Print this page
Saturday, 03 August 2013 10:44

የአክሱማዊያን ገንዘብና የጣሊያኖቹ “ጠረጴዛ”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

“የኢትዮጵያ ታሪክ ቀደምትነት ከብዙ አገሮች በፊት የታወቀና ከፍ ያለ ቢሆንም ዕውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፊያ በየዘርፉ የተዘጋጁ መፃሕፍት አለመኖሩን ማስተዋሌ ገንዘብና ባንክ፤ አገልግሎትና ጥቅሙ” በሚል ርዕስ ያሳተምኩትን መጽሐፍ እንዳዘጋጅ አነሳስቶኛል ይላሉ - ያሉት ደራሲ በላይ ግደይ በመፅሃፋቸው መግቢያ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ40ኛው ዘመነ መንግሥት (በ1963 ዓ.ም መሆኑ ነው) የታተመው የበላይ ግደይ መጽሐፍ፤ በገንዘብና ባንክ ዙሪያ በርካታ መጃዎችን አስፍሯል፡፡
መጽሐፉ ከታተመ 38 ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን ሊያነጋግሩ የሚችሉና ለጥናትና ምርምር የሚጋብዙ ሐሳቦችንም መያዙ እኔንም ለዳሰሳ እንድመርጠው አነሳስቶኛል። አገራችን ኢትዮጵያ ገንዘብን የሚያስተድድር ባንክ ቤት በማቋቋም ከዓለም የመጀመርያዋ አገር ስለመሆኗ የሚያረጋግጡ መረጃዎች አሉ የሚል መጽሐፍ ትኩረት መሳቡ አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው የመጽሐፉ ሐሳብ ዛሬም ቢሆን ለምርምርና ጥናት ያነሳሳል ያልኩት፡፡ ደራሲ በላይ ግደይ “አክሱም በሥልጣኔ በጣም የተራመደች ስለነበረች ገንዘብ መሥራት ብቻ ሳይሆን ሰፊ ንግድና መገናኛ ስለነበራት የባንክም ድርጅት እንደነበራት መገመት ይቻላል” ቢሉም ስለ ባንክ አመሠራረት ታሪክ ማጣቀሻዎችን ያቀረቡት ግን ከአገር ውስጥ ሳይሆን ከውጭ ነው፡፡
የጣሊያኖቹ ጠረጴዛ
ባንክ የሚለው ቃል “ባንኮ” ከሚለው የጣሊያንኛ ቋንቋ ተወስዶ ነው፤ በብዙ የዓለም አገራት ገንዘብን ከመቆጣጠርና ማስተዳደር ጋር በተያያዘ አልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት መጠሪያ ሊሆን የቻለው፡፡ የበላይ ግደይ መጽሐፍ “ባንኮ” የሚለው የጣሊያንኛ ቃል ትርጉም ወደ አማርኛ ሲመለስ ጠረጴዛ ማለት ነው ይልና የጣሊያን ነጋዴዎች ገንዘባቸውን ጠረጴዛዎች ውስጥ ማስቀመጣቸው ለባንክ ቤት ስያሜ መነሻ መሆኑን ይገልፃል፡፡ እንግሊዞች ዕዳውን መክፈል ያልቻለን ነጋዴ “ባንክራፕት” ብለው የሚጠሩት ከጣሊያውያን ልማድ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን ሲያመለክትም “በዚያን ጊዜም ከነጋዴዎቹ መካከል አንዱ በስምምነቱ መሠረት ዕዳውን ለመክፈል ያልቻለ እንደሆነ ጠረጴዛው (ባንኮው) ይሰበርበትና እሱም እንደከሰረ ተቆጥሮ ከሥፍራው ይነሳ ነበር፡፡” ይላል፡፡
ለገንዘብ መፈጠር
ምክንያት የሆኑት ማዕድናት
