Saturday, 03 August 2013 10:39

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ተናጋሪዋ ምድር

“ጋዜጠኝነት የተጀመረው አክሱም ውስጥ ነው”

የዛሬው ጉብኝታችን የሚጀምረው ከሳባ ቤተመንግሥት ነው። ከአክሱም ከተማ ምዕራባዊ አቅጣጫ፣ ትንሽ ወጣ ብሎ የሚገኘው የሳባ ቤተመንግሥት ልዩ ልዩ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ 42 ክፍሎች አሉት፤ ሌሎች አራት አብያተ መንግሥታትም አክሱም ውስጥ ተቀብረው እንደሚገኙ ተረድተናል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአገራችን ያን የመሰለ ህንጻ ይገነባ ነበር ብሎ ለማስረዳት ይከብዳል፤ ግን እውነት ነው፡፡ ራሱ ህንጻው ዛሬም በእማኝነት እንደቆመ ይገኛል - ቆሞ የሚገኘው ሙሉ ለሙሉ አለመሆኑን ግን አንዘንጋ፤ በቁፋሮ የተገኘ ነውና!
ከሳባ ቤተመንግሥት ፊት ለፊት የቆሙ፣ ያዘነበሉና የወደቁ በርካታ ሃውልቶች ይገኛሉ። ቦታውም የነጋዴዎችና የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች መቃብር የነበረ መሆኑን የዘላቁ ቱሪዝም ልማት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ አብርሃም አስረድተውናል።
በንግሥተ ሣባ ቤተመንግሥት ውበትና በሥራው ውስብስብነት እየተደነቅን ወደ አክሱም ሰሜናዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ተጓዝን፤ ትግራይ ውስጥ በጥንቃቄ መጓዝ ብቻ ያስፈልጋል፡፡ ጥንቃቄው ደግሞ ዕርባና የሌለው የሚመስል ድንጋይ፣ ውሃ፣ ወይም ጉብታ በአስደናቂ ታሪክ የተዋበ ሊሆን ስለሚችል ሳናየው እንዳያመልጠን ነው፡፡
አሁን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የተሠራውንና በሃገራችን የመጀመሪያ እንደሆነ የሚነገርለትን ማይሹምን እየጐበኘን ነው፤ “ማይሹም” ማለት “የሹም ውሃ” ማለት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ እንዲያውም “የአክሱም ሥያሜ የተገኘው ከዚሁ ነው” የሚሉም አሉ፤ ምክንያታቸው ደግሞ በአገውኛ ቋንቋ “አክ” ማለት “ውሃ” ማለት ሲሆን “ሱም” ደግሞ “ሹም ማለት ነው” የሚል ነው፡፡ “አክ” እና “ሱም” በአንድ ላይ “አክሱም” ይሆናል ማለት ነው፡፡
ለማንኛውም ግድቡ የንግሥቲቱ መዋኛ እንደነበር፣ አሁንም ለአካባቢው ነዋሪዎች ልዩ ልዩ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስጐብኚያችን ነግረውናል፡፡ ግድቦቹ ሁለት ናቸው፤ የህጻናትና የአዋቂዎች መዋኛ፡፡ ግድቡ የመጀመሪያ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚያስገርመው በርካታ አብያተ መንግሥትና አብያተ እምነት፣ እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችና መቃብር ቤቶች ተቀብረው ሲገኙ ግድቡ ግን ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ በደለል ሳይሞላ እስካሁን መገኘቱ ነው፡፡
ከግድቡ ከፍ ብሎ ውሃ ከቦረቦረው የመሬት አካል አንድ የህንጻ ግድግዳ ይታያል፤ “እናንተ ቆፍራችሁ ባታወጡኝም በወራጅ ውሃ አጋዥነት እኔው እወጣና ምን እንደ ነበርኩ ለትውልዱ እመሰራክለሁ” የሚል ይመስላል፡፡ ከእሱ ፊት ለፊት ከሚገኝ የእርሻ መሬት ጫፍ ወደተቀለሰች ዛኒጋባ አስጐብኝያችን ወሰዱንና ሌላ ተአምር አየን፡፡
