Saturday, 03 August 2013 10:58

ጥልቅና አንኳር አስተያየት በ”የተረሳ ወራሽ” ላይ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)
(ይህን አስተያየት ለጋዜጣ በሚያመች መልኩ ለመቃኘት ሞክሬያለሁ)

ባለፈው እትም እንዳስቀመጥኩት “የተረሳ ወራሽ” የተባለው መጽሐፍ መጠንጠኛ ፍለጋ ነው፡፡ ትውልድን ፍለጋና ትምህርትን ፍለጋ መሪ መሽከርክሪት ናቸው፡፡ መለወጥ፣ መፀፀትና ይቅርታ መጠየቅ፣ መራራትና ይቅርታ ማድረግ መፍትሔ ጭብጦች ናቸው (Resolution themes)። ይኸውም ትውልዶችን ማቀራረብ፣ ስህተትን የማረምና መጪውን ትውልድ የማነጽ ዓላማ ያለው አድርጌ እንዳየው አድርጐኛል፡፡ 

ምዕራፎቹን ስንመረምራቸው፤ ደራሲዋ የኤች አይ ቪን አደጋና ከቫይረሱ ጋር የመኖር ጥንካሬን እንደማጓጓዣ (leverage) በመጠቀም፤ (እንደጠቋሚ - ታሪክ (prologue) ከምናየው የመጀመርያ ምዕራፍ ውስጥ) ከዋናዋ ገፀ ባህሪ ጋር ታስተዋውቀናለች። በኋላ ላይ በዝርዝር የህይወት ውጣ ውረዷን የምናያት ወ/ሮ ትዝታን፤ ታገናኘናለች (“ትዝታ” የሚል ስም የሰዋዊ አገላለጽ ወይም ተምሳሌታዊ ስም መሆኑን በውል አናውቅም፡፡) ከእሷ ጋር የምናገኘው ሐኪሙዋ ዶክተር ግርማ፤ ትውልድ ያወደመው፣ ሥርዓት የጐዳው ባለሙያ ሲሆን “የሥራ ተነሳሽነቱ በኑሮ ጫና እየተጨፈለቀና ርህራሄው ከሰብአዊነቱ ውስጥ እየተሸረሸረ ሲወጣ ይሰማው ነበር፡፡ ዶ/ር ግርማ ውጪ በመሄድና የግል ሥራ በመሥራት መሃል የባከነ ህይወትን የሚወክል ገፀ - ባህሪ ሲሆን ያም ሆኖ እንደ ትዝታ ጠንካራ የዘመን - ሰለባዎችን የሚታደግ፣ ተስፋ የሚሰጥ ሰው ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ ሰው አንዱ የዘመን ጠባሳ ነው፡፡
ኢያሱ መምህር ነው፡፡ እንደ ትዝታ ዋና ገፀ - ባህሪ ነው፡፡ እንደ ዶክተር ግርማ እሱንም ህይወት አጐሳቁሎታል፡፡ ታስሯል፡፡ መካን እስኪሆን ድረስ ተገርፏል፡፡ ተፈቷል፡፡ ኑሮ አበሳጭቶታል። የባለታሪኳ የትዝታ አሳዳጊ ነው፡፡ ከህፃንነት ለአካለ - መጠን እስክትደርስ አሳድጓታል፡፡ በኋላ ግን በድሏታል፡፡ በሁለቱ መካከል የሚፈጠረው ግጭት የታሪኩ መላ - ሰውነት ነው፡፡ በኋላ የመጽሐፉ ቁልፍ ቁልፍ ገፀ - ባህሪያት እነ አብሮ - አደጉ አወቀ፣ ዲያስፖራው የለህወሰን፣ ጓደኛው ኤፍሬም በወጉ ተሰናስለው የምናገኛቸው እያሱ በሚያደርገው የትዝታን ፍለጋ ሂደት ውስጥ ነው። ይህን መሠረታዊ ግጭት ደራሲዋ ያቀረበችው እንዲህ ነው:-
ገፅ 24 ላይ እንዲህ ታሳየናለች
የትዝታ ሃሳብ
“ትዝታ በህይወት ጥሪ በተሞላ ዕድሜዋ ላይ ስለነበረች ወደ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ አባቷን ከብቸኝነት ጋር አጋፍጣው መሄድ ስላልፈለገች ትዳር እንዲመሠርት የምታደርግበትን መንገድ ታሰላስላለች”