በግብይት ታሪክ ውስጥ ዕቃን በዕቃ መለዋወጥ በሁሉም አገራት የታየ ክስተት ነበር የሚለው “ገንዘብና ባንክ አገልግሎትና ጥቅሙ” መጽሐፍ፤ ከብቶች በግሪክ፤ በጐች በጣሊያን፣ ሩዝ በጃፓን፣ ሻይ ቅጠል በቻይና፣ በኢትዮጵያና በጐረቤት አገራቷ ደግሞ አሞሌ ጨው፣ ቁርጥራጭ ጨርቆች፣ ልዩ ልዩ እህሎች…ለዕቃ በዕቃ መገበያያነት ማገልገላቸው ያመለክትና በዘርፉ ከነበሩት ችግሮች አንዱ ስንዴ ተሸክሞ የሄደ ገብስ ተሸክሞ መመለሱ የፈጠረው ድካም መፍትሔ እንዲዘየድለት መነሻ ሆኗል ይላል። ለዕቃ በዕቃ መገበያያነት መዳብ፣ ብረትና ወርቅ የመሳሰሉት ቁርጥራጭ ማዕድናትን መጠቀም መጀመሩ ለገንዘብ መፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህም ሸክምና ድካምን የሚያስቀር ነገር ተገኘ፡፡
የባንክ ኖት አፈጣጠር
መዳብ፣ ብርና ወርቅ የመሳሰሉት ማዕድናት ለመገበያያ ተመራጭ ከሆኑ በኋላ ልዩ ጥበቃና ክብር የሚሰጣቸው በዛ፡፡ በብርና ወርቅ የተለያዩ ጌጣጌጦችን በመስራት የሚታወቁ አንጥረኞች ሀብታቸውን የሚያስቀምጡበት ምቹ ስፍራ ስለነበራቸው ሌሎችም እየመጡ ብርና ወርቃቸውን በአደራ ማስቀመጥ ጀመሩ፡፡
ለተቀበሉት የአደራ ዕቃ የማረጋገጫ ሰነድ እየፈረሙ ይሰጡ ነበር፡፡ ለሚሰጡት አገልግሎት መጠነኛ ክፍያ መቀበል ጀመሩ፡፡ ወደ በኋላ ላስቀመጡበት ማስከፈሉን ትተው ተቀማጩን ሀብት ለሌሎች በማበደር ከሚገኘው ወለድ ለአስቀማጮችም ተጨማሪ ገንዘብ መስጠት ጀመሩ፡፡ በጣሊያኖቹ ጠረጴዛ የተጀመረው የባንክ አሰራር በዚህ መልኩ ወደ ባንክ ኖት አድጐ አሰራሩ ተመራጭና ተጠቃሚውም የበዛ ሆነ፡፡
የንስሐ አባቶችና ባንክ
በክርስትና ሃይማኖት ቀሳውስቱ ለምዕመኖቻቸው በቤተ ክርስቲያናት ከሚሰጡት አገልግሎት ውጭ በንስሐ አባትነት እየተመረጡ የብዙ ሰዎችን የግል ሚስጥርና ችግር ሰምተው ምክር ይሰጣሉ፡፡ ውድ ሊባሉ የሚችሉ ሃብትና ሰነዶችን በአደራ ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለሀብት ያፈራው ንብረት እነማን እንዴትና በምን መልኩ መውረስ እንዳለባቸው በሕይወት እያለ በኑዛዜ የሚያስቀምጠው ሰነድ በንስሐ አባት (በቄስ) ዘንድ የማኖር ልማድ ከጥንት እስከ አሁን ዘመን ሲሰራበት ይታያል፡፡ ባንክ ቤቶች በየአገሩ ተቋቁመው አዳዲስ አገልግሎች ሲፈጠሩ ከተገኙት ጥቅሞች አንዱ የግለሰቦችን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ውድ ጌጣጌጦች፣ ሰነዶችና ሚስጢራዊ ጉዳዮችን ማስቀመጫ ግለሰቡ እራሱ የሚከፍተውና የሚዘጋው ልዩ ሳጥን ማቅረባቸው ነው፡፡
ቼክን የተካው ካርድ
የባንክ ቤቶች መቋቋም በገንዘብ አገልግሎትና አጠቃቀም ላይ በርካታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉ በተለያዩ ማስረጃዎች ያስረዳው የበላይ ግደይ “ገንዘብና ባንክ” መጽሐፍ፤ “ቼክና ጥቅሙ” በሚለው ምዕራፍ “ቼክ እያደረ ገንዘብን ሳይወርሰው አይቀርም፡፡ አሁንም ዓለም ዋና የመገበያያ ዘዴ አድርጐ የያዘው ቼክን ነው” ይልና ቼክ በተለያዩ አገራት ሥራን እንዴት ባለ ሁኔታ እያቀላጠፈ እንደሆነ ሲያመለክትም “አንድ ሰው 750 ብር በኪሱ ተሸክሞ ሄዶ ቆጥሮ ከመስጠትና፤ የቼክ ወረቀት ይዞ ሄዶ ጽፎ ከመስጠት የትኛው ይቀለው ይመስላችኋል?