው፤ ስለ ስብሐት ስንፍና አውርተው አይጠግቡም፡፡

ነገር ግን ይሄ ክሳቸው አንባቢን እንዲያስነሳ የሚያደርጋቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ ስብሐትን የመሰለ የአለምን ታሪክና ስልጣኔ የለወጡ ታላላቅ መፅሐፍትን በመመርመር ዘመኑን ያሳለፈ፣ በርከት ያሉ ልብ ወለዶችን የፃፈ እንዲሁም ቁጥራቸው የማይታወቅ የጋዜጣና የመፅሔት ፅሁፎችን ይፅፍ የነበረ ሰው፣ እንዴት በስንፍና እና በዲስፕሊን ማጣት ሊታማ ይችላል? ድህነቱም ቢሆን ግዳጅ ሳይሆን ውዴታዊ (Voluntary Poverty) እንደነበረ ለማሰብ የሚያስደፍሩ አያሌ ምክንያቶች ቢኖሩም (አቶ ሚካኤል ራሳቸውን እየተጣረሱ ያቀበሉንን ጨምሮ) ለጊዜው ግን አስተማማኝ የገንዘብ ዋስትና ሊያገኝበት ይችል የነበረውን እና ስነውበታዊ ነፃነቱን ላለማጣት ሲል የሰዋውን የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሥራውን ማስታወሱ ይበቃል፡፡
ስለ ስነፅሁፍ ስራዎቹ
አቶ ሚካኤል፤ የስብሐት ስነፅሁፉን አስመልክተው በሰነዘሩት ሂስ፣ አሁንም እርስ በርሱ የሚጣረስ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አንድ ቦታ ላይ “በርግጥ በየሳምንቱ በየጋዜጦች ከሚፅፋቸው ትርጉም እና ፋይዳቸውን ለመረዳት የሚያስቸግሩ… አብዛኛዎቹ በሃሺሽና በአረቄ በነፈዘ አእምሮ ሳለ የሚፅፋቸው ፅሁፎች (ገፅ 146) ሲል፣ በሌላ ቦታ ደግሞ ስለ ስብሃት ስነፅሁፍ ስራዎች ስናወራ አንድ ልንክደው የማንችለው እውነታ ቢኖር፣ አገላለፆቹ የአንደበተ ርቱእ ጨዋታ ቁጭ ብሎ የማዳመጥ ያህል ግልፅ፣ ቀላል እና ተነባቢ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ችሎታው ተፈጥሮአዊ ተሰጥኦ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ለረጅም ዘመናት ያለማቋረጥ ከመፃፍ የዳበረ መሆኑን ማየት ይቻላል (ገፅ 177) ብለዋል፡፡ መቼም ሁለቱንም ፅሁፎች የሚያነብብ አንባቢ፣ አቶ ሚካኤል ምን እያሉ እንደሆነ ግራ ገብቶት ከመዋለል ውጪ ምንም የሚጨብጠው ነገር እንደማይኖረው ግልፅ ነው፡፡ ፀሐፊው ተቃራኒ የሆኑ ሃሳቦችን በተለያየ ቦታ ላይ ከመጠቀም ይልቅ ወገኛው መስፍን ሐብተማርያም እንደሞከሩት፤ የስብሀት ፅሁፎች የሚቀሉበትን እና የሚከብዱበትን ሁኔታና ምክንያት በአንድ ላይ አያይዘው ለማፍታታት ቢሞክሩ የተሻለ ነበር (ገፅ 226)፡፡ ይህንን ባለማድረጋቸው በሀሽሽና ባረቄ በነፈዘ አእምሮ የተፃፉ እያሉ እርሳቸው የተሳለቁበትን ዘይቤ፣ የዘርፉ ምሁራን ሱሪያሊዝም እና ፋንታሲ በሚባለው ዘይቤ ውስጥ መድበው ሲተነትኑት የሚያይ አንባቢ፣ አቶ ሚካኤልን ከመታዘብ ውጪ ምን ምርጫ ይኖረዋል?