የእያሱ ሃሳብ
“…ጊዜው ያመጣውን ችግር አንድ እርምጃ ቀድሞ ግብግብ ሊገጥመው በማሰብ፣ ዕውነታው የተጋረደበትን መጋረጃ ቀድዶ ከታሪኳ ጋር ሊያላትማት ወስኗል፡፡ ውሳኔውንም በተግባር አረጋገጠው፡፡ ሀቁን ከፊት ለፊት አስቀምጦ የአንቺነትሽን እውነታ እነሆ ተቀበይ አላት፡፡ “እኔኮ አባትሽ አይደለሁም፡፡
የዚህ ግጭት ውጤትም የእሱ የፍቅር/የወሲብ/ ፍላጐትና እርካታ ሆነ!! ደራሲዋ ቀጥላ እንደምትነግረንም፤
“ለዓመታት የኖሩት አባትና ልጅ በአንድ አፍታ በተከሰተ ሰይጣናዊ ድርጊት ወደተለያየና ጭራሽ ወደማይቀራረብ ተቃራኒ አለም ተሰማሩ፣ ሁለቱም በየፊናቸው ነጐዱ፡፡
የትዝታ ውሳኔ
ቀስ በቀስም ህሊናዋ መካሪ ዘካሪ፣ ቀጪና ተቆጪ ሆኖ ተጋፈጣት፤ ከዚያም እራስሺን ፈልጊ ብሎ አዘመታት (ገጽ 29) ይሄ ማንነትን ፍለጋ ነው የመጽሐፉ መሽከንተሪያ!!
ደራሲዋ፤ ዶክተር ግርማ ለትዝታ በሚመክራት ምክር በኩል የምታስተላልፍልን መልዕክት ጠንካራ የህይወት ፍልስፍና ሲሆን ትዝታ ወደፊት እምትከተለውን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ - “…ሁኔታዎች የፈጠሩትን ችግር መጋፈጥ እንጂ መሸሽ አይጠቅምም፡፡ ሽሽት የፍርሃት ውጤት ነው፡፡ አንዴ ሽሽት ከጀመርሽ ደግሞ ሁሉም ነገር አሳዳጅሽ ይሆናል፡፡ ማብቂያ ማቆሚያ የሌለው ሽሽት፣ መጨረሺያውም ሽንፈትና ውድቀት ነው፡፡ መቼም ውድቀት አማራጭሽ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡”
እያሱ ትዝታን የበደለበት ሁኔታ ሰብዓዊ ድክመት (Human folly የሚሉት ዓይነት) የፈጠረው፣ እሱ አፍቅሬያታለሁ የሚልበት፣ ከፍቅር ይልቅ የወሲብ ስሜት ክጃሎት (Sexual lust or desire) የሚንርበት ሁኔታ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ድርጊቱ ተዓማኒና ጥንካሬ እንዲኖረው አመክንዮው/ያነሳሳው ሁኔታ፤ ብርቱ ትንታኔ ቢሰጥበት መልካም ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ያደገ ስሜት መሆኑን የሚያጠይቅ (justification የሚሰጥ) ማሠሪያ አንቀጽ ቢኖረው የገፀ - ባህሪውን ድርጊት እንድንዘጋጅበት ያደርገን ነበር፡፡ በተለይም በሁለኛው ምዕራፍ በወጉ የምናገኛት ዋናዋ ገፀ ባህሪ ትዝታ ግን ከእያሱ መለያ ሰበቧ ተዓማኒ ነው፡፡ ወደፊት የሚጠብቃትን ህይወት ለመጋፈጥ ቆርጣ ስትወጣ የምናይባት ወኔም ገፀ - ባህሪዋን በቅጡ የሚሸከም ነው፡፡ ለመማር ያላት ፍላጐት፣ ወላጅ አልባነትን መቋቋም፣ የማንነት ፍለጋን መጋተር፣ ማህበራዊ ኑሮን ማሸነፍ፣ ሥራ ፍለጋ፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ ልጆች ማሳደግና ማስተማር…ከሁሉም በላይ ፍላጐቷን የማይረዳላት ማህበረሰብ ውስጥ መኖር (misunderstood እንዲሉ)፤ ለገፀ - ባህሪዋ በጠንካራ ድርና ማግ መሠራት ምስክር ነው፡፡
