Print this page
Saturday, 27 July 2013 14:02

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ

Written by  በኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(6 votes)

ተናጋሪዋ ምድር
“ትግራይ ተነብባ የማታልቅ ግዙፍ መጽሐፍ ናት”

ዛሬ ከሁሉም በላይ የሚያስደምመውንና እንደ ጥሩ ልብ ወለድ አዕምሮን ሰቅዞ የሚይዘውን የታላቋን አክሱምን ፋይል እናገላብጣለን፡፡ አክሱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ “ገናና” ከነበሩት የዓለም መንግሥታት ጐራ ትሰለፋለች፡፡ 
በንግድ፣ በወታደራዊ መስክ፣ በሥነ ጽሑፍ እና በሥነ ሕንፃ መጥቃ የነበረችው አክሱም በአካባቢው አገሮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደር ትችል እንደነበርም ብራናን ተክተው ዛሬም የሚናገሩት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ይመሰክራሉ፡
ይችን የታሪክ፣ የሥልጣኔ፣ የዕውቀትና የማንነት ጐተራ ለማየት የተነሳነው በጥዋት ነው። ዛሬ እንዳለፉት ዕለታት ቀስቃሽም ተቀስቃሽም የለም፡፡ የሁሉም ተጓዦች አይንና ህሊና አክሱምን ለማየት በእጅጉ ጓጉተዋል፡፡
አክሱምን ለማየት የሄደ ሰው፣ የጉብኝቱ መጀመሪያ ትውልዱን ለመታዘብ የቆሙ የሚመስሉት ሃውልቶች ናቸው፡፡ ጐልተው የሚታወቁትም እኒሁ የፈረደባቸው ሃውልቶችና የጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡
እኛም መጀመሪያ ያመራነው ወደ ተናጋሪዎቹ ሃውልቶች ነው፡፡ ከቦታው ስንደርስ በአክሱማውያን ባህል መሠረት፣ በእምቢልታና በከበሮ የ“እንኳን ደህና መጣችሁ” የክብር አቀባበል ተደረገልን፡፡ ከዚያም ተናፋቂዎቹን ሃውልቶች መጐብኘት ጀመርን፡፡
ሃውልቶቹ የተሰሩትም ሆነ የቆሙት ቅድመ ክርስትና ቢሆንም ዛሬም አዲስ ይመስላሉ፡፡
በ1928 ዓ.ም በነበረው የጣሊያን ወረራ ምክንያት ወደ ሮም ተወስዶ በቅርቡ የተመለሰው ሃውልት በተለይ አዲስ ሆኖ ይታያል፡፡ በጣም ትልቅ የነበረው ሃውልት ግን የጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ወዳለችበት ቦታ ወድቋል፡፡
የሃውልቱን ወድቆ መሰበር ያዩ የዚያኔዎቹ ነገሥታት ጉዳዩን እንደክፉ ሚልኪ አይተውት ሃይማኖታቸውን ወደ ሌላ መቀየራቸውን አቶ ቴዎድሮስ አብርሃም የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ ባለሙያ አስረድተውናል፡፡ በወቅቱ ያምኑባቸው የነበሩ አማልክትም የፀሐይ አምላክ፣ የመሬት አምላክ፣ የጨረቃ አምላክ ወዘተ ነበሩ፡፡
