Saturday, 03 August 2013 10:23

ህገወጥ ደላላ ልቡን የሚያሸፍተው ህዝብ እንዴት በዛ?

Written by  ሰለሞን ጓንጉል
Rate this item
(8 votes)

Progress in a country is measured not by industry or infrastructure or the wealth that its citizens possess, but by the quality of life they lead. Civilization on the other hand, is measured by the quality of character of the citizens. The strength of a society is its social capital.
የአንድ ሐገር እድገት የሚለካው ባሏት ኢንዱስትሪዎች እና በዘረጋቻቸው መሰረተ ልማቶች ወይም ዜጎቿ ባፈሩት ሃብት ሳይሆን በሚመሩት የተሻለ ሕይወት ነው፡፡ የስልጣኔም መለኪያው የዜጎች የምግባር ጥራት ነው፡፡ የአንድ ማሕበረሰብ ጥንካሬም በእጁ ያለው ሶሻል ካፒታል ወይም መልካም እሴት ነው፡፡
ከላይ የቀረበው የእንግሊዝኛ ሃሳብና ተቀራራቢ ትርጉሙ ታዋቂው ሕንዳዊ ጸሃፊ ሼቭ ኬራ፤ “ፍሪደም ኢዝ ኖት ፍሪ” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ያሰፈረው ነው፡፡ ይሄንን ሃሳብ እያሰላሰልኩ በእርግጥ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ያለን ትልቁ የጋራ እሴት ምንድን ነው? የሐገር ፍቅር፣ መረዳዳት፣ መከባበር ወይስ ምን? ስል ራሴን ጠየቅሁ፡፡ መልስ ብፈልግም ያላገኘሁለት ጥያቄ ሆነብኝ፡፡ የሀገር ፍቅር፣ መረዳዳት፣ መከባበር… የነበሩን ግን እያጣናቸው የመጡ እሴቶቻችን እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ ከእነዚህ ሃሳቦች በተቃራኒ ገንዘብ ከሁሉ በላይ ነግሶ የትኛውም መንገድ ገንዘብ ጋ እስካደረሰ ድረስ ብዙ ዜጎች በመንገዱ ለመጓዝ የሚደፍሩባት፤ እውነተኛ ስሜት የወለዳቸው መረዳዳትና መከባበር እየሸሿት ያለች እና “የሰረቀ የድርሻውን አነሳ” እየተባለ የሚሞገስባት ሃገርም ሆናብኛለች፡፡ የኋላ ታሪካችን እንዲህ ነበርን? ሳናውቀው በእጃችን ያለውን እሴትስ እያጣን አይደለምን?
ለዚህ ሁሉ መነሻዬ ሕገወጥ ስደትን በተመለከተ በቅርቡ ሲነሱ የነበሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሃሳቦቹ በመነሳታቸው ተቃውሞ የለኝም፡፡ የአንድም ሰው ሕይወት በሕገወጥ ስደት እንዳያልፍ ትልቁ ምኞቴ ነው፡፡ ምኞቴ ምኞት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር የሚያሰጋኝ ግን ለሕገወጥ ስደቱ ጆሯችን እስኪደነቁር ድረስ የምንሰማው፤ “ሕገ ወጥ ደላሎች ቀዳሚ ምክንያት ናቸው” የሚለው ግራ ቀኙን ያልተመለከተ የድፍረት አባባል ነው፡፡ ድፍረቱ የሚመነጨው ሕገ ወጥ ደላሎችን ምክንያት አድርጎ ከማቅረቡ አይደለም፡፡ በዘወርዋራው ሕገ ወጥ ደላሎች ላለፉት በርካታ አመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን አግዘው፣ በሺህ የሚቆጠሩትን ለሞት ሲያቀብሉ ዝም ብዬ ተመልክቻለሁ፤ በሃገር ውስጥ ያሉ ሕገወጥ ደላሎችን መቆጣጠር ተስኖኝ ነበር ብሎ በአደባባይ ከማወጁ ላይ ነው፡፡ ሕገ ወጥ ደላሎች ለስደቱ አስተዋጽኦ የላቸውም ብዬ አልደመደምኩም፡፡ በግሌ ያነጋገርኳቸው ብዙ ተጓዦች ለደረሰባቸው መከራ ሁሉ የደላሎቹ እጅ እንዳለበት ነግረውኛል፡፡