ከዛኒጋባዋ መሃል አንድ በሶስት ማዕዘን የተጠረበ ድንጋይ በኩራትም በትዝብትም በሚመስል አኳኋን ቆሟል፡፡ ሃውልቱን ያቆመው ኢዛና መሆኑን ራሱ ሃውልቱ ይመሰክራል፤ እንዲያውም ከቦታው ያነቃነቀው ሰው ዘሩ ሁሉ የተረገመ እንዲሆን ተጽፎበታል፡፡ በሃውልቱ ሶስቱም ማዕዘናት፤ በግዕዝ፣ በሳባ እና በግሪክ ቋንቋዎች የተጻፈ ተመሳሳይ መልእክት አለ፡፡
የሃውልቱ አጠራረብም ሆነ የተጻፈበት ቁም ነገር ከድንጋይነት ይልቅ ብራና አስመስሎታል። የቆመውም ኢዛና ኑብይ ወርዶ የገደለውን፣ የማረከውንና በአጠቃላይም ያገኘውን ድል የሚያበስረውን የጦር ሜዳ ዘገባ ይዞ ነው፡፡ ይህንን ምሥጢር ሳይና ስሰማ ትዝ ያለኝ ስለጋዜጠኝነት አጀማመር ሲነገረን የኖረው ምን ያህል ከእውነቱ የራቀ መሆኑን ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ሲነገር የምንሰማው “የተማርነውም” ጋዜጠኝነት የተጀመረው አውሮፓ (ሮም) ውስጥ መሆኑን ነበር፤ ግን የእኛ አባቶች ገና ብራና እንኳ መፋቅ ሳይጀምሩ የጦርነት ዘገባዎችን ድንጋይ ላይ ያሰፍሩ ነበር፡፡ በመሆኑም የአገራችን የጋዜጠኝነት ምሁራን ርቃ ከምትገኘው ሮም ይልቅ ፊታቸውን ወደ አክሱም በማዞር ጥልቅ ጥናትና ምርምር ሊይደርጉ ይገባ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ ፈረንጅ ካልነገረን በቀር የራሳችን ሃቅ እውነት አይመስለንም፡፡ ይህ ክፉ ልክፍት ነው፡፡ እንዲያውም “ፊደል የመጣው ከሌላ አገር ነው” እያሉ የሚከራከሩ ሰዎችም አጋጥመውኛል፡፡ ግንኮ እኒያ ህያው ድንጋዮች የሚመሰክሩት እውነት ሌላ ነው፤ ተናጋሪዋ የትግራይ ምድር “ሹክ” የምትለን ምሥጢርም በእጅጉ የሚያኮራ ነው፡፡
ኢኖ ሊትማንን የመሰሉ አለም አቀፍ ምሁራን፤ የሃውልቶቹና ጥርብ ድንጋዮቹ ምሥጢር አማልሏቸው ወደ እኛ ይጐርፋሉ፤ በተቃራኒው እኛ ደግሞ ፈረንጅ እናመልካለን ወይም መመራመር ሳንከጅል የእነሱን መጻሕፍት ለመቃረም ወደ ፈረንጅ ሰፈር እንጋልባለን፡፡ በኔ እምነት ይህ ሐፍረት ነው፡፡ ፈረንጆች ግዕዙን ተምረው በሃውልቶቻችን እና በብራና መጻሕፍት ላይ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉትን ምሥጢራት ሃተታ ሰርተውባቸዋል፤ እየሠሩም ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ “ጊዘር” የተባለ ጀርመናዊ ምሑር፤ ከአራት ዓመት በፊት የአጼ ገብረ መስቀልን አጽም ማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡ እኛ ግን ዛሬም እጃችንን አጣጥፈን የፈረንጅ ማረጋገጫ እንሻለን፡፡
እርግጥ ነው የአፄ ካሌብና የአፄ ገብረ መስቀል መካነ መቃብር አካባቢ፣ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሥነ ስብእና የሥነ ምድር ምሑራን የምርምር ሙከራ እያደረጉ መሆኑን ተገንዝበናል፤ ይህ በእጅጉ ሊበረታታ የሚገባው ድንቅ ጅምር ነው፡፡
የአፄ ካሌብ መቃብር ወይም አፄ ካሌብ ለራሳቸው እንዳስገነቡት የሚነገርለትና በ6ኛው መቶ ክ.ዘመን ተሠራ የሚባለው መቃብር አሠራር ግሩም ነው፡፡ ጣራውም፣ ግድግዳውም ወለሉም ሆነ ሳጥኑ የተሠራው ከትላልቅ ጥርብ ድንጋዮች ነው፡፡ ይህን ስመለከት እኒያ ድንቅ ጥበበኛ እጆች፣ እኒያ እጅግ ጠንካራ ሰውነቶች የማውቃቸው ያህል በፊቴ ድቅን አሉና ቀናሁባቸው፤