የሃውልቶቹ መቆም ምሥጢሩ ለመቃብር ምልክትነት ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ሃውልት ሥር የነገሥታት፣ የነገሥታት ቤተሰቦች፣ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የነጋዴዎች ወዘተ መቃብሮች መኖራቸው በተመራማሪዎች ተረጋግጧል፡፡ በነገሥታት መቃብሮች ላይ የቆሙት ሃውልቶች አንድም በቅርጽ የተዋቡ ናቸው፤ ወይም ዓለምን እንደቆሙ በተለያዩ ቋንቋዎች ተጽፎባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ አክሱም አካባቢ ከ600 በላይ ሃውልቶች እንዳሉ አቶ ቴዎድሮስ ነግረውናል፤ በየቦታው ወድቀው፣ ዘመው፣ ወይም ቆመው የሚታዩት ሃውልቶች ለዚህ በእማኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሃውልቶቹ የሚሠሩበት ቦታ ከአክሱም ምዕራባዊ አቅጣጫ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የጐቦዱራ ተራራ ነው፡፡ በቦታው ተገኝተን እንዳየነው፤ ድንጋዩን እንደ እንጨት የሚፈልጡበት፣ ወይም የሚሰነጥቁበት መሣሪያ ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ እኛ የተመለከትነው አንድ ድንጋይ ለሶስት ሃውልቶች ተሰንጥቆ በመዘጋጀት ላይ ሳለ ሥራው ተቋርጧል፡፡ ግን ከ800 ዓ.ዓለም ጀምረው ሲያከናውኑት የነበረውን ጥበብ ምን አግኝቷቸው ይሆን ያቋረጡት? ሥልጣኔያችን በጅምር የቀረው ጐቦዱራ ላይ ይመስለኛል፤ ገናናነታችን “እንክት” ብሎ የተሰበረውም ታላቁ ሃውልት ወድቆ ሲከሰከስ ይመስለኛል፡፡
የአክሱም ሃውልቶች በሚገኙበት አካባቢ ቤተ ጊዮርጊስ ይገኛል፤ ድሮ ይህ ቦታ “ደብረ ማክዳ” ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ የአክሱሞች ዋና ከተማ እንደነበርም ተነግሮናል፡፡ በ4ኛው መቶ ክ.ዘመን ክርስትና ወደ አገራችን የገባውም በዚችው በተናጋሪዋ ምድር (አክሱም) በኩል ነው፡፡
በ6ኛው መቶ ክ.ዘመን የመን ተሻግሮ ክርስቲያኖችን ያሳድዱ የነበሩ አይሁዶችን የቀጣው አፄ ካሌብ የነበረውም በዚችው ውብ ምድር ነው። ዘጠኙ ቅዱሳን ከአሳዳጆቻቸው ሮማውያን ሸሽተው ወደ አገራችን የገቡትም በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን አክሱም ምን ያህል ዓለምአቀፍ ዝናን ያተረፉ ጠንካራ መሪዎችና ገናና ህዝብ ይኖርባት እንደነበረ ነው፡፡ አለዚያ ለተገፉት ሁሉ መመኪያና መጠለያ ልትሆን አትችልም ነበር። በሀገራቸው ጣኦት አምላኪዎች ተሰድደው ወደ አክሱም የመጡት የእስልምና እምነት ተከታዮችም ሌላው የመመኪያነታችን ማሳያ ነው፡፡
ያ ሁሉ ገናናነት፣ ያ ሁሉ ዕውቀት ለአደጋ የተጋለጠው እና አገራችን የተዳከመችው በ7ኛው መቶ ክ.ዘመን የባሕር በሮችዋ በእስልምና መስፋፋት ምክንያት ሲዘጉባት መሆኑን አስጐብኝያችን አቶ ቴዎድሮስ አስረድተውናል፡፡
ሆኖም “ፍሥሐ ለይኩን ለአሕዛብ (ለአህዛብ ሁሉ ደስታና ሰላም ይሁን)” የሚል ማህተም የነበረው ንጉሥ አርማህ ተቀብሎ ያስተናገዳቸው ሙስሊሞች፤ ከኢትዮጵያውያን ጋር በሰላም እየኖሩ እምነታቸውን በነፃነት ማስፋፋት ችለዋል፡፡
አክሱምን እየጐበኘን ነው፡፡ ስንጐበኝ ግን ዝም ብሎ ተራ ጉብኝት አይደለም፡፡ በትምህርት አቀራረቡ የተካነ መምህር፣ ተማሪዎቹ በማይሰለቹት መንገድ ጭልጥ አርጐ እንደሚወስዳቸው፤ ወይም እጅግ የተዋጣለት ልብ ወለድ እንደሚያነብ ሰው ፀጥ፣ ጭልጥ እያልን ነበር ጉብኝቱን የምናከናውነው። ትልቁ ችግር ግን ከአንዱ የታሪክ አምድ ጋር ፎቶግራፍ እንነሳለን ስንል ሌላው ያመልጠናል፤ ስለሰማነው ወይም ስላየነው ማስታወሻ ለመጻፍ ስንንደፋደፍ ሌላ ተአምር የሚመስል ቁም ነገር ያመልጠናል፡፡