ሌሎች ገፀ ባህሪያት
ኤፍሬም የእያሱ ጓደኛ በዘመን - የታሰረ (ወይም ባሁኑ ዘመን አነጋገር “የተቸከለ” stuck in time) ገፀ ባህሪ ነው፡፡ ሚናው እየጐላ የሚሄደው ወደኋላ ላይ በመሆኑ ገፀ - ባህሪውን ገና ስናውቀው ፋይዳው ግራ ያጋባል፡፡ ዋለልኝ ከውጪ የመጣና የሸሸውን ማህበረሰብ ሊክስ የመጣ ዳያስፖሬ ነው፡፡
የእያሱ ሠራተኛ ብርቄ በቅጡ የተሳለች የቤት ሠራተኛ ባህሪ ናት፡፡ ሆኖም የወሰደችው ቦታ የበዛ ይመስለኛል፡፡ አጠር አድርጐ ፋይዳዋን ማሳየት ይቻል ነበር፡፡
አንድ እጅግ የማረከኝ ሃሳብ፤ እያሱ ወደ ወላጆቹ ቤት ጂጂጋ ሄዶ ከታሰሩት ጓዶቹ እነማ እንደሞቱና እነማን እንደተረፉ ለመመዝገብ መነሳቱ ነው፡፡ ታሪክን ለመፃፍ ትውልድን ለማስታወስ፣ደራሲዋ ያላትን ፍላጐት ለማርካት የጣረችበት ዘዴ ወይም መላ - ይመስለኛል፡፡ ደስ ብሎኛል፡፡
መጽሐፉ በእናትና ልጅ የተሞላ ነው፡፡ ልዩም፣ ማህበረሰብ -ተኮርም፤ የሚያደርገው ያ ነው፡፡ በማንኛውም ህብረተሰብ የችግር ገፈት ቀማሾች እናትና ልጅ ናቸው እንደማለት ነው መጽሐፉ ያሰመረባቸው! ባለታሪኳ ትዝታ የሁለት ልጆች እናት ናት፡፡ የቤት ሠራተኛዋ ብርቄ ባለልጅ ናት፡፡ የትዝታ እናት አራሷን ትዝታን ይዛ የመጣች ናት፡፡ ትዝታ ደሴ የኖረችባት እናት ልጆች አሏት፡፡ የዐወቀ ሚስት ባለልጅ ናት፡፡
የሺመቤት፣ ትልቁ ልጇ የተገደለና ከትንሽ ልጇ ጋር የምትኖር ነበረች…እናትና ልጅ!
እንግዲህ መጽሐፉን በውርድ ስናየው፡፡ የአንዲት ወላጅ አልባ ሴት ህይወት፣ በኤችአይቪ መያዝና በወጉ ከቫይረሱ ጋር ለመኖር መቻል፣ እያሱ የተባለው መምህር ዋናዋን ባለታሪክ ትዝታን በአደራ ማሳደግ (እናት ወ/ሮ መውደድ ቤቱ ድረስ መጥታ ያስረከበችው መሆኑ፤) አደራውን ለማሳካት ለወላጆቹ መስጠቱ፣ ባለታሪኳ አድጋ ወደሱ መምጣቷ፤ ለአካለ መጠን ስትደርስ ስለተኛትና ስለደፈራት ቤቱን ጥላ መጥፋቷ፣ የአሳዳጊዋ እያሱ መታሰር፣ የወጣቶች እጅ መስጠት፣ የእያሱ ከእስርና ከሞት የተረፉ ወጣቶችን መመዝገብ፣ በፋሲካ ዋዜማ የብዙ ወጣቶች መረሸን፣ ሰፊ መቼት ፈጥረው፤ እያሱና አዲሱ ትዳሩ፣ የእያሱ አወቀን ከልጁ ማገናኘት ድረስ ተጉዞ፣ የማራዘሚያ መድሃኒት መውሰድ የጀመረችውንና የኤች አይ ቪ ጉዳይ አስተማሪ የሆነችውን ትዝታን እስክናገኝ የሚዘልቀውንና የዳያስፖሬው የዋለልኝ የሞቱ ባለታሪኮችን ፍለጋ መምጣት፣ የእያሱ፣ የኤፍሬምና የየለህወሰን የተወሳሰበ ግንኙነት ተንተርሶ የየለህወሰን ማንነት መገለጥ፣ የትዝታ ወንድም ልጅ መገኘት፡፡ የታሪክ ፍሰቱን እንዲፈታተነን በሚሞክር መንገድ የሚወርድ ነው የትዝታ የነኤፍሬምና የአክስቶቿ ግንኙነትና የቤተሰብ ድርጅት በ3ኛው ሚሌኒየም ማቋቋም፤ ማክተሚያው ነው፡፡