መቃብሮቹ የተለያየ ቅርጽና መጠን አላቸው፤ አንዳንዶቹ በዋሻ አይነት ቅርጽ ተሠርተው ለቤተሰቡ ጭምር እንዲሆኑ የተገነቡ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ በመስቀል ቅርጽ ተሰርተው አራት ኪሶች አሏቸው፡፡ በአብዛኞቹ መቃብሮች ውስጥ የተገኙ ማስረጃዎች እንሚያስረዱት፤ የያኔዎቹ ወገኖቻችን ይቀበሩ የነበረው ድንጋዩን እንደ እንጨት እየጠረቡ በድንጋይ ሳጥን የመቃብር ፋካ መሥራት ነበር፡፡
የተጀመውም ያኔ ይመስለኛል፡፡
አንዱን የድንጋይ ሣጥን የጀርመን ተመራማሪዎች ለሁለት ቆርጠው ወደአገራቸው ሊወስዱት ሲሉ የአካባቢው ሕዝብ “ቅርሳችን ከቦታው ንቅንቅ አይልም” ብሎ አስቀርቶታል፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስሁት ምርምሩ በሀገራችን ምሑራን መካሄድ አለበት ያልሁትም ሊከሰት የሚችለውን የዚህ ዓይነቱን ዘረፋ ለማስቀረት ስለሚረዳና ታሪካችንን ገልብጠው ለባዕድ እንዳያወርሱብን በመስጋት ጭምር ነው፡፡
ፈረንጆች እኮ እንኳን ግኡዙን ታሪካችንን እንደፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ያሉ ምርጥ አዕምሮዎችን ሊዘርፉን በእጅጉ ሞክረዋል፡፡ እናም “ሐይ” ባይ ያስፈልጋል፡፡ ለነገሩ እንኳን ከምድር ውስጥ ያለው ቅርሳችን ሊጠናና ሊታወቅ ቀርቶ፣ አዕላፍ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ሕያው የሆነው ትውፊታችን ገና አልተመዘገበም፡፡ የአውሮፓ በተለይ የግሪክና የሮማ፣ እንዲሁም የአፍሪካ የዕምነት ትውፊቶች በአግባቡ ተጠንተዋል፤ ተመዝግበውም ለትውልድ እየተላለፉ ናቸው፡፡ እኛ ግን ዛሬም ፈረንጅ ካልጻፈልን ጉዳዩን ከቁብ አንቆጥረውም፡፡
ለምሳሌ ከአክሱም ከተማ ወደ ሰሜን በግምት አራት ወይም አምስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ አንድ ቀጥ ብሎ የቆመ ሹል ተራራ አለ፤ የቦታው ስም “ተመን ዘውገ (የዘንዶ ወገን)” ይባላል፡፡ አካባቢው ደግሞ “አድ ጸሐፊ (የጸሐፊ አገር)” በመባል ይታወቃል፡፡ ከዚያ ተራራ ጋር የተያያዘ አንድ ትውፊት ይነገራል፡፡
በጥንቱ ዘመን ዘንዶ ይመለክ ነበር አሉ፤ ዘንዶው በዚያ ተራራ ይኖር ነበር፤ ውሃ መጠጣት ሲያምረው ጅራቱን በተመን ዘውገ (ተራራ መሆኑን ልብ ይሏል) ያስርና ከመረብ ወንዝ ይጠጣ ነበር የሚል ትውፊት አሁንም ድረስ በሰፊው እንደሚነገር ከአካባቢው ነዋሪዎች ተረድተናል፡፡
ጉዳዩ “ራ” ከምትባለው የግብጽ የፀሐይ አምላክ ጋር፣ ወይም ከኬንያዎቹ የዝናብ አማልክት ጋር ይመሳሰላል፡፡ “ዘንዶ ወይም እባብ ዝናብንና ቀስተደመናን የመፍጠር ችሎታ ያለው ነው፤ ቆዳውን በየጊዜው በመቀያየር ስለሚኖርም ዘለዓለማዊ ነው” ተብሎ ይታመን እንደነበር “አፍሪካን ሚቲዮሎጂ” የተባለ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡
የእኛው የዘንዶና የዕምነት ትውፊት ግን ፕሮፌሰር ስርግው ሐብለሥላሴ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተባለ መጽሐፋቸው፡፡ በአጭሩ ከመነካካታቸውና አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ “ከጣኦት አምልኮ ወደ ክርስትና” በሚለው መጽሐፋቸው በአጭሩ ከመዳሰሳቸው በቀር ራሱን ችሎ አልተጠናም፡፡ ሕዝቡ ግን አሁንም ትውፊቱን እየተቀባበለ ለልጆቹም እየቀበለ ነው፤ ሳምንት እንገናኝ፡፡

Read 2486 times