አቶ ሚካኤል ሌላም የማይባል ነገር ይላሉ። ስብሐት ክርስቲያን ካልሆነ ኢየሱስን ለምን ያደንቃል? የቡድሀን ቃል ካላከበረ ለምን ስሙን ይጠራዋል? እያሉ ሲከሱት ጋንዲ እና ማርክስ እንኳን አይተርፋቸውም፡፡ ይህንን ሲሉ ግን “ፍልስፍና (2)” መፅሐፍ ላይ እሳቸው ከክርስትና ይልቅ ለቡዲዝም እምነት በእጅጉ የሚያደሉ ሰው ሆነው ሳለ፣ ክርስቲያናዊ ሀሳቦችን በፍቅር በተደጋጋሚ እንደተጠቀሙ ዘንግተውት ነው፡፡ እርሳቸው ለምን በስብሐት አፍ ተጠራ ሲሉ የተቆረቆሩለት ጋንዲ ራሱ፣ የሰላማዊ ትግል ዘዴውን የወሰደው እጅግ ይወደውና ያደንቀው ከነበረው ከኢየሱስ የተራራው ስብከት ነበር፡፡ ጋንዲ እራሱ ግን ክርስቲያን አልነበረም፡፡ ታዲያ ይህን እና ሌላም የሚያውቅ አንባቢ፣ ስብሐት ከጋንዲም ሆነ ከቡድሐ፣ ከማርክስም ሆነ ከኢየሱስ የተመቸውን ወስዶ ቢጠቀም ብርቅ ነው እንዴ? ብሎ ቢጠይቅ የሚገርም አይሆንም፡፡
ስለ ንባብ ህይወቱ
ፀሐፊው ባንድ ወገን በሰፊው የሚታወቀውን እና ብዙዎች የመሰከሩለትን የስብሐትን ከባድ አንባቢነት እንደሚቀበሉ እየገለፁ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በረቀቀ መንገድ (Subtly) ስብሐት የሚባልለትን ያህል ጥልቅ እና ሰፊ አንባቢ ሳይሆን ጥራዝ ነጠቅ እንደነበር እንዲሰማን የሚያደርገንን ነገር ይነግሩናል፡፡ ስብሐት የታወቁ ፈላስፋዎችን እና ደራሲዎችን አንዳንድ አባባሎች እንደ በቀቀን ሺህ ጊዜ ለደቀመዛሙርቱ በመደጋገም ያሰለቻቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ዋንኛ ማስረጃ የሚጠሩትም ስለፍፎይድ ቲዎሪ አስተምረን ብንለው፣ ሁሌ የሚግረን “የኦዲፐስ ኮምፕሌክስን ፅንሰ ሃሳብ ብቻ” ይላሉ፡፡ ራሱን ፈፅሞ እንደ ፕሮፌሰር ማየት ከማይፈልገው እና የአስተማሪነቱን ሞያ ከተወ ዘመን ካስቆጠረው ስብሐት ታዲያ የፍሮይድን እና የኒቼን ፍልስፍናዎች ትንተና የመጠበቁ ተገቢነት ቢያጠያይቅም፤ ያነበበውን ሁሉ ከአፉ ሊያስተፉት እየወተወቱ ሰላም ይነሱት የነበሩትን አፍላ ወጣቶች፣ ባንዲት አባባል ቢገላግላቸው ጥራዝ ነጠቅነቱ የቱ ጋ እንደሆነ ማየት ያስቸግራል፡፡ የስብሀት ልዩ ክህሎት (Genius) ያለው ያነበበውን ጥልቅ ፍልስፍና አካዳሚያዊ በሆነ መንገድ በመተንተን ሳይሆን በወግ መልክ እያዋዛ እና እያለዘበ በማቅረብ ነበር፡፡ አቶ ሚካኤል አንካሳ በሆነ ማስረጃ የንባቡን ጥልቀት እና ስፋት የሚመሰክሩ በየመፅሄቱና በየጋዜጣው ላይ ያሉ በርካታ ማስረጃዎችን ትተው፣ የስብሐትን ብርቱ አንባቢነት ጥያቄ ውስጥ ለመክተት መነሳታቸው ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል፡፡
መደምደሚያ
አቶ ሚካኤል መጣጥፋቸው መጀመሪያ አካባቢ ስለ ሲኒሲዝም (የውሻ ፍልስፍና) አውርተውልን ነበር፡፡ ፀሐፊው እዚያ ላይ አንድ ቁም ነገር የዘነጉ መስሎኛል፡፡ ውሻን ውሻ የሚያደርገው ከሰው እጅ የሚበላው ፍርፋሪ ብቻ እንደሆነ አስበዋል፡፡ እንደ እኔ እምነት ይህ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ስብሐት ራሱ ባንድ ወቅት እንደተናገረው እና ቅዱሳት መፅሐፍት እንደሚሉት፤ ሰው ሆኖ ተቀባይ ያልሆነ ማንም የለም፡፡ ሁላችንም የምንሰጠው የተቀበልነውን ብቻ ነው፡፡ ተቀባዮች መሆን ውሾች አያደርገንም፡፡ ባይሆን ገደብ ያለን ፍጡሮች መሆናችንን ያመለክት እንደሆን እንጂ፡፡ ውሻን ውሻ ያደረገው ከሰው እጅ መቀበሉ ሳይሆን ከሰው እግር ስር ማደሩ ነው፡፡ ስብሐት ደግሞ በዚህ አይታማም፣ ቢታማም እንኳ ልቅ በሆነው ነፃነቱ እና ሽፍታነቱ እንጂ በሎሌነቱ አይደለም፡፡ እርሳቸው ግን በዚህኛውም መፅሐፍ ሆነ በ “ፍልስምና 2” ላይ እንዳየናቸው፤ ከስብሐት እግር ስር ቢያመልጡም በሌላ ሰው እግር ስር ከማደር ግን ዛሬም አላመለጡም፡፡ በቡድሃ ማለቴ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ የበለጠ ሲኒሲዝም ከየት ይመጣል? ዛሬም ከሰው ጉያ ሳይወጡ የስብሐትን ነፃነት እና ሽፍታነት ለመደምሰስ ምን አይነት አስተማማኝ መሰረት ይኖርዎታል?

Read 4776 times