Saturday, 03 August 2013 10:20

ዘወር ካለማለት ነገሩ ሰፋ ቶሎ ካለመሻገር ጐርፉ ሞላ (የትግሪኛ ተረት)

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ዘማሪ ወፍ በወጥመድ ተይዛ በቆንጆ ድምጽዋ ትዘምራለች፡፡ ድምፁዋ በጣም ከማማሩ የነሳ ሌሎች ወፎች ሁሉ ፀጥ ብለው ያዳምጡዋታል፡፡
“ስበር እውላለሁ፡፡
ስከንፍ አረፍዳለሁ፡፡
ማን ይየኝ ማን ይስማኝ
መች እጨነቃለሁ?
የምሮጥ ለራሴ፣
የመኖር ለራሴ፣
ይድከመኝ ይመመኝ፣
ራሴ ነኝ ዋሴ፡፡
ሰው ግን ይከፋዋል፣
ጥላዬ ሲያርፍበት
ላይከብደው ላይጐዳው፣
ድንገት ባለፈበት፡፡
ሊያጠምደኝ ይለፋል፤ ጉዳዩ አይገባኝም፡፡
ወፍ ይዞ በማሰር፣ ምን እንደሚጠቀም?
ሽቦ - ቤት ባልገባም፤ መዘመሬ አይቀርም…
ሽቦ ቤት ብገባም መዘመሬ አይቀርም!!”
ይህን መዝሙሯን ሁሌ ማታ ማታ ስታሰማ የሌሊት - ወፍ መጥታ በጥሞና ታዳምጣታለች፡፡ አንድ ቀን እንዲህ ስትል ጠየቀቻት፤
“እመት ወፊት?”
“እመት” አለች ወፊት፡፡
የሌሊት ወፍ - “ሁሌ ስትዘምሪ እሰማሻለሁ”
ወፊት - “አዎን”
የሌሊት ወፍ - “ለተኙት ወፎች?”
ወፊት - “አይደለም”
የሌሊት - ወፍ- “ታዲያ ለማነው?”
ወፊት - “ለራሴ!” አለች ፍርጥም ብላ፡፡
የሌሊት ወፍ - “ግን ሁሌ ማታ ማታ ነው የምትዘምሪው?”
ወፊት - “አዎን”
የሌሊት - ወፍ - “ለምን ቀን ቀን አትዘምሪም”
ወፊት - “ቀን ቀን ችግር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ቀን ቀን ስዘምር የሰው ልጅ ሰማኝ፡፡ ‘መጥቼ አጠገብሽ ቁጭ ብዬ ላድምጥሽ፡፡ በጣም ቆንጆ ነው የምትዘምሪው’ አለኝ፡፡
እሺ ብዬ አጠገቡ ሆኜ ስዘምር ድንገት ቀጨም አደረገኝ፡፡ ይሄው እዚህ የሽቦ እሥር ቤት ውስጥ ከተተኝ!”
የሌሊት ወፍም፤ “እመት ወፊት፤ ሰው ጠላትሽ መሆኑን ማወቅሽ ድንቅ ነው፡፡ ግን አንድ ነገር ልብ በይ። አንዴ እሥር ቤት ከገባሽ በኋላ ቀንም ዘመርሽ ማታም ዘመርሽ ለውጥ የለውም፡፡ ሰውዬው ለሁለተኛ ጊዜ ሊያጠምድሽ አይመጣም፡፡ ምክንያቱም በእጁ ነሻ!” አለቻት
* * *
የማናቸውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ቁልፍ ጉዳይ ጊዜ ማወቅ ነው (timing)፡፡ ከዕለቱ አስቀድሞም መንቀሳቀስ፣ ዕለቱ ካለፈም በኋላ መንቀሳቀስ፣ ችግር ላይ ይጥላል፡፡ ትክክለኛ የጊዜ ምጣኔ ያለው የፖለቲካ ሰው፤ ብዙውን የጨዋታውን ሰዓት በእጁ ያስገባ ኳስ ተጨዋች እንደማለት ነው - የሚቀረው ጐል ማግባት ብቻ ነው!