ሊዋጥልኝ ያልቻለው ግን የሚገባውን ያሕል መስራት ተስኖት ለአመታት በቸልታ ሲመለከት የነበረው መንግስት፤ ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ሕገ ወጥ ደላሎችን በዋነኛ ምክንያትነት ለማቅረብ ሲጣደፍ ማየቴ ነው፡፡ ከልብ አስቦ የችግሩን መንስኤ ካላወቁ ከመፍትሄው መድረስ አይቻልምና የተሰማኝን ልተንፍስ ብዬ ነው፡፡
ሕገወጥ ስደት፤ በሃገራችን በእጅጉ ተባብሶ የታየው በስልጣን ላይ ባለው የኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ የደረጃው ልኬት በሀገራችን ያለው “ሰላም” ነው፡፡ ሰላምን በትምእርተ ጥቅስ ውስጥ መክተቴ የሰላምን ትርጉም ጦርነት ካለመኖሩ ጋር አቻ ተደርጐ እንዳይተረጐም ነው (peace is not the absence of conflict) ጦርነት በሌለባት ሀገር፣ ድሕነት ሰላም የነሳው በርካታ ኢትዮጵያዊ ይኖራልና፡፡ ከሶስት አመት በፊት የወጣ የስደተኞች ሪፖርት፤ ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር፣ ከመንግስት አልባዋና በጦርነት ከምትታመሰው ሶማሊያ ከሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ልቆ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡

እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ ብሎ መጠየቅ ተገቢ የሚሆነው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ደርግ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን፣ በፖለቲካ የተቧደኑ እና እርሱን ለመቃወም የተነሱትን በማሳደድ በርካቶች የሱዳንን በርሃ አቋርጠው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ የእርስ በእርስ ግጭቱ ያሰደዳቸው ሰዎች ቁጥር ግን በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን ከተሰደዱና ከሚሰደዱ ሰዎች ጋር ፈጽሞ የሚነጻጸር አይደለም፡፡ ታዲያ ከሃያ አመታት በፊት በጦር መሳሪያ የታጀበ ግጭት ካሳደደው ኢትዮጵያዊ፣ በጦርነት አልባው በዚህ ጊዜ የተሰደደው ቁጥር እንዴት ሊበዛ ቻለ? ለመብዛቱስ ሕገ ወጥ ደላላ እንዴት ቀዳሚ ምክንያት ይሆናል? ይሁን ቢባል እንኳን ደላላ በቀላሉ ልቡን የሚያሸፍተው ሕዝብስ እንዴት እንዲህ ሊበዛ ቻለ? ከደላላው በላይ በራሱ ማወቅ የተሳነው፣ የሰማውን ብቻ የሚያምን ብዙ ሰው አለን ማለት ነውን? ህገወጥ ደላሎችን በዋና ምክንያትነት የሚያቀርቡ ወገኖች ሊመልሱልን የሚገባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ሶሻል ካፒታል እና ሕገወጥ ደላላ
በመግቢያዬ ያነሳሁት ሺቭ ኬራ፤ የአንድ ሃገር እድገት የሚለካው በዘረጋቻቸው መሰረተ ልማቶች ወይም በዜጐችዋ የሀብት መጠን ሳይሆን በእጅ ባለው፣ ዜጐችዋ በሚጋሩት መልካም እሴት ነው የሚለው አባባል ለአሁን አጀንዳዬ ትልቅ ሃሳብ ሆኖልኛል፡፡ ከጋራ እሴቶች አንዱ ደግሞ የሀገር ፍቅር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ ይሄ ሁሉ ስደተኛ ለማመን የሚከብድ አደጋ ከፊቱ እየጠበቀው በረሐ እና ባሕር የሚያቋርጠው፣ በሃገር ከመኖር ሞትን የሚመርጠው፣ ከየትኛውም ምክንያት በላይ በሕገወጥ ደላላ እየተታለለ ነው ብሎ መቀበል ይከብዳል፡፡ ለሀገሩ ያለው ፍቅር እና ተስፋ ተሟጥጦ እንዳልሆነ ማን ጠየቀው፡፡ በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምስራቅ ግንኙነት ላይ ጥናት የሚያደርጉት አደም ካሚል የተባሉ ተመራማሪ ለ “ሰንደቅ” ጋዜጣ መጋቢት 11 ቀን 2005 ዓ.ም እትም በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ በሕገ ወጥ መንገድ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን አይወዷትም ብለዋል፡፡ ፀሐፊው ሃሳባቸውን በማስረጃ ሲያረጋግጡ፤ በ2012 እ.ኤ.አ ብቻ 338‚000 ኢትዮጵያውያን በህገወጥ መንገድ ሳኡዲ ገብተዋል፡፡ ይህ ቁጥር የተያዙትን ብቻ የሚገልፅ ነው፡፡ የፀሃፊውን ሃሳብ ይበልጥ ያጠናከረው ባለፈው ዓመት በህጋዊ መንገድ ለሐጂና ኡምራ ሳኡዲ ገብተው ያልተመለሱት ሰዎች ቁጥር ነው፡፡ 36ሺ ተጉዘው የተመለሱት 9997 ብቻ ነበሩ፡፡ ታዲያ ይሄንን ቁጥር እያነበቡ ከሕገወጥ ደላላ ሌላ ያሉ ምክንያቶችን በደንብ መፈለግ አይገባምን?
አንገት የሚያስደፋው ይሕ ሕገ ወጥ ስደት ገደቡን ከሳተና በርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይወትና አካላቸውን ካጡ በኋላ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት የመገናኛ ብዙሐን የምንሰማውና የምናያቸው በጉዳዩ ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞች አስፈላጊ ቢሆኑም ከልብ የሆነ ጥረትን እና ሕገወጥ ስደትን ለማቆም ቁርጠኝነትን የሚያሳዩ፣ ከሚፈለገው ውጤትም የሚደርሱ አይመስሉኝም፡፡ ፖለቲካዊ ምክንያትና ተጠያቂነት ያለበት ትልቅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሃላፊነት የተሰጠው መ/ቤት እስከዛሬ የተጓዘበትን፣ በጉዞውም ለውጥ ከማምጣት ይልቅ የስደቱ መጠን እንዲጨምር የጨመረበትን ምክንያትና የአሰራር መንገዱን ጭምር መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ መስሪያ ቤቱን የሚመሩት ሰዎች አልቻሉምና የሚችል ሰው ሊፈለግ ይገባል፡፡ የመደመጥ አቅሙ ያላቸው ባለስልጣናትም የሃይማኖት አባቶች ጭምር ለቁጥር የሚያስደነግጥ የጅምላ ሞት ለሰማንባቸው “ሃገሬ እነዚህን ሁሉ ልጆችሽን በማጣትሽ አዝነናል” ሲሉ የሐዘን ቀን ሲያውጁ መስማትን እንፈልጋለን፡፡ ከልባቸው ለልባችን መቅረባቸውን የምናውቀው ያኔ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የፈረንጅ ሃገር ናፋቂ የሆንበትን፣ አማርኛ ቋንቋ መናገር በአንዳንድ ት/ቤቶች በአደባባይ ሲከለከል የሰማንበትንና የመንግስትን ዝምታ ያየንበትን ይሄንን ጊዜ ቆም ብሎ ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ አንዳንድ ባለስልጣኖቻችንና የከተማችን ሃብታሞች ነፍሰጡር የሆኑ ሚስቶቻቸውም፣ ልጆቻቸውም የአሜሪካና አውሮፓ ዜግነት አግኝተው እንዲወልዱ፣ ወደዚያው የመሰደዳቸውን ምክንያት እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት ገሸሽ የተደረገበትን እንቆቅልሽ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ የገዢው ፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ለስራ፣ ለትምሕርት እድል እና ለስልጣን (የሕዝብ አገልጋይነት) መስፈርት ሆኖባቸው ያኮረፉ ዜጎችንም ቁጥር እና ስሜት ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ሁሉ መደምደሚያው ጥያቄ ውስጥ የወደቀ የሚመስለውን የሃገር ፍቅር ስሜት መልሶ ለማግኘት ይጠቅማል፡፡ ያኔም ያዋረደንን የሕገወጥ ስደት ትክክለኛ ምክንያት መለየት እንችል ይሆናል፡፡ በቀናን!

Read 3707 times