ካለፈው የሥርዓት አውዳሚ እርምጃ በኋላ በተፈጠረው ሁኔታ ላይ የተመሰረተው የመጽሐፉ የግራና ቀኝ የፍትጊያ አቅጣጫዎች (war zones):- ወገን አልባነት፣ የማንነት እጦት፣ ሥር - አልባ መሆን፣ መገለል፣ መገፋት፣ መቀጨት፣ ሥራ - አጥነት፣ የትምህርት እጦት፣ የኢኮኖሚ ችግር ባንድ ወገን፡፡
በሌላ ወገን መለወጥ፣ ቁርጠኝነት፣ በራስ መቋቋም፣ ራስን - መቻል፣ ፀፀትንና መከፋትን መጽሐፍ በመፃፍ መወጣት፣ ጽንዓትና ትዕግስትን የያዘ ነው፡፡ እንደዋና የመጽሐፉ ውጤት ልናገኘው የምንችለው ቁም ነገር:- ስህተትን ተረድቶ ይቅርታ መጠየቅ፣ ይቅርታ ማድረግና ለቀጣይ ህይወት ተዘጋጅቶ መንገድ መቀየስ ነው፡፡
በመጽሐፉ መሀል መሀል የምናገኛቸውን ቁምነገሮች በንዑስ ርዕሶች አንዳንዶቹን ልነቁጥ :-
በወቅቱ ት/ቤት - የተማሪና መምህራን ግንኙነት
“ተማሪዎቹና መምህራኑ የመሰረቱት የጠበቀ ግንኙነት ወደኋላ በአገሪቱ ውስጥ ለተስተጋባው የትግል ጥሪ የጋራ ምላሽ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል…ህይወት በራሱ ስጋት ሆነ - ከተሞች የሰላም መንፈስ ራቃቸው፡፡ በከተማው የተከሰተው ሁኔታም የእያሱንና የሌሎች መምህራንን የትግል ተሳትፎ በእጥፍ አጐለበተው፡፡ የትግል ሥልታቸውንም ለወጠው፡፡ በየዕለቱ የሚጐርፉትን ወጣት ተሰዳጆች በማስጠለልና ከአደጋ ጠብቆ በማቆየት ተግባር ተጠመዱ፡፡ አስተማማኝ መሸሸጊያ ወደሆነው የገበሬ መንደር ወጣቶችን ማሸጋገር የመምህራኑ የዘወትር ሥራ ሆነ፡፡” የእያሱ ገፀ - ባህሪ የተሳለው በዚህ ሚሥጥራዊ ክንዋኔ ውስጥ ነው እንግዲህ፡፡
የትውልዱ የጋራ ስሜት በሚከተሉት መስመሮች ይታያል
እያሱ ቤት፤ በእንግድነት የመጣችውን መውደድን ስለታቀፈችው ልጅ የሚጠይቅበት ሁኔታ፡-
“ልጅሽ ወንድ ነው ወይስ ሴት?”
“ሴት ናት” ህፃኗን በስስት ጐንበስ ብላ እያየች መለሰችለት፡፡
“የማናት? ማለቴ አባቷ ማን ነው?”
“የሁላችንም ናት፡፡ የእኔ፤ የአንተ፣ የትግሉ የዘመኑ ልጅ ናት” አለችው ፍርጥም ብላ፡፡
የትውልዱን የጋርዮሽ ስሜት ብቻ ሳይሆን መጽሐፉ የልጅቷን ማንነት ሚሥጥራዊ በማድረግ ቀጣይነቱን ያረጋግጥልናል፡፡ ፍለጋ እንድንቀጥልም ይገፋፋናል፡፡
ትዝታን የአባቷ መክዳት ጐድቷታል
ትዝታ እያለቀሰችና ውስጧ በቁጭት እየተቃጠለ፣ለትዳሯና ለልጆቿ ስትል የከፈለችውን መስዋዕትነት፣በባሏና በዘመድ አዝማዶቹ የደረሰባትን ግፍ በዝርዝር አስረዳችው (ገጽ 472)
ከመጽሐፉ ያገኘሁት ትምህርት
የእያሱ መረጃ የማሰባሰብ ሙከራ ለእኛ ትውልድ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው ብዬ ገምቼዋለሁ፡፡ ትውልዳችን የት ደረሰ፣ ምን ደረሰበት? ምን ተማርንበት? ለማለት ያለና የሞተውን፣ የጠፋውንና የተሰደደውን፤ መመዝገብ ለብዙ ታሪካዊ እሴት አስተዋጽኦ ያደርግ ይመስለኛል፡፡
ዘናና ላላ የሚያደርጉ ትዕይንቶች አለመኖር