የቅርጫት ኳስ ተጨዋችን ምሳሌ ብናደርገው ደግሞ የመጨረሻዋ ሶስት - ሴኮንድ - ክልል በምትባለው ሳጥን ውስጥ ከገባ፤ ያለው ዕድል ወደ ቅርጫቱ መወርወር ብቻ ነው፡፡ ከዘገየ ቀለጠ፡፡ “ቦታን ደግመን ልንይዘው እንችላለን፡፡ ጊዜን ግን በጭራሽ ደግመን አናየውም” እንዳለው ነው ናፖሊዮን ቦናፓርት፡፡ የጥንቱ የጧቱ ፖለቲከኛ ሌኒንም “Seize the time, seize the gun” ይለዋል፡፡ “ጊዜን ያዝ፣ ጠመንጃህን ጨብጥ!” እንደማለት ነው፡፡
“ለድል የሚያበቃህ፤ አደለም ጀግንነት
አዛዡ ጊዜ ነው፣ በጊዜ እወቅበት!” እንዳለው ነው የአገራችን ገጣሚ፡፡
ባለፈው ሥርዓት ዝነኛ ከነበሩት መፈክሮች አንዱ፤ “ማፍረስ ቀላል ባይሆንም መገንባት የበለጠ ከባድ ነው” የሚል ነበር፡፡ ዕውነት ነው፡፡ የምናፈርሰውን በጊዜ ማፍረስ፣ እምንገነባውን በጊዜ መገንባት፣ ፍፁም ብልህነት ነው፡፡ በእርግጥም ከማፍረስ ይልቅ መገንባት የበለጠ ከባድ ነው፡፡ የምናፈርሳቸው ቤቶች የሚተኩበትን ህንፃ በማሰብ ብቻ ከተጓዝን፣ የሚያመጣውን አፍራሽ ውጤት (Repercussions) ልብ ሳንል እንቀራለን፡፡ ደምረን ማስተዋል አለብን፡፡ “ነገሮች ምድር ላይ ሰላም ሆነው ይታያሉ፤ እሳቱ ያለው ከሥር ነው” ይላሉ ቱርኮች፡፡ ምንጊዜም ተናጠል ሁነቶች አድገው አስተፈሪ የማይሆኑ ይመስሉናል፡፡ ድምር ውጤታቸውን ግን ዐይን ያለው ነው የሚያይ፡፡ ስለዚህ እንይ! እንይ! እንይ! የቅሬታዎች ሥርና ክር፤ የቱን ያህል እንደሚርቅና የቱን ያህል እንደሚከር እናስተውል፡፡ ካፈረስን በኋላ የፈረሰባቸው ምን ሆኑ? በፈረሰው ቦታ ላይ ምን ተካን? ብለን ደጋግመን እንጠይቅ!
“ብዙዎች የነዳጅ ታንካቸውን ለመሙላት ሲጨነቁ ሌሎች በዓለም ዙሪያ ያሉ ደግሞ ሆዳቸውን ለመሙላት ይታገላሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ከቀን ቀን እየባሰ፣ ከቀን ቀን እየከፋ ነው የመጣው” ይላሉ፤ የዓለም ባንኩ ፕሬዚዳንት ሮበርት ዞሊክ፡፡ (ዳምቢሣ ሞዮ)
የኑሮ ልዩነት ክፍተት እየሰፋ፣ ጥቂቶች እየተመቻቸው ብዙዎች እየተራቡ የሚሄዱበት ሁኔታ ውሎ አድሮ ጦሱ አይጣል ነው፡፡
ዛሬ ሰላም የሚመስለን ጐዳና ነገ በብሶተኛ ይሞላል፡፡ ጐርፉ መቼ እንደሚሞላ አናውቅም፡፡ የጐርፉን ምንጭ ግን እናውቃለን፡፡ እሱን ለማድረቅም እንችላለን - ልብ ካለን! ነገሮችን በትክክል አይተን በትክክል ካልፈታናቸው፣ በተለይ ትክክለኛ የጊዜ አጠቃቀም ከሌለን፤ እያደር ከድጡ ወደማጡ እንዳንሄድ፣ ወይም እንደዱሮው አነጋገር “ወጣ ወጣና እንደሽምበቆ ተንከባለለ እንደሙቀጫ” ዓይነት ሁኔታ እንዳይገጥመን፤ በእጅጉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ መተው ያለብንን መተው፣ በጊዜ መራመድ ያለብንን መራመድ ያሻናል፡፡ አለበለዚያ የትግሪኛው ተረት እንደሚነግረን፤ “ዘወር ካለማለት ነገሩ ሰፋ፣ ቶሎ ካለመሻገር ጐርፉ ሞላ”፤ ማለት ይሆናል ትርፋችን፡፡

Read 3679 times