አክሱምና አካባቢዋ እንዲህ በወከባ፣ እንዲህ ብዙ ተጓዦችን ይዞ የሚጐበኙ ቦታዎች አይደሉም፤ ይልቁንም ረዘም ያለ ጊዜ ተይዞ በአግባቡና በሰከነ መንገድ ሊታዩ፣ ሊመረመሩ፣ ሊታወቁ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ትግራይ ውስጥ አንድ የቆመ ድንጋይ ብታዩና ብትጠጉት ወይ በሳብኛ፣ ወይ በግዕዝ፣ ወይም በግሪክ ቋንቋ፣ አለዚያም በሶስቱም ጥንታዊ ቋንቋዎች የተጻፈ ድንቅ ምሥጢር የያዘ ማስረጃ ልታነብቡ ትችላላችሁ፡፡ ውሃ የቦረቦረውን መሬት ብታስተውሉት የአንድ ቤተመንግሥት፣ ወይም ቤተ አምልኮ፣ ወይም መቃብር ግማሽ አካል ልታዩ ትችላላችሁ፡፡ መቆፈሪያ አንስታችሁ ትንሽ አፈሩን ጫር ጫር ብታደርጉም አንድ የተቀበረ ቤተመንግሥት ወይም ሌላ ምሥር ያዘለ ቅርስ ልታገኙ ትችላላችሁ፡፡ ወደ አንዱ ተራራ ጐራ ብላችሁ “ይህ ተራራ ማን ይባላል?” የሚል ጥያቄ ብታቀርቡም የተራራው ስም ብቻ ሳይሆን ምን ዓይነት ታሪክ እንደ ተፈፀመበት ጭምር ትረዳላችሁ። “ትግራይ ተነብባ የማታልቅ ግዙፍ
መጽሐፍ ናት” ያልሁትም ለዚህ ነው፡፡
የንጉሥ ረምሐይ መቃብር እንደሆነ የሚነገርለትን አስደናቂ ቦታ ካየን በኋላ ወደ ጽዮን ቤተክርስቲያን አመራን፡፡ ጽዮን በርካታ የዓለማችን ተመራማሪዎች ጥልቅ ጥናት አድርገው አንዳንዶች “ኢትዮጵያ ውስጥ አለች” ብለው ሲያምኑ፣ ሌሎች መኖሯን ለመቀበል ሲያቅማሙ፣ እንደ ግራሃም ሐንኮክ ያሉት ደግሞ ግራ በመጋባት ጥናታቸውን ሲደመድሙ፤ ሌሎችም ገና ምርመራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ጽዮን ለፈረንጆች፤ በተለይ ደግሞ ለአይሁዶች እስካሁንም እንቆቅልሽ ናት፡፡
ለማንኛውም ጽዮን ማርያም የምትገኘው በ1950 ዓ.ም እቴጌ መነን ባሰሩት ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ አብርሃ ወአጽብሐ ያሰሩት ባለ 12 ቤተመቅደስ በዮዲት ጉዲት መፍረሱን፣ በኋላም በግራኝ መሃመድ መቃጠሉን አስጐብኝያችን ነግረውናል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ የሚካሄደው ግን በ1957 ዓ.ም አፄ ኃይለሥላሴ ባሰሩት ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ጽዮንን የሚጠብቃት ግን አንድ በቅድስናው የተመረጠ መነኮስ ብቻ መሆኑን ተረድተናል፡፡ እሱ ሲደክም በራዕዩ የታየውን ሰው ይተካል፡፡ በተረፈ ወደ ጽዮን ማንም አይቀርብም፡፡ ፓትርያርክ እንኳ ቢሆን ጽዮንን ማየት አይችልም፡፡ ይህ የቆየ ሥርዓት ነው፡፡ አክሱሞች ደግሞ የሥርዓት ፈጣሪዎችና በሥርዓት የሚመሩ ጠንካሮች ናቸው፡፡
“ክብረ ነገሥት” የተባለው መጽሐፍ እንደሚያስረዳን፤ የጽዮን ጽላት የመጣችው ከክርስቶስ ልደት በፊት በቀዳማዊ ምኒሊክ አማካይነት ነው፡፡ የመጣችበት ቦታም ከጠቢቡ ሰሎሞን ቤተመቅደስ ውስጥ ነው፡፡ ጽዮን እስራኤላውያን በባቢሎናውያን ተማርከው ሲሄዱ አብራ ተማርካ ነበር፡፡ ከእሥራኤላውያን ጋር ስትሰደድና ስትንገላታ ኖራ ወደ ኢትዮጵያ መጣች፡፡ ኢትዮጵያን የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሟት ጽዮንም በተለያዩ ቦታዎች ኖራለች፤ ለምሳሌ በጣና ቂርቆስ ለ800 ዓመታት ያህል በድንኳን ነበረች፤ መከራ የማይበግራቸው አባቶቻችን ዝዋይ ሃይቅ በሚገኙት ደሴቶችም ከዮዲት ጉዲት አደጋ በማሸሽ ለብዙ ጊዜ ማቆየታቸው ይታመናል፡፡