ጽሑፉ ባለፈው እንዳልኩት የምሬትና የሐዘን ምርቅ የበዛበት በመሆኑ ዘናና ላላ የሚያደርጉ ትዕይንቶች (relief scenes) ያስፈልጉታል፡፡ የዚህ ዓይነት ትዕይንት አንድ ቦታ ብቻ ነው ያየሁት - ገጽ 459 ላይ የምናገኘው፡፡
እንደዋዛ ማዳበሪያ ሆኖ የገባው ዝናቡ ጭሮ ወይም ዝናቡ በርጮሌ ነው፡፡ ለአብነት እንየው:-
“ታዲያ ወደፊት እንዴት ላገኝህ እችላለሁ?” አለው የለህወሰን ከቦርሳው አውጥቶ አስር ብር እየሰጠው፡፡
“ግዴለህም አታጣኝም፤ ዝናቡ ጭሮ ወይም ዝናቡ በርጮሌ ብለህ ብትጠይቅ ማንም ያሳይሃል፤ ገንዘብ እንጂ ሰውና ችግር ፈልገው አጥተውኝ አያውቁም… ይልቅ መኪናው ላይ ላሳፍርህ” አለው፤ 10 ብሩን ግንባሩን አስነክቶ ወደ ደረት ኪሱ እያስገባ፡፡ የለህወሰን በልጁ አነጋገር አዝኖ ሌላ 10 ብር ጨመረለት፡፡ ልጁ በደስታ ዘለለ! አቀፈው፤ ሳመው፡፡ ካሣፈረው በኋላ የለህወሰን የሰው ብዛት ሲያንስበት ተበሳጨ፡፡ ዝናቡ ግን “አንተ ማሰብ ያለብህ ስለሰዓቱ ነው…አምስት ሰዓት እየሆነ አይደል…በዚህ ሰዓት የማይሆን ነገር የለም፡፡ ሾፌሩ ከነሸጠው ያላችሁትን ተሳፋሪዎች እንደ አምሳ ሰው በመቁጠር ተነስቶ እብስ ለማለት ይችላል” ይለዋል፡፡
መምህር አበጀ እና ትዝታ
አበጀ የትዝታ ባለውለታ - ብቸኛ ሠናይ ባህሪ ነው፡፡ ደሴ ወስዶ ት/ቤት ያስገባት እሱ ነው፡፡
እሱም ግን እንደ ዶ/ር ግርማና እንደ እያሱ በሚሰራው ሥራ ደስተኛ አልነበረም፡፡ (የሰራተኛው የሥራ ተነሳሽነት ማጣት አንዱ አንኳር ጉዳይ መሆኑን እዚህም እናያለን) ውጪ ድርጅት ሲቀጠር ቤተሰቡን ይዞ ወደ ወሎ ሄደ፡፡ ትዝታን ወደ ደሴ ይዟት የሄደው ለዚህ ነው፡፡ ይህም ነው የትዝታን ደብዛ ከእነ እያሱ የጠፋባቸው፡፡
የሀገራችን ማስታወቂያዎች
ደራሲዋ፤ ስለሀገራችን ማስታወቂያ ባህል እግረ መንገዷን ልታሳየን ሞክራለች፡፡ በገጽ 450 እንዲህ ትላለች - በየለህወሰን አስተሳሰብ ውስጥ ሆና “በቲቪ ማስታወቂያ ሁሉም ከማሳየት ይልቅ በመናገር ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ሁለት መነሻዎችን አሰበ
1) ምናልባት ምንጫቸው የቴአትር ጥበብ መሆኑና በወጣትነታቸው
በድራማ የኖሩ መሆናቸው
2) በልምድም በትምህርትም ከትያትር ጥበብ ጋራ ራሳቸውን ያጣበቁ ግለሰቦች ከድራማ ውጪ መልዕክት ማስተላለፊያ የሌለ ስለሚመስላቸው
(3ኛው)ና ዋንኛው፤ የህብረተሰቡ አንድ መልዕክት ከማየት ከሁለት ሦስት ሰው ለመስማት የመምረጡ ባህል ነው!
መጽሐፉ እንደመጀመርያ መጽሐፍ፣ እንደማሟሻ፣ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡
እንደምክር
የገጽ ብዛት ለሚያስደነግጠው የዛሬ አንባቢ፣ ከዋናው ጉዳይ የራቁ በጣም የተዘረዘሩና የተደጋገሙ አንቀፆችን በማውጣት ብንተባበረው ደግ ነው፡፡ ማቀላጠፍ ማለት ነው፡፡
የገፀ - ባህርያት መብዛት የመጽሐፉን ሰንሰለት እንደሚያስረዝመው፣ አልፎ አልፎም ሊያደናግረው እንደሚችል ማስተዋል፡፡

Read 1801 times