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ደራሲ በላይ ግደይ መጽሐፋቸውን ባሳተሙበት ዘመን ላይ ሆነው ቼክ እያደር ገንዘብን ሳይተካው አይቀርም ብለው የነበረ ቢሆንም አሁን ገንዘብን እየተካ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው “ካርድ” የቼክ አሰራርን ኋላቀር እያደረገው ነው፡፡
አነጋጋሪው ርዕሰ ጉዳይ
ደራሲ በላይ ግደይ ገንዘብና ባንክን ርዕስ ያደረገ መጽሐፍ ሲያዘጋጁ፤ ስለ ባንክ አመሰራረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽፎ የሚገኘውን ታሪክ በማሳያነት ያቅርቡ እንጂ “ኢትዮጵያ በአክሱም ዘመነ መንግሥት የራሷን ገንዘብ ሠርታ ለአገልግሎት አውላ ከነበር ገንዘቧን የምታስተዳድርበት ባንክ ቤቶች እንደነበሯት መገመት ይቻላል” በሚል ያቀረቡት ሃሳብ እውነትነት እንዳለው አንዱ ማሳያ በመጽሐፉ የቀረበው የባንክ ስያሜና አመሠራረት ታሪክ ነው፡፡ የጣሊያኖቹ ጠረጴዛ (ባንኮ) ከገንዘብ ማስቀመጫነት ጋር በተያያዘ ለባንክ ቤቶች መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ለብዙ መቶ ዓመታት የተለያዩ ገንዘቦችን ሰርተው ለመገበያያነት አውለው የነበሩት አክሱማዊያን ገንዘባቸውን የሚያስተድድርላቸውና የሚያስቀምጡበትን ተቋም ምን ብለው ይጠሩት ነበር? የሚለው ጥያቄ አጓጊና አነጋጋሪ ነው፡፡
ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ.ም በታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ታሪካዊቷ የትግራይ ምድር” በሚል ርዕስ (ገ.ኃ) ባቀረቡት ጽሑፍ፤ በጥንቱ የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ግብፅ በኢትዮጵያዊያን ትተዳደር እንደነበር፤ ግብፃዊያን ያላቸው ድንቅ ሀብት ምንጭ ኢትዮጵያ፣ መሆኗን፤ ግብጽ ከኢትዮጵያዊያን ያገኘችውን ጥበብና ዕውቀት ለሮምና ለግሪክ አሳልፋ እንደሰጠች በመረጃ አስደግፈው አስነብበዋል፡፡ ይህንን መረጃ ደራሲ በላይ ግደይ በገንዘብና ባንክ መጽሐፋቸው ካነሱት መላ ምታዊ ጥያቄ ጋር አጣምረን ብንመለከተው ተጨማሪ ጥያቄዎች እንዲነሱ ይጋብዛል፡፡ ምላሹ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም የአክሱማዊያኑ ገንዘብ ከጣሊያኖቹ “ጠረጴዛ” ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንድነው? የሚለው ከሚነሱት ጥያቄዎች አንዱ ይሆናል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እንዳልተጫረ ክብሪት የታመቀ ኃይልና ብርሃን ያለው የሚመስለው የዚህች አገር ጥንታዊ ታሪክ መቼ ይሆን ግልጽ ሆኖ አገርና ሕዝቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትም ያሰኛል፡፡

Read 2122 times