ጽዮን የረጅም ዘመን ባለ ታሪክ ብቻ ሳትሆን ጥልቅና ጥብቅ ምሥጢራትም ተጽፈውባታል፡፡ በዚህ ምክንያት የዓለም ሊቃውንት ሲያድኗት ኖረዋል፤ አሁንም አደኑ አልቆመም፡፡ ግን አክሱማውያን ይህን ያህል ረጅም ዘመን ሲጠብቋት ስንት ፈተና አልፈው ይሆን? ዮዲት ጉዲት አክሱምን ስታቃጥል፣ ግራኝ መሐመድ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያወድምና ካህናትን ሲፈጅ፣ ጣሊያን በተደጋጋሚ አገራችንን ሲዳፈር፣ ቱርኮች፣ ግብጾችና ማህዲስቶች፣ ወዘተ ሲፈታተኑን፤ አሰቃቂ የእርስ በርስ ጦርነቶች እጅ እጅ እስኪሉን ድረስ ሲካሄዱ ጠባቂዎቹ ምን ያህል ጽኑዎች፣ ምን ያህል ጥበበኞች እንደነበሩ ሲታሰብ “እውነትም የጽዮን ኃይል የዋዛ አይደለም” ያሰኛል፡፡
አሁን ወደ ጽዮን ሙዚዬም እየገባን ነው፡፡ እዚህ ግን ማስታወሻ ካልሆነ በቀር የፎቶግራፍም ሆነ የቪዲዮ ካሜራ ይዞ መግባት በፍጹም አይፈቀድም፡፡ በውስጡ ያሉትን እጅግ ውድና ብርቅዬ ቅርሶች ሳይ እና በሀገራችን ያለውን የቅርስ ዘረፋ ሳስታውስ ጽዮናውያኑን “አበጃችሁ” አልሁ፡፡ ለቁጥር ከሚያታክቱ ቅርሶች መሃል የአቡነ ሰላማ፣ የአፄ ስርፀ ድንግል፣ የአፄ ፋሲል፣ የአድያም ሰገድ ኢያሱ፣ የአፄ ዳዊት፣ የአፄ በካፋ፣ የአፄ ኢያሱና የወይዘሮ ተዋበች ከልዩ ልዩ ማዕድናት የተሰሩ ዘውዶች የሚገኙ ሲሆን የአፄ ዮሐንስ 4ኛ ፀጉር ከወርቅ ወለባው ጋር ሲታይ አንጀት ያላውሳል፡፡
አፄ ዘርዓ ያዕቆብ የጻፉትን “ክብረ ነገሥት” የተባለ መጽሐፍ ጨምሮ፣ ከ550 በላይ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት በሙዚዬሙ ውስጥ በክብር ይጠበቃሉ፡፡ ከዚህ ሌላ የነገሥታት፣ የራሶችና የእቴጌዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት የነበሩ ሰዎች የክብር አልባሳት፣ መስቀሎች፣ ሥዕላት፣ የአንገትና የእጅ ጌጣጌጦች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ የከሣቴ ብርሃን ሰላማ የሁለት እባቦች ምስል የተቀረፀበት የክብር ዘንግ…እጅግ በርካታ ቅርሶችን ይዟል፡፡ ቦታው በመጥበቡ ምክንያት ቅርሶች እየተጐዱ በመሆናቸው ዘመናዊ ሙዚዬም እየተገነባ በመሆኑ “ይበል” ብለናል፡፡
የሙዚዬሙን ጉብኝት እየተደነቅን ስናጠናቅቅ፣ ሌላ ድንቅ ነገር ማየትና መስማት ጀመርን፤ ድሮ ነገሥታት የትም ቦታ ሆነው ዘውድ ቢጭኑም አክሱም ጽዮን ሄደው ቅብዓ መንግሥት ካልተቀቡ ንግሥናቸው አይጸናም ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት የመጣው ደግሞ ከኦሪታዊቷ ኢየሩሳሌም ይመስላል፡፡ የዚያኔዎቹ የእስራኤል ነገሥታት በነቢያት ካልተቀቡ መንገሥ አይችሉም ነበር፡፡ ቢነግሡም ሕገወጥ ንግሥና ተብሎ ይኮነን ነበር እንጂ በአይሁድ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡
በአገራችንም ጣና ቂርቆስ፣ መርጡለማርያምና ተድባበ ማርያም ደርሶ የሚገባውን ሥርዓት ከፈፀመ በኋላ ወደ አክሱም ጽዮን ሄዶ መቀባት አለበት፤ አለዚያ ንጉሠ ነገሥት ሊሆን አይችልም፡፡ (“ዝክረ ነገር” የተባለውን መጽሐፍ ይመለከቷል) በጉልበቱ ቢነግሥም የጠቀስኋቸውን አብያተ ክርስቲያናት፣ በተለይም የአክሱም ጽዮንን ካህናት ፈቃድ ካላገኘና ቅብዓ መንግሥት በአክሱም ንቡረ ዕድ ካልተቀባ) ህጋዊ ንጉሥ መሆን አይችልም ነበር፡፡
እናም 261 ነገሥታት በዚህ መንገድ ተቀብተው መንገሳቸውን አስጐብኛችን አስረድቶናል፡፡ ይህ ታዲያ ከክርስትና መግባት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ሥርዓተ ንግሥ ይፈጽሙበት የነበረው ድንጋይ ዛሬም ለእማኝነት ቁጭ ብሏል፡፡ ዘውድ ባንደፋበትም፣ ቅብዓ መንግሥት ባንቀባበትም ቁጭ ብለን ፎቶግራፍ ተነሳንበት፡፡
ንጉሡን ይፈትኑ ነበር የተባሉ ደናግል ምሳሌ እንዲሆኑ የቆሙ አምስት ድንጋዮች፣ ለንግሥና የሚመጡ ነገሥታት ጫማዎች ይቀመጡባቸው የነበሩ ሁለት የድንጋይ ኮመዲኖዎች፣ ወዘተ ዛሬም ዝግጁ ሆነው “ባለተራውን ንጉሥ” ይጠብቃሉ፡፡
ከመናገሻ ሥፍራው ብዙም ሳንርቅ “ሙራደቃል (የቃል መውረጃ)” በመባል የሚታወቀውንና የተንዠረገገ ዋርካ ያለበትን ቦታ ጐበኘን፡፡ ቦታው እጅግ ታሪካዊ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ “ግዕዝ፣ ዕዝልና ግራራይ’ የተባሉ ዜማዎችን ከመላእክት የተቀበለበት ቦታ ነው” ተብሎ ስለሚታመን አሁንም ድረስ በክብር ይጠበቃል፤ “ቅዱስ ቦታ” ተብሎም ተሰይሟል፡፡
ወር ከገባ ጊዜ ጀምሮ ሁልጊዜ አንድ ሳምንት ሙሉ ልዩ ሥነስርዓት የሚካሄድበት ሲሆን ማንኛውም ሃይማኖታዊ በዓል የሚከበረው ከዚሁ ቅዱስ ሥፍራ ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ የዜማ መነሻና ዜማዎቹ በመላ ኢትዮጵያ ይታወቃሉ፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ጉዳይ ነው፡፡
ግን ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ፣ የካሕናት አገር ከሆነችው አክሱም መወለዱን ራሱ ከነገረን ውጭ አንድም አሻራ የለውም፤ ወይም የሚያሳየን አላገኘንም፡፡ ምን አልባት የቤተ ክህነት ሊቅ ሆኖ እያለ ሃይማኖቶችን በመዳፈሩ ይሁን ወይም በዘመኑ ሲያሳድደው የነበረው ጠላቱ ወልደ ዮሐንስ አይነቶች በዝተው የታሪኩን መሠረቶች ነቃቅለው አጥፍተዋቸው ይሁን…የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
ለማንኛውም ትግራይ ዛፉም፣ አፈሩም፣ ድንጋዩም፣ ተራራውም በምስጢር የተሞላ የምስጢር አቁማዳ ነው፤ ገና እንጓዛለን፡፡
በነገራችን ላይ ባለፈው ሳምንት ጽሑፍ ልይ “አልሙጋህ የተባለው ጣኦት ይመለክ የነበረው ከ2006 ዓ.ዓለም በፊት ነው” የተባለው በስህተት ስለሆነ “ከክርስቶስ ልደት 2600 ዓመት በፊት” ተብሎ እንዲነበብ ከይቅርታ ጋር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

Read